በአንድ የስራ አጋጣሚ በአማራ ክልል በሚገኘው የላልይበላ ከተማ ተገኝቻለሁ። ከተማዋ ስያሜዋን ያገኘችው በመሰረታትና ፍልፍል አብያተ ክርስትያናቱን ባነፃቸው ቅዱስ ላሊበላ ነው። የቀደመ ስሟ ሮሃ ይባላል። በትክክለኛው አጻጻፍ «ላል ይበላ» ሲሆን ቃሉ በአገውኛ «ማር ይበላል» እንደ ማለት ነው። በቀደመ ስሟ ሮሃ የአሁኗ ላልይበላ ከ12ኛው እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በመሆን አገልግላለች። የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን ከአለት በመፈልፈል ያነፃቸው ከ11ዱ የዛጉዬ ነገስታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ላሊበላ /1120 -1197 ዓ.ም/ ነው። እነዚህ በአሰራር ጥበባቸው ዓለምን ያስደመሙና በመንፈሳዊ መዓዛ የተሞሉ አብያተ ክርስቲያናት፤ ከኢትዮጵያን የጥበብ መኩሪያ እና ሃብትነት ባሻገር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በ1979ዓ.ም የዓለም ቅርስ ሆነው ተመዝግበዋል። እንግዲህ በዚች ከተማ ስላገኘኋት ጠንካራ ሴት ነው የማጫውታችሁ።
ተወልዳ ያደገችው እዚሁ ላልይበላ ከተማ ነው። ብዙ የህይወት ውጣ ውረዶችን አሳልፋች። ቆሎ ትሸጥ ነበር። ሆቴል ቤት ተቀጥራ ሰርታለች። አንድ ጊዜ ብልጭ ሌላ ጊዜ ደግሞ ድርግም የሚል ህይወትን ተጋፍጣለች። ብዙ የህይወት ፈተናዎችን አልፋ ተስፋዋ የጨለመበትና ብርሃን የፈነጠቀበት እውነታዎችን አይታለች። የ34 ዓመቷ ወይዘሮ ማናህሌ ተጫኔ። ከልጅነት እስከ እውቀት ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈችው ወይዘሮ ማናህሌ በመንግስት ሆቴል በኮንትራት ተቀጥራ ስትሰራ ቆይታ ተቀንሳለች። በወቅቱ በእጇ የነበረውን 690 ብር ይዛ ነው የራሷን አነስተኛ ምግብ ቤት የከፈተችው። ስራ ስትጀምርና ቤቱ በደንበኞች እስኪለመድ ድረስ ምግብ ሰርታ ተመጋቢዎች ባለመኖራቸው ምግቡን ለኔ ቢጤዎች የሰጠችበትና ሲበላሽም የደፋችበት ጊዜ ነበር።
በየወሩ 110 ብር የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷትም ከዛሬ ነገ እከፍላለሁ ስትል የዕዳ ጫና ተከምሮባት በህይወቷ ላይ ተስፋ የቆረጠችበት አጋጣሚ ነበር። ስራ ስትጀምር የታሸገ ውሃም ሆነ ቢራ በአሸዋ እያቀዘቀዘች ስትሸጥ ቆይታለች። ገበያው እየሞቀ ትርፉ እየጨመረ ሲሄድም ፍሪጅ በመግዛት ውሃና ለስላሳ መጠጦች እያቀዘቀዘች በመሸጥ ገቢዋን አሳድጋለች። የተስፋ ብርሃን ማየት በጀመረችበት ወቅት አንድ ክፉ ቀን አጋጠማት። የንግድ ቤቷ በእሳት ተቃጠለ። ፍንትው ብሎ የነበረው የመለወጥ ተስፋዋ መልሶ ጨለመ።
‹‹በህይወቴ ትልቁን ፈተና ያጋጠመኝ በዚህ ወቅት ነበር። በክስተቱ እጅግ በጣም አዘንኩ፣ ተናደድኩም ግን ምንም ላመጣ ስለማልችል እንደገና ተፅናናሁ። የአካባቢው ነዋሪዎች ደገፉኝ፤ ተሟጦ የነበረውን ተስፋዬን አለመለሙት። ብር አዋጥተው ቤቱን እንደገና ሰሩልኝ። የቤቱ ባለቤትም አንቺ ጠንካራ ሴት በመሆንሽ እንደ አዲስ መስራት ትችያለሽ ብሎ ለተወሰነ ጊዜ ቤቱን ያለ ክፍያ እንድሰራበት ፈቀደልኝ። ሰውዬው ደግ ስለሆነ እንጂ ሌላ ሰው ቢሆን ኖሮ ቤቴን አቃጠልሽ ብሎ ተጨማሪ ገንዘብ ይጠይቀኝ ነበር፤ ያባርረኝም ነበር። የእርሱ ድጋፍና የሌሎች ሰዎች ማበረታታት ተጨምሮበት እንደገና አቅሜን አደራጅቼ ስራውን ጀመርኩ›› ትላለች። ወይዘሮ ማናህሌ ከዚህ በኋላ በአካባቢው በምግብ ስራ ታዋቂ እየሆነች መጣች። ስትጀምር በቂ ገንዘብ ስለሌላት የምታስፈጨው ከሀያ ኪሎ በታች ነበር። ቀስ በቀስ ግን እያደገ ሄዶ አራትናአምስት ኩንታል ማስፈጨት ጀመረች። ገቢዋ እያደገ በመምጣቱ ስራዋን በማስፋፋት የተሻለ ኑሮ መኖር ብትጀምርም ሌላ ችግር አጋጠማት። አንዱን ፈተና አልፍኩ ስትል ሌላ ተስፋ አስቆጣጭ ችግር ከፊቷ ተደቀነ።
የህይወቷ አጋር ከሚሆን ከአንድ ወንድ ጋር ተዋውቃ የፍቅር ግንኙነት ጀመረች። ይሁን እንጅ አብሮነታቸው ረጅም ጊዜ ሊዘልቅ አልቻለም። ባሏ ልጅ ስትወልድ ሸሻት። «የልጄ አባት ሊረዳኝ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ኑሮዬ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነብኝ። ቤቱን የሚቆጣጠረው የቅርብ ሰው ባለመኖሩም ዳግም ለኪሳራ ተዳረኩ» ስትል የለመለመ ተስፋዋን ያጨለመውን አጋጣሚ ታስታውሳለች። ወይዘሮ ማናህሌ እመጫት በመሆኗ ቤቱን የምትቆጣጠረው ሰራተኛዋ ነበረች። ከመውለዷ በፊት 20 ሺ ብር ነበራት።ይሁን እንጅ ያገኘችው አንድ ሺ ብር ብቻ ነበር። ከዚህ በኋላ ብቻዋን ልጅ ማሳደግም ግዴታዋ ሆነ። የመስራት ፍላጎት ቢኖራትም መንቀሳቀሻ ገንዘብ ስላልነበራት የመንግስትን በር ለማንኳኳት ተገደደች። መንግስትም የብድር ጥያቄዋን ተቀብሎ ሰባት ሺ ብር አበደራት። ሁለት ሰው በሰራተኝነት ቀጥራ እርሷም ልጇን አዝላ የምግብ ቤቱን ስራ ለሶስተኛ ጊዜ እንደ አዲስ ማንቀሳቀስ ጀመረች።
ፈጣሪ አገዛትና ሁሉም ነገር እንደ በፊቱ መስመር እየያዘላት መጣ ፤ ስራዋ እየሰመረ ሄዶ ጥሩ ደረጃ ላይ ደረሰች። ወይዘሮ ማናህሌ ቀደም ሲል የቤት ኪራይ የምትከፍለው 200 ብር ነበር። ታማኙን አከራይዋን «አሁን መክፈል እችላለሁ ዋጋ ጨምር» በማለት አንድ ሺ ብር አደረገችለት።ይህን እየከፈለች ለስድስት ዓመታት ሰራች። ስራውም በጣም እየሰፋ ገበያውም እየደራ ሄደላት፤ የተከራየችበት ቤት ባለቤትም ቤቱን ሊሸጠው እንደሚፈልግ አማከራት። ይሁን እንጅ ለመግዛት በቂ ገንዘብ ስላልነበራት ሌላ ቤት በአምስት ሺ ብር ተከራይታ መስራቷን ቀጠለች።
ወይዘሮ ማናህሌ ገንዘብን ቆጥቦ የመያዝ ልምድ የላትም፤ የተቸገረ ትረዳለች፤ ልጆቿንም በግል ትምህርት ቤት ታስተምራለች። በዚህ ምክንያት ገንዘብ አይጠራቀምላትም። በአንጻሩ ደግሞ እዳ ስለማትወድ የተበደረችውን ፈጥና ከፍላለች። አሁን ደግሞ ከምግብ ቤቷ ውስጥ ከምትሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ጨረታ በመወዳደር አሸንፋ ከመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በተጨማሪ ለውጭ ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት ጀምራለች። አሁን ሥራዋ እየሰፋ በመምጣቱ በአምስት ሺ ብርየተከራየችው ቀይራ በ14 ሺ ብር ተከራይታ እየሰራች ትገኛለች። አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ናት።
በአካባቢው ሰው የምትወደደው ወይዘሮ ማናህሌ ምግብ ቤቷም በጾም ምግብ የታወቀ ነው። የምትሰራው አርስቶም እጅ የሚያስቆረጥም እንደሆነ ተጠቃሚዎች ይመሰክሩላታል። ‹‹ሰው መርዳት ያስደስተኛል››የምትለው ወይዘሮ ማናህሌ 2000 ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጣት ለከተማ አስተዳደሩን ጥያቄ አቅርባለች። መልስ ካገኘች ስራዋን አስፋፍታ ለብዙ ወገኖች የስራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ አላት። ሰዎችን በገንዘብ መርዳት ባትችልም ቋሚ የስራ ዕድል ፈጥራ የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ ምኞቷና ደስታዋ ነው። «ህይወት የዘላላም ትምህርት ቤት ናት» የሚል ሀሳብ ያላት ወይዘሮ ማናህሌ ከህይወት ልምዷ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፋ ለዚህ ስኬት መብቃቷ ለሌሎች ምሳሌ እንዳደረጋት ትናገራለች። በአሁኑ ወቅት ለአስር ሰዎች የስራ ዕድልም ፈጥራለች።
ሰራተኞቿም አንዷ ራሷን ችላ ቁርስ ቤት ከፍታለች። አንዱ ደግሞ መንጃ ፈቃድ አውጥቶ ሹፌር ሆኗል። ላልይበላ የቱሪስት መዳረሻ መሆኗ እሷም ሆነ የአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚ ናቸው። የላልይበላ ጥንታዊ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትም ለላልይበላ ከተማ ነዋሪዎች ኢንዱስትሪያቸው ነው። ‹‹እርግጥ ነው ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ቱሪስቶች ስለሚጠቀሙ እኛ ከቱሪስቶች ቀጥታ ተጠቃሚ ባንሆንም ከቱሪስቶቹ ቀጥታ ገንዘብ የሚያገኙት አስጎብኝዎችና /ጋይዶች/ ሌላ አገልግሎት የሚሰጡት ሰዎች ደግሞ ወደ እኛ መጥተው ይጠቀማሉ›› ብላለች። በንግድ ስራ ከተሰማራች 10 ዓመታትን ያስቆጠረችው ወይዘሮ ማናህሌ በአሁኑ ጊዜ ከ200ሺ ብር በላይ ካፒታል አፍርታለች።
ሴት አንድ ነገር ማሳካት ካሰበች በጣም ጠንካራ ስለሆነች ታሳካዋለች። ለስኬት መነሻው ደግሞ አንደኛ ስራውን በፍላጎት መስራት ነው። ሁለተኛ ውስጥን ለስኬት እንደሚበቃ ማሳመን ያስፈልጋል። ልጅ እያለች የራሷን ምግብ ቤት ለመክፈት ትመኝ ነበር። ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ እንደሚባለው ዛሬ የምግብ ቤት ባለቤት ሆናለች። ወይዘሮ ማናህሌ «ፍላጎትን መሰረት አድርጎ ከተሄደ የፈለገው ውጣ ውረድ ቢያጋጥም ያሰብከውን ማሳካትህ አይቀርም» የሚል ጸኑ እምነት አላት።
ምክንያቱም ትምህርርቷን የተማረችው ቆሎ መንገድ ላይ እያዞረች በመሸጥ ነው። ትልቅ ደረጃ ላይ እንደምትደርስም ታስብ ነበር ይህም ተሳካቶላታል። ወይዘሮ ማናህሌ በምግብ ስራ ዲፕሎማ አላት። በኮሌጅ ቆይታዋም ከ80 ተማሪዎችም አንደኛ ነው የወጣችው። በአሁኑ ጊዜ ህልሟ ተሳክቷል። እናም ሰው በፍላጎቱ ከሰራ የፈለገው ቦታ ላይ መድረስ ይቻላል። በአሁኑ ጊዜ ሁለት ቤት ብቻዋን እየመራች ነው። ፈተና ቢለያይም ፈተና የሌለበት ህይወት የለም።
ፈተና ይበዛል ግን ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ከፈተናው እንዴት መውጣት እንደሚገባ ግን ማሰላሰልና መዝኖ የተሻለውን መምረጥ ግድ ይላል።በተለይ ደግሞ ሴት ልጅ በአግባቡም ቤቷን ከመራች አገር መምራት ትችላለች የሚልም እምነት አላት። ወይዘሮ ማናህሌ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አድናቂ ናት። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ለአገርና ለሴቶች ባለው መልካም አስተሳሰብ በጣም ትወደዋለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ሲሉም ስራዋን አቋርጣ ነው ንግግራቸውን የምትከታተለው። ላሊበላ የሄዱ ጊዜም ቦታው ላይ ተገኝታለች። ራዕይና በጎ ሀሳብ ያለው ሰው ከልቧ እንደማይጠፋ ነው የምትናገረው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት23/2011
በጌትነት ምህረቴ