ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚ ከሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ አገሮች መካከል እንድትመደብ መንግስት እየሰራ መሆኑን ይገልፃል። ለተፈፃሚነቱም የተለያዩ ህጎችን በማርቀቅና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ይፋ እያደረ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ስር ነቀል የአደረጃጀት ለውጥ ማድረግ አንዱ ነው። እምቅ የቱሪዝም ሃብቶችን በገበያ ልማትና ፕሮሞሽን በማገዝ የጎብኚዎች መዳረሻ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ ዋነኛ ስራው መሆኑም ይታወቃል።
በዘርፉ ሌላኛው የመንግስት ዋነኛ ግብ አካታች ቱሪዝምን መገንባት ነው። ቱሪዝም ለጎብኚዎች የመስህብ ስፍራዎችን ማስቃኘት ብቻ ሳይሆን አገር ከዚያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል ነው። በጥቅሉ የአገር ኢኮኖሚ ያድጋል እንበል እንጂ እያንዳንዱ ዜጋ ድምር ውጤቱ ተቋዳሽ መሆኑ የማይቀር ነው። በቅንጅትና ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ የሚገነባው የቱሪዝም ዘርፍ ደግሞ በጥቅሉ ኢትዮጵያን በውብ መዳረሻነትና የላቀ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያደርስ ነው። ይህ ሲሆን ሁሉን አቀፍ (አካታች) የቱሪዝም እድገት ተገንብቷል ማለት እንችላለን።
ዶክተር ተስፋዬ ዘለቀ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአገር ልማት ጥናት ኮሌጅ የምርምርና ስርፀት ተባባሪ ዲን ናቸው። በተጨማሪ በዩኒቨርስቲው የቱሪዝም ትምህርት ክፍል በመምህርነት ያገለግላሉ። በቅርቡ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ ስለ “አካታች ቱሪዝምና ሁለንተናዊ እድገት” ጥናታዊ ፅሁፍ በማቅረብ አማራጭ መፍትሄዎችን አስቀምጠዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ “አካታች ቱሪዝም” ማለት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ የቱሪዝም አገልግሎትና እንቅስቃሴ ማድረግ ነው። የዝግጅት ክፍላችንም ይህንንና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው እንደሚከተለው አሰናድቶታል።
ፖሊሲና ፕላኑ ስለ አካታች ቱሪዝም
ዶክተር ተስፋዬ አካታች ቱሪዝም በፖሊሲ፣ በማስተር ፕላንና ሌሎች ዝርዝር ህጎች ሊደገፍና በአስፈፃሚ አካላት ሊተገበር እንደሚገባ ይናገራሉ። ይህን አስመልክተውም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፖሊሲና ሌሎች ማስፈፀሚያ መመሪያዎችን ይገመግማሉ።
“በኢትዮጵያ ቱሪዝም ልማትና አስተዳደር ፖሊሲ ውስጥ በቀጥታ አካታች የሚለውን ቃል ባናገኘውም በተለያዩ አገላለፆች እናገኘዋለን። በተለይ በአስር ዓመት የአገሪቱ መሪ እቅድ ውስጥም በቀጥታም ባይሆን ተቀምጧል” የሚሉት ዶክተር ተስፋዬ፤ በምሳሌነት የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ሁሉም ማህበረሰብ እንዴት መሳተፍ እንዳለበት የሚገልጽ ነገር እንዳለ ይናገራሉ። በተለይ ከዘርፉ የስራ እድልን በሚመለከት ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በኢኮ ቱሪዝምና በሌሎች የቱሪዝም ሃብቶች ላይ ተደራጅተው መስራት እንዳለባቸው በልማት እቅዶቹና ፖሊሲው ውስጥ በተብራራ መልኩ መካተቱን ይገልጻሉ። ይሄንንም እንደ በጎ ነገር ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ በቀጥታ ስለ አካታች ቱሪዝም “inclusive tourism” እራሱን ችሎ አለመቀመጡን እንደ ክፍተት እንደሚያዩት ሳይጠቅሱ አያልፉም።
በዓለም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዘላቂ የልማት ግቦች “sustainable development goal” ከፀደቁት 17 ግቦች ውስጥ አካታች እድገትን የተመለከቱ ጉዩዳዮች ቀርበዋል። ኢትዮጵያም እነዚህን ግቦች ለማስፈፀም በርከት ያሉ ተግባራቶችን ሰርታለች። ዜጎች በሁለንተናዊ እድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ደግሞ የቱሪዝም ዘርፉ ምቹ አጋጣሚን ይፈጥራል።
አካታች ቱሪዝም ከአዲስ አበባ አንጻር
ዶክተር ተስፋዬ ስለ “አካታች” ቱሪዝም ጥናታዊ ፅሁፍ ሲሰሩ በዋናነት የቃኙት የአዲስ አበባን ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን የጥናት ውጤቱ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የማሳየት አቅም ቢኖረውም ነገር ግን በአገሪቱ ዋና ከተማ ውስጥ ያለውን የቱሪዝም እድገት ማነቆዎችና መፍቻ ቁልፍ መፍትሄዎች በልዩ ሁኔታ ያሳየ ነው። ከዚህ አኳያ የሚከተሉትን ነጥቦች ለማንሳት እንሞክራለን።
“በአዲስ አበባ ውስጥ እየተነቃቃ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በዘላቂነት ለማስቀጠልና እድገቱን ለማረጋገጥ የአቅም ግንባታ ስራዎች ያስፈልጋሉ” የሚሉት ዶክተር ተስፋዬ በዋናነት ግን በታችኛው መዋቅርና መስህቡ በሚገኝባቸው ወረዳዎች አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ አደረጃጀቱ ሊፈተሽ ይገባል ይላሉ። ይህን መስራት ከተቻለ ወጣቶችን፣ ሴቶችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን አደራጅቶ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መዘርጋት እንደሚቻል ይናገራሉ። ከአደረጃጀት አንፃር መፈተሽ ያለበት ጉዳይን ሲያነሱ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ መለያየቱንና ይሄም እስከታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ መውረድ እንደሚኖርበት በማሳያነት ይገልፃል።
ዶክተር ተስፋዬ ቀደም ባሉት ርእሰ ጉዳዮች የተመለከትናቸው በፖሊሲና በዘላቂ እድገት እቅዱ ላይ የተቀመጡ ሃሳቦችን አመራሩ መገንዘብና ወደ መሬት ማውረድ ይጠበቅበታል ይላሉ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ብቁና በእውቀትና በቁርጠኝነት የተገነባ አስፈፃሚ አካል ሊኖር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ያሳስባሉ። ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የሚያመለክቱ ህጎች ቢኖሩ፣ በእቅድና ፖሊሲዎች ውስጥ ቢካተት እርሱ ብቻ ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል ይናገራሉ። ከዚህ አንፃር ህጉንና ፅንሰ ሃሳቡን ወደ ተግባር የሚቀይር ባለሙያ የቱሪዝም ዘርፉ በእጅጉ እንደሚያሻ ይጠቁማሉ።
የጥናቱ ጥቁምታዎች
ዶክተር ተስፋዬ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ለረጅም ግዜ በዘርፉ ከሚሰሩ ግለሰቦች ትብብር ጋር በሰሩት ጥናት መሰረት የሚከተሉትን ክፍተቶች መለየት ችለዋል። በዋናነትም በአዲስ አበባ እጅግ በርካታ የቱሪዝም መስህብ ሃብቶች ቢኖሩም እነርሱን አልምቶ፣ አስተዋውቆና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የጋራ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበትን እድል ለመፍጠር በርከት ያሉ እንቅፋቶች መኖራቸው ተለይቷል። ለዚህ እንደ ቀዳሚ ምክንያት የጠቀሱትም ከበላይ አመራሩና የታችኛው አመራር መካከል ያለ ክፍተት፣ አለመናበብ፣ በቂ ሃብት አለመመደብና ውስብስብ ቢሮክራሲዎች ይነሳሉ። በተለይ አመራሩ አካባቢ የቱሪዝም ፅንሰ ሃሳቡን በሚገባ ተገንዝቦ የመምራትና ለማስፈፀም የአቅም ክፍተት እንዳለ መለየት ተችሏል።
“እንደ ዘርፉ ተመራማሪና ዩኒቨርስቲ መምህርነቴ በአብዛኛው በዘርፉ ላይ የተገነዘብኩት ክፍተት የአቅም ማነስ ነው” የሚሉት ጥናቱን ይፋ ያደረጉት ዶክተር ተስፋዬ፤ የአቅም ማነስ ነገሮችን ሰፋ አድርገን ማየት እንዳንችል ያደርገናል ይላሉ። በዚህ ምክንያት የቱሪዝም ዘርፉ በሚገባው መንገድ ሁለንተናዊና አካታች በሆነ መልኩ እድገት እንዳያሳይ ማነቆ ሆኖ እንደሚገኝ ይገልፃሉ።
ሙያና ቱሪዝም
ዶክተር ተስፋዬ ጥናታቸውን የአካታች ቱሪዝም ትግበራው ተቀላጥፎ ተግባር ላይ ያልዋለበትን ምክንያት ሲዳስሱ አያይዘው “ፕሮፌሽናሊዝም” አሊያም ዘርፉና ከሙያው ጋር በቀጥታ የሚያገናኙ ባለሙያዎች ጋር በማገናኘት የሚነሱ አከራካሪ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ሞክረዋል። እንደ እርሳቸው የጥናት ውጤት ግኝትም “የተማሩና አስጎብኚና መሰል ለቱሪዝሙ እድገት እርሾ የሆኑ ሙያዎች ላይ እውቀትና እውቅና ያላቸውን ከማሳተፍ ይልቅ በዘመድ ዘርፉ ላይ የሚገቡ ይበዛሉ” የሚል ትችት መኖሩን አንስተዋል። በእርግጥ ይህ አሰራር በግሉም ሆነ በመንግስት የቱሪዝም መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚታይ መሆኑን ይናገራሉ። ሆኖም አሁን ላይ የቱሪዝምን ፅንሰ ሃሳብ የሚያስጨብጡ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሃብቶች ለማልማትና ከዚያ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል እውቀትን የሚያደረጁ የትምህርት ተቋማት እየበዙና በየደረጃው እየተከፈቱ ሲመጡ ከፍተኛ የሰው ሃብት ፍሰት እንደሚመጣ ይናገራሉ። ይህን ተከትሎ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ ዘርፉ በሙያተኛ የሚታገዝ እንዲሆን በየግዜው ውይይት ሲካሄድ የሚነሳው “የሙያና ፕሮፌሽናሊዝም” ችግር እየተቀረፈ እንደሚመጣ ያነሳሉ። ይሁን እንጂ በአንድ ሌሊት ይህን ችግር መፍታትና ዘርፉን በበቂና በቀልጣፋ ባለሙያ መምራት እንደማይቻል ነው አስተያየታቸውን የሚሰጡት።
በተመሳሳይ መንገድ በተለያየ የትምህርት መስክ የተመረቁ (የታሪክ፣ የመልክአምድር፣ የተፈጥሮ ሳይንስና፣ ባዮሎጂ) ባለሙያዎች በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። እነዚህ ባለሙያዎች በቀጥታ ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር የተገናኘ ትምህርት ባይወስዱም ለዘርፉ በተዘዋዋሪ አስፈላጊ የሙያ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ያነሳሉ። ስለዚህ በዚህ በኩል ከሙያው ውጪ ናቸው በሚል የሚነሳው ትችት አግባብነት የሌለውና እንዲያውም ለዘርፉ ሁለንተናዊ እድገት አስፈላጊ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የዘርፉ ምሁራንና የቱሪዝም እድገት አስተዋፆ
ቱሪዝም በግሉም ሆነ በመንግስት አካላት ውስጥ በሚገኙ በርካታ ባለድርሻ አካላት ካልተደገፈ ውጤታማ አይሆንም። በዋናነት ቅንጅት፣ ተግባቦትና ምክክርን የሚሻ ልዩ ልዩ ተቋማትን የሚያሳትፍ ዘርፍ ነው። በተለይ ከዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጀምሮ በመስኩ የተሰማሩ ልዩ ልዩ አካላትን በማካተት ሁሉን አቀፍ የቱሪዝም እድገት ለማምጣት ምሁራኑ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ የድርሻቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ዶክተር ተስፋዬ የሚሉት አለ። “እኔም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ሆነ በሌሎች የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉት የሙያ አጋሮቼ ምሁራዊ እይታ የሚፈልጉ የቱሪዝም ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እናደርጋለን ። በልዩ ልዩ ቦታዎች ቦርድ ውስጥ በመሳተፍም ሆነ ምርምሮችን በማድረግ አስተዋፆ እያበረከትን ነው” ብለው፤ ወደፊትም የጋራ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ከአዲስ አበባም ሆነ ከፌደራል የቱሪዝም መስሪያ ቤቶች ጋር እንደሚሰሩ ይናገራሉ። እንደ መምህርነታቸውም የተማረ የሰው ሃይል ከማፍራት ባሻገር በአጫጭር ስልጠናዎች የአቅም ግንባታ መስጠት ላይ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
እንደ መውጫ
በርካታ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ አገር ነች። ከሶስት ሚሊዮን ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው “የሉሲ” ወይም ድንቅነሽ አፅም መገኛ አገር፤ ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡና ዝርያ መገኛም ነች። የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ጥቁር አባይም የሚገኘው በኢትዮጵያ ነው። የኤርታአሌ የእሳተ ገሞራ ሀይቅና የዓለማችን እጅግ ረባዳና ሞቃት ስፍራ ዳሎልም የሚገኙት በኢትዮጵያ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ የንግስት ሳባ አገር ነች፣ የሙሴ ፅላትም በኢትዮጵያ ይገኛል ተብሎ ይታመናል፤ በአክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያን።
ከእነዚህ ሌላ ለመዝናናት አመቺ የሆኑ በርካታ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆችና ፍል ውኃዎች እንዲሁም የዱር እንስሳት ፓርኮችና መጠበቂያዎች ይገኛሉ። በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ እጅግ በርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሃብቶችም እንዳሉ ይታወቃል። እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፤ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ለመሆን በቅታለች። ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የበለፀገች፤ የቱሪስት መስህብ ያላትና እነዚህንም ቅርሶች በዩኔስኮ መዝገብ በብዛት በማስመዝገብ ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚዋ ብትሆንም የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ግን የሚፈለገውን ያህል ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ወይም የሚገባውን ያህል አለማደጉን መረጃዎች ያሳያሉ። በመሆኑም የእውቀት፣ የቁርጠኝነት፣ እንዲሁም የሚገባውን ትኩረት በመስጠት አገራችን ከቱሪስት መስህቦች ተጠቃሚ የምትሆንበትን መንገድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ምሁር አመላክተዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም