በጎ አሻራ ማንነት ነው። ሁላችንን ከሁላችን የሚለይ መታወቂያ። በዚህም በአኖርነው አሻራ ብዙዎች ይለዩናል፤ ምስክርነታቸውንም ይሰጡልናል፤ ወደፊትም እንድንራመድ ያደርጉናል። ሚዛን የደፋ ሀቅን ይዘን ስለምንተክለውም ነጸብራቁን በሰራነው ልክ ያሳየናል። ሰውንና አገርን እየገነባልንም ይሄዳል። በተለይ ግን ትውልድን ቀርጾ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ብሩህ ለማድረግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው። ዘመን ተሻጋሪ፣ ታሪክ ተናጋሪ የማንነት ሀውልት ገንቢም ይሆንልናል። ነፍሶች የሚለመልሙበትን መንገድ የሚጠርግም ነው። ይህንን ሀሳብ ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም። በጎ አሻራቸውን በማኖር ምስክር የሆነ ሰውን የሕይወት ተሞክሮ ለማንሳት ስላሰብን ነው።
ወጣቱ ሽመልስ ካሳሁን ይባላል። በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፎ በሰዎችና በተቋማት እገዛ ተምሮ በላብራቶሪ ቴክኒሽያንነት እያገለገለ ይገኛል። ፈተናዎቹ ከባድ ቢሆኑም ትንሽን ችሮታ ትልቅ አድርጎ ለዚህ በቅቷል። ሆኖም ‹‹እነርሱ ባይተክሉኝና አሻራቸውን ባያኖሩብኝ ኖሮ ለዛሬ አልበቃም ነበር›› ይላል። ተቋማቱ የእኛው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፤ የአንበሳ ባንክ ሠራተኞችና የአዲስ አበባ ሜዲካል ኮሌጅ ሲሆኑ፤ ብዙ እንዳገዙት ያምናል። እናም ፈተናዎቹና ትግሎቹ የሌሎች እገዛና አጠቃቀሙን በተመለከተ ብዙ የሚያስተምረን የሕይወት ጉዞ አለውና ሁኔታውን እንዲያወጋን ጋብዘነዋል። ለእናንተም የሕይወት ልምዱ ብዙ ስንቅ የሚሰጥ በመሆኑ ለዛሬ ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምዳችን እንግዳ አድርገነዋል።
በኩርነትን በልጅነት
ሽመልስ አንድ መርህ አለው። ይህም ልጅን የሚሰራውና ምርጥ አለምን እንዲገነባ የሚያደርገው ምሰሶና ማገር የሚያቀርቡለት በጎ ሰዎች ሲኖሩ ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የመጀመሪያውን ድርሻ የሚይዙት ወደዚህ አለም ያመጡን ቤተሰቦቻችን ናቸው። ቤተሰብ የመጀመሪያው እውቀታችን የመጀመሪያው ሰውነታችን የሚጀምርበት ጎዳና ነው። ከዚያ ማንነታችን የሚገነባው የአካባቢያችን ነጸብራቅ ነንና በአካባቢያችን ያሉ ሁሉ ድርሻ አላቸው። የአካባቢያችን ምቹ መሆን ነገ ላይ ለምንገነባው አዲስ አለም ወሳኝነት አለው። የምንመርጣቸው ጓደኞችም እንዲሁ። ስለዚህም እርሱ እነዚህ ነገሮች በብዙ መልኩ እንደተሟሉለት ያምናል። በተለይም እናቱ ለእርሱ ትልቅ ዋጋ እንደነበራቸው ያስረዳል።
እናቱ በበቃ የቡና ተክል ልማት ድርጅት ውስጥ ቡና በመልቀም ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩ ናቸው። ወላጅ አባቱን ግን አያውቃቸውም። እስከተወሰነ ዓመቱም በእናቱ እንክብካቤ ነው ያደገው። ሁኔታዎች ሲከብዷቸው እናት ሌላ ባል አገቡ። ግን እርሱም ቢሆን ለሽመልስ እንደአባት ሆኖ እንደተንከባከበው ያምናል። ይሁን እንጂ የእናቱ ሁኔታ ያሳስበዋልና እርሱም በቤተሰቡ ጫንቃ ላይ ላለመቀመጥ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ቢያንስ ራሴን ልቻል በሚል ከፍ ካለ ጀምሮም በአካባቢው ያለውን ሥራ ይሰራል። በተለይም ለመንግስት ሠራተኞቹ ልብስ ማጠብና ውሃ መቅዳት ዋና ሥራው እንደነበር ያስታውሳል። እስከ 10ኛ ክፍልም ሲማር ከቤተሰብ የትምህርት ቤት ወጪ አንድም ቀን ጠይቆ አያውቅም።
እንግዳችን በባህሪው ዝምተኛ ልጅ ሲሆን፤ በጨዋታም ቢሆን አይታማም። ከጓደኞቹ ጋር የሚፈልገውን ያደርጋል። በእርግጥ ብዙ ጊዜ ላይሰጥ ይችላል። ምክንያቱም ታላቅና የቤቱ የበኩር ልጅ በመሆኑ ብዙ ኃላፊነት አለበት። ስለዚህም ታናናሾቹን በተለያየ ነገር ከማገዝ ባለፈ ለራሱ የሚሆን የገቢ ምንጭ ላይ ተሰማርቶ ይውላል። ከብቶችንም መመገብ ቢሆን የእርሱ ድርሻ ነው። ማንበብና የነገ ተስፋውን ማጎልበትም ግዱ ነውና ብዙ የሚጫወትበት ጊዜ አልነበረውም። ይህንን ማድረጉ ደግሞ ዛሬ ጭምር የሚደሰትበት ነው። አላደረኩትም የሚል ነገር ልጅነቱ ላይ እንዳይኖር አግዞታልም።
ሽመልስ ተወልዶ ያደገው በደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን ሲሆን፤ ልዩ ስሙ በበቃ ይባላል። ቦታዋ ምንም እንኳን ግብርናን የተማረባት ባትሆንም ለግብርናው ዘርፍ ማደግ የበኩሉን ማበርከት ይፈልግ ነበር። በዚህም የልጅነት ህልሙ የግብርና ባለሙያ መሆንና ማህበረሰቡን የዘመናዊ ግብርና ተጠቃሚ ማድረግ ነው። ግን ነገሮች ተቀይረው ያሰበው ላይ ሳይደርስ ቀርቷል። ይህ ህልሙ ግን አንድ ቀን እንደሚሳካለት ያምናል። በዚህም ዛሬ ድረስ ትምህርቱን እያሰበና ነገ እማረዋለሁ እያለ እንደሚገኝ አጫውቶናል።
ከበሮ መምታትና የኪነጥበብ ሥራዎች ላይ መሳተፍም ልዩ ተሰጥኦው ነበር። በዚህም ብዙ ጓደኞቹ ይደሰቱበታል፤ ይመርጡታልም። እንደውም ከጨዋታ ሁሉ እንዲጫወትላቸው የሚፈልጉት በከበሮ መምታት እንዲሳተፍላቸው ነው። ምክንያቱም በማንኛውም ባህል፤ በዘመንኛም ከዚያ አልፎ በግጥሞችና ተውኔቶች ጭምር የከበሮ አመታት ስልትን በሚገባ ያውቃልና የልባቸውን ያደርስላቸዋል።
ትምህርትን በፍጋት
ሽመልስ ከአንደኛ እስከ 10ኛ ክፍል የተማረው በዚያው በትውልድ አካባቢው ሲሆን፤ ትምህርት ቤቱ በበቃ ቡና ተክል ልማት ድርጅት ተብሎ ይጠራል። በትምህርቱ በጣም ጠንካራና ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ የሚሰለፍም ነበር። ለያውም በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፈ። ለነገሩ ማንኛውም ነገር አልጋ በአልጋ የሚከወንና የሚመጣ አይደለም። ፍጋትን ይጠይቃል። ስለዚህም ሽመልስም ቤተሰብ ባያግዝም ራሱን ግን ራሱ መቻል እንዳለበት ያምናል። በዚህም እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን ከሥራ ጋር ያደርጋል። ትምህርትን በሚመለከት መክፈል ያለበትን ዋጋም ይከፍላል።
የተለፋለትን ያህል ያልከፈለው የትምህርት ጉዞው ግን 10ኛ ክፍል ላይ ሌላ አቅጣጫ እንዲያይ አስገደደው። ምክንያቱም ወደ ቀጣዩ ክፍል የሚያልፍበትን ውጤት አልሰጠውም። ስለዚህም ደጋግሞ ሞከረና ለዲፕሎማ የሚያስገባ ውጤት ሲያመጣ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ አደረገ። አዲስ አበባ ሲመጣ ብዙ ነገሮች ከብደውት ነበር። የመጀመሪያው ለመማር ስለነበር የመጣው ያንን በቀላሉ ማድረግ አለመቻሉ ነው። በእርግጥ ለጊዜው ዘመድ ጋር ተቀምጦ ሠርቶ ባገኘውና ቤተሰቡ በሚልክለት ገንዘብ የተወሰኑ ወራትን ማለፍ ችሎ ነበር። ነገሮች ሲከብዱበትና በሰው ጫንቃ ላይ መሆኑ ሲሰማው ቤት ተከራይቶ ወጣ። ይህም ቢሆን ቀላል አልሆነለትም።
የቤት ኪራይና ለትምህርት እየከፈሉ መቀጠል አይደለም በፓርኪንግ እየሠራ ለሚኖር ከፍ ያለ ደሞዝ ለሚያገኝም ፈታኝ ነው። ስለዚህ ሥራ ወደ መቀየሩ ገባ። ይህም ካፌ ላይ ተቀጥሮ መሥራት ነው። ይህ ደግሞ እንደአሁኑ አልተከለከለም ነበርና ትምህርቱን በአዲስ አበባ ሜዲካል ኮሌጅ በጤና ሙያ በማታ ቅዳሜና እሁድ እንዲከታተል አስቻለው። ይህም ሆኖ ውጤቱ በጣም ጥሩ ቢሆንም ትምህርት ቤት ክፍያን መክፈል አልቻለውም። ስለዚህም ለማቆም ወስኖ ትምህርት ቤቱን ወደ መጠየቁ ገባ። እድል ቀናውናም ኮሌጁ አድቫንስ ሰጥቶት እንዲቀጥል ሆነ። ትምህርቱም ተጠናቀቀ።
የትምህርት ጉዞው በምንም ችግር ውስጥ ቢሆን መቆም እንደሌለበት የሚያምነው ሽመልስ፤ አሁን ድግሪውን እየተማረ ይገኛል። በእርግጥ በቀደመ ሙያው መቀጠል ይችል ነበር፤ ይፈልጋልም። ይሁን እንጂ ነገሮች ምቹ ባለመሆናቸውና መንግስትም በጤናው ዘርፍ በኤክስቴንሽንና በርቀት መማርን ስለከለከለ ሌላ የትምህርት መስክን እንዲመርጥ ሆኗል። በዚህም በቢዝነስ ኤንድ ማኔጅመንት በሰቨን እስታር ኮሌጅ እየተማረ ነው። በቀጣይ ደግሞ ነገሮች ከተመቻቹለት የልጅነት ህልሙን ማለትም የግብርና ሙያን እንደሚማር ነግሮናል።
እስከዛሬ በሚማረው ነገር የልቡ ሊሞላለት አልቻለም። ምክንያቱም መስኮችን ሲመርጥ ዛሬን ለመሻገር በሚያስችለው ነገር ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ነው። ነገን ለማየት ዛሬን በፈተና ውስጥ ቢኮንም ማለፍ ግድ ነው። ይህንን ለማለፍ ደግሞ የሚያበላ የትምህርት መስክ መምረጥ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆነበት። ስለዚህም በጊዜው የነበረውን መስክ መርጦ እንዲማር ሆነ። አሁንም ብዙ መሻሻሎች ያስፈልጉታልና ቢዝነስ ኤንድ ማኔጅመንትን መማሩን ቀጠለ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ማታ በአንዱ ሲሠራ ቀን ላይ በአንዱ መሥራት እንደሚችል ስለሚያምን ነው። ነገ ላይ የተሻለ እንደሚሆንለት ያምናልና ያን ጊዜ የምወደውን መስክ እማራለሁም ብሎናል። እንደሚያሳካውም እምነት አለው።
አሻራ + ጥረት
እንደ ሽመልስ አገላለጽ፤ የሌሎች አሻራ ባይኖር ማንም ብቻውን ተለውጦ የራሱ ጌታ አይሆንም። የሌሎች ደግ መዳፎች ባይዳብሱም እንዲሁ ሰው ሆኖ መቆም በራሱ ከባድ ነው። ዛሬ ላይ ብዙ ነገራችን ልክ ያጣም ነበር። የሌሎች ቅን ዓይኖች ባያዩን ኖሮ ከወደቅንበትም አንነሳም። የሌሎች መልካም እጆች ባይዙን ኖሮ ዛሬን አንሻገርም። ሌላ ሰው ሆነን በበቀልንም ነበር። ስለዚህም ከትላንቱ ማንነታችን ዛሬ ለመድረሳችን የብዙ ሰዎች እጅ አለበት። ለሕይወታችን ማማር፣ ለኑራችን መሳካት፣ ለሥራና ለትዳራችን ብዙ ዋጋ የከፈሉ ባለ በጎ አሻራዎች አሉ። ከእነዚህ መካከልም ቤተሰቤ እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የአንበሳ ባንክ ትልቁን ቦታ ይይዛሉ። የዛሬው ውጤት የእነርሱ አሻራ ነውና።
ምንጊዜም ቢሆን እያንዳንዱ ዘመንና ወቅት የሚፈልገው፣ የሚጠይቀው የራሱ የሆነ ፍላጎት አለው። በተለይም አንዳንድ ያልተለመዱ፤ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ልዩ ገጠመኞችን እንደሚሰጡኝ በሕይወቴ ውስጥ አይቻለሁ የሚለው ባለታሪካችን፤ የካፌ አስተናጋጅ ሲሆን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞችንና የአምበሳ ባንክ ሰራተኞችን አገኘ። ድጋፉንም አበረታ። ከዚህ በተጓዳኝ የዛሬውን እጮኛውን የወደፊት ሚስቱንም እንዲሁ ተተዋወቀ። በዚህም ብዙ ችግሮቹና ፈተናዎቹን በእርሷ አለፈ። ስለዚህም አደጋዎች ሲያጋጥሙ ያ ሁኔታና ችግር ያጋጠመው በዘመንና በጊዜ ይፈታል ብሎ እንዲያምን አደረገው። በእርግጥ የዘወትር አስቸኳይ ተግባርን ይፈልጋል። ተግባሩም ይፈፀም ዘንድ ጊዜው ያስገድደዋል። እናም ያለንበት ጊዜ ላይ ሆነን ወደፊቱን እያየን የዛሬውን እየሠራን እሱ ላይ መነጋገር ይገባናልም ባይ ነው።
‹‹ለእኔ በጎ አሻራ በሌሎች ልብ ውስጥ በጎ ሆኖ የሚቀመጥ መልካምነት እንደሆነ ያየሁት የሆነልኝን መረዳት ስጀምር ነው። ስለዚህም በጎ አሻራ መልካም በማድረጋችሁ ብቻ የሚገለጥ አይደለም ልላችሁ እወዳለሁ። ምክንያቱም መልካም በተደረገላችሁ ውስጥ መልካም ማድረግን ትማራላችሁና። ከዚህ አልፋችሁም አሻራውን ያኖረባችሁን አካል ስታስቡ ትላንት ላይ እንዳትነሱ አድርጎ የጣላችሁን ሰው ጭምር ወደመደገፉ ትገባላችሁ። ዛሬ ከወደቀበት እንዲነሳ ታግዙታላችሁም። ይህ እውነት ልባችሁ ውስጥ ሳትወዱ ጭምር የሚቀመጥ ነው። በዚህ ደግሞ ሁሌም አሸናፊ ሁሌም ባለታሪክ መሆን ይቻላል›› የሚለው ሽመልስ፤ እርሱ በቻለው ሁሉ ማንንም ሰው ያግዛል። ለአገሩም ማገልገሉን ከልብ በመነጨ ስሜት ነው የሚያከናውነው። ምክንያቱም በተቋማቱና በሰዎቹ ውስጥ አድሮ ያስተማረውንና ከችግር ያላቀቀውን አገር መተው አይፈልግም። የድጋፉ ስሜት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ፤ የስብዕና ቁጥር ስፍር የሌለው ልኬት እንደሆነም ያምናል። ስለዚህም ማገልገልን ከሰው አንጻር እንጂ ከወዳጅነት አንጻር አይመለከተውም።
ሽመልስ ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ነገር ያነሳል። ሰዎችን ማመስገን እንዲበረቱና ያደረጉትን ነገር በስፋት እንዲቀጥሉበት እድል መስጠት ነው። እነዚህን ተቋማትም የማመሰግነው ከዚሁ የተነሳ ነው። እንደእኔ አይነት ሰዎችን በብዙ መንገድ አንስተው ይሆናል። ነገር ግን ልፋታቸው ስለማይነገራቸው ዳግም ለማድረግ እንብዛም ይሆናሉ። ውጤታቸውን ሲያዩ ግን ዳግም በርታ የሚሉትን ችግረኛ ይፈጥራሉ፤ ይደግፋሉም። ስለዚህ ተደጋፊዎች አመስጋኝ መሆን እንዳለባቸው ያሳስባል።
ሌላው ያነሳው ነገር ተደጋፊውም ሁለት ነገሮችን መያዝ አለባቸው የሚል ነው። የመጀመሪያው ሁልጊዜ እጅ ጠባቂ መሆን የለበትም። በተሰጠው ልክ የሚሠራና ለውጥ የሚያመጣ፤ ስላደረጋችሁልኝ አመሰግናለሁ የሚል መሆን ይጠበቅበታል። ሁለተኛው ወደፊት እንጂ ኋላን እያሰበ የሚቀመጥ መሆን የለበትም። በአለህበት እርገጥ ሊሆን አይገባውም። ያገኘውን ድግሪ አለያም ዶክትሬት ይዞ ምቹ ላይ ነኝ ማለትም ይጥለዋል እንጂ አያነሳውም። ስለሆነም ከዚያ ይልቅ አርቆ አሳቢነቱን ማስመስከር አለበት። ወደ አዲስ ቀን የሚመለከት ሰውኛ ጥበብን ተላብሶ ሩቅ አላሚም መሆን ይገባዋል ይላል።
ሕይወት ውስጥ ምርጥ ለመሆን ሁሌም ሁለት ምርጫዎችን ማየት ግድ ይለናል። እነዚህም መሆንና አለመሆን ናቸው። ሁላችንም በዚህ እውነት ውስጥ የምንኖር በመሆናችን መሆንን ማስቀደም ይገባናል። አይሆንም ካልን ህልማችን ይነጠቃል። ምክንያቱም ተስፋ አይኖረንም፤ መሥራት የሚባልም አይታሰብም። የህልማችንና ራዕያችን ሁሉ መነሻ መሆን ብቻ ነው። እናም በመሆን ውስጥ ብዙዎች እንደሚሻገሩ ማመንና ሥራን ሳይንቁ መሥራት፤ ለራስ ለውጡ መንገድ መሆን ያስፈልጋል ይላል። እርሱም ቢሆን ይህንኑ ነው እያደረገ ያለው።
ከሠራቸው ሥራዎች ውስጥ ደግሞ የማስተናገድ ሥራ ሰፊውንና ረጅሙን ጊዜ የሚይዝበት ሽመልስ፤ ያልሞከረው የሥራ አይነት አልነበረም። ለአብነት ወፍጮ ቤት ሚዛን መዛኝ ሆኖ ያውቃል፤ ጥበቃ መሥራትም ለእርሱ ብርቁ አልነበረም። እንዲያውም ዲፕሎማውን እንደያዘ ነበር የተቀጠረው። ምክንያቱም ወዲያው ተመርቆ ሥራ መያዝ ችግር ነውና። ኑሮውን ለማሸነፍ ደግሞ ሥራ መምረጥ አይቻልም። እናም ጥበቃ የመሆን ምስጢሩም እርሱ ነው። ለተወሰነ ወርም ሠርቶበታል። የፓርኪንግ ሠራተኛም ሆኖ ያውቃል። በቃ ገንዘብ ያስገኝ እንጂ በማህበረሰቡ ዘንድ ዝቅተኛ ነው የሚባለውን ሥራ መስራት ለሱ ምኑም አልነበረም። በራስ ጥረት የሚሆኑ ሥራዎችንም ከመሞከር ወደኋላ አይልም።
እርሱን ይለውጠኛል ብሎ ያሰበውን ሥራ ላቡን ጠብ አድርጎም ይሠራል። በእርግጥ ይህንን ያዳበረው በቀላሉ አልነበረም። የመሥራት ልምዱን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ አሳድጎት ስለኖረ የመጣ ነው። እንደውም የሥራ ጅማሮው በልጅነቱ ይሠራው የነበረው እንደሆነ ያስታውሳል። ሥራው በየተቋማቱና የግልም ሆነ የመንግስት ሠራተኞች ቤት በመሄድ የሚከናወን ሲሆን፤ ተቋማት ላይ ውሃ እየቀዳ ሳንቲም ይቀበላል። ሠራተኞቹ ቤት በመሄድ ደግሞ ልብሳቸውን ያጥብና በወር ይከፈለዋል። ይህ ደግሞ ትምህርቱን ያለምንም ችግር እንዲያጠናቅቅ አግዞታል።
እንደ ሽመልስ እይታ ሰው ሲፈጠር ራቁቱን ነው። ከሀብት ጋር፣ ከጥበብ ጋር፣ ምድራዊ ከሆኑ ትሩፋቶች ጋር የተወለደ አይደለም። ጥበብም ድንቁርናም፣ እውቀትንም፤ ማግኘትና ማጣትንም በምድር ቆይታው የሚያገኛቸው ናቸው። ስለዚህም የምንፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ሰው ከሆንን በኋላ በጥረታችን እናሳካቸዋለን። ለጥረታችን መሳካት ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሌሎች በጎነት ያስፈልገናል። የእኛ መኖር፣ የእኛ በጎ መሆን እኛ የቆምንበት ቦታ ላይ ሌሎች እንዲቆሙ መፍቀድ ነው። ስለዚህም የበጎ ሰዎች እርዳታ ሲደመር የእኛ የጥረት ጉዞ በምድር ላይ የምንቆይባትን ጊዜ ፈጥሮልናል ባይ ነው።
የእኛ ምርጥ አለም በእኛ ምርጥ አስተሳሰብ ብቻ የሚጸና አይደለም በሌሎችም መልካም እይታ የሚገነባ እንደሆነ የሚያነሳው ሽመልስ፤ በጤና ሙያ ከተመረቀ በኋላ ለተወሰኑ ወራት የቀደሙ ሥራዎችን ነበር ሲሰራ የቆየው። ምክንያቱም በተደጋጋሚ አዲስ አበባ ላይ ሲኦሲ ቢፈተንም በኑሮ ጫናው ውስጥ በመሆኑና ተረጋግቶ ስላልነበር ፈተናውን የወሰደው አልተሳካለትም። እናም ሥራውንም ፈተናውንም ሌላ ቦታ መሞከር እንዳለበት አመነ። ወደ ጎጃም በመሄድም ደብረወርቅ ላይ ‹‹እናት ክሊኒክ›› ውስጥ መሥራት ጀመረ። ዋና ሥራው ጤና ኤክስቴንሽንነት ነበር። ዓመት ከስድስት ወርም ቆይቶበታል።
ፈተናውን በጥሩ ውጤት ከአለፈ በኋላ ደግሞ ቅጥሩን መንግስት ቤት አደረገ። ይህም መአዛ ገነት የሚባል ቦታ ላይ ሲሆን፤ የጤና ጣቢያው ስም እናርጅና እናውጋ ይባላል። ዓመት ከስምንት ወርም የሰራበት ነው። ይህ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ዳግም ወደ አዲስ አበባ መምጣትን ፈለገ። ለውጥንና ትምህርትን ከአሰቡም ከዚህ ውጪ የሚሆን አልመሰለውምና ጉዞውን የአጠራቀማትን ገንዘብ በመያዝ መጣ። በእርግጥ ቀደም ብሎ የተዋወቃት እጮኛው ነበረችና በብዙ ነገር እንድታግዘው ሆናለች። እርሱም ቢሆን በትርፍ ሰዓት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። ከዚያ አሁን ያለበትን ክሊኒክ በቋሚነት አገኘ። ይህም ፍሎረንስ መካከለኛ ክሊኒክ ይባላል። በላብ ቴክንሽያንነትም ነው የሚያገለግለው።
ጫናዎች ሲቀንሱ የመሥራት አቅም ይዳብራል ብሎ የሚያምነው ባለታሪካችን፤ አሁን የጀመረውን ትምህርት ሲያጠናቅቅ በግብርናው ዙሪያ ኤክስፐርት ለመሆን አስቧል። ለዚህ ደግሞ ሌላ ትምህርት እንደሚማርም ነው ያጫወተን። ምክንያቱ አንድና አንድ ነው። አገር የምትለወጠው በግብርናው ዘርፍ መሠራት ሲችል ብቻ ነው ብሎ ያስባል። እናም በተለይ እንደ እርሱ አይነት ከገጠራማይቱ ኢትዮጵያ የወጡ ልጆች ሁሉን ነገር የማወቃቸው እድል ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ ቢሠሩበት ውጤታማ ይሆናሉ ብሎ ያምናልና የቀጣይ እቅዱን ይህንን አድርጓል።
የሕይወት ፍልስፍና
የሰው ልጅ ተነሳሽነት ያለውና አንድ ነገር ላይ ተወስኖ የሚቆም መሆን የለበትም። ለውጥ ፈላጊነትን ሁልጊዜ ለአዕምሮው የሚነግር መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ሥራ ያስፈልጋል፤ ተደጓሚነትን ማስቀረትና የራስን አሻራ እያኖሩ መጓዝ ግድ ነው የሚል አቋም አለው።
ማንም ሰው ኖሮትና ተርፎት ላይሆን ይችላል የሚያግዘው። ስለዚህም በታገዝነው ልክ ምን ያህል ውጤታማ ነን ብለንም ማየት አለብን የሚል እምነት አለው። ቁጭ ብሎ በችሮታ መኖር አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ነገን እንዳያዩ የሚያደርግ ነው። ራስንም ከአንድ ቦታ ላይ አስቀምጦ ለማኝ ከመሆን አይተናነስም። ለጋሹ ጭምር የሚበሳጭበት ይሆናልም። ስለዚህም በተለይም ከነበሩበት ችግር ለመውጣት በተለያዩ አካላት ድጋፍ የሚያገኙ ሰዎች ጊዜውን ተጠቅመው ከችግራቸው መላቀቅ እንዳለባቸውም ያምናል። ያ ደግሞ ብዙ የሚያሻግሩ እድሎችን እንደሚሰጡም ራሱን አብነት አድርጎ ያነሳል።
በብዙ ችግር ውስጥ እያለ የሚማር ሰው የዛሬውን ፍጋቱን መቁጠር የለበትም ብሎ ያስባልም። ለዚህም እንደምክንያትነት የሚጠቅሰው ሩቅ አላሚ ቅርቡን ሲያገኝ መጠቀም እንዳለበት ማመኑ ነው። ቅርብ ያለ ሩቁን ያሳያል፤ ያስገኛልም የሚል አቋም አለው። ነገር ግን ማለምና ቅርቡንም አለመያዝ ከሆነ ስኬቱ መቼም እውን አይሆንም፤ መክኖ ይቀራልም ብሎ ያስባል። ስለሆነም እንደእርሱ እምነት ያገኙትን እየያዙ በችግር ውስጥ እያለፉ መጓዝና ያራቅነውን ማቅረብ ያስፈልጋል። የሰው እጅ አይቶ መለወጥ በራሱ ብልጠት እንደሆነም ማመን ይገባል አቋሙ ነው።
መልእክት
ሥራው ውጤታማ እንደሚያደርገን እየአመንን መሥራትና ማከናወን ያለብንን ታላቅ ነገር ሳናከናውን ያለፍን ሞልተናል። በተለይም የተፈጠርነው ለሌሎች ብርሃን እንድንሆን፤ ካለን ላይ ለማካፈል የታደልንና ግን ያላደረግንም እንዲሁ። በዚህ ደግሞ አገራችን ድሀ አገር በመሆኗ በዙሪያችን እርዳታ የሚሹ ብዙ ወገኖች እንዲታዩ ሆኗል። ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒም ደግና አስተዋይ ሰዎች አሉ። ብዙ አይደሉም እንጂ። እነርሱን ረስተን የሚኖረን ልዕልና የለም የሚሉ ሰዎች ታላቅ መሆንን የሚያዩት ታናናሾቻቸውን ወዳጅ በማድረግ ነው። ብዙ ድሆች፣ ብዙ ችግረኞች በዙሪያቸው ያያሉ፤ ያሻግራሉም። ከእነዚህ መካከልም አንዱ እኔ ነኝ። እናም እንደእነርሱ በራቸውን የሚከፍቱ ሰውነት የገባቸው ያስፈልጉናልና እዚህ ላይ መሠራት ቢቻል ይላል።
ሌላው መልእክቱ ለወጣቱ ያስተላለፈው ሲሆን፤ አገርን ከእግዚአብሔር ቀጥሎ የሚጠብቃት እርሱ ነውና በብሔር መከፋፈሉን አቁሞ አሁን ያለንበትን ችግር ለመወጣት የተቻለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበት ያሳስባል። እገዛውን ጦርነቱ ላይ በመዝመት ብቻ አድርጎ ሊያየው አይገባም። በሙያ፣ በገንዘብ ማገዝ ከጎን መሆንን ማሳየት ነውና ይህንን አጥብቀን ልንሠራበት ይገባልም ባይ ነው።
‹‹ሰዎች እኔን አይጠቅምም ቢሉኝ ኖሮ ዛሬ ላይ እዚህ ቦታ ልገኝ አልችልም›› የሚለው ሽመልስ፤ ባለማሰብና ባለማስተዋል ሌሎች ጠቃሚዎቻችን እንዳይደሉ እናስባለን እንጂ ስኬታችን ደስታችን ሁሉ አይጠቅሙም ያልናቸውን ሰዎች ታኮ የሚመጣ ነው። ስለዚህ የማይጠቅም ሰው ምድር ላይ አልተፈጠረም። ዓይኖቻችንን ገልጠን ብናይ በዙሪያችን ብዙ ጠቃሚ ሰዎችን ማየት እንችላለን። እናም በአጉል አመለካከት የማይጠቅመንን አመለካከት የምናራምድ ሰዎች ከአሁኑ ማስወገድ አለብን። እውነተኛ ሰውነት ሁሉም ሰው ለሁሉም አስፈላጊ ነው ብሎ ማመን ነው ሌላው ምክሩ ነው።
የዛሬ መጥፎነታችን በነገ የልጆቻችን ሕይወት ላይ አርፎ እንደሚያሰቃየን መርሳት የለብንም። በሌሎች በጎነት እንደለመለምን ሁሉ የእኛን በጎነት የሚፈልጉም እንዳሉ እንመን። ሀገር ከእኔና ከእናንተም በኋላ ትቀጥላለች፣ አዲስ ትውልድ፣ አዲስ አስተሳሰብ ከፊት አለ። ነገ ለሚፈጠረው ሀገርና ሕዝብ ደግሞ የእኛ ዛሬ ላይ በጎ መሆን የማይተመን ዋጋ አለው። እናም በብዙ ነገር ውስጥ ያለፍን ሕዝቦች ነንና እየወደቅንና እየተነሳን መቀጠል አለብን። ለመነሳት እየፈለግን የጣሉን ብዙ እጆች አሉ። በጎ ልብ ግን በቀል አያውቅም፣ መልካም ነፍስም በደልን አትቆጥርም እንዲያውም መጥፎ ትላንትን ማሰብ ጊዜ ማጥፋት ነው። ስለሆነም ከእኛ የሚጠበቀው የጠሉንን እየወደድን፣ ለበደሉን ምህረት እያደረግን ወደ ፊት መሄድ ነው። በአገር ከመጣ ግን ማንንም መደራደር አያስፈልግም ሲል ይመክራልም።
ሽመልስ በጎ አሻራ ከምናስበው ሀሳብ፣ ከምንሠራው ሥራ፣ ከምንኖረው ሕይወት ወደ ሌሎች የሚንጸባረቅ ሞገስ እንደሆነ ያምናልና በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ የበጎ ሰዎች ዘመን ተሻጋሪ በጎ አሻራ አለ። ይህ ደግሞ እኛም አሻራ አኗሪ እንድንሆን መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው። ስለሆነም በተለይ አንዳንድ የአዲስ አበባ ወጣት ሁለት ነገሮችን ከዚህ አንጻር ማድረግ አለባቸው ይላል። የመጀመሪያው ለሌሎች ወጣቶች አርኣያነቱን ማሳየት አለበት። ለዚህ ደግሞ ከቤተሰብ ጥገኝነት መላቀቅና ሥራ ሳይመርጡ ሠርቶ መለወጥ ይኖርባቸዋል። ሁለተኛው ከሱስ መራቅ ይጠበቅባቸዋል። ሱስ አዕምሮን፤ ማንነትን ያስጥላል። መሥራትንም አያስወድድም። መለወጥም አያስመኝም። እናም ይህንን አስበው ልክ እንደ ክፍለአገሩ ልጅ ፈግተው ቢሰሩና ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው እንዲሁም ለአገር ደስታ ይሆናሉ የሚለው የመጨረሻ መልእክቱ ነው። እኛም መልእክቱ ለወጣቱ ተግባራዊነት ይዋል እያልን ለዛሬ አበቃን። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም