ዘንድሮ ሰኔና ሰኞ እንዲሉ የሕዳር ሲታጠን ሰሞናትና የእፉኝቱና ከሀዲው ትህነግ እጥነት ተገጣጥመዋል። ቀጥለዋል። በጦር ግንባርም በከተማም። ጭፍራዎቹም እየታጠኑ ነው። የሕዳር በሽታን ያመጣው ቆሻሻ ተጠርጎ በአንድ ቦታ ተሰብስቦ ይቃጠላል። ወረርሽኙ ከጭሱ ጋር ይሸኛል። በጀ ያላለውም አመድ ሆኖ ይቀራል። አምና ተሸኝቷል። ግን ሰኮናውና ቅሪቱ አፈር ልሶ ተነስቶ ሀገሬን እንደገና አቆሸሻት። አመድ ሆኗል ተብሎ ተዘናጋን። ዘንድሮ ግን ያ መዘናጋት አይደገምም። ዘንድሮም ቆሻሻ እንዳያዳግም ሆኖ ይጠረጋል። ተሰብስቦ ይቃጠላል። አመድ ይሆናል።
የዚችን ሀገር ታሪክ፣ ተረክ፣ አብሮነት፣ እሴት፣ ፍቅር፣ ሲሳይ፣ ሀብት፣ ዜጋ ፣ እምነት፣ ቃል ኪዳን፣ መልክዓ፣ አየር፣ ስንቱን ዘርዝሬ እገፋዋለሀ አቆሽሾና በክሎ የክህደትን፣ የጥላቻን ፣ የልዩነትን፣ የዘረኝነትን፣ የሌብነትን፣ የዘረፋን ፣ የውሸትን ፣ የጭካኔን፣ የሴረኝነትን፣ የስግብግብነትን ፣ የፈላጭ ቆራጭነትን ፣ ወዘተረፈ ተስቦና ወረርሽኝ ያጋባብን አሸባሪው እፉኝቱና ቆሻሻው ትህነግ በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት በልዩ ኃይሎች በሚሊሻዎች በመላ ኢትዮጵያውያን ክንድ እስከወዲያኛው እየተጠረገ ነው።
ትግራይ ብሎም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከስፓኒሽ ፍሉው ትህነግ ነፃ እንዲሆኑ በደንብ እየታጠኑ ነው ። የዘንድሮው ለየት የሚያደርገው አዲስ አበባን ጨምሮ በየከተሞች የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎችና ጭፍራዎችን አብሮ እያጠነ መሆኑ ነው። ለ30/47 ዓመታት የተቆራኘ ተስቦ በዋዛ ፈዛዛ አይለቅምና በቀጣይም ሀገርና ሕዝብ ከመርዙ፣ ከእፉኝቱና ከወረርሽኙ ትህነግ አሻራ / ሌጋሲ / ይታጠናል ። ሰንኮፉም ተነቅሎ ይጠረጋል ። ሰኔና ሰኞ ማለት ዛዲያ ይህም ይደል !? ስለ አሸባሪውና ጭፍራዎቹ እጥነት ይህን ያህል ካልሁ ወደ ሕዳር ሲታጠን ልለፍ ።
“… በኢትዮጵያ የኀዳር በሽታ የሚባለው የ1ኛውን የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ተከትሎ የተከሰተውና በመላው ዓለም ለ200 ሚሊዮን ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው’ እስፓኒሽ ፍሉ ‘ ነው ። ወረርሽኙ በ 24 ሳምንታት የቀሰፈው ህይወት ፤ ኤች አይ ቪ ኤድስ በ24 ዓመታት ከቀሰፈው በአያሌው ይበልጣል። ወረርሽኙ አዲስ አበባ ከገባ በሇላ ብዙ ሰው የጨረሰው በኀዳር ወር ስለነበር ‘ የኀዳር በሽታ ‘ እየተባለ ይጠራ ነበር ። ወረርሽኙ ወደ ወለጋ በመዛመቱ የንፋስ በሽታ ‘ ዱኩባ ቂሌንሳ ‘ የሚል ስም ወቶለት ነበር ። ይህ መቅሰፍት በሀገራችን በ1911 ዓ.ም ወርዶ ብዙ ሰው ጨርሷል ።
ወረርሽኙ በጉንፋን በሳል ይጀምርና ትኩሳት፣ ማስለቀስ ፣ ነስር ፣ ተቅማጥና ትውከት ከማስከተሉ ባሻገር አእምሮም ያስት ነበር ። ከዚያም በሦስት በአራት ቀን ይገድላል ። የቤተሰቡ አባላት በሙሉ አልጋ ላይ ይውሉ ስለነበር አስታማሚ ስለሚጠፋ በርሀብና በውሃ ጥም ብዙ ሰው ይጎዳ ነበር ። ከአራት ቀን ያለፈ ሕመምተኛ ግን ይድናል። አፍላው በሽታ ከኀዳር 7 እስከ 20 ፣ 1911 ዓ.ም ነበር። በየቀኑም ሁለት ሦስት መቶ ከዚህ በላይም ይሞት ነበር ። በአንድ መቃብር ሁለት ሦስት ሬሳ እስከ መቅበር ተደረሰ ። በዚህ ሰሞን መቃብር የሚቆፍርና ሬሳ ተሸክሞ ወደቀብር የሚወስድ ሰው ማግኘት ችግር ነበር። ባል የሚስቱን፤ አባት የልጁን ሬሳ እየተሸከመ ቀበረ። መቃብር ይቆፍርና ቤቱ ሄዶ ሬሳ ይዞ ሲመለስ ሌላው ቀብሮበት ያገኘዋል። ቤተሰብ በሙሉ የታመመባቸው በየቤታቸው እየሞቱ አውሬ በላቸው።
በበሽታው ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪና ልዕልት ወ/ሮ መነን በጠና ታመው ነበር፤ ንግስት ዘውዲቱም አልጠናባቸውም እንጅ ታመው ነበር። ከመኳንት ከንቲባ ወሰኔ ዘማኒኤል፤ ከካህናትም ሐዲስ አስተማሪው አለቃ ተገኘ ሞቱ።/አምናና ዘንድሮ ኮቪድ 19 በርካታ ወገኖቻችንን እንደነጠቀን። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን፤ ዶ/ር ጥበበ የማነ ብርሃንን፤ ወ/ሮ ዘሚ የኑስን፤ ወዘተረፈ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን አሳጥቶናል። በተለይ ዴልታ የተሰኘው 3ኛው ወጀብ ዛሬም እየተፈታተነን ይገኛል።
/አለቃ የመምህር ወ/ጊዮርጊስ ደቀ መዝሙር ነበሩ። በዚያ ወራት በአዲስ አበባ የነበረው ጭንቀት በስፍራው ተገኝቼ ተመልክቼዋለሁ። የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ በሰፈራቸው በጉለሌ ክፍል በየቤቱ እየዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውሃ ሲያድሉ ሰነበቱ። በእግዚአብሔር ቸርነት ከበሽታው አምልጠን ነበርና እኔንና ጎጃሜ ኃይለ ማርያምን ውሃ በገንቦ እያሸከሙ እሳቸው ቁራሽ እንጀራ ይዘው ይሄዱና ከቤቱ ደጃፍ ሲደርሱ እኛን ውጭ አስቀርተው ውሃውንና ቁራሹን ይዘው ይገቡ ነበር። እኛን ማስቀረታቸው በሽታ እንዳይዘን ስላሰቡልን ነው። በሌላ ስፍራም የዚህን አይነት ትሩፋት የሰሩ መንፈሳውያን ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ሙሴ ሴደርኩይስት የተባሉ ስዊድናዊ ሚስዮናዊ አስተማሪ በየሰፈሩ እየዞሩ ለበሽተኞች እህልና ውሃ መድሀኒት በመስጠት ትሩፋት መስራታቸውን ሰምቻለሁ። እኒህ ሽማግሌ ከጥቂት ቀናት በኋላ በዚሁ በሽታ ታመሙና ሞተው ጉለሌ ተቀብረዋል።
የኀዳር በሽታ (ግሪፕ) በአዲስ አበባ ብቻ አልተወሰነም። ወደ ባላገር ተላልፎ ብዙ ሰው ፈጅቷል። ሆኖም በባላገር የአዲስ አበባን ያህል አልጠነከረም ይባላል። በዚህ በሽታ በመላ ኢትዮጵያ የሞተው የሕዝብ ቁጥር እስከ 40 ሺህ ድረስ መገመቱንም አስታውሳለሁ።
በተለይ ኀዳር 12፣ የሚካኤል ዕለት ብዙ ሰው ሞተ። ስለሆነም ወረርሽኙ እስከዛሬ በየዓመቱ የህዳር ሚካኤል ዕለት በየሰፈሩ ቆሻሻ ሰብስቦ በማቃጠል‘ ኀዳር ሲታጠን ‘ በሚል ይዘከራል ። …” በማለት ‘ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ‘ ደራሲ መርስኤ ኀዘን ወ/ቂርቆስ ይነግሩናል። በነገራችን ላይ እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ፣ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ እና ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ያለስስት የመሰከሩለትን ይህን ድንቅ መፅሐፍ ካላነበባችሁት እንድታነቡት እና ከመፅሐፍት መደርደሪያችሁ እንድትጨምሩት በታላቅ ትህትና እጋብዛለሁ ።
እንደ መውጫ
ትኩረት የተነፈገው “ ኀዳር ሲታጠን “ ባለፈው ዓመት 102ኛ ዓመቱን ደፍኗል ድፎ ቆርሶ ሻማ ለኩሶ መዘከሩ ቢቀርበት እንኳ ጤና ሚኒስቴርም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ዕለቱን በመላ ሀገሪቱ የፅዳት ስራ ንቅናቄን ለማቀጣጠል ከተማዋ እንደ ስሟ አበባ ለዛውም አዲስ አበባ እንድትሆነ የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ስራ ለመስራትና ነዋሪውን ለማነሳሳት መልካም አጋጣሚ የነበር ቢሆንም አልተጠቀምንበትም። ዘንድሮ 103ኛ ዓመቱን ይይዛል። ሆኖም ዘንድሮም የሚገርመው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሀገራችን ተከስቶ ከፍተኛ የጤና እና የኢኮኖሚ ቀውስ እየጎነቆለ ባለበት እንኳ ሕዳር ሲታጠንን ኮቪድን የመከላከያ አጋጣሚ ተደርጎ ሀገራዊ ንቅናቄ ማቀጣጠያ ሊሆን ሲገባ ምንም አይነት ትኩረት ሳያገኝ አልፏል ።
እንደ እነዚህ አይነት ወንዝ አፈራሽ ሀገራዊ፣ ሕዝባዊ ንቅናቄ የማቀጣጠያ ተሞክሮዎች ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ ተጠንተው የጎደላቸው ተሞልቶ ያላቸው ይበልጥ ጎልብቶ ጥቅም ላይ ቢውሉ ኖሮ ኮቪድ 19ን ጨምሮ ሊውጡን የደረሱ ዙሪያችንን የከበቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዲህ ግዘፍ ባልነሱ። አሰፍስፈው ሊውጡን ባልደረሱ። ወይም ከእነ አካቴው ባልኖሩ። ሀገር በቀል የትምህርት፣ የግብርና፣ የባህላዊ ሽምግልና ዕርቅ፣ በደቦ በጅጌ በሕብረት የመተጋገዝ ፣ እንደ ዳጉ ያሉ መረጃ የመለዋወጥ፣ እንደ ገዳ ያሉ የአስተዳደር ስርዓቶችን፣ በጉዲፈቻ ልጅን ማሳደግ፣ ደንንና የዱር እንስሳትን የመጠበቅ፣ እንደ ሕዳር ሲታጠን ያሉ የአካባቢ ንፅህና መጠበቂያ ዕውቀቶቻችን የጎደለውን ሞልተን አዘምነን ጥንካሬአቸውን ይበልጥ አጎልብተን ቀምረን ብንጠቀምባቸው ኖሮ ምን አልባት ዛሬ ለምንገኝበት ውስብስብ ችግሮች በዚህ ደረጃ ባልተዳረግን።
ባህላዊ፣ ቀደምትና አካባቢያዊ የምንላቸው እነዚህ ዕውቀቶች በአግባቡ ተጠንተውና ተቀምረው ስራ ላይ ቢውሉ ልማትን እድገትን ለማሳለጥ ከማገዝ አልፈው በየአውዳቸውና በየመልክዓቸው ንቅናቄን በቀላሉ ለመለኮስና ለማቀጣጠል ያግዙ ነበር። ዛሬ ቆሻሻን ሰብስቦ በማቃጠል ለ103ኛ ዓመት የምናስበውን” ሕዳር ሲታጠን “ባህላዊ ክዋኔ በአግባቡ እያጎለበትነው ብንመጣ ኖሮ ዛሬ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተሞቻችን በቆሻሻ ክምር፣ አየራቸውም በሚከረፋ ሽታ ባልተሞላ። ባልተበከሉ።
ወንዞቻችን የፍሳሽ ማስወገጃ ባልሆኑ። የመዲናችን አየር ንፁህና air quality አሳሳቢ ደረጃ ላይ ባልደረሰ። ኮቪድም እንዲህ ለአዛዥ ለገናዥ ባላስቸገረ። በ”ሕዳር ሲታጠን“ ባህላዊ እውቀት ላይ ተመስርተን እየሰራን ብንመጣ ኖሮ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ኃይለማሪያምም ሆኑ የአሁኑ መጥረጊያ ይዘው ባልወጡ ። ዛሬም አንድ ሰሞን በወረት የወጣንለትን ፅዳት እርግፍ አድርገን ትተነው ቆሻሻ መልሶ በከተሞቻችን ጎጆውን ቀልሷል። ዛሬም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ እንደማጠጣቱ መጥረጊያ ይዘው እስኪወጡ እንጠብቃለን። መቼ ይሆን ጥበቃችን የሚያበቃው! ?
ሀገራችን ኢትዮጵያ በእውነተኛ ልጆቿ ከአሸባሪው ሕወሓት ወረርሽኝ ትታጠናለች !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም