ኢትዮጵያ ታሸንፋለች…ግን እንዴት? ዛሬ ይሄን እውነት በጋራ እንገልጣለን። በጋራ ያልኳችሁ ኢትዮጵያዊነት የጋራ መልክና የጋራ ታሪክ ስለሆነ ነው። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የብቻና የተናጠል ሕይወት የለም። ከትላንት ዛሬን ያየነው፣ ከዛ እስከዚህ የተራመድነው በመደጋገፍና አብሮ በመብላት ባህል ውስጥ ነው። ለዚህ ደግሞ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ከሚያስገርሙኝ እውነቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ይሄ የአብሮነት ሕይወታችን ነው።
አሁን ግን ኢትዮጵያዊነት ምንድነው አልላችሁም…ብላችሁም ማሸነፍ…ማሸነፍ..ማሸነፍ እንደምትሉኝ አልጠራጠርም። ወይም ደግሞ እውነትና ፍትሕ ጽናትም ያቆሙት ገናና ሥጋና ደም እንደምትሉኝም አምናለሁ፣ ወይም ደግሞ ዓለም ላይ አንድን ውድ ነገር ጠቅሳችሁ የክብር ጥግ፣ የነጻነት ምኩራብ ብላችሁ እንደምትነግሩኝ እምነቴ የጸና ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት እንደዛ ስለሆነ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት ከዛ ውጪ ትርጉም ስለሌለው።
ወቅቱን ዋጅቼ፣ ሰሞነኛውን ሁኔታ አጢኜ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች.. ግን እንዴት? ስል የመጣሁት በምክንያት ነው። ሁላችንም ኢትዮጵያዊነት ማሸነፍ እንደሆነ እናውቃለን፣ ሁላችንም ኢትዮጵያዊነት እውነትና ፍትሕ እንደሆነ እናውቃለን፣ ሁላችንም ኢትዮጵያዊነት ገብቶን የምንኖር ነፍሶች ነን። በዚህ ማሸነፍ ውስጥ፣ በዚህ እውነትና ፍትሕ ውስጥ ያለውን የማሸነፍ ሚስጢር የምናውቀው ግን ጥቂቶች ነን።
ኢትዮጵያዊነት ስም ብቻ አይደለም..ከስሞች ሁሉ፣ ከክብሮች ሁሉ፣ ከነጻነቶች ሁሉ፣ ከጥበብና ከማስተዋል ሁሉ በላይ የሆነ ማንነት ነው። ይሄ ማንነት እንዴት ተገነባ ?ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት ለአሁነኛ ችግራችን ወሳኝ እንደሆነ ይሰማኛል ። በኢትዮጵያ ምድር ኢትዮጵያዊ ሆናችሁ እስካላችሁ ድረስ እውነት አላችሁ…ለዛውም ገናና እውነት። አድዋ የተሳለው..ኢትዮጵያዊነት የመጣው በአባቶቻችን አጥንትና ሥጋ ነው።
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች..ግን እንዴት? ይሄ ሀሳብ ጥያቄ ብቻ አይደለም መልስም ብቻ አይደለም። በዚህ ሀሳብ ውስጥ ጥያቄና መልስ አለ። በዚህ ሀሳብ ውስጥ አገርና ህዝብ ትውልድም አለ። በአገር ጉዳይ ላይ ጥያቄው ምንም ይሁን መልሱ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ነው። በአገር ጉዳይ ላይ መልሱ ምንም ይሁን ጥያቄው አገርና ሕዝብ ነው።
የሰሞኑ የአገራችን እጣ ፈንታም ከዚህ ጋር የሚገናኝ ነው። ኢትዮጵያን የሚችሉ መስሏቸው ከኢትዮጵያ ጋር ትግል የገጠሙ አንዳንድ አገራት አሉ። ኢትዮጵያዊነት የአትንኩኝ ባይነት ስፍራ እንደሆነ ዘንግተው ለሞታቸው ጉድጓድ የሚቆፍሩም ጥቂቶች አይደሉም። “አይጥ ላመሏ የድመት አፍንጫ ታሸታለች” እንዲሉ ትዕግስታችንና ዝምታችን ፍራቻ መስሏቸው የሚነካኩንም አልጠፉም የሆነው ሆኖ ግን ይሄ ሁሉ አንድ መልስ ነው፤ እርሱም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ነው።
የአሸባሪው ህወሀትን ክፋትና ሴራ አንግበው በፍትህ ስም የበግ ለምድ ለብሰው ገናና እውነታችንን ሊያቆሽሹ ባህር አቋርጠው ከባህር ማዶም ሆነው አተካራ የገጠሙን ሀገራት አሉ። የኢትዮጵያን መነሳት ፈርተው ብርሀኗን ሊያጨልሙ፣ ተስፋዋን ሊነጥቁ ከትልቅ ህልሟ ሊያሰናክሏት ሴራ የሚሸርቡ ልማደኛ እጆች በውስጥም በውጪም እየተጠቋቆሙ ነው።
እኚህ አገራት፣ እኚህ የክፋት ቡድኖች ጥያቄዎቻችን ናቸው መልሶቻችን ደግሞ እኛ ጋ ነው ያለው። እርሱም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች የሚለው ነው። ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ አገርና ሕዝብን በተመለከተ ጥያቄው ምንም ይሁን መልሱ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች የሚል ነው። አዎ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች..ሕዝቦቿ ወደ ብርሃናቸው፣ ወደ ናፈቁት ንጋታቸው ይራመዳሉ። ግን እንዴት?
ኢትዮጵያ ከሁሉም በኋላ ቀና ትላለች፣ ከሁሉም በኋላ አይኖች ሁሉ ወደ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ያያሉ። ጆሮዎች ኢትዮጵያ የምትለውን ለመስማት ይከፈታሉ..አንደበቶች ስለ ጥቁር ሕዝቦች ይናገራሉ ግን እንዴት?
ከዛ ምድር ተአምራቶች ይፈጠራሉ። ሀበሻዊነት በዓለም ዙሪያ ይናኛል። ይሄ እውነት ትንቢት አይደለም በቅርቡ የሚሆን እውነት ነው። ኢትዮጵያ እንደምታሸንፍ፣ ኢትዮጵያዊነት እንደሚልቅ ጥርጥር የለኝም..እናንተም ታምናላችሁ። ወደረኞቻችን ፍትሕን አንጋደው፣ እውነትን አዛብተው በርባንን ሊፈቱ ክርስቶስን ሊሰቅሉ እያሸረቡ እንደሆነ ብናውቅም እኛ ግን እናሸንፋለን…ግን እንዴት?
አሸናፊነት ዝም ብሎ አይገኝም ከኋላው አንድ የሆነ ታሪክ ይኖረዋል..ውብና ድንቅ ታሪክ። አሸናፊነት የነፍሶች ሁሉ ጥም ርሀብ ነው..የሰው ልጅ ሁሉ የጋራ ስሜት ነው። አሸናፊነት ውጤት ነው። ከውጤቱ በኋላ ያለው ታሪክ ምን እንደሚመስል ዓድዋን ማሰቡ ብቻ በቂ ነው እላለሁ። በሳይንሱ እንደምታውቁት ሁሉም ነገር በምክንያትና ውጤት የተቀመረ ነው። በዚህ ቀመር ውስጥ ከትላንት ወደ ዛሬ ከዛሬም ወደ ነገ እንሽከረከራለን ምክንያቱም በምክንያትና ውጤት ቀመር ውስጥ ነንና።
ለአሸናፊነት ምክንያታችን አገራችንና ሕዝባችን ነው፤ ውጤታችን ደግሞ በዚህ ምክንያት ላይ ተረማምደን የፍትህና የጋራ ምድርን መፍጠር ነው። ይሄ የአንድ ወይም የጥቂት ሰዎች እውነት አይደለም አገሩን ለሚወድ ሁሉ የተሰጠ ነፍሳዊ በረከት ነው። አገር በመውደድ ውስጥ ያለውን ደስታ ለማወቅ መጀመሪያ ራስን መውደድ ያስፈልጋል። ራስን መውደድ ሌሎችን ወደ መውደድና ወደማፍቀር ይተላለፋል፤ ይሄ ሂደት ያድግና ወደ አገር ፍቅር ይለወጣል።
አንድ ሰው በአእምሮም በስነ ልቦናም ሙሉ የሚባለው በዚህ ሂደት ውስጥ ሲያልፍ ነው። ጥልቅ በሆነ ጥላቻ አገራቸውን የሚጠሉ ወይም ደግሞ በሌሎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎች ራሳቸውን የማይወዱ ናቸው። በሕይወት ውስጥ ሁሉም ጥያቄዎች መልስ አላቸው፣ ሁሉም መልሶችም እንዲሁ ጥያቄ አላቸው። የትኛውም ጥያቄ፣ የትኛውም መልስ ግን እንደ አገርና ሕዝብ የመሆን ኃይልና አቅም የለውም።
ምክንያቱም አገር ማለት ሰው ማለት ነውና። ሰው ማለት ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ዘፍጥረትን አሊያም ደግሞ የፈላስፎችን እውነት አንብቡ። በዚህም አልን በዛ አገርና ሰው መዳፍና አይበሉባ ናቸው..ልክ እንደ አየር ማስገባትና ማስወጣት አንዱ ያላንዱ ሕልውና የለውም።
‹አገር ማለት ሰው ነው ያሉህን ተቀበል
ሰው በሞተ ቁጥር አገሬ ሞተች በል› ያለው ገጣሚው ከዚህ እውነት በመመንጨት ነው።
ታዲያ ይሄ ሁሉ የአገርና የሰውነት ቁርኝት እስከሞት ድረስ በሚያደርስ የሕይወት መስዋዕት የተገመደ ነው። ከዚህ እስከዛ የሚባል አጥርና ድንበር የለውም..ጉዳዩ አገርና ሕዝብ እስከ ሆነ ድረስ፣ አላማው ትውልድ ማዳን እስከሆነ ድረስ ለአገርና ሕዝብ የማይከፈል መስዋዕት አይኖርም። የአገራችን የማሸነፍ ሚስጢር አገርና ሕዝብ የተቆራኙበት የአንድነት አብራክ ነው። ኢትዮጵያ ታሸንፋለች..ግን እንዴት? ለሚለው ጥያቄ መልሱ አንድነት ነው።
አንድነት ስላችሁ ሌላው አገርና ሕዝብ እንዳለው አንድነት እያልኳችሁ አይደለም፤ በየትኛውም መመዘኛ ቢታይ የኢትዮጵያ አንድነት ከሌላው አገርና ሕዝብ አንድነት የተለየ ነው። ምክንያቱም እኛ በአንድነታችን አገር ነው የፈጠርነው። የነጻነት ምድርን ነው የገነባነው። ሌላው አገር በአንድነቱ የኢትዮጵያን ያክል አገር አልገነባም…ነጻነት አልሰራም። ዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ያለች በአንድነቷ አገርና ሕዝብ የገነባች አገር የለችም።
የእኛ አንድነት ዓድዋን ነው የሰራው። የእኛ አንድነት በካራማራና፣ በኡጋዴን ታሪክ ነው የጻፈው። ስለ አንድነት ስናወራ ስለኢትዮጵያዊነት እያወራን እንደሆነ ይሰመርበት። ዓለም ስለአንድነት ካወራ የሚያወራው ስለኢትዮጵያዊነት እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል። ምክንያቱም አገር ብለን ኢትዮጵያ ከማለትና አንድነት ብለን ኢትዮጵያዊነትን ከመጥቀስ የዘለለ ታሪክ ስለማይኖር ነው። በአንድነት የጻፍናቸው ብዙ ታሪኮች አሉን። ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት፣ ሕዝቦች አርነት የወጡበት በርካታ የአንድነት ገጾች አሉን። አሁን እንኳን ከጋራ ጠላታችን ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር በአንድነት እየተፋለምን ነው ያለነው። ኢትዮጵያ እንደምታሸንፍ እናምናለን ምክንያቱም በአንድነት ቆመናል።
አገራችንን ከአሸባሪው ሕወሓትና ከምዕራባውያን የሴራ ተንኮል ለመከላከል ትክክለኛ ጊዜ ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያ ታሸንፋለች የምታሸንፈው ግን ከላይ እንዳልኳችሁ በአንድነት ስንቆም ብቻ ነው። ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ አሁንም እንደምደግመው የአንድነትን ዋጋ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን በቀር የሚያውቀው አለ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም አብዛኞቹ ትላንታዊ በረከቶቻችን በአንድነት ስም የመጡ ስለሆኑ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ የተሸነፉ አገራት አንድነት የሌላቸው አገራት ናቸው።
ቀደም ባለው ጊዜ ጣሊያን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ያላት አገር ነበረች፤ በተቃራኒው እኛ ደግሞ ባህላዊ መሳሪያ እንኳን በቅጡ ያልነበረን ነበርን። በአንድነትና በአገር ፍቅር ስሜት ግን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ከታጠቀው ጣሊያን እንበልጥ ነበር። በዚህም ዘላለማዊ ታሪክ ጻፍን። ሌሎች ታሪኮቻችንን በአንድነታችን ስም የመጡ ነበሩ። አሁንም ኢትዮጵያን ለመታደግ በተፈጠረው የሕዝቦች ንቅናቄ የሕወሓትንና የምዕራባውያንን ተንኮል እንደምናከሽፈው ስነግራችሁ ከልቤ ነው። እየታገልን፣ እየሞትንና እየተንገላታን ያለነው አገርና ሕዝብ ለመፍጠር ነው።
የዚህ ጽሑፍ ትልቁ አላማ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች..ግን እንዴት? የሚል ነው። ኢትዮጵያ እንደምታሸንፍ አምነናል ማመን ብቻ አይደለም ተቀብለናል። ይሄ የማሸነፍ አቅማችን ከምን እንደሚነሳ ይሄንንም ተረድተናል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም እንደምታውቁትና እኔም እንደተረዳሁት ሁሌም ቢሆን በኢትዮጵያ ማሸነፍ ውስጥ የሕዝቦች አንድነት አለ። በዚህ አንድነታችን አሸባሪውን ሕወሓትንና የኃያላኖቹን ድብቅ ሴራ በጣጥሰን አገራችንን ወደ ከፍታ እንደምናሻግራት ስነግራችሁ ከልቤ ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም