በቅርቡ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ዙሪያ 12 ጊዜ ስብሰባ ማድረጉ ይታወቃል። በስብሰባዎቹ የኢትዮጵያ መንግሥትንና ትህነግን አስመልክቶ ሀገሮች የተለያዩ አቋሞችን አራምደዋል። በ11ኛው ስብሰባ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ወኪል አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ሀገራቸው በኢትዮጵያው ጦርነት ጉዳይ ለሕወሓት ድጋፍ ታደርጋለች መባሉ ፍጹም ስህተት እንደሆነ ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል። በእውነቱ በወቅቱ የሴትየዋን በስሜት የተሞላ ንግግር ለሰማ ሰው ውሸታቸውን ነው ለማለት በጣም ቢቸገር እንኳ አይገርምም።
ይህን የሴትየዋን ንግግር ውሸት መሆኑን ለማወቅ ብዙ ቀናት አልተቆጠሩም። እሁድ እለት ኖቬምበር 14 ቀን 2021 እ.ኤ.አ (ህዳር 4 ቀን 2014 በእኛ) የወጣው የታዋቂው የፖለቲካ (POLITICO) መጽሄት ዘገባ የአምባሳደሯ ንግግር ቅጥፈት እንደሆነ እና አሜሪካ ለሕወሓት ድጋፍ እንደምታደርግ እንዲሁም የአሜሪካ የእርዳታ ሥራ ለፖለቲካ አገልግሎት እንደዋለ የሚያመላክት ሆኗል።
Power moves: Samantha Power’s celebrity draws spotlight to USAID — and questions about her future በሚል ርእስ የወጣው እና በአሜሪካ የልማት ተራድአፖ ድርጅት መሪ ሳማንታ ፓወር የስልጣን ጥም ዙሪያ የሚያተኩረው ይህ ጽሁፍ ስለ ሳማንታ ፓወር እዩኝ እዩኝ ባይነት ብቻ ሳይሆን ስለ አሜሪካ አደገኛ አካሄድ እንዲሁም ለሕወሓት ስለምታደርገው ድጋፍ የሚያትት ነው።
ሌላውን ሀተታ ትተን እኛን ወደሚመለከተው ጉዳይ እንግባ። በዘገባው ውስጥ ሳማንታ ፓወር ከእርዳታ ድርጅት መሪነቷ ባለፈ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አንቶኒ ብሊንከንን የሥራ ድርሻ ሁሉ እየተጋፋች ፖለቲካውን እንደምትፈተፍት ለማሳየት የኢትዮጵያ ጉዳይ በማሳያነት ቀርቧል። አሳፋሪው ሥራዋ የሚታየውም እዚህ ላይ ነው።
ዱ ኖ ሀርም ‘Do no harm’ በሚል ርእስ በቀጠለው የዚሁ ጽሁፍ ክፍል ላይ አንድ አንጋፋ የዩኤስ ኤይድ ባልደረባ እንደተናገረው ወ/ሮ ሳማንታ ፓወር በአንድ የቢሮ ውይይት ላይ በትግራይ ክልል ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የዩ ኤስ ኤይድ ሰራተኞች የኢትዮጵያ መንግሥትን የማዋረጃ መንገዶች ይኖሩ እንደሆነ እንዲጠቁሟቸው ጠይቀዋል።
ልብ አድርጉ ፤ አሁን ፖለቲካ እንደነገረን ዋነኛ ሥራዬ እርዳታ ማዳረስ ነው በሚለው ዩ ኤስ ኤይድ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማዋረድ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር ፤ እቅድም ወጥቶ ነበር። አስደንጋጭ ነው። አምባሳደር ሊንዳ አሜሪካ ለየትኛውም ወገን እንደማታደላ በስሜት ሆነው ተናግረዋል። ነገር ግን ሌላኛዋ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር በበኩላቸው የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ክንፍ የሆነውን እና በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን የሚያንቀሳቅሰውን የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅትን ይዘው ሕወሓትን ወግነው የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማዋረድ ስብሰባ ተቀምጠው ነበር።
እንግዲህ እርዳታ ሰጪው ድርጅት ይህን ያህል በፖለቲካ ሥራው ውስጥ ተነክሮ ለሕወሓት ወግኖ የኢትዮጵያን መንግሥት ለማዋረድ ከተጋ መደበኛ ሥራቸው የፖለቲካ እና የጸጥታ ጉዳይ የሆነ ድርጅቶች የኢትዮጵያን መንግሥት ከማዋረድም ያለፈ ሥራ ሊሰሩ እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው።
በእርግጥ ሴትየዋ ስብሰባ ብቻም አይደለም የተቀመጡት። ከዚያም በኋላ እሳቸው ብዙ ተከታይ ባለው የትዊተር አካውንታቸው ፤ ድርጅታቸው በፕሬስ ክፍሉ በኩል ፤ ሚዲያውም በራሱ መንገድ የኢትዮጵያን መንግሥት ለማዋረድ የቻሉትን አድርገዋል። የአሜሪካ መንግሥት የፖለቲካ እና የደህንነት ክፍሎች ደግሞ የተቀናጀ ቅይጥ ጦርነት (hybrid war) ከፍተዋል።
እርግጥ የአሜሪካ እርዳታ መቼም ቢሆን ሰብዓዊነትን ብቻ ያነገበ እና ከፖለቲካ የጸዳ ሆኖ አያውቅም። ይሄ ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው። ነገር ግን በሳማንታ ፓወር ጊዜ ይህ ሁኔታ ተባብሷል። በፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ( ዩ ኤስ ኤይድ) የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት አባል የሆነ ሲሆን፣ ይህም አሜሪካ እርዳታን ለብሄራዊ ደህንነት ጥቅሟ ለማዋል መቁረጧን አመላካች ነው።
ሳማንታ ፓወር ከዚያም አልፋ ሄዳለች። ይህም በብዙዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል። የፖለቲካ ዘገባ እንደሚለው ከሆነ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የዩ ኤስ ኤይድ ሰራተኞች የሴትየዋ በፖለቲካው ውስጥ አላግባብ መነከር የኢትዮጵያን መንግሥት እንዳያስቆጣ እና ነገሮችን የበለጠ እንዳያበላሽ ሰግተዋል። በእርግጥም ነገሩ ከስጋትም ሳያልፍ አይቀርም። ፖለቲካ እንደሚለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወ/ሮ ፓወር አዲስ አበባ በመጡ ጊዜ ሊያገኟት ያልፈቀዱት የመንግሥታቸውን መከፋት ለመግለጽ ነው።
ይህ የወ/ሮ ሳማንታ ፓወር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍቆ መፈትፈት ለአንዳንድ የአሜሪካ መንግሥት እንደራሴዎችም አሳሳቢ በመሆኑ ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት ደርሰዋል። ለምሳሌ ያህል በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ውስጥ ካሉት አንጋፋ ሴነተሮች መሀከል አንዱ የሆኑት ሴነተር ጂም ሪች በሐምሌ ወር ውስጥ በተደረገ አንድ የሴኔቱ ስብሰባ ላይ ሳማንታ ፓወርን አስጠንቅቀው ነበር። ሴነተሩ በወቅቱ “የዩ ኤስ ኤድ አመራር ማንንም አትጉዳ የሚለውን መርሀችንን ተከትሎ እርዳታውን ማዳረስ ብቻ ነው ያለበት። የአሜሪካ እና ኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተመለከተ እሱን ለዲፕሎማቶቹ ተውላቸው” ብለው ነበር።
የሆነ ሆኖ ይህ ዘገባ ፍንትው አድርጎ የሚያሳየው የአሜሪካ መንግሥት አንድም ለሕወሓት ወገንተኛ ሆኖ ኢትዮጵያን እየታገለ መሆኑን ሲሆን፣ ሁለተኛም በሰብዓዊነት ስም የሚምሉ የሚገዘቱት የእርዳታ ድርጅቱ ሰዎች ከእርዳታ ያለፈ ሥራ እንደሚሰሩ ነው። በኢትዮጵያ በኩል ከዚህ ትምህርት ሊወሰድ የሚችለው ነገር የእርዳታ ድርጅቶች ሊታመኑ እንደማይገባ እና መንግሥት አሁንም እርዳታ ከማድረስ አልፈው የፖለቲካ ሥራ የሚሰሩ ሰዎችን ከሀገር የማባረር እርምጃውን ሊያጠናክር እንደሚገባ ነው።
የዩ ኤስ ኤይድ ቃል አቀባይ ለፖለቲኮ እንደተናገረው ከሆነ ፤ ወ/ሮ ፓወር አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠታቸውን ይቀጥላሉ። ይህም ማለት በእርዳታ ስም የሚደረገው ፍትፈታ ይቀጥላል ማለት ነው። ይህ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥትም ልታዋርደው ለተነሳችው ሴትዮ እና ለምትመራው ድርጅት ብሎም የነሱን ፈለግ ለሚከተሉ ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች ለሚሰጠው ምላሽ መዘጋጀት አለበት። ምክንያቱም ሴትየዋ በመናገር ብቻ አታቆምም። የኢትዮጵያን መንግሥት ለማዋረድ ስብሰባ የተቀመጠች እና እቅድ የነደፈች ሀገር ፣ ከተሳካላት የኢትዮጵያን መንግሥት ከስልጣን ለማውረድ አትመለስምና።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014