ዓለም ወደ አንድ መንደር በተጠቃለለችበት በዚህ ዘመን አፍሪካውያን አንድነት ሃይል፣ ህብረትም እንዲሁ የድል ምስጢር መሆኑን እምብዛም አልተረዱምና እርስ በእርስ ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር እጅግ ደካማ የሚባል ነው። በዚህ ሁኔታ አገራቱ በጋራ ከማበር ይልቅ የግል ብልጽግናቸውን በመሻታቸው ምክንያት በተለይም በኢኮኖሚው መስክ ዕድገታቸው የሚፈለገውን ያህል እንዳይሮጥ ጨምድዶ ይዞታል።
በአሁን ወቅት የድህነት ተምሳሌትነቷ ተቀይሮ የተስፋ ምድርነት መገለጫ በመሆን ላይ የምትገኘው አፍሪካ ለጋራ ትስስር ጉድለት የተለያዩ ችግሮች በምክንያትነት ይዘረዘራሉ። በተለይም በኢኮኖሚ ግንኙነት ረገድ አገራቱን ለማስተሳሰር የሚያስችል የአቬሽንና መሰረተ ልማት ውስንነትና እጦት ቀዳሚውን የማነቆነት ድርሻ ይወስዳሉ።
በእርግጥም በአፍሪካ የአቪዬሸን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት እጅግ ደካማ ነው። በአህጉሪቱ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር የሚደረግ ጉዞም አብዛኛው በቀጥታ በረራ ለመጓዝ የማይቻል፤እጅግ ረጅም፤አድካሚና ጊዜ አባካኝ ነው። ይህ ችግርም ዜጎች ከቦታ ቦታ በቀላሉ እንዳይንቀሳቀሱና አህጉሪቱ በተለይ በኢኮኖሚ ረገድ እርስ በእርስ እንዳትተሳሰርና ዕድገቷንም ፈጣን እንዳታደርግ አድርጓቷል።
ከዚህ በተጓዳኝ የንግድ እንቅስቃሴ በጎለበተባትና እጅግ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ በምትገኘው አፍሪካ ምድር የአገራትን የእርስ በእርስ ንግድ በማጠናከር ሂደት ለዓመታት ትልቅ ማነቆ ሆኖ የቆየው ዋነኛ ችግር እንደልብ ቪዛ የማግኘት ጉዳይ ነው።
በአፍሪካ ምድር ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ቪዛ ማግኘት እጅግ አሰልቺ፤ ምናልባትም በትንሹ ከሦስት እስከ አራት ሳምንት ድረስ መጠበቅ የሚጠይቅ ነው ። ይህ ፈተናም በተለይ ለአህጉሪቱ ንግድ ሰዎች ከፍተኛ ራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል።
ይህን እርስ በእርስ ያልተሳሰረ የጉዞ ችግር ለማስቀረት ታዲያ የአጉሪቱ የጋራ ተቋም የሆነው የአፍሪካ ኅብረት ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግና የተለያዩ እስትራቴጂዎችን ሲቀይስ ቆይቷል። በተለይ በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው 27ተኛው ጉባዔ ላይ የየቅል ጉዞን በማስቀረት ሁለንተናዊ ትስስርን መፍጠር ዓላማው ያደረገ አንድ የጋራ ፓስፖርትና በተለይም እኤአ በ 2018 የነፃ ቪዛ እንቅስቃሴን ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ አስቀምጧል።
በሁለተኛው ዕቅድም ድንበር አልባ አፍሪካን በመፍጠር በዜጎች መካከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ማጠናከር ዓላማው ያደረገ የአህጉሪቱ ዜጎች ካለ ቪዛ በነፃነት ከአንድ አገር ወደ ሌላ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችልና የሚፈቅድ ነበር።
ምንም እንኳን ተቋሙ የአንድ ፓስፖርትና የነፃ ቪዛ ዕቅድ ይፋ ካደረገ ዓመታት ቢያልፉም፤ዕቅዱን የማስተግበር እርምጃ ግን በሚፈለገው መጠን ሲጓዝ አልተስተዋለም። ይህ ማለት ግን ዕቅዱን እውን ለማድረግ የሚተጉ አገራት ፈፅሞ የሉም ማለት አይደለም።
በአሁን ወቅትም የነፃ ቪዛ እንቅስቃሴን የተገበሩ አገራት ወደ ሃያ በመቶ መጠጋታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። እነዚህ ድንበራቸው ከቪዛ ነፃ ያደረጉ አገራትም በተለይ የቱሪዝም ገቢያቸው በእጅጉ እንዲያድግ ማድረግ ችለዋል።
ይህን ተከትሎም የአህጉሪቱ ዜጎች ካለ ቪዛ በነፃነት ከአንድ አገር ወደ ሌላ በቀላሉ መንቀሳቀስ መቻል መጀመራቸው በሚነገርበት በዚህ ወቅት፤ኬንያና ሞዛንቢክ የነፃ ቪዛ ስምምነትን መፈፀማቸውን ዴይሊ ኔሽንን ጨምሮ ሌሎችም መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።
በኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና በሞዛንቢኩ አቻቸው ፍሊፔ ናዩሲ ፊርማ የተረጋገጠው ይህ ስምምነትም የየአገራቱ ዜጎችን ካለምንም የቪዛ ጥያቄ የመዘዋወር ነፃነት ከመስጠት ባሻገር የንግድ አጋርነቱን ማጎልበት ዓላማው ማድረጉም የካፒታል ኤፍ ኤም ዘገባ አመላክቷል።
ሁለቱ የታሪክ የባህል ተጋሪ አገራት በመካከላቸው ያለው ዝምድና እጅጉን የተቀራረበ ሲሆን በተለይ የሱዋህሊ ቋንቋ ተናጋሪ መሆናቸውና በመካከላቸው የቪዛ ጥያቄን ማስወገዳቸው የትላንት አብሮነታቸውን ነገም ለማስቀጠል የሚኖረው ሚና ግዙፍ መሆኑ ታምኖበታል።
የኬንያንና ሞዛንቢክን ተግባር ዋቢ በማድረግ አሁን ላይ እየወጡ የሚገኙ መረጃዎች ታዲያ አገራቱ የቪዛ ጥያቄን ማስቀረት ቢችሉ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን ሊያቋድሳቸው እንደሚችል በማመላከት ተጠምደዋል። በተለይ ቪዛን በቀላሉ ባለማግኘት መጎብኘት ያልቻሉ ዜጎች እንዲጎበኙና ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በማድረግ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸው መጎልበት ሁነኛ ፋይዳ እንዳለው ታምኖበታል።
ለዜጎቿ የሥራ ዕድል መፍጠር ራስ ምታት ለሆነባት አፍሪካ ይህ ሁኔታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ስራን ከሥራ ፈላጊዎች በማገናኘት በሚፈጠር የንግድ ግንኙነት አደገኛ በሆነ መልኩ በባህርና በበረሃ ወደ አውሮፓ የሚደረግን የስራ ፍለጋ በማስቀረት የበርካቶችን ህይወት የማትረፍ አቅሙም ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።
የነፃ ቪዛ ተግባራዊ መሆን ለአህጉሪቱ ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ ብዙ መሆኑን የመነገሩን ያህል አሉታዊ መዘዞች እንዳሉትም የሚናገሩ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እንደ እሳቤው አራማጆች ገለፃም፤የቪዛ ነፃነት ተግባራዊ መሆን ቀዳሚው ችግር የደህንነት ነው። አሸባሪዎች ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ይፈጥራል። የሰውና የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ሊጧጧፍ ይችላል።
ከዚህም በተጓዳኝ የሽብርተኝነት ጉዳይ ዋናውና አንገብጋቢው የነፃ ቪዛ ፈተና መሆኑም ተመላክቷል። በርካቶቹ የአፍሪካ አገራት ሽብርተኝነትን የመከላከል አቅማቸው ደካማ በሆነበት በዚህ ወቅት የነፃ ቪዛ መስተጋብር ተግባራዊ ማድረግ ከባድ ኃላፊነትን የሚፈልግ መሆኑን ታሳቢ በማድረግም ከሁሉ ቀድሞ የውስጥ ደህንነት እቅምን ለማጠናከር ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ተመላክቷል።
ሌላኛው ችግር የስደት ቀውስ መሆኑም ሲሆን ለአብነት የቪዛ ጥያቄን መቅረትን ተከትሎ በአንፃራዊነት በደሃ አገራት የሚገኙ ዜጎች በኢኮኖሚ ልዕልና ከፍተኛ ደረጃ ወደ ደረሱ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት በገፍ መጓዛቸው እንደማይቀርም ተሰግቷል። በዚህም ምክንያት በኢኮኖሚ የተሻሉ አገራት በርካታ ዜጎችን በመቀበል ከመጎዳታቸውም በላይ ዜጎቹን ለማስተናግድ ፍላጎት አይኖራቸውም።
አንዳንዶች እንደሚሉት በአንፃሩ ቪዛው ተግባራዊ ሲደረግ ማንኛውም ተንቀሳቃሽ ከየት ወዴት እንደሚሄድ በቂ መረጃ የሚያዝ ይሆናል። ይሁንና አሁንም ቢሆን በርካቶች በነፃ ቪዛው ላይ ሙሉ እምነት በመጣል ድንበራቸውን ለመክፈት ፈቃደኛ አይደሉም። ሁሉም አገራትም ይህን ተግባራዊ ማድረግ በሚችሉበት አቅምና ደረጃ ላይ አልደረሱም።
ይሁንና ለአፍሪካ ህዳሴና ሁለንተናዊ ዕድገት ከአብሮነት ውጭ አይታሰብምና አገራት ይህን ማጠናከራቸው የግድ ነው። ለነፃ ቪዛ ድንበራቸው በመክፈትና የእርስ በእርስ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ማጠናከራቸው ፋይዳው ሁነኛ ነው። አገራቱም ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ትክክለኛውና ወሳኝ ወቅት ላይ ይገኛሉ።
በተለይ ኅብረቱ እኤአ 2021 በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው ነፃ የንግድ ልውውጥ በእጥፍ በማሳደግ ወደ 28 በመቶ በማድረስ የድህነት ተምሳሌትነቷ፤ተቀይሮ የተስፋ ምድርነት መገለጫ በመሆን ላይ የምትገኘው አፍሪካም እድገት ፈጣን ለማድረግ እንደ ኬንያና ሞዛንቢክ ሁሉ ሌሎችም የነፃ ቪዛ አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግ ፋይዳው ነጋሪ አያሻውም ተብሏል። በእርግጥም የአገራት የቪዛ ጥያቄን ማስቀረት የ2063 የታሰበው በድንበር ያልታጠረችና የተሳሰረች አፍሪካ የመፍጠር አጀንዳ እውን ለማድረግ የማገዝ አቅሙ እጅጉን ግዙፍ ነው።
ታምራት ተስፋዬ