አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ወቅት የተጎናፀፈችው ድል በዓለም ላይ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ያገዘፈና የጥቁር ህዝቦች ታሪክ ያጎላ ክስተት መሆኑን ተገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በተለይም ለጋዜጣው ረፖርተር እንደገለፁት፤ በአድዋ ላይ የተካሄደው ጦርነት በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት መጠናቀቁና ጥቁሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በነጮች ላይ የበላይነት የተጎናፀፉበት በመሆኑ በርካታ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ፈጥረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአድዋ ላይ የተቀዳጀችው ድል በኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ መነቃቃትና የጀግንነት ስሜት የፈጠረ ሲሆን፤ በዓለም አራቱም ማዕዘናት ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦችም መነሳሳትን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከአድዋ ድል ማግስትም በአፍሪካ ጉዳይ እንደማትደራደርና የአህጉሪቱ መጪው ዘመን በብሩህ መሰረት ላይ የቆመ እንዲሆን በሰፊው ስትሠራ ቆይታለች፤ አሁንም እየሠራች ነው፡፡ በተለይም የጥቁር ህዝቦች የጭቆና ዘመን እንዲያበቃና የፓን አፍሪካኒዝም ስሜት በትልቁ እንዲጎላና የዓለም ጥቁር ህዝቦች የንቅናቄ መሠረት ሆኖ አገልግሏል፡፡
ከድሉ በኋላ ኢትዮጵያ ለዲፕሎማሲ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ ስትሠራ ነበር፡፡ ለአብነትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲመሠረት ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት፡፡ 56 ዓመታት ያስቆጠረው የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረትም ኢትዮጵያ በደማቅ ቀለም የሚፃፍ ታሪክ አኑራለች፡፡
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳይ የማይዋዥቅ አቋም እንዲኖራት አስችሏታል፡፡ ይህ በመሆኑም አድዋ ለአዲሱ ትውልድ የዲፕሎማሲ ድል ማስተማሪያና የአገራዊ ድል ማብሰሪያ ሆኖ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር