ዓለም በርካታ ጦርነቶችን አስተናግዳለች ፤ እያስተናገደችም ትገኛለች። ይሁንና ከጦርንት ምንም የሚተርፍ የለምና ሲያጎድል እንጂ ሲያተርፍ አይታይም። ኢትዮጵያም እንዲሁ ተገዳ በገባችበት ጦርነት የአገር ህልውናን ለማረጋገጥ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች። ‹‹የወደቀ እንጨት ምሳር ይበዛበታል›› እንዲሉ አበው በኢትዮጵያ ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ ላይ አፍጣጭ እና ገልማጮች በዝተዋል።
በተለይም ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያ ጉዳይ ጉዳያችን ነው በማለት በሚዲያዎቻቸው ሲያነሱ ሲጥሏት ይታያሉ። “ወፍ እንዳገሩ ይጮሃል” ነውና ተረቱ ፤የአንድ ሀገር መገናኛ ብዙሃን የሥርዓቱ ነጸብራቅ ስለመሆኑም ይታመናል። በመሆኑም ጦርነቱ በተጀመረ ማግስት ጀምረው የኢትዮጵያን እውነታ ወደ ጎን በመተው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲውተረተሩ ይታያሉ። የሐሰት ዘገባዎችን በሚዲያዎቻቸው በማቀነባበር ዓለምን ሲያሳስቱ ሰነባብተዋል።
እርግጥ ነው ለሀገራዊ ልማት መፋጠንና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው መጎልበት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ የመገናኛ ብዙሃን የመኖራቸውን ያህል፤ ሀገራትን ለከፍተኛ ቀውስና ዕልቂት የዳረጉ ሚዲያዎችም በዓለማችን ተስተውለው አይተናል። የመገናኛ ብዙሃን በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ መዋል ከቻሉ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ሁሉ፤ ያ ካልሆነና በተቃራኒው ሲውሉ የሚያስከትሉት አደጋ በቀላሉ የሚገመት እንደማይሆን መረዳት ይቻላል።
የትኛውም የጋዜጠኝነት መርሆች ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆን ፍትሐዊነት፣ ርትአዊነት፣ ትክክለኛነት፣ ተጨባጭነት… ወዘተ ከመርሆዎቻቸው ውስጥ በጉልህ የሚጠቀሱ ናቸው። ይሁንና ከሰሞኑ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተለይም የጋዜጠኝነት ‹‹ሀ…ሁ›› አስተማሪ ነን እያሉ የሚለፍፉቱ በሠሩትና እየሠሩ ባሉት ዘገባ የኢትዮጵያን እውነት አሽቀንጥረው እየጣሉ ነው። ይህም ማንነታቸውና የቆሙለት ዓላማ ፍንትው ብሎ እንዲታይ እያደረገ ነው ።
የምዕራባውያኑ ሚዲያዎች መሬት ላይ ያለውን እውነታ አርቀው ለመቅበር በተጉ ቁጥር ፍላጎታቸው ይበልጥ ተጋልጧል። ከፍላጎቶቻቸው እንዱም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራትን የማይፈልጉ እንደሆነ ግልጽ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያታቸው ኢትዮጵያዊነት የጥቁር ህዝቦች ነፃነት መገለጫ ዓርማ፤ የአልበገር ባይነት ምልክት፤ የነጮች የበላይነትን ማርከሻ መድሃኒት መሆኗ ነው። ይህ ታሪክ የሚጎረብጣቸውና ምቾት የሚነሳቸው ምዕራባውያኑ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል ፤ አሁንም እያደረጉት ነው።
ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ፈተናም እንደ ጥሩ ዕድል ተጠቅመው ከአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጋር በማበር አገር በማፍረስ ዘመቻ ላይ ተጠምደዋል። የአገሪቷን ህልውና በመናድ የሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት አጥፍቶ ሕዝቡ እርስ በእርሱ ሲባላ ዳር ቆሞ ለመመልከትና በእሳቱም ለመሞቅ ቋምጠዋል።
ምዕራባውያኑ ለአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት የሆነች እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገርን አፍርሰው እንደ አዲስ ሊሠሯት ካልሆነ በቀር እንድትኖር አይፈልጉም። ይህን ፍላጎታቸውን ተግባራዊ ለማድረግም ሚዲያዎቻቸው ዋነኛ መሳሪያዎች ናቸው። ከሰሞኑም ሚዲያዎቹ በሠሯቸው የሐሰት ዘገባዎቻቸው የመንግሥታቱ ፍላጎቶች ማስፈጸሚያ ስለመሆናቸው በግልጽ ታይቷል። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሟጋች ነን በሚል ሽፋን ኢትዮጵያን አፍርሰው መልሰውም በሚፈልገው መንገድ ለመሥራት እየሞከሩ ነው።
ለዚህም የኢትዮጵያን ጉዳይ ጉዳያችን ነው በሚል ከጋዜጠኝነት መርህ ባፈነገጠ መንገድ አጀንዳ እየቀረጹ ኢትዮጵያን የሚያጠለሹ ዘገባዎችን መዘገባቸው አንዱ ማሳያ ነው። አሸባሪው የትህነግ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ክህደት መነሻ ያደረገው ህግ የማስከበር ዘመቻ ወደ ጦርነት እንዲቀየርና አገሪቱ ወደ ለየለት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ምዕራባውያኑ በሚዲያዎቻቻው አማካኝነት ሰፊ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።
በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያወጧቸው ዘገባዎች ተዓማኒነት የጎደላቸውና ከባድ ጥያቄ የሚነሳባቸው እየሆኑ መምጣታቸው የአደባባ ምስጢር ነው ነው። እንዲህ ዓይነቶቹን ዘገባዎች አንዳንድ ወገኖች “ፌክ ኒውስ” የሚል ሥያሜ ሲሰጧቸው ሌሎች ደግሞ “ዲስኢንፎርሜሽን” ሲሏቸው በተለያዩ ወገኖችም ሐሰተኛ መረጃ፣ ሐሰተኛ ዘገባና፣ የተዛባ መረጃ፣ ወዘተ. እየተባሉ ይፈረጃሉ። ታድያ እነዚህ የግጭቱን ሁኔታ የሚቃኙ መረጃዎች በሙሉ ዓላማቸው አንድና አንድ ኢትዮጵያ የምትባል ታላቅ አገርን ለማፍረስ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው።
አሸባሪዎቹ ሸኔ እና ትህነግ አዲስ አበባን ሊቆጣጠሩ ተቃርበዋል፣ ከተማዋን ከበዋል፣ ባለሥልጣናት ከአገር እየወጡ ነው ከሚለው የሰሞኑ የሐሰት ዜናዎች ጀምሮ ኢትዮጵያ በቅርቡ ያጸደቀችውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማስታከክ አሁን ደግሞ “በኢትዮጵያ የብሔር ማንነትን የሚገልጽ መታወቂያ ግዴታ ሆኗል” ሲሉ እየተሰሙ ነው። የብሔር ማንነትን ከመታወቂያ ደብተር ላይ ለማስወገድ እየሠራች ያለችውን ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ መዘገባቸው የምዕራቢያኑ መገናኛ ብዙሃኑን ስህተት ከማጋለጡም ባለፈ የጣቢያዎቹን ወገንተኝነትን በግልጽ ያሳየ ነው።
ሲ ኤን ኤ ፣ ሮይተርስን ጨምሮ ሌሎች የውጭ ሚዲያዎች አገር ለማፍረስ ሁሉን ትቶ መቀመቅ የገባውን አሸባሪ የትህንግ ቡድንን በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ዘመቻ እያደረጉ ይገኛሉ። በይህ ሁሉ የግጭቱን ሁነት በተዛባ መንገድ ለማሳየት የሚሠራው ዘገባና ሀተታ የፕሮፓጋንዳ ግብ ያለው ስለመሆኑ መንገር የሚያስፈልገው አይደለም።
ሰብዓዊ ድጋፍ እናደርጋለን፣ ንጹሐንን እናወጣለን፣ እናግዛለን በሚል ሰበብ ወደ ውስጣችን ለመግባትና ያሻቸውን ማድረግ እንዲችሉ አጋጣሚውን የመረጡት ምዕራባውያኑ ጣልቃ የመግባት ሙከራቸው የሚሳካላቸው አይደለም። ይሁን እንጂ አካላዊ ከሆነው ጦርነት በበለጠ ጦርነቱን ሥነልቦናዊ በማድረግ በየዕለቱ በሚፈበርኩ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች ህዝቡን ውጥረትና ሽብር ውስጥ የመክተት ዓለማ ያነገቡ ናቸው።
እውነታው ግን ከዚህ የተለየ መሆኑ ነው። ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ላይ እየፈጠሩ ያሉትን ጫናዎች በመረዳት እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ምላሽ ለመስጠት በአንድነት መነሳታቸው ፣ በተለይም አሸባሪው የትህንግ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል እንዲሁም እየመጣ ያለውን አደጋ ከወዲሁ ለመቀልበስ ወጣት አዛውንቱ፣ ሴት ወንዱ እንዲሁም አረጋውያን ሳይቀሩ አገሬ የጠላሽ ይጠላ በማለት አጸፋውን ለመመለስ መዘጋጀታቸው ነው። ሕዝባዊ ንቅናቄውም ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተስተጋባ ባለበት በዚህ ወቅት በዘር ፖለቲካ ተለያይቶ የነበረው ኢትዮጵያዊነትም ወደ ቀደመው ማንነቱ የመመለስ ዕድል አግኝቷል።
ኢትዮጵያ በቀደመው ታሪኳ ቅኝ ያልተገዛች ነፃ አገር መሆኗ የቆጫቸው ምዕራባውያኑ በተለያየ መንገድ እያደረሱት ካለው ዘመናዊ ባርነት ባለፈ ለህመማችሁ ፈውስ፤ ለችግሮቻቹ መፍትሔ ያለው እኛው ጋር ብቻ ነው። በማለት ጉዳያችንን ጉዳያቸው አድርገው አዛኝ ቅቤ አንጓች እንዲሉ በለመዱት ቅኝ አገዛዝ አፍሪካን ለመቀራመት ኢትዮጵያን ዋነኛ መሳሪያ አድርገው ሊያፈርሷት ቢያሰፈስፉም ህልማቸው ቅዠት ይሆን እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም።
ታድያ ከሰሞኑ ኡጋንዳዊው ጋዜጠኛ ጦርነቱ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት እየተዋጋች ነው ማለቱም ለዚሁ ነው። ቅኝ ግዛት የአፍሪካ ካንሰር ነው። አፍሪካ እንዳታድግ ሰቅዞ የያዛት በእጅ አዙር እየተካሄደ ያለው የቅኝ ግዛትና የባርነት መንፈስ የተሞላው የምዕራባውያኑ ፖሊሲና አካሄድ ለአልበገር ባዮቹ ኢትዮጵያውያን ግልጽ ነው። ስለዚህ አፍሪካውያን ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያለችው የአፍሪካን ጦርነት መሆኑን በመረዳት በቻሉት ሁሉ ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆሙ ይገባል።
በደም የተጻፈው ደማቅ ኢትዮጵያዊ ጀግንነት በተራ ፕሮፓጋንዳ አይደበዝዝም!
መልዕክታችን ነው።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ህዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም