አዲስ አበባ፡-ወጣቱ የአድዋ ድል ለአገ ራዊ አንድነት የማያልቅ ስንቅ መሆኑን በመገንዘብ የአባቶቹን ለአገራዊ አንድነት በጋራ የመቆም እሴትን ጠብቆ መራመድ እንዳለበት ምሁራን ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተርና የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር አህመድ ሀሰን እንደገለጹት፣ ከወታደራዊ ድል ባሻገር አገራዊም ሆነ ታሪካዊ እሳቤው ትልቅ ነው፡፡ዘላለማዊ ነጻነት፣ኢትዮጵያዊ አንድነት በማጠናከር በኩል ጉልህ ሚና አበርክቷል፡፡
ወጣቱ አያቶቼና ቅድመ አያቶቼ በአንድነት ታግለው የውጭ ወራሪውን ድል መንሳታቸውን የገለጹት ዶክተር አህመድ፣ የአድዋን ድል ታሪካዊ አሻራውን ጠብቆ እንዲሄድ መንግስት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር፣የወጣቱን መልካም ሰብዕናን መገንባት፣ታታሪ መሆንና አገራዊ አንድነትን ማላበስ ይገባል፡፡
በሀረማያ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁሩ ዶክተር መሀመድ አሊ የአድዋ ድል የፖለቲካ አመለካከት፣የሀይማኖትና የብሄር ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተው አንድ የምታደርገቸውን አገር ኢትዮጵያን ብለው የዘመቱበት ነው፡፡ድሉም የአገራዊ አንድነት ትልቁ ማሳያ በመሆኑ አሁን ያለው ትውልድ በድል በዓሉን ከማክበር በተጓዳኝ አንድነቱን ጠብቆ የጋራ ጠላታችን በሆነው ድህነት ላይ በጠንካራ የስራ መንፈስ መዝመት አለበት ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ብዙ ችግር ሲያጋጥም እንኳ ኢትዮጵያዊነት በጠንካራ መሰረት የተገነባ በመሆኑ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን አልፋለች ያሉት ምሁሩ፣ ይህም የህዝቦች መስተጋብር የማይበጠስ መሆኑን ያሳያል፡፡በቀጣይም ህዝቦች የሚከባበሩበትና የሚፈቃቀሩበት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከመገንባት አኳያ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡የአሁኑ ትውልድ ከአባቶቹ የተረከበውን ለውጭ ሃይል የማይደፈር ጠንካራ አገር ለመጪው ትውልድ ጠብቆና አበልጽጎ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአክሱም ዩኒቨርስቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር አቶ ግርማይ ሀላፎም፣ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት የጎላ አስተዋጸኦ እንዳለው አውስተው፣ ጀግኞች አባቶቻች ከደቡብ፣ከምስራቅ፣ከሰሜን፣ከምዕራብና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ልዩነታቸውን በመተው ለአገር ሉዓላዊነት በአንድነት የተሰለፉበት የጦር ግንባር ነው፡፡የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን ብሄራዊ መግባባትና አገራዊ አንድነት አንዱ ስንቅ ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡
‹‹ የአድዋ ድል አባቶቻችን የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ፣ትራንስፖርት፣መረጃና መሳሪያ ሳይኖር ከሀረር ፣ከሶማሌ ፣ከሞያሌ፤ከወለጋ፣ ከጅማና ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል ሳይቀር ረጅም ኪሎ ሜትር በእግራቸው ተጉዘው ከወራሪ ሀይል ጋር ጦርነት በመግጠም ድል የነሱበት መሆኑን ገልጸው ድሉም የዓላማ ፅናታቸውን፣ ቁርጠኝነታቸውን፣ አንድነታቸውንና የአገር ፍቅር ስሜታቸውን በተግባር ያረጋገጡበት ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድም ከአባቶቹ በመማር በተሰማራበት መስክ ሁሉ ለአገሩ ብልፅግና መትጋት ይኖርበታል ሲሉ መክረዋል፡፡
የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ አንድነት ስንቅ ብቻ ሳይሆን በቅኝ ግዛት ለነበሩ ሀገሮች የነጻነት ተምሳሌት ነው ያሉት ምሁሩ፣ጦርነቱ የተካሄደው ለእኩልነት፤ ለፍትህ፣ ለሉዓላዊነትና ለነጻነት በመሆኑ አገራዊ አንድነትን ማምጣቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለአፍሪካ አንድነትም የበኩሉን ሚና ተጫውቷል ፡፡ወጣቱም የአድዋ ድል ታሪኩን አውቆና አጥንቶ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍና የኢትዮጵያ አንድነትና ብልጽግን አረጋግጦ በመሄድ የራሱን ታሪክ አሻራ ማስቀመጥ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የዛሬ 123 ዓመታት በፊት በአድዋ ጦርነት ጊዜ ከንጉሱ ጋር የተጣሉና ያኮረፉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሳይቀር ለሀገር ልዕልና አንድነት በጋራ ዘምተው ወራሪውን የውጭ ኃይል ድል አድርገዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
ጌትነት ምህረቴ