የ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በለውጥ ላይ ነው። ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችል አስተሳሰብ መፍጠርን ተቀዳሚ ዓላማው አድርጓል። ይህን ተከትሎም ለሰራተኞቹ አነቃቄ ሃሳቦችን ሊመግብ መጋቤ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁን በእንግድነት ጋብዟቸው ነበር። ባለፈው ሳምንት በክፍል አንድ «አዲስ ሃሳብ የሌለው አዲስ ሰው መሆን አይችልም» በሚል ገዥ ርዕስ አዕምሯችንን መግበውናል።
በተለይም በተለያዩ ሙያዎችና ሃላፊነቶች ተቋማትን ያገለገሉ ሰዎችን እውቅና መስጠት ሌሎች እንዲበረታቱ፤ እውቅና የተሰጣቸውም በማገልገላቸው ኩራት እንደሚሰማቸው እንደሚያደርግ ነግረውናል። ስለ ጭብጨባና መድረክ፣ ስለመለወጥ በማንሳትም ማራኪ የአዕምሮ ምግብ ያካፈሉንን አካፍለናችኋል። ለዛሬም ክፍል ሁለትን ይዘን ቀርበናል።
ለዩኒቨርሲቲዎች እና ለተማሪዎቻቸው
አንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ሲመሰረት የሚያስፈልገው ነገር ተሟልቶ ነው፤ ለምሳሌ ዳቦ ቤት ሲከፈት ለዳቦ የሚያስፈልጉ ነገሮች መሟላት አለባቸው። የሚቀጠሩ ሰራተኞችም ሥራው የሚፈልገውን አይነት ሥርዓት መከተል አለባቸው። ለዳቦ መጋገር የሚቀጠሩ ንጽህናቸውን መጠበቅ አለባቸው። የትምህርት ተቋማት ሲመሰረቱ ጥሬ ዕቃቸው የተማረ መምህርና የተማረ ተማሪ መሆን አለበት። ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ላይ ነው ማተኮር ያለባቸው፤ ግን ፖለቲካው ተጭኗቸዋል። በውጭ አገራት የአዲስ ነገር መገኘት ዜና የሚሰማው ከዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲ የሃሳብ ማፍለቂያ ነው፤ የግኝት ቦታ ነው መሆን ያለበት። ይህ እንዲሆን ግን ዩኒቨርሲቲዎቻችን ላይ በሚገባ አልተሰራም። ሚዲያው የሚጠበቅበትን አልሰራም፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያው ሃላፊነቱን አልተወጣም፤ የሃይማኖት አባቶች አልሰሩም።
እዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማንበብ አለባቸው። የሚያነብ ሰው ያስተውላል፤ የማንም የሃሳብ መስጫ ሳጥን አይሆንም፤ ወደነዱት አይነዳም። ወጣቶች የፌስቡክ ሰለባ እየሆኑ ነው። አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለዕረፍት ቤተሰብ ጋር ሲሄድ ሞፈር ቀንበር ብርቅ ሆኖበት ከሞፈር ጋር ፎቶ ይነሳል። ያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እኮ ሞፈርን በሌላ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ነበር መቀየር ያለበት።
አሁን ያለው ድንጋይ የሚወረውር ወጣት ነው። ይሄን መቀየር የሚቻለው በትምህርት ስለሆነ ትምህርቱ ላይ መሰራት አለበት። ከምንም ነገር በላይ አስተሳሰባችን መቀየር አለበት። ብዙ ጊዜ በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ‹‹ሲስተም ጠፋ›› ሲባል እንሰማለን። የጠፋው ግን የጭንቅላት ሲስተም ነው። ድሮ አባቶቻችን አሳቢ ነበሩ።
አጼ ምኒልክ የዓድዋን ዘመቻ ሲጠሩ እንደአሁኑ ሞባይል አልነበረም፤ ሬዲዮ እንኳን አልነበረም። ነገር ግን በአንዲት አዋጅ ብቻ መላው ኢትዮጵያውያን መልእክቱ ደርሶት ዘመቻው ላይ ተሳትፏል። መሪዎችን እንደሰው መቀበል መልመድ ኢትዮጵያውያን ያለብን ችግር መሪዎቻችንን እንደሰው የመቀበል ልምድ የለንም። መሪዎች መላዕክትም አይደሉም፤ ሰይጣንም አይደሉም፤ ሰው ናቸው። እንደ መላዕክት ካየናቸው ለወቀሳአይመችም።
እንደ ሰይጣንም ካየናቸው ለምስጋና አይመችም፤ መሪዎቹ ሰው ናቸው። አጼ ኃይለሥላሴ ወይም መንግስቱ ኃይለማርያም ወይም አቶ መለስ ዜናዊም ሆኑ ዶክተር አብይ ገብርኤል ወይም ሚካኤል አይደሉም፤ ሰው ናቸውና ይሳሳታሉ። ሰው ማለት ደግሞ የሚሳሳት፣ የሚያለማ፣ የሚያጠፋ ማለት ነው። ከሚያጠፋው የሚያለማው ይበለጥ ነው መባል ያለበት። ሰው ሆኖ ምንም ካላጠፋማ እንዲያውም ሌላ ጣጣ ነው የሚያስነሳው።
መቶ በመቶ ትክክል ከሆነ ሰው ነው? አይደለም? የሚለው ሊመረመር ይገባል! ብዙ ጊዜ ባልና ሚስት እየተጠናኑ ነው ሲባል ይገርመኛል። የሰው ልጅ ተጠንቶ አያልቅም። መቶ በመቶ ማወቅ አለብኝ ከተባለ ወይ ማበድ ወይም መፋታት መምጣቱ አይቀርም። ስለዚህ በሰው ልጅ ባህሪ ውስጥ ያለውን ነገር መረዳት ነው። መሪዎችንም እንደሰው ነው ማየት ያለብን። አገራችን ውስጥ ህጉ እንኳን የኃይለሥላሴ ህግ፣ የደርግ ህግ፣ የኢህአዴግ ህግ እየተባለ እንጂ የኢትዮጵያ ህግ እየተባለ አይጠራም። አሜሪካ ውስጥ የትራምፕ ህግ፣ የክሊንተን ህግ የሚባል የለም፤ ያለው የአሜሪካ ህግ ነው። ይሄንን ነው መልመድ ያለብን። ህግ ሊመራን ሲገባ እኛ ህግን እየመራን ነው ማለት ነው።
የጋራ የሆነ ነገር ያስፈልገናል
በአገራችን የጋራ የምንላቸውን ነገሮች በጣጥሰን ጥለናቸዋል። ከአገሪቱ ከተለያየ አካባቢ የሚመጡ ወጣቶች ልክ ከሌላ አገር የሚገናኙ ያህል ሆነዋል። ፖለቲከኞች በሃሳብ መከራከር ሲያቅታቸው ሃሳባውያንን መምታት ነው የሚፈልጉት፤ በዚህ የጋራ የሆነ ነገር አጥተናል። አመጽ እንደማያዋጣ ከሌሎች ማየት ነበረብን። እነ ደቡብ ሱዳን 99 በመቶ እንገንጠል ብለው ወስነው ነበር፤ ዛሬ ቢጠየቁ ይቆጫቸዋል፤ የሊቢያ ህዝብ ጋዳፊን ለመጣል ከምዕራባውያን ጋር መረጃ እየተለዋወጠ አስደብድቦ ነበር፤ ዛሬ ጋዳፊ ሊቢያ ውስጥ ቢመጣ እንደ ፕሬዚዳንት ሳይሆን እንደ አምላክ ነበር የሚታየው። ሊቢያውያን ዛሬ የከፋ ድህነት ላይ ናቸው።
ሕዝብ ለውጥ አያመጣም አዲስ ሃሳብ ስለሆነ ልትበሳጩ ትችላላችሁ፤ እኔ ግን የለውጥ ሃይል ህዝብ ነው ብየ አላውቅም። በፖለቲካም ይሁን በሳይንስና ቴክኖሊጂ መሪዎች አሉ። እነዚህ መሪዎች በተለያየ ሁኔታ ራሳቸውን ያበቁ ናቸው። ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ ብዙ የቴክኖሊጂ ፈጠራ አለ፤ በዚያ ዓለምን እየመሩ ነው። ፌስቡክንየፈጠረው ሰው ይሄው እኛን እየመራ ነው። ይሄ ሲሆን ግን የአሜሪካ ህዝብ በሙሉ ሳይንቲስት ነው ማለት አይደለም፤ በየዘመኑ እንዲህ አይነት ጀግኖች አሉ። እንደ ጨው ሟሙተው፣ እንደቅቤ ቀልጠው እንዲህ አይነት ታሪክ የሚሰሩት ውስኖች ናቸው። እዚህ ላይ ነው ምሁራን መስራት ያለባቸው። ምሁራን ማስተማር፣ አዳዲስ ነገር ማሳየት አለባቸው። ገበሬው አፈር ገፍቶ፣ እጅና እግሩ እየተላላጠ ያስተማረው ልጁ ሞፈርን በትራክተር መቀየር ነበረበት። ይህን ለማድረግ እንግዲህ ገና የተማሪውና የምሁራኑ ጭንቅላት መታረስ አለበት ማለት ነው። ጭንቅላት ይታረሳል። አንዳንዱ ግን ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ጭራሽ ጭንቅላቱ ጫካ ሆኖ የሚወጣ አለ።
16 ዓመት ሙሉ ትምህርት ላይ ቆይቶ ጭንቅላቱ ምንም ያልተዘራበት ሆኖ ይገኛል። ምሁራን ገለልተኛ መሆን የለባቸውም፤ ማንም ከአገር ጉዳይ ገለልተኛ ሊሆን አይችልም። አገር ሲኖር ነው ሁሉም ነገር የሚሆነው። አገር ከሌለ ማንም ሊኖር አይችልም። ለማበድ እንኳን አገር ያስፈልጋል። ምሁራንም ሆኑ የሃይማኖት አባቶች ገለልተኛ ሆኖ መኖር አይቻልም። በአገር ጉዳይ ላይ ማንም ነው መሥራት ያለበት፤ የአስተሳሰብ ቀረጻ ላይ መሰራት አለበት። አንድ ኢትዮጵያዊ አሜሪካ ውስጥ ቢያብድ ማደንዘዣ ተወግቶ ቦሌ ይጣላል። አንድ ሰው ‹‹እግዚአብሔር የለም›› ማለት ይችላል፤ ‹‹ኢትዮጵያ የለችም›› ማለት ግን አይችልም። እግዚአብሔር የለም ቢል የሚመጣውን ራሱ ይቀበላል፤ ኢትዮጵያ የለችም ካለ ግን ሀገሩን ለቆ ኬንያ መግባት አለበት።
በሌለች አገር ታዲያ እንዴት ይኖራል? ከራስ ጋር መታረቅ ሰውን ማኩረፍ በጣም ቀላል ነው፤ ራስን ማኩረፍ ግን ትልቁ ችግር ነው። ከራስ ጋር መጣላት ነው ለብዙ መጥፎ ነገር የሚዳርገው። አንዳንዱ ማታ ሲስቅ አምሽቶ ጠዋት ሲነሳ ይጨፈግጋል፤ ምን ሆነህ ነው? ቢባል መልስ የለውም፤ ለዚህ ነው ሰው አይጠናም ያልኩት። ባሌን እያጠናሁ ነው ይላሉ እህቶች፤ 40 ዓመት ብታጠኝው አታውቂውም፤ አብሮ ሆኖ መግባባት ነው የሚበጀው። ፍቅር ወጪ ቆጣቢ ነው ሰው ሲጣላ ዱላ ይቆርጣል፤ ከተማ ከሆነም ብዙ ሺህ ብር አውጥቶ ሽጉጥ ይገዛል።
ሰባት ኩንታል ጤፍ መግዛት ሲችል አንድ ሽጉጥ ገዝቶ ሰው ይገልበታል። በቴስታ ቢመታቱ እንኳን ሁለቱም ተጎጂ ናቸው። ግን ተመችው ይበልጥ ይጎዳል፤ መችው ብዙም አያመውም፤ ብትሩ እኩል ነው፤ ግን መችው የመችነት ወኔ አለኝ ስለሚል ነው የሚደሰተው። መንግስት ብዙ ከባድ የጦር መሳሪያ እየገዛ ነው፤ ብንግባባ ግን የዳቦ መግዣ ይሆነን ነበር። የታንክ መግዣውን ትራክተር መግዣ ማድረግ ይቻል ነበር። ኢትዮጵያና ኤርትራ ሲዋጉ ብዙ ብክነት ደርሷል፤ ለጦር መሳሪያ ግዥ ብዙ ወጭ ወጥቷል፤ ዶክተር ዐብይ አህመድ ለፍቅር ሲሄዱ ግን ምንም የወጣ ወጭ የለም፤ ምናልባት የአውሮፕላን ነዳጅ ተሞልቶ ቢሆን ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011