በቅርቡ የታሰረ የቅርብ ጓደኛችንን ለመጠየቅ ከጓደኞቼ ጋር ወደ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ሄደን ነበር፡፡ እስረኛው ሲታሰር ያስረከባቸውን የቤት ቁልፍ እና ሌሎች መሰል ዕቃዎች ለቤተሰቦቹ ለማስረከብ ተፈቅዶለት በፖሊስ ታጅቦ ዕቃው ወደ ተቀመጠበት ክፍል እየሄድን ነው፡፡
በመሀል በዕድሜ ጠና ያለች ሴት በቁጣ ተመለሱ አለችን፤ ቁጣው ስድብ መሰል ነገር የተቀላቀለበት ነበር። ሴትዬዋ በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ያላትን ኃላፊነት አላውቅም፤ የለበሰችውም የሲቪል ነው፡፡
እኛ ግን በትህትና ‹‹እቃ ለቤተሰቡ እንዲሰጥ ተፈቅዶለታል›› አልናት፡፡ አሁን ደግሞ በቁጣው ላይ ግልምጫ ጨመረችበት ፤ገፈታተረችንም፡፡ እስረኛው ‹‹አይ! ሰኞ ፍርድ ቤት ትቀርባለህ ስለተባልኩ…›› የአፉን ሳይጨርስ ‹‹ማን ነው የሚያቀርብህ! ደግሞ አንተ ነህ የምታውቀው!…›› እያለች እሱንም ቁጣ በተቀላቀለበት ሁኔታ ገፈተረችው። ፖሊሶች ዕቃ ሊረከብ መሆኑን አስረዷት፤ ሌላ ቀን አለቻቸው፡፡ ልጁ ተመልሶ እንዲገባ አደረጉት፡፡ ዕቃውንም ሳንወስድ ቀረን፡፡
የገረመኝ ነገር እኛ ምንም ሳናጠፋ ያ ሁሉ ቁጣ እና ግልምጫ አንዴት ሊወርድብን ቻለ? የገባነው ተፈቅዶልን ነው፤ ያስገቡንም ፖሊሶች ሆነው ሳለ ያ ሁሉ ግልምጫ ለምን አስፈለገ? ይቻላል ብሎ መስጠት፤ አይቻልም ከሆነም የማይቻልበትን ሁኔታ አስረድቶ መከልከል አይሻልም ነበር? በትህትና መጠየቃችን ለግልምጫና ስድብ ሊዳርግን አይገባም ነበር፡፡
ፖሊስ ጣቢያ እና እስር ቤት አካባቢ ይህን ዓይነት ነገር ሲፈጸም ብዙ ጊዜ ተመልክቻለሁ፡፡ እዚህ አካባቢ የሚሄድ ሰው ከመረጃ እጥረት ጋር በተያያዘ አገልጋዮችን ሊያሰለች ይችል ይሆናል፡፡ እስር ቤት ውስጥ አንዲቆይ የሚደረገው ሌባ እና ብዙ ስነ ምግባር የጎደለው ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህ እስረኞች መሰረታዊ ችግር ስላለባቸው ቢናገሩ አይሰሙም ተብሎ ከሆነ ስህተት ነው፡፡
ከዚህ ውጪ ሰዎች በአጋጣሚ ለእስር ሊዳረጉ ይችላሉ፤ የሆነ ወንጀል ተፈጽሞ ጉዳዩ እስከሚጣራ ድረስ በሚል በአካባቢው የተገኙ ሁሉ ሊታሰሩ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ ግለሰቦች ላይ እንደተለመደው ችግር መፍጠር ተጠያቂ መሆንና ለቅጣት መዳረግም ሊከተል ይችላል፡፡ የታሰረው ሁሉ ስነ ምግባር የጎደለው ነው ብሎ መደምደም ግን አይገባም፤ ይህ ዓይነቱ የእስረኞች እና ጠያቂዎች አያያዝ አንድ ቀን ሊያስጠይቅ እንደሚችል መረዳት ተገቢ ነው፤ እስረኛውን አጥፊ የሚለው ፍርድ ቤት ነው፡፡ እዚያው ድረስ ግን መያዝ ያለበት በስርዓት ነው፡፡
የስነ ምግባር ችግሩ የሚታየው በአገልጋይ በኩል ብቻ አይደለም፤ በተገልጋዮች በኩልም ችግር አለ፡፡ በአንድ የግል ባንክ ውስጥ የተመለከትኩት ነገርም ለእዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ አራት ኪሎ አካባቢ ነው፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ ዘራፍ ባዩ ደንበኛ ነው፡፡ ያው እንግዲህ በየባንኩ ደንበኞች የሚስተናገዱት በወረፋ ነው፡፡ ተራ ቁጥር ይሰጣል። በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፡፡ አንድ ተገልጋይ ቁጥሩ ሲጠራ ወደ ተጠራበት መስኮት ሄዶ ነው መገልገል ያለበት፡፡ አንድ ተገልጋይ ከዚህ ወጣ ያለ መንገድ ለመጠቀም ፈለገ፡፡ ሳይጠራ ሠራተኛ ወደሌለው መስኮት ሄደ፡፡ ሁኔታው ግራ የገባው አንድ የባንኩ ሠራተኛ ተገልጋዩን ጠራው፡፡ ተገልጋዩም የሞላውን ቅጽ ለጠራው ሠራተኛ ለመስጠት እጁን ሰነዘረ፡፡
ሠራተኛውም ‹‹አይ ምናልባት ብር ለመዘርዘር ወይም ለሌላ ቀላል ጉዳይ መስሎኝ ነው፤ ለሌላ አገልግሎት ከሆነ ቁጥርህ እስኪጠራ ጠብቅ›› አለው፡፡ የባንኩ ሠራተኛ ትኬቱን ተቀብሎ ሲያይ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ ‹‹አይቻልም›› ብሎ ከለከለው፡፡
ደንበኛው ‹‹ታዲያ ለምን ጠራኸኝ?›› ብሎ መቆጣት። የባንክ ሠራተኛውም በትዕግስት ሊያስረዳው ቢሞክር አልሆነም፡፡ ‹‹የሄድክበት መስኮት ሠራተኛ የለውም፤ መስተናገድ አትችልም፤ ባልጠራህ ባዶ መስኮት ጋ ምን ልትሠራ ነበር?›› ሲል ሠራተኛው ነገረው፡፡
ይሄ ደግሞ ተገልጋይ ባሰበት፡፡ ደንበኛው ሙሉ በሙሉ ጥፋተኛ ሆኖ ሳለ ቁጣውም የራሱ ሆነ፡፡ ይባስ ብሎም የተቋማት ሠራተኞችን ዝርክርክርነት እየጠቀሰ ይሳደብ ጀመር፡፡
ሌሎች ተገልጋዮች ጉዳዩን እየተከታተሉት ነበር፤ አንዳንድ ንዴታቸውን ቻል አድርገው እንደ መሳቅ ይቃጣቸው ነበር፤ አንዳንዶቹም በትዝብት ተመለከቱት፡፡ እርግጥ ነው በተቋማት ውስጥ ብዙ የተዝረከረከ አሠራር አለ፤ ይህ ሰው ግን እነዚህን አገልጋዮች የመተቸት ሞራል ከየት ሊያመጣ ቻለ? ሠራተኛው እንጂ ተገልጋዩ ስነ ሥርዓት መያዝ የለበትም አልተባለም። ግለሰቡ የዚያን ሁሉ ተገልጋይ ሰዓት አባክኗል፤ የአሠራር ደንብም ጥሷል፡፡
እያለ እያለ ክርክሩ ፈሩን ሳተ፤ የባንክ ሠራተኛውም ትዕግስቱ እያለቀ መጣ፡፡ ሌሎች ተገልጋዮች ጣልቃ መግባት ጀመሩ፡፡ የባንክ ሠራተኛው ዝም አለ፡፡ ተገልጋዩ ቀጠለበት፤ የሠራተኛው ዝም ማለት ተገልጋዩን በጣም ያናድደው ጀመር። ነገሮችን ንቆ መተው ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ተገልጋዩ ለፍልፎ ለፍልፎ ባንኩን ትቶ ወጣ፡፡ የባንክ ሠራተኛው ነገሩን ንቆ ባይተወው ኖሮ እነዚህ ሰዎች እስከ መደባደብ ይደርሱ ነበር፡፡
ከተገልጋዮች በትህትና ለቀረበ ጥያቄ ትህትና የተሞለባት ምላሽና ማብራሪያ ከአገልጋዮች የማይሰጠው ለምንድን ይሆን? ትህትና ሊያስከብር ጉዳይን ቶሎ ሊያስፈጽም ሲገባ ለምንስ ያስደፍራል? ተገልጋዮችስ በትክክለኛው መንገድ መገልገልን ለምንድን የማይፈልጉት ? አቋራጭ መንገድ ለምን ይፈልጋሉ ?
ትህትና ትልቅ ዋጋ ያለው እያንዳንዱ ሰው ሊኖረው የሚገባ ስነምግባር ነው፡፡ አንዳንዶች ግን የዚህን የትህትና ዋጋ አይገነዘቡትም፤ ቢገነዘቡትም በተለያዩ ምክንያቶች ሊያዳምጡት አዳምጠውም ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡበት አይፈልጉም፡፡ በትህትና ቀርበው ጉዳያቸው መፈጸም አይደለም የማይደመጥላቸው በርካታ ናቸው፡፡ ደጋግመው ለማስረዳት ቢሞክሩም አድማጭ አጥተው በተራ ጉዳይ ውለው የሚመለሱ ብቻ አይለም ለቀናት የሚመላለሱ ሞልተዋል፡፡ በእዚህ ጽሑፍ እየተመለከትን ያለውም ይህንን ነው፡፡ የእስራኛውና የጠያቂዎቹ ጉዳይ አለመፈጸም የሚያመለክተውም ይህንኑ ነው፡፡
የጉዳይ አፈጻጸም በተለያየ ምክንያት ችግር ሲገጥመው ይታያል፡፡ ከሁሉም ከሁሉም እንደ የተቋሙ ማንነት፣ አንደ ተቋሙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች/ ከጥበቃ አንስቶ ዋና ሥራ አስኪያጅ ድረስ/ ማንነት ሲወሰን መታየቱ ያሳስባል፡፡
አንዳንዱ ጉዳይ ፈጻሚ ሠራተኛ ፊቱን ስለከሰከሰ ፣ ሠራተኛን ስላንገላታ የሠራ ይመስለዋል፡፡ ፖሊስም ሆነ ሌላ የህግ አካል ቢሆን በስርዓቱ ነው ባለጉዳይን ማስተናገድ ያለበት፡፡ የተጠርጣሪን እና ተጠርጣሪን ብለው የሚመጡ አካላትን ማስናገድ ያለባቸው በስርዓቱ ነው፡፡ ፖሊስን አንዲከበር እንጂ አንዲፈራ የሚያደርግ ተግባር መፈጸም ትክክል አይደለም፤ አሁን በአንዳንዶች ዘንድ እየታየ ያለው ይሄው ነው፡፡ ባለጉዳይን አንዴት አድርጌ ባስተናግደው አረካዋለሁ ብሎ መሥራት አንጂ ባለጉዳዩ ላይ ፊት መከስከስ ወይም አንዲደነግጥ ማድረግ የሚናገረውን እንዲያጣ ሊያደርገው ይችላል፡፡
ሁሉም ባለጉዳይ እንዲሁ አንደማንኛውም ባለጉዳይ ነው መስተናገድ ያለበት፡፡ ተራውን ጠብቆ በተቋሙ ስርዓትና ህግ መሰረት፡፡ አንዳንዶች በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ጉዳይ ማስፈጸም ይለምዱና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው በሌሉበት ቦታ ተቋማትን ቤታቸው አርገው ሲመለከቱ ይታያሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ተገልጋዮች የተቋማት ሠራተኞችና ባለጉዳዮቾ ሊያጋልጧቸው ይገባል፡፡
ተራ የሚጠብቁትን በተለያዩ መንገዶች በማለፍ ጉዳያቸውን ማስፈጸማቸውን እንደ አራዳነት እና ብልጥነት ተራ የሚጠብቁትን አንደ ሞኝ መቁጠር የበለጠ ስህተት መፈጸም ነው የሚሆነው፡፡ ጉዳይ ለማስፈጸም እየተጠቀምክበት ያለው መንገድ ተገቢ አይደለም ፤ ታረም ሲባል የማይሰማም ትህትናን አንደተጫወተባት ነው የሚቆጠረው፡፡ በባንክ ቤት ተወራጭቶ ተወራጭቶ የሄደው ባለጉዳያም እንደዚያው ነው። በትህትና ላይ የሚመጡትን በጋራ ማሳፈርም ሆነ ማረቅ ይቻላል፡፡ ህገወጦችን ስርዓት ማስያዝ ሲቻል ትህትናም የሚያስከብር እንጂ የሚያስደፍር አይሆንም፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2014