እንደነ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ እና ሲ ኤን ኤን ያሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንን የጋዜጠኝነት መለኪያ አድርገን ኖረናል። ከጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ጀምሮ በየሥልጠናው ምሳሌ የሚሰጠው የእነዚህ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሥራ ነው፡፡ በየግላችንም ምሳሌ የምንጠቅሰው እነርሱን ነው፡፡
የተታለልነው እነዚህን መገናኛ ብዙኃን የምናውቃቸው በውጭ አገራት ሁነት ነበር፡፡ ለእኛ ቅርብ ባልሆነ ጉዳይ ነው የምናውቃቸው፡፡ ለእኛ ቅርብ ያልሆነ ጉዳይ ደግሞ እውነት ይሁን ውሸት በቅርበት አናውቅም፡፡ የምናየው እሳት እየነደደ ዘገባ ማሳየታቸውን፣ የጥይት እሩምታ እየወረደ ሪፖርተሩ ‹‹ላይቭ›› ገብቶ መዘገቡን፣ በየትኛውም የዓለም ጫፍ የተከሰተን ክስተት መዘገባቸውን ነው፡፡
እነዚህን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በተከታታይ መዘገብ ከጀመሩ ወዲህ ግን ስለነሱ የነበረንን እይታ እንድናስተካክል እያደረገን ነው ፡፡ አጋጣሚው ስለተቋማቱ እውነተኛ ስብእና እንድናውቅ እየረዳን ነው። እርግጥ ነው ምሁራን እና የዕድሜ ባለፀጎች በተለያየ አጋጣሚ እነዚህን ተቋማት ታዝበዋቸው ይሆናል፡፡ አሁን ላለው ወጣቱ ትውልድ ግን በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ክስተት ለኢትዮጵውያን ትልቅ ትምህርት የሰጠ አጋጣሚ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ እውነትም ታላቅ አገር መሆኗን እና ዓለምም ምን ያህል በትኩረት እንደሚያየት ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው፡፡ ከእነርሱ በመጣ ‹‹ቲዎሪ›› የአገራችን ጋዜጠኞች ሲሽኮረመሙ የዓለም ተምሳሌት የሚባሉት እነ አልጀዚራ፣ ሲ ኤን ኤን ዓይናቸውን በጨው አጥበው የቱን ያህል የጥፋት መንገድ ውስጥ እንዳሉ ለማየትም የተሻለ አጋጣሚ ተፈጥሮልናል፡፡ ከቅርብ ክስተት ልጀምር፡፡
ባለፈው ሐሙስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ አምባሳደሩ ስለድርድር አስረግጠው የተናገሩት ነገር፤ የተጀመረ ነገር እንደሌለ ነው፡፡ አንድ በመግለጫው ላይ የነበረ የኦን ላይን ጋዜጠኛም የአልጀዚራን ዘገባ አይቶ የጻፈው የአምባሳደሩን ግልጽ መልዕክት ነው፡፡
አልጀዚራ ግን ዓላማው ሌላ ነበርና ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት እደራደራለሁ አለ›› የሚል ርዕስ ያለው ዜና ይዞ ወጣ፡፡ በማህበራዊ የትስስር ገጹም ለጠፈው፡፡ ከዚያ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ደግሞ ሲ ኤን ኤን የተባለው የአሜሪካ ቴሌቭዥን አዲስ አበባ በሕወሓት ወታደሮች ተከባለች ብሎ እርፍ!፡፡ በነገራችን ላይ ሲ ኤን ኤን በዚያ ዘገባው አደገኛ ክስረት ነው የከሰረ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ነው ታማኝነቱን ያጣው፡፡ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ያልተቀለደበት ቀልድ አልነበረም፡፡
ሊሆኑ ነገሮችን እየጻፉ ‹‹ምንጭ CNN›› ሲባል ከርሟል። ለምሳሌ ‹‹አንድ በሬ በወሊድ ምክንያት ሞተ፤ ምንጭ CNN›› የሚል ተስተናግዷል ፡፡ ጉዳዩን እንደ ተራ ቀልድ የምናልፈው አይደለም፡፡ ሲ ኤን ኤን የሚሰራው ዜና ከዚህ ምንም የማይለይ እየሆነ መጥቷል፡፡
በሲ ኤን ኤን ላይ ከተቀለዱት አንዱን ጠቅሼ ልለፈው። አንድ ሰው ‹‹ከዚህ በኋላ ሲ ኤን ኤንን የምከፍተው ለስፖርት ዜና ብቻ ነው›› ብሎ ለጠፈ፡፡ ከሥር የተሰጠው አስተያየት፤ ‹‹እሱንም ‹አርሰናል እና ወላይታ ዲቻ 2 ለ1 አቻ ተለያዩ› ሲልህ ትተወዋለህ›› የሚል ነበር፡፡ ይህ አስተያየት ‹‹ስክሪንሹት›› ተደርጎ በሺዎች የሚቆጠሩ ገጾች ሲቀባበሉት ነበር፡፡ ‹‹የሕወሓት ወታደሮች አዲስ አበባን ከበዋል›› ብሎ የሰራው ዜና፤ ሁለት ለአንድ የሆነን ውጤት ‹‹አቻ›› ብሎ ከመዘገብ በምንም አይለይም፡፡
ይሄው ሲ ኤን ኤን በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የፕሬስ ሴክሬተሪ ከሆኑት ቢለኔ ሥዩምን፤ ቀጥሎም ጌታቸው ረዳን አቅርቦ ነበር፡፡ ጋዜጠኛዋ ሁለቱን የጠየቀችበት ሁኔታ ግልጽ የሆነ አድሎ ነበር፡፡ ቢለኔ ሥዩምን በፍጹም ልታስወራት አልቻለችም፤ የውጭ አገር አስተያየት ሰጪዎች ሳይቀር በአስተያየት መስጫው ላይ የፈረዱት ነበር፡፡ በአንፃሩ ጌታቸው ረዳ ብቻውን ነው ያወራው ማለት ይቻላል፤ ለዚያውም ለእርሱ የሚመቹ ጥያቄዎች ስትጠይቅ የዋለችው፡፡
በነገራችን ላይ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት ፕሮፖጋንዳ ማሰራጫዎች ናቸው ብለን የምንወቅሳቸው በቅርበት ስለምናውቃቸው ነው፡፡ የሚዘግቡትን ጉዳይ በመኖር ስለምናውቀው ነው፤ በራሳችን የምናየውና የምንሰማው ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹አወቅኩሽ ናቅኩሽ›› አይነት ስለሆነ ነው፡፡ ከእነዚህ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የተረዳነው ነገር ለአገራቸው ጥቅም ሲባል የት ድረስ እንደሚሄዱ ነው፡፡
ለመሆኑ ኢትዮጵያን ለምን እንዲህ ጠመዷት?
የዓለም አገራት (በተለይም ምዕራባውያን) የአፍሪካ አገራትን እንደፈለጋቸው ማዘዝና መገተት ነው የሚፈልጉት። ከአፍሪካ አገራት ደግሞ ተፅዕኖ ፈጣሪ ትሆናለች ብለው የሚፈሯት ደግሞ ኢትዮጵያን ነው፡፡ ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም አርዓያና ተምሳሌት ትሆንብናለች ብለው ይፈሯታል፡፡ ምክንያቱም የከዚህ በፊት ታሪኳን ያውቃሉ፡፡ ለአፍሪካ አገራት ሁሉ ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት አርዓያ ሆና የወጣች ናት፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ምን እንደሆነች ያውቃሉ፡፡
በነገራችን ላይ ብዙ አፍሪካውያን ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ምን እንደሆነች ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ከሰሞኑ አንድ የኡጋንዳ ጋዜጠኛ ስለ ሲ ኤን ኤን ቅጥፈት የጻፈውንም አስተውለናል፡፡ ሌሎች ጋዜጠኞችም እንዲሁ ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ በር መሆኗን ሲናገሩ ነበር፡፡
እነ አሜሪካ ብዙ አገራትን አፈራርሰው አይተናል። ከዚህ የማንማር ከሆነ ዓይናችን እያየ አገራችንን ማስፈረስ ነው የሚሆነው። እነርሱ የሚፈልጉት ደካማ መንግሥት እና ደካማ አገር መፍጠር ነው፡፡ ለአሸባሪው ሕወሓት ይህን ዓይን ያወጣ ወገንተኝነት ሲያሳዩ ሕወሓት ካላፈረስኳት የሚላትን አገር ሲያስተዳድር በነበረበት ዘመን ምን ሲያደርጋት እንደነበር ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡
እነ አሜሪካ አሸባሪው ሕወሓት እንዲመለስ የሚፈልጉበት ዋናው ምክንያት፤ አገሪቱን ደካማና ኋላቀር አድርጎ እንደሚያስቀርላቸው ስለሚያውቁ ነው፡፡ በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር እንዳይኖር ለሚያደርጉት ጥረት ኢትዮጵያን ስለሚያዳክምላቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ምን እንደሆነች ደግሞ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እና ጋዜጠኞች የሚሉት ምስክር ነው፡፡
እነ አሜሪካ አሸባሪውን ሕወሓትን ጠንቅቀው ያውቁታል። ሰሞኑን አንድ ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያ የጻፉትን እያነበብኩ ነበር፡፡ በሊቢያ ቀውስ በተነሳ ጊዜ የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸውን እያስወጡ ነው፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን ይመራ የነበረው ሕወሓት መሩ የኢትዮጵያ መንግሥትም ወግ ይድረሰኝ ብሎ ዜጎቹን ውጡ አለ፡፡ እነ ሲ ኤን ኤን እና የአሜሪካ ድምጽ (ቪ ኦ ኤ) የወቅቱን የኢትዮጵያ መንግሥት ባህሪ ያውቁ ስለነበር የኢትዮጵያን ዜጎች ማናገር ጀመሩ። ዜጎቹ የሰጡት ምላሽ ‹‹የመጣነው እኮ መንግሥት የሚያደርስብንን ግፍና መከራ ሸሽተን ነው፤ እዚያ የሚጠብቀን እዚህ ከሚሆነው የተሻለ አይደለም›› የሚል ነበር፡፡ እነ አሜሪካ ይሄን መንግሥት ነው እንግዲህ ይመለስ እያሉ ያሉት፡፡ ምክንያቱም የሚፈልጓትን ደካማ ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን አይተውታል፡፡
የህልውና ዘመቻው ለምን ዳግማዊ ዓድዋ ተባለ?
አንዳንድ ወገኖች ‹‹ዓድዋ ከውጭ ጠላት ጋር በተደረገ ጦርነት የተገኘ ድል ነው፤ ለምን ከአገር ውስጥ ጦርነት ጋር ይነፃፀራል?›› የሚሉ አሉ፡፡ የዋህነታችን እዚህ ላይ ነው፡፡ የዓድዋ ጦርነትም፤ የአሁኑ የህልውና ዘመቻም ከነጭ ወራሪ ጋር የሚደረግ ነው። ዓድዋ የነጮችን ሴራ ያከሸፈ ድል ነው፤ ይሄም የነጮችን ሴራ ለማክሸፍ የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ልትወር የመጣችው ብቻዋን መክራ እና ዘክራ አልነበረም፤ የአውሮፓ አገራት ተሰባስበው በርሊን ላይ የመከሩት ሴራ ነበር፡፡ አፍሪካን ለመቀራመት ያሴሩትን ሴራ ያከሸፈ የጥቁር ድል ነው፡፡
የአሁኑ ጦርነትም የዚያው አካል መሆኑን እነሆ የነጮች ልሳን መገናኛ ብዙኃን እያሳዩን ነው፡፡ ስለዚህ ጦርነቱ እየተደረገ ያለው ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ብቻ ሳይሆን ከአውሮፓና አሜሪካ ሴረኞች ጋር ነው፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት በታሪኩ በውሃ ጉዳይ ላይ መክሮ የማያውቀውን በኢትዮጵያ ውሃ ላይ የመከረው በሴራው ባለቤቶች ትዕዛዝ ነው፡፡ ተላላኪና ደካማ አገር መፍጠር ስላልቻለ ነው፡፡ ይሄን ዓይን ያወጣ እና ይሉኝታ ቢስ ሴራ እያየን ታዲያ ጦርነቱ ከዓድዋ ያንሳል ብለን እናምናለን? ዓድዋ ድል የመላው ጥቁሮች ድል እንደተባለ ሁሉ፤ የአሁኑ የህልውና ዘመቻም የመላው ጥቁሮች የአሸናፊነት ማሳያ ይሆናል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2014