– የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችም ድርሻቸውን ተወጥተዋል
አዲስ አበባ:- በአድዋ ጦርነት ወቅት ከተጓዙ ከ20 ሺ እስከ 30 ሺ የሚጠጉ ከተዋጊው ጀርባ የነበሩ ሰዎች አብዛኛዎቹ ስንቅ አቅራቢ ሴቶች መሆናቸው የታሪክ ተመራማሪዎች ተናገሩ።
የዓድዋ ጦርነት የእናቶች ደጀንነት የታየበት በመሆኑ ውለታቸው ከቶም አይረሳም ሲሉ ነው የታሪክ አጥኚዎች የተናገሩት። በአድዋ እና የሴቶች ሚና ላይ ጥናት የሰሩት የደብረብርሃን ዩኒቨረሲቲ የታሪክ መምህር አቶ ታምራት ገብረማርያም እንደገልጹት፤ አድዋን ያለሴቶች ስንቅ አቅርቦት ማሸነፍ አይታሰብም ነበር።
የጀግንነት ክህሎታቸው ዛሬም ነገም ሲዘከር ይኖራልና ከታሪክ ማህደር እየቆነጠርን ብንናገር እንጂ በቦታው የነበረውን ከፍተኛ የጀብድ ስሜት መግለጽ እንደሚከብድ በርካታ ጸሐፍት እንደገለፁት አስታውሰው፤ በአድዋ ጦርነት ወቅት አፈር እየላሱ ድንጋይ ተንተርሰው ከተዋጉ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ስንቅ አቅራቢ እና ወኔ ቀስቃሽ ሆነው የድርሻቸውን የተወጡት ሴቶችና አዝማሪዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
እንደ አቶ ታምራት ማብራሪያ፤ በምኒልክ ጦር በአራተኛው ምድብ ላይ የነበሩት ስንቅ አቅራቢ ሴቶች በየጦርነቱ ላይ እየተዘዋወሩ በዘጠኝ ድንኳኖች ምግብ ያቀርቡ ነበር። በጦርነቱ ከተጓዘው ሰው አንድ አራተኛው በቀጥታ ያልተዋጋ እና የተለያየ ሙያ የተሳተፈ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኛዎቹ ምግብ አቅራቢ ሴቶች ናቸው። እናቶች በድንጋይ ወፍጮ የፈጩትን ዱቄት ይዘው፣ ማጣፈጫ ጨው ቋጥረው በጦርነቱ አውድማ ተሳትፈዋል። ያለእነርሱ አጋዥነት ተዋጊውም እንደማይጠነክር ይታወቃልና ሚናቸው ልዩ ነበር።
ጸሓፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ፣ በ«ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ዐጤ ምኒሊክ» መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ አጼ ምኒልክ ባዳራሹ፤ እቴጌ ጣይቱ በእልፍኝ ባለሟሎቿን ወይዛዝሩን ይዘው ግብሩ አንድ ቀን ሳይጎድል መዝመታቸውን ጠቅሰዋል።
ሴቶች ምግብ አብስለው የእናትነት እና እህትነት ፍቅራቸውን እየለገሱ ከባሌም፣ ከሶማሌም፣ ከሽሬም፣ ከሞያሌም፣ ከወላይታም፣ ከአፋርም ለመጣው መግበዋል። አገሬን አላስነካም በሚል ስሜት የተመመውን በወቅቱ አጠራር ወቶአደር/ ወታደር/ ለመመገብ በአድዋ ጦርነት በሙያቸው መቀነታቸውን ያጠበቁ እናቶች ነበሯት ብለዋል።
የጦርነቱ መጀመር አይቀሬነት ሲታወቅ የወይዛዝርቱ ዝግጅት ማብሰያውንም ታሳቢ ያደረገ ነበር። ክብ የሸክላ ምጣዶች በብዛት ተሰርተዋል፤ አክንባሎው፤ የሸክላ ድስቶችም በብዛት ተዘጋጅተዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሸክላ ሰሪው ህብረሰተብ የእጅ ጥበብ ለድሉ የነበረውን ሚና ከፍተኛ ነበር። ለመጠጫነት የሚሆኑ ቀንዶች በብዛት በባለሙያዎች ተዘጋጅተው ተጓጉዘዋል። ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ የሚቆየው ማርም የእናቶች የምግብ ዝግጅት አንድ አካል እንደነበር አቶ ታምራት አስታውሰዋል።
ዝግጅቱን ያጧጧፉት እናቶች በሶ እና ቋንጣ እንዲሁም ለአዋዜ የሚሆን በርበሬ ይዘዋል። ቶሎ የማይበላሹ ደረቅ ምግቦችን ለውጊያ ወቅት ሲያዘጋጁ ቆሎውን ሲፈትጉ ከርመዋል። ይሁ ሁሉ ዝግጅት ሲጠናቀቅ ስንቅ ወደ አድዋ ተራሮች በአህያ እና በፈረስ እንዲሁም አነስ አነስ ያለውም በጀርባቸው ተሸክመው ተጉዘዋል። ለቆሰለው ተዋጊ እንደነርስ ሆነው የማከም እና የመንከባከብ ሃላፊነቱም የሴቶቹ ነበር። በጦርነቱ ውሃ የማቀበል እና የሞራል ድጋፍ በመስጠትም አይነተኛ ሚና ስለነበራቸው ታሪክ እንደማይዘነጋቸው አቶ ታምራት አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
ጌትነት ተስፋማርያም