ፍሬ ነገሩ
ወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መጥተው በጠራራ ፀሐይ ቤቴን ተቀማሁ ሃብት ንብረቴንም አጣሁ ብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ እኔና ልጆቼ፣ ለዘመናት የደከምንበት የመኖራችን ዋስትና ይሆናል ብለን ያሰብነው ንብረት ያለአግባብ ልንቀማ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
እንደ ወይዘሮዋ ገለፃ ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት የእርስዎ ቤት አይደለም በሚል ፍርድ የተሰጠበት የመኖሪያ ቤት ፍርድ ቤት የአንቺ ቤት አይደለም ብሎ እንደበየነው ሳይሆን በላቤ፣ በአንጡራ ሃብቴ እና በልጆቼ ድካም የተገዛና የተገነባ እንጂ እንዲሁ የመጣ አይደለም ባይ ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ልጆቼ ደክመው በላኩት ገንዘብ ተሽከርካሪዎችን ገዝቼ ሥራ እየሰሩ ሳለ የአንቺ አይደለም በሚል ውሳኔ ንብረቱን ሌላ አካል እንዲጠቀም ተወሰነ ሲሉ በእንባ በታጀበ ስሜት ምሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡
ቤቱ ከመነሻው የማነው?
ሰኔ 16 ቀን 2003 ዓ.ም የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ውል ሥምምነት በሚል ደብዳቤ ላይ እንዲህ ሲል ሰፍሯል። ‹‹ሻጭ አቶ ዘውዱ ገብረሚካዔል ኤፍሬም የተባሉ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ አድራሻቸውም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/14 የቤት ቁጥር 515 ነው፡፡ በተጨማሪም ወይዘሮ ሃና ሙሉጌታ ብሩ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ዜጎች መሆናቸውን ያትታል፡፡ በዚህም በውክልና ሥልጣን ቁጥር 429/13/2000 በተሰጠ መሰረት ቤቴ ለሌላ ወገን ስለመሸጡ ያትታል፡፡ ገዥ ላይ ስማቸው የሰፈረው ደግሞ ወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ የተሰኙ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ የፓስፖርት ቁጥራቸው EP1279303 የሆኑ ግለሰብ ናቸው፡፡
የውሉ ሙሉ ቃልም ‹‹እኔ ሻጭ በራሴና ወኪል አድራጊ ባለቤቴ ሥም በመሆን የወኪል አድራጊዬ ሥም ተመዝግቦ በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ ምስራቅ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ 17 ቀበሌ 20 በአሁኑ ቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 የቤት ቁጥር 774 የቦታው መለያ ካርታ ቁጥር 22469 የተዘመገበውን ቦታ ስፋት 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገኘውን የጋራ ንብረታችን የሆነውን የመኖሪያ ቤት ባለበት ሁኔታ በብር 7000 000 (ሰባት ሚሊዮን) ለገዢው ሸጫለሁ፡፡ በዚህ ውል ደረሰኝነት ተቀብዬ ቤቱንና የቤቱን ኦርጅናል ካርታ እና ሌሎች ለቤቱ የሚያስፈልጉ ኦርጅናል ማስረጃዎችን በሙሉ እንዲሁም መኖሪያ ቦታ ለገዢ አስረክቤ ሽያጭ መፈፀሜን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ፡፡ ይህ ቤት ከመሸጡ በፊት የነበረ ማንኛውም የመንግስት ሆነ የግለሰብ ዕዳ እና ዕገዳ ቢኖር ኃላፊነቱ የእኔ የሻጭ ነው፡፡
እኔም ገዥ በወይዘሮ ሀና ሙልጌታ ብሩ ስም ተመዝግቦ በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ ምስራቅ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ 17 ቀበሌ 20 በአሁኑ ቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 የቤት ቁጥር 774 የቦታው መለያ ካርታ ቁጥር 22469 የተዘመገበውን ቦታ ስፋት 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገኘውን የጋራ ንብረታችን የሆነውን የመኖሪያ ቤት ባለበት ሁኔታ በብር 7000 000 (ሰባት ሚሊዮን) ከሻጭ ላይ ገዝቻለሁ፡፡ የሽያጩንም ገንዘብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ በቼክ ቁጥር 0171827153200 በዛሬው ዕለት በዚህ ውል ደረሰኝ ከፍዬ ኦርጅናል ካርታ እና ሌሎች ለቤቱ የሚያስፈልጉ ኦርጅናል ማስረጃዎችን በሙሉ እና የመኖሪያ ቤቱን ጭምር ባለበት ከሻጭ ተረክቤ ግዥውን መፈፀሜን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ፡፡
ይህ ውል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1889፤1890 መሠረት በህግ ፊት የጸና ሲሆን በውሉ መሰረት የማይፈጽም ወይንም ውሉን ለማፍረስ የሞከረ እና የሚሞክር ወገን ቢገኝ ውል ለፈረሰበት ወገን ብር 10000 (አስር ሺህ ብር) ከፍሎ ውሉ መሰረት በህግ ፊት በፍ/ሕ/ቁ/1731፤2005፤ 2266 የጸና ይሆናል›› ይላል፡፡
ስለቤቱ ህጋዊ ማስረጃዎች
ወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ ቤቱ የእኔ ስለመሆኑ ከቃል እና ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ በሰነዶች የተደገፈ በቂ መረጃ አለኝ ባይ ናቸው፡፡ ለአብነትም ቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 01 አስተዳደር ፅህፈት ቤት ለወረዳው ገቢ አወሳሰንና አሰባሰብ ክፍል በጥቅምት 22 ቀን 2004 ዓ.ም በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ወ-1/1994/03 በፃፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ሰፍሯል፡፡
‹‹አቶ/ወሮ/ወ/ሪት/ እነ መስታወት አማረ ማሞ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ወይንም በቀድሞ ወረዳ 17 ቀበሌ 20 ለሚገኘው ይዞታቸው ግብር መጠን ተገልፆ እንዲፃፍላቸው ጠይቀዋል፡፡ ስለሆነም የቦታው ስፋት በሰነድ 500 ካሬ ሜትር ሲሆን ዓመታዊ የቦታ ግብር 10.00 ብቻ የቤቱ ዓመታዊ የኪራይ መጠን ብር 22781 ነጥብ 61 ሲሆን ሊከፈል የሚገባው ዓመታዊ የቤት ግብር 923 ነጥብ17 ጠቅላላ ብር 933 ነጥብ17 ነው›› ይላል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ የተገኘው መረጃ ደግሞ በቤት ቁጥር 774 ህዳር 3ቀን 2004 ዓ.ም ወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ በ2004 የግብር ዘመን 933ነጥብ17 ብር መክፈላቸውን ያሳያል፡፡ መለያ ቁጥሩም 7907 እንደሆነ ይናገራል፡፡ በተመሳሳይ በዚሁ የቤት ቁጥር 11735 በሚል መለያ ቁጥር ከ2005-2010 ዘመን ደግሞ 7ሺ978 ብር ከ60 ሳንቲም 12/7/2010 ክፍያ መፈፀሙን ያሳያል፡፡
ተሽከርካሪዎቹም በተመሳሳይ ሁኔታ በወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ ሥም ስለመገዛታቸው የሚያስረዱ በርከት ያሉ መረጃዎች አሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህጋዊ ሰነዶችም በእኝሁ ሰው ሥም የተሰነደ መሆኑን ማስረጃዎቹ ያስረዳሉ፡፡
ቤቱን ለመግዛት ገንዘብ ከየት መጣ?
ወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ በሰባት ሚሊዮን ብር የተገዛውና 500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ቤት እንዲሁ እንደቀልድ የተገዛ አለመሆኑን ያስረዳሉ። የትዳር አጋራቸው በህይወት ሳሉ እስከ ሐረር ድረስ ሄደው ሰፊ እርሻዎችን ይሰሩ ነበር፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል የቡና እርሻም ነበራቸው፡፡ ይህን ገንዘብ በዓመታት ውስጥ አጠራቅመው ቤት ይኖራቸዋል። ታዲያ ይህ ቤት ለልጆቻቸውና ለእርሳቸው በቂ አልነበረም። እንግዳ ሲጨመርበት ደግሞ ቤታቸው እየጠበበ መሆኑን ተረዱ፡፡ በዚህን ጊዜ ጉዳዩን የተረዱት ልጆቻቸው መላ ዘየዱ፡፡
ወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ ካጠራቀሙት ሃብት በተጨማሪ አራት ልጆቻቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ይኖሩ ስለነበር ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንዲሉ አበው፤ ልጆቻቸው ገንዘብ በአንድ ላይ ማጠራቀም ጀመሩ፡፡ በእናታቸው ሥም በተከፈተ አካውንት ገንዘብ እየላኩም እናታቸውም ካጠራቀሙትና በዘመናቸው ካከማቹት ጥሪት ጋር አቀናጅተው በሰባት ሚሊዮን ብር ቤት ገዙ፡፡
ዘመደ ብዙ የሆኑት ወይዘሮ መስታወት ከጠባብ ጓዳ ወደ ሰፊ እልፍኝ ተሻገሩ፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማም ሰፋ ያለ ቤት ገዝተው እንግዳም ሲመጣ ልጆቻቸው ሲሰባሰቡ ያለ መሳቀቅ ለማስተናገድ በቁ፡፡ ታዲያ ይህ የዘመናት ህልማቸው ልጆቻቸው ሲደርሱላቸው ተፈታ፤ በልጅ የሚጦሩበትም ወግ ማዕረግ ለማየት ከመጀመሪያው ምዕራፍ ደረሱ፡፡ ነገር ግን ይህ ህልማቸው በአንድ ጎን የተፈታ ቢሆን በሌላ ጎኑ ግን በህልማቸው ላይ ውሃ የሚቸልስ ጣጣ የኋላ ኋላ በማያውቁት መንገድ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ የወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ ልጆች በትብብር የገዙት ቤት የእርሳቸው እንዳልሆነ የሚበይን ፍርድ ሰሙ፡፡ ታዲያ ይህ ነገር የቤታቸው እንቆቅልሽ ሆኖ ቤተሰቡን ጭንቀት ውስጥ ከተተ፡፡
ተሽከርካሪዎችን ማን ገዛቸው?
ወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ ምስራቅ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ 17 ቀበሌ 20 በአሁኑ ቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 የቤት ቁጥር 774 የቦታው መለያ ካርታ ቁጥር 22469 የተዘመገበውን ቦታ ስፋት 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገኘውን ቤት በብር 7000 000 (ሰባት ሚሊዮን) ከገዙ በኋላ ሌላ ሃብት ንብረት ማፍራትና መግዛትም እንዳለባቸው አመኑ፤ አደረጉትም፡፡
ቤቱን እንደገዙት በተመሳሳይ መልኩ ተሽከርካሪዎችን ገዝተዋል፡፡ እነዚህ በርከት ያሉት ተሽከርካሪዎችም ልጆቻቸው በመተባበር በላኩት ገንዘብ የተገዙ ሲሆኑ ሃብት ንብረት በማራዘምና በብርቱ ድካም የተገኘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎችም ከጥንስሱ ጀምሮ የባንክ ሂደቶች ሙሉ ወጪው በእርሳቸው የተሸፈነ ስለመሆኑ በእጃቸው ላይ መረጃዎችን ይዘዋል፡፡ በእነዚህ ተሽከርካሪዎችም በአስጎብኚነትና በሌሎችም ሥራዎች ሲውሉ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ ተሽከርካሪዎቹ እየተከራዩ ገቢ ሲያመነጩ የቆዩ ስለመሆናቸው እና ስለቀጣይ ሥራ ከልጆቻቸው ጋር ስለመመካከራቸው ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮዋ መስታወት ፍርድ ቤት ለምን ሄዱ?
የወይዘሮ መስታወት አማረ ሴት ልጅ የሆነችው ወይዘሮ ሀያት ሙሳ አማረ እና የትዳር አጋሯ አቶ መሐመድ ሰዒድ ኢብራሂም ነዋሪነታቸው በዱባይ ሀገር ነበር፡፡ በመሃል ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ትዳራቸው በፍቺ ተቋጨ፡፡ ታዲያ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አመራ፡፡ በዚህም የተካረረ ክርክር ተጀመረ። በዚህ ሂደት ውስጥ ባልና ሚስት በጋራ ያፈሯቸውን ንብረቶች ለመካፈል ተስማሙ። በዚህም ሃያት አካባቢ በጋራ የገዙትን ቤትና ሌሎች ንብረቶችን ተካፈሉ፡፡ ጉዳዩ ግን በዚህ አላበቃም፡፡ አቶ መሐመድ ሰዒድ ኢብራሂም ከባለቤታቸው ጋር ሃብት ንብረት ከተካፈሉ በኋላ ሌላ ክስና ክርክር ጀመሩ፡፡ በዚህም ይገባኛል በሚሉት ጉዳይ ላይ ሁሉ ዱባይ ሆነው በጠበቃቸው አማካይነት ኢትዮጵያ ውስጥ መከራከር ጀመሩ፡፡ ታዲያ በዚህ የክስ ሂደት ውስጥ ወይዘሮ መስታወት አማረ ወደ ፍርድ ቤት ተጠሩ፡፡ እኔ ፍርድ ቤት ተጠርቼ የሄድኩት በእኔ ቤት እና ንብረት ልመሰክር አልነበረም፤ በዚህም ጉዳይ ላይ ምንም የተጠየኩት ነገር አልነበረም ሲሉ የሆነውን ያስረዳሉ፡፡
የሰጠሁት ቃል
ወይዘሮዋ ወደ ፍርድ ቤት ከተጠሩ በኋላ ሲጠየቁ የነበረውን ሁኔታ በሚገባ ያስታውሳሉ፡፡ እኔ ተሳስቼ እንኳ ቢሆን የተቀዱ ድምጾችን መስማት ይቻላል ይላሉ፡፡ በፍርድ ቤት በተደረገላቸው ጥሪ በቦታው ተገኝተው እንዲያስረዱ የተጠየቁት ነገር ቢኖር በወለዷት ሴት ልጃቸው ጋብቻ ላይ የተፈጠረውን ሁኔታ እንዲያስረዱና በጋራ ያፈሯቸው ንብረቶች እንዳሉ ለማስረዳት እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡
ታዲያ በዚህ ወቅት ከተጠየቁት መካከል ጋብቻቸው እንዴት እንደፈረሰ እንደነበር አስታውሰው፤ ለፍርድ ቤቱ እኔ በምን እንደተጋጩ አላውቅም የሚል ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ ሁለቱም ልጆቼ ናቸው ቢቻል ቢስማሙ እንጂ ፀባቸው ምን ሊፈይደኝ ብለው አስረዱ፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እርሳቸው እየኖሩበት ስላለው ቤት ምንም ነገር አለመጠየቃቸውን በሚገባ አስታውሳለሁ ባይ ናቸው፡፡ ይህ ጥያቄው ቢኖር ቤቱ የአንዲት ሴት ልጄ እና አማቼ የገዙት ቤት ሳይሆን በባዕድ ሀገር ለዓመታት ሲንከራተቱ የነበሩ ልጆቼ አንድ ላይ ገንዘብ አሰባስበው በእኔ እናታቸው ሥም የተገዛ የሁሉም ቤት ስለመሆኑና እኔም የራሴን ጥሪት እንደጨመርኩበት ከማሳወቅ ውጭ ሌላ ምን ምላሽ ይኖረኛል ሲሉም ይናገራሉ፡፡ ዳሩ ግን ስለዚህ ጉዳይ አለመጠየቃቸውንና የባል እና ሚስት ክርክር አካል እንዳልነበረም ያስታውሳሉ፡፡
የፍርድ ቤት ውሳኔዎች
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀን በወይዘሮ ሀያት ሙሳ አማረ እና በአቶ መሐመድ ሰዒድ ኢብራሂም መካከል ስላለው ክርክር 11/03/203 በቁጥር የፍ/ብ/መ/ቁ191069 መዝገብ መርምሮ ባሳለፈው ውሳኔ እንዲህ ይላል፡፡
ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቦሌ ሩዋንዳ ተብሎ የሚጠራው ሰፈር አካባቢ ያለውን ቤት በተመለከተ አመልካችና ተጠሪ ተነጋግረው በተጠሪ እናት ስም የተገዛ ቤት በመሆኑ የጋራ ተብሎ አመልካችና ተጠሪ እንዲካፈሉት እንዲወሰን ሲጠይቁ፤ አመልካች በበኩላቸው የተጠሪ ቤተሰብ እና የጋራ አይደለም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህን ከማስረጃ አንፃር አጣርቷል፡፡
‹‹በተከራካሪዎች በተጠየቀው መሰረት ይህ አከራካሪ ቤት በተመለከተ ማስረጃ እንዲቀርብ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቶ የቦሌ ክፍለ ከተማ ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ይ/አስ/የሽ/ጊ/አ/ፕ/ፅ/ቤት291410/13 በ11/01/13 በሰጠው ምላሽ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በካርታ ቁጥር ቦሌ 9/15/1//22469/19347/01 የሚታወቅ የቦታው ስፋት 500 ካሬ ሜትር የሆነ ይዞታ በወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝ የተገለፀ
ሲሆን የቤቱን የነባር የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አያይዞ ልኳል›› ይላል ማስረጃው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ በግራ እና በቀኝ ምስክሮችን መስማቱን ያትታል፡፡ በዚህም ውስጥ አሻሻጮች፣ ደላሎች፣ ሌሎች ምስክሮችና የመንደር ውሎችን አንደማስረጃ መጠቀሙን ፍርድ ቤቱ ያመለክታል፡፡
ታዲያ እነዚህ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ግራ ቀኝ ተመልክቻለሁ ያለው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቤቱን አስመልክቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ቤቱ የእኔ እና የልጆቼ የጋራ ሃብት እንጂ የአንድ ግለሰብ ብቻ አይደለም በማለት፣ ወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ ፍርድ ቤት ቀርበው ስለመናገራቸው ፍርድ ቤቱ ባሰፈረው ሃሳብ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ፍርድ ቤት የተለያዩ መረጃዎችንና መመዘኛዎችን ስለመጠቀሙም ይናገራል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ እና ቀኝ ምስክሮችን ሰምቷል። በአመልካች በኩል የቀረቡት ማስረጃዎች ሲታዩና ምስክሮች ከሰጡት ቃል በመነሳት፤ የአከራካሪው ቤት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ስለ ሃብቱ በተጠሪ እናት ስም የተመዘገበ መሆኑን የሚሳይ እና ግራ ቀኙ ይህን ያመኑ መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል፡፡
ሆኖም ቤቱ በአመልካችና በተጠሪ የጋራ ገንዘብ የተገዛ ስመ ሃብቱ በተጠሪ እናት ስም የሆነበት ምክንያትን ግራ ቀኙን ገዝተው ተጠሪ እናት ባለንብረት እንዲሆኑበት ሳይሆን አመልካች ጊዜያቸው ደርሶ ወደ ዱባይ ስለተመለሱ ግዥውን ባሉበት ጨርሰው በስማቸው ማድረግ ስላልቻሉና ተጠሪም እዚህ ሀገር ስላልነበሩ ሂደቱን እንዲያጠናቅቅ ውክልና ስልተሰጣቸው በስማቸው በመግዛታቸው እንደሆነና ይህንን እውነትም የተጠሪ ወንድም (ባለንብረት ናቸው የተባሉት የወይዘሮ መስታወት አማረ ልጅ) የሆኑት ለሦስተኛ ምስክር በተጠሪ እናት ስም የተመዘገበው ቤት አመልካች የገዙት ለመሆኑና ምርቃት ላይ እንዲገኙ ጠይቀዋቸው እንደነበር ከመሰከሩት ቤቱ የአመልካችና የተጠሪ የጋራ ሃብት መሆኑን ያሳያል፡፡
በእርግጥ በማስረጃነት የተያያዘው የይዞታ ማረጋጋጫ በተጠሪ እናት ስም በመሆኑ ባለንብረት መሆናቸው ግምት የሚወሰድበት ቢሆንም በአመልካች ማስረጃዎች የንብረቱ አመጣጥ ሥመ ሃብቱ በእርሳቸው ሥም የሆነበት አግባብ በአመልካች ማስረጃዎች በተገቢው የተረጋገጠ ስለሆነ የተጠሪ እናት ባለንብረት ናቸው ሊባል የማይችል በመሆኑ ባለንብረት የተጠሪ እናት ወይንም የተጠሪ ቤተሰብ አይደለም፤ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ቁጥር 62(2) መሰረት የግራ ቀኙ የጋራ ንብረት ነው በማለት ፍርድ ቤቱ ደምድሟ ሲል ያጠቃልላል፡፡
ይህን መደምደሚያ የሚያጠናክረው ደግሞ፤ የተጠሪ እናት ራሳቸውም በዚህ መዝገብ በተጠሪ በኩል ምስክር ሆነው ቀርበው በዚህ ቤትና ሌሎች በስማቸው የሚገኙ ንብረቶች ላይ እየተደረገ መብታቸውን ለማስከበር ያቀረቡት ክርክር አለመኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ የተጠሪ ቤተሰቦች ነው የሚል ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም ሲል ያብራራል፡፡
በእርግጥ አከራካሪው ቤት በተጠሪ እናት ስም መሆኑ ቢታይም የተጠሪ እናት በመዝገቡ ይህ ክርክር መኖሩን እያወቁ ምስክርም ሆነው ቀርበው በመመስከራቸው የሚታይበት በዚህ እና ሌሎች የተጠሪ እናት ንብረቶች ናቸው በተባሉ ንብረቶች ላይ ክርክር መኖሩን አውቀው መሳተፍን ስላልመረጡ ወደ ክርክር እንዲሄዱ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም የሚል ድምዳሜ ይሰጣል- ፍርድ ቤቱ፡፡
ፍርድ ቤቱ ከዚህ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በካርታቁጥርቦሌ9/15/1/11/22469/19347/01 የሚታወቅ የቦታው ስፋት 500 ካሬ ሜትር የሆነ ይዞታ በወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ ሥም ተመዝግቦ እንደሚገኝ ከተገለፀው ንብረት በተጨማሪም በሁለቱ ወገኖች የጦፈ ክርክር በተደረገበት ተሽከርካሪ ላይም ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በዚህም ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ሩዋንዳ አካባቢ ፓርሴል ቁጥር 7፤ 500 ካሬ ሜትር የሆነ በካርታ ቁጥር ቦሌ 9/15/1/11/22469/19347/01 የሆነ በወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ ስም የተመዘገበ ቤት እና ሰሌዳ ቁጥራቸው 03-01- 68801 እና 03-01-68803 ተሽከርካሪዎች የከሳሽ ተከሳሽ የጋራ መብት ናቸው በማለት ፍርድ ቤቱ ድምዳሜ ሰጥቷል።
ግራ ቀኙ የሰሌዳ ቁጥር 03-01-68803 ላይ እኩል የጋራ መብት እንዳላቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ተሸከርካሪው ወደ ሌላ ሰው ሥም ከተዘዋወረ ከሳሽ ግማሽ ድርሻቸውን ይህን ከወይዘሮ መስታወት አማረ ላይ ከሰው የመጠየቅ መብታቸው ተጠብቋል፤
ከሳሽና ተከሳሽ ንብረቶቹን ከተቻለ በዓይነት፤ በዓይነት መከፋፈል የማይችሉበት ሁኔታ ካለ ግምቱን በሥምምነት በመወሰን አሊያም መስማማት ካልቻሉ በሥምምነት በመሸጥ የሽያጭ ገንዘቡን ድርሻ በመውሰድ በዚህ ካልተስማሙ ደግሞ በሃራጅ ተሸጦ ገንዘቡን በመውሰድ እንዲከፋፈሉ ተወስኗል ይላል። ተከሳሽ ከሳሽ የጠበቃ ዓበል ከተከፈለው ውስጥ 50000 (ሃምሳ ሺህ ብር) ይተኩ ከሚል ድምዳሜ በኋላ ‹‹ይግባኝ መብት ነው መዝገቡ ተዘገቷል›› ሲል ይደመድማል፡፡
ፍረዱኝ
ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ነገር ይገርመኛል ይላሉ፡፡ ልጆቹ በሙሉ ተሰባስበው በጋራ ወስነው በእኔ እናታቸው ሥም የገዙትን ቤት ከምኑም የሌለበት አካል እንዲወስደው ሲፈረድ እንዴት እውነት ሊመስል ይችላል፤ ማንስ ያምናል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ለመሆኑ የወለድኳቸው ሰባት ልጆች ዕድሜ ዘመናቸውን ያፈሩትን ሃብት ድንገት ለሌላ አካል እንዲሰጥ ሲወሰን እንደምን አድርገው ችግሩን ይቋቋሙታል፤ እንደምንስ ከዚህ በኋላ ህይወት ትቀጥላለች ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
እኔ ለዘመናት ባፈራሁት ጥሪት የአንቺ አይደለም ተብዬ ቤቴ ላይ ፈራጅ ከመጣ እንደምን ልኖር እችላለሁ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ሁኔታ በጤናዬ ላይም ትልቅ እክል ፈጥሮብኛል-ለስኳር በሽታም ተጋልጫለሁ ይላሉ። በገዛ ንብረቴ ሃብቴን እንድነጠቅ ሲፈረድብኝ፤ ጤናዬም ከዳኝ ይላሉ። ብቻ ይህ ጉድ የሰማ እና ያየ ይፍረድ በጠራራ ፀሃይ ሃብት ገንዘቤን ተቀማሁ ‹‹ፍረዱኝ›› ይላሉ፡፡
ነገስ?
አሁንም ቢሆን አንድ ነገር ተስፋ አደርጋለሁ ይላሉ- ወይዘሮ መስታወት አማረ፡፡ ምንም እንኳን በማላውቀው እና ነገሮች ያለ ቅጥ ተወሳስበው በሃብት ንብረቴ ላይ ቢፈረድብኝም አሁንም ተስፋ የማደርገው የእኔ የሆነ ነገር የእኔ ነው፤ ማንም ሊጠቀምበት አይገባም ባይ ናቸው፡፡ ጉዳዩንም ህግ እንዲመለከተው ብዙ ጥረት አድርጌ የነበረ ቢሆንም ሰሚ ጆሮ አላገኘሁም፤ ግን አሁንም ቢሆን ህግ አለና ፍርድ ይስተካከላል የሚል ዕምነት አለኝ፤ ፍርድ ተጣሞ አይቀርም፤ ይላሉ- ወይዘሮ መስታወት አማረ ማሞ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2014