አዲስ አበባ፤- ነፃ የትምህርት እድል በሚል በህገወጥ ደላሎች የተጭበረበሩ እና በአደንዛዥ እጽ ዝውውር መረብ ሰለባ የሆኑ 47 ኢትዮጵያውያን በቻይና ለእስር እና እንግልት እየተዳረጉ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትናንትና መግለጫ ሰጥተዋል፤ በተጭበረበረ የትምህርት ዕድል እና በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ምክንያት 47 ኢትዮጵያውያን ለእስር ተዳርገዋል። ከታሰሩት ውስጥ ገሚሱ ፍርድ የተጣለባቸው ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የፍርድ ሂደታቸውን የሚከታተሉ ናቸው።
እንደ አቶ ነቢያት ገለጻ፤ ወደ ቻይና በተሳሳተ የነጻ ትምህርት እድል ሰበብ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ገንዘብ ከመክሰራቸው በተጨማሪ ህገወጥ ተብለው እንዲታሰሩ ምክንያት ሆኗቸዋል። አንዳንዶቹም በነጻ የትምህርት እድል ሰበብ የሄዱ ወጣቶች የያዙት የተሳሳተ መረጃ መሆኑን ሲያውቁ ወደ ኢትዮጵያ ከመመለስ ይልቅ ያለፈቃድ ቻይና ውስጥ እየኖሩ ነው። ሌሎች ደግሞ ስርቆት እና የአደንዛዥ እጽ ዝውውር ውስጥ እየተሳተፉ በመሆኑ ለእስር ተዳርገዋል።
በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና በሚደረግ ጉዞ ማንኛውም ሰው ጫት እና የተለያዩ አደንዛዥ እጾችን ይዞ መጓዘ አይችልም። በቻይና ህግ መሰረት ጫትም ሆነ ሌሎች እጾችን ይዞ መገኘት እስከእድሜ ልክ የሚደርስ የእስር ቅጣት ያስከትላል። በመሆኑም የተለያዩ ሰዎች ከአየር ማረፊያዎች ጫት አድርሱልን በሚል ሰበብ ተቀብለው የሚወስዱ ተጓዦች ቻይና በሚደርሱበት ወቅት በእጽ ዝውውር ለእስር መዳረጋቸውን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።
አቶ ነቢያት እንደገለጹት፤ ቻይና ቤይጂንግ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በጉዋንጆ፣ ሻንጋይ እና ቻንቺን ከተሞች የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንጽላዎች አማካኝነት የኢትዮጰያውያንን ጉዳይ ክትትል እየተደረገበት ነው። የህገወጥ ደላሎችን ስራ ለመከላከል አዲስ አበባ ከሚገኘው የቻይና ኤምሳሲ እና የቻይና መንግስት ጋር የጋራ ጥረት እየተከናወነ ይገኛል። በመሆኑም ማንኛውም ተማሪ ነጻ የትምህርት ዕድል ከቻይና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲደርሰው ስለትክክለኛነቱ እና ህጋዊነቱ በቂ ማጣራት አድርጎ መጓዝ ይኖርበታል።
ቻይና የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን በህገወጥ ደላሎች አማካኝነት ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን በመገንዘብ ማንኛውም ሰው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከቻይና ኤምባሲ ጋር ስለጉዳዩ ቅድሚያ ማጣራቶችን ማድረግ ይገባዋል። በተጨማሪ ወደ ቻይና የሚጓዝ መንገደኛ ከሌላ ሰው የተቀበለውም ይሁን ራሱ የያዘው ጫት እና ሌሎች እጾች ካሉ መዳረሻው ላይ እስራት እንደሚያጋጥመው አውቆ ከድርጊቱ መታቀብ እንዳለበት አቶ ነቢያት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ቃል አቀባዩ እንደገለጹት፤ በህገወጥ መንገድ ከሚጓዙ ኢትዮጵያውያን መካከል በዚህ ሳምንተ 1 ሺ 40 ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ እንዲሁም 1ሺ415 ዜጎችን ደግሞ ከፑንት ላንድ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ተደርጓል። በቀጣይም በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በኩል 1ሺ17 ዜጎች ከሳዑዲ አረቢያ እና ከፑንት ላንድ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
ጌትነት ተስፋማርያም