እናቶቻችን ድሮ ከአደዋ ጦርነት ጀምሮ ለባሎቻቸውና ለወንድሞቻቸው ስንቅ ያዘጋጁ ነበር።ያለ እንደዚህ ዓይነቱ የሴቶች ተሳትፎ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ጦርነት አላሸነፈችም።ያኔ ኢትዮጵያ ላይ ፋሽሽት ኢጣሊያ ከአንድ ሁለቴ ጦርነት ስትከፍት አብሮ ከመዝመት ባሻገር የስንቁን ጉዳይ የያዙት እናቶች ነበሩ።
ሴቶች ሀገር እንዲህ አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ትና ኦነግ ሸኔ እንደከፈቱት ባለው ጦርነት በምትገባበት ወቅት ግንባር በመዝመትም ሆነ በደጀንነት ጥንድ አስተዋጾ ማበርከታቸው አዲስ አይደለም።በተለይ ከዚህ አስተዋጾ ዋንኛው የሆነው ሥንቅ ዝግጅት ከአደዋዋ ጀግና ከእቴጌ ጣይቱ ቡጡል ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ታሪክ በመሆኑ አይገርምም። ባሳለፍነው ቅዳሜ ‹‹መቶ ኩንታል በሶ ለሠራዊታችን የስንቅ ድጋፍ እንቅስቃሴ›› በሚል በአራዳ ክፍለ ከተማ ጊቢ ውስጥ በአምስት ታዋቂ ሴት ጋዜጠኞች አስተባባሪነት በይፋ የተጀመረው ስንቅ ዝግጅት መርሐ ግብር ግን አዲስም አስደናቂም ነበር።ይሄን የሚያስብለው አንድም ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም መደረጉ፤ሁለትም ዝግጅቱ የእህትና እናቶችን ድካም በሚቀንስ ሂደት መከናወኑ ሦስትም በቀላሉ፣በፍጥነትና ጥራት የሚዘጋጅ መሆኑ ነው።
አንገት የሚያስደፋው የአባታዊው ስርዓት በሴት ልጆች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያዊያን ባህል ለሴት ልጅ ትልቅ ክብር ይሰጣል።ሴት ልጅን ቀና ብሎ ከማየት ጀምሮ መጎንተልና ማዋረድ አሳፋሪ ነውር ነው።ሆኖም ጾታ ሳይለይ ፤ሴት ሆነውም ነግ በኔ ሳይሉ አንዲት ሴት ለአራት እስከ መድፈር ለደረሰውና በገዛ ሀገሩ ላይ ጦርነት ላወጀው ቡድን የሚወግኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች አሉ።ይሄን ዕውነታ ሆን ብለው ሀገር የሚበትንን ሀሳቡን ሼርና ፖስት እያደረጉ ከሚያራግቡት በተጨማሪ ቡድኑ በሰሜንና ደቡብ ወሎ ከፍቶት በነበረ ጦርነት የበግ ለምዳቸውን በመልበስ ወጣቱን መስለው የሴት ልጆችን ስም ዝርዝር ለወራሪው ኃይል እየሰጡ ያስደፈሩትን በመጥቀስ መግለፅ ይቻላል።
ቡድኑ በዓለም በተለይም በምዕራባዊያኑ ዘንድ የሀሰት ፕሮፓጋንዳው እውነት እንዲመስል ያደረገውም ከቢሮና ጎረቤቶቻችን ጀምሮ በሀገርና በዓለም ዙርያ የተበተኑ እነዚህ አዛውን ነካሽ ክፍሎች የሀሰት አካወንት በመክፈት ጭምር በማህበራዊ ሚዲያ (በማህበራዊ ድህረ ገጽ)የሚጮሁለት እኩይ ጩኽት ነው።ጩኽታቸው ሀሰተኛ ቢሆንም ወደድንም ጠላንም ኃያላን ነን የሚሉት ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳርፉ አስችሏል።የመከላከያ ሠራዊት ቴሌቪዢንዋን ሻለቃ ወይንሀረግ በቀለንና የኢሳቷን ጋዜጠኛ የምሥራችን ጨምሮ እናቶችን የተመለከቱ ጉዳዮችን በማስተዋወቅ የምትታወቀው ሮዝ መስቲካ እንዲሁም የሥራ ፈጠራ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን አማካሪዋ አዜብ ታምሩና ታዋቂዋ ጋዜጠኛ ስመኝ ግዛው የስንቅ ዝግጅቱን ማዘጋጀት የቻሉት ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ነገር በመጠቀም ነው።
አምስቱም ጋዜጠኞች ማህበራዊ ሚዲያ አንድ ቤተሰብ ያደረጋቸው ሲሆኑ የሀሳቡ ጠንሳች ለረጅም ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያዋ የምትታወቀው ስመኝ ግዛው ነች።ስመኝ በአሁኑ ሰዓት በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሚኒስትሯ የኮሚኒኬሽን አማካሪ በመሆን እየሠራች ብትገኝም በስነጽሑፉ ዓለም በተለይ በግጥም ሥራዋም ታዋቂ ነች።እንዳጫወተችን ይሄ ተደማምሮ በማህበራዊ ድህረ ገጽ ከስምንት ሺህ በላይ ተከታዮች እንድታፈራ አስችሏታል።ቢሆንም ጥቅምት 27 .2014 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ ሀገራችን ጦርነት ውስጥ ናት።ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የጾታ አጋሮቻችንን ከወንድሞቻቸው ጎን በግንባር በመሰለፍ እየተዋደቁ ነው።እኛ እዚህ ማህል ከተማ ያለነው ሴቶች በጦር ሜዳ ባንዋደቅም አንድ ነገር ማድረግ አለብን።
ይሄ አንድ ነገር ደግሞ ከእናቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ የወረስነው ስንቅ መሆን አለበት በሚል በአእምሮዋ ያቃጨለውን ሀሳብ መነሻ በማድረግ ‹‹የዚህ መንደር ቤተሰብ ሴቶች ለሠራዊታችን ለምን ስንቅ አናዘጋጀም›› ስትል በፌስ ቡክ ፖስት ያደረገችው በሳምንቱ በሀገር ውስጥና በውጪ ያሉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ፈጣን ምላሽ አግኝቶ ለዝግጅት ይበቃል ብላ አላሰበችም።ቅዳሜ ሀሳቡ በተፀነሰበት መልኩ ተነሳ። አምስቱ እንስቶች ለዚህ ለተቀደሰ ዓላማ ማህበራዊ ሚዲያና አብዝተው መጠቀም እንዳለባቸው ተስማሙና ሀሳቡን በመቀባበል በየፊናቸው ፖስት ሲያደርጉት ዋሉ።
እሁድ የሚዘጋጀው ስንቅ ቆሎ ይሁን በሶ እየተባለ ሲብላላ ቆየ።በሦስተኛው ቀን ሰኞ በማህበራዊ ሚዲያው ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያኖች ያገኙት ፈጣን የአፃፋ ምላሽ እንስቶቹን መቀመጥ አላስቻላቸውም።አዎ ስንቅ እናዘጋጅ፣እሰይ አበጃችሁ!፣አለን፣ምን እናግዛችሁ፣በርቱ የሚለው ንፁህ የኢትዮጵያዊነት ፍቅርና ትህትናን እንዲሁም የመረዳዳት ባህልን የተላበሰው የድጋፍ ድምፅ ከየአቅጣጫው ተዥጎደጎደላቸው።ሀሳቡን ያመነጨችው ጋዜጠኛ ስመኝ ሁኔታውን ፦
‹‹ጭራሽ አካወንታችሁን ውለዱ አሉን።አካወንት አልከፈትንም ገና ነው ብንላቸው ሊሰሙን አልቻሉም።በፍጥነት ላኩልን እያሉ በጥያቄ ወተወቱን›› ትለዋለች።ይሄን ምክንያት አድርጎ ሀገሩ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ከልብ ያዘነ፣ያለቀሰ፣መጨነቅና መጠበቡን በስልክና በጽሑፍ የገለፀላቸውም ዜጋ ስፍር ቁጥር አልነበረው። በአጠቃላይ የሀገር ጉዳይን የተመለከተውን ይሄን ድንቅ ሀሳብ እንደዋዛ በሚል አቃላይ ቃል መግለፁ ቢጎረብጥም ጋዜጠኛዋ እንደዋዛ ያነሳችው ሀሳብ በማህበራዊ ሚዲያው ያቀጣጠለው ንቅናቄ እጅግ ከፍተኛ ሆነ።እንስቶቹ በመደዋወል በግንባር ተገናኝተው በፍጥነት እንዲወያዩበትም አስገደዳቸው።በግንባር ተጋናኝተውም ተወያዩበትና ‹እኛ ሴቶችና እናቶች ነን።የምናደርገው ጥሪ በእናት ሀገር መሰየም አለበት በሚል ስም አውጥተው ማክሰኞ ዕለት አካወንት ከፈቱለት።100 ኩንታል በሶ የማዘጋጀት ዕቅዳቸውንም ይፋ አደረጉ።
‹እኔ 10 ኪሎ ገብስ፣ አንድ ኩንታል ፉርኖ ዱቄት፣ይሄን ያህል ስኳር፣ይሄን ያህል ብር እሰጣለሁ፣ምን በሶ ብቻ ዳቦ ቆሎ ጨምሩበት፣ቆሎ ጨምሩበት፣ ድርቆሽ ጨምሩበት›የሚለው ተበራከተ።የምን 100 ኩንታል 500 ኩንታል አዘጋጁ እንጂ አሏቸው።ማንነታቸውን ሳያውቁና ገንዘባችን ይበላብናል የሚል ቅንጣት ስጋት ሳይገባቸው የሀገር ጉዳይ የጋራ ጉዳይ ነው በሚል ዕምነት ምን እናድርግ፣ምን እናግዛችሁ በማለት ገንዘባቸውን እየላኩ ይገኛሉ።ከነዚህ የእንስቶቹ የፌስ ቡክ ቤተሰቦች ሀገር ውስጥ ያሉት የስንቅ ዝግጅቱ መርሐ ግብር ባለፈው ቅዳሜ በአራዳ ክፍለ ከተማ በይፋ ሲጀመር ተገኝተዋል። በተለይ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ምን እናድርግ ብለው እየተጠራሩ ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር የገለፁበትን ይሄን ምላሽ ጋዜጠኛ ስመኝ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ያየንበት ነው።በቃላት ልገልፀው አልችልም ››ትለዋለች።
አንዳከለችልን እንስቶቹ ቃል ማስገባቱንና መመዝገቡን አፋጠኑት።ሀሳቡ በተነሳ በሦስተኛው ቀን ብቻ ፌስ ቡክን በመጠቀም ከሀገር ውስጥና ከውጪ ከ350 ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ መሰብሰብ ቻሉ።በአካል መጥቶ ይሄን ያህል የበሶ ዱቄት፣ይሄን ያህል የፉርኖ ዱቄት፣ይሄን ያህል ሊትር ዘይት፣ይሄን ያህል ኪሎ ስኳር እሰጣለሁ በማለት ቃል የገባውን አይጨምርም።ይሄንኑ የሰጠውንም አያካትትም።የተቆጠረው እስከ ሦስት ቀን በጥሬ ገንዘብ የተሰበሰበው ብቻ ቢሆንም ገንዘቡ ሳያሰልስ ወደ ቋቱ እየገባ በመሆኑ ከሦስት ቀን በኋላ የሚሰበሰበው የታቀደውን ያህል እንደሚሆን ይገመታል።
መነሻው 100 ኩንታል ይሁን እንጂ መድረሻው 400 ኩንታል የሆነውንና በአንድ ኪሎ የሚፈለገውን መቶ ብር ሂሳብ ጥሪት ያሳካል ተብሎ ታስቧል።ጋዜጠኛ ስመኝ እንደነገረችን ይሄን እሳቤ የሰነቀው ስንቅ ዝግጅት በአራዳ ክፍለ ከተማ ጊቢ ወደ መሬት ወርዶ በይፋ መተግበር ሲጀምር በዋናነት በስንቅ ዝግጅት የተሻለ ልምድ ያላቸውና በክፍለ ከተማው ሥር በሚገኘው ወረዳ ስድስት ሥር ያሉ እናቶች ተሳትፈውበታል።ከሙቀጫ ዘነዘናና ብረት ምጣድ ጀምሮ የተለያዩ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችንም አቅርበዋል።በየግላቸውም በሶ ዱቄት፣ፉርኖ ዱቄት፣የቆሎ ገብስ፣ስኳር፣ዘይት ለግሰዋል።
ከነዚህ የወረዳው ተሳታፊ እናቶች አንዷ ወይዘሮ ያሳብ ተፈራ ናቸው።እንደገለፁልን በወረዳው የብሎክ 59 ሰብሳቢ ናቸው። በአዲስ በተዋቀረው የፀጥታ ጉዳይ በሻንበልነት 81 የብሎኩን ነዋሪ እማ ወራዎች ያስተባብራሉ።በክፍለ ከተማው ጊቢ ውስጥ ዳቦ ቆሎ ሲቆርጡ አግኝተን አነጋግረናቸው፦
‹‹ሴት ሁሌም ደጀን ናት።ሴት ከሌለች ሀገር የለም።በዚህ መርሐ ግብር ላይ እኔ ከማስተባብራቸው ሴቶች ጋር የተገናኘነውም ይሄን በተግባር ለማረጋገጥ ነው››ብለውናል።ከበሶ ዱቄት ዘይት፣ለድርቆሽ የሚሆን ደረቅ እንጀራ ጀምሮ አባላቱ በየግላቸው አዋጥተዋል።‹‹ቁመቴ ካልጣለኝ በበኩሌ ግንባር ድረስ ሄጄ ለመዋደቅ ወስኛለሁ››ያሉን ወይዘሮ ያሳብ እንዳከሉልን በየቀጠናና በየመንደሩ ተደራጅተው ቤት ለቤት እየዞሩ ዳይፐር፣ሞዴስ፣ፓስታ፣ማኮሮኒና አልባሳት እያሰባሰቡ ይገኛሉ።
የሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ነዋሪና የመቶ መሪዋ ወይዘሮ ተዋበች አንዳርጌ ዳቦቆሎ፣ቆሎና በሶ ከማዘጋጀት ባሻገር አስፈላጊ ከሆነ እስከ ግንባር በመሄድ ከመከላያው ጎን ለመቆም ቆርጠው መነሳታቸውን ገልፀውልናል።ምዕራባውያኑ አርሰን መብላት የምንችል የአርሶ አደር ልጆች መሆናችንን ማወቅ የከተማው ነዋሪዎችም በከተማ ግብርና ተሰማርተው የዕለት ጉርሳቸውን የማይሸፍኑበት እንደሌለ ማወቅ አለባቸው።በመሆኑም በእርዳታ ስም በአገራችንንና በግላችን ጉዳይ ጣልቃ መግባት ያቁሙ ብለዋል።
‹‹ከተማ ስለተቀመጥን ያልተነካን ከመሰልን ተሳስተናል›› ሲሉም ሁሉም ያለውን በማካፈል የመከላከያ ሠራዊቱን መደገፍና መሳተፍ እንዳለበት ገልፀውልናል።በበኩላቸው 10 ኪሎ ዱቄት ፣አንድ ሊትር ዘይት ሁለት ኪሎ ስኳር ይዤ ነው በስንቅ ዝግጅቱ እየተሳተፍ ያለሁት ብለውናል።በተጨማሪም ሁለት ኩንታል ተኩል ጫማ ፣10 ኩንታል ልብስ ፣ ሁለት ኩንታልማኮረኒ ሰብስበው ደብረብርሃን ትምህርት ቤት ውስጥ ለፈሰሱትና በጦርነቱ ለተፈናቀሉት ለመስጠትና በወረዳው ዛሬ በሚጀመረው ደም ልገሳ ለመሳተፍ ማቀዳቸውን ገልፀውልናል ።
ሌላዋ በስንቅ ዝግጅት ከሁለት ጊዜ በላይ በመሳተፍ የስንቅ ዝግጅት ልምድ ማካበታቸውን የገለጹልንና ዳቦ ቆሎ ሲቆሉ ያገኘናቸው የወረዳ 4ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት አያሌው በዝግጅቱ በራሳቸው ተነሳሽነት መሳተፋቸውን ነግረውናል።ከወረዳ አራት ብሎክ 16 አመራር ወይዘሪት የዓለም ዘርፍ ይርዳው እንደገለፀችልን ሴቶች ከስንቅ ዝግጅቱ ባሻገር አካባቢያቸውን ከአሸባሪው ቡድን ለመጠበቅም ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረጉ ነው።እሷ 27 ሴቶች ትመራለች ከሁሉም ጋር በመሆኑም ማታ ማታ በፈረቃ በመውጣት እየዞሩ አካባቢያቸውን ከሰርጎ ገቦች ጥቃት ይከላከላሉ።
የኢፌዴሪ መነከላከያ ሠራዊት የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀርጄነራል ጥሩዬ አሰፌ በማስጀመርያ መርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ሴቶች በግንባር ከወንዶሞቻቸው ጎን በመሰለፍም ሆነ በስንቅ ዝግጅቱ እያደረጉት ያለው ድጋፍ አሸባሪው በከተሞች ሊሰነዝር የሚችለውን ጥቃት ለመመከትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።በአጠቃላይ ስመኝና ተሳታፊዎቹ እንደገለፁልንም ሆነ እኛም እንዳስተዋልነው ስንቁ የሚከናወንበት ቦታ ምቹ ካለመሆን ጀምሮ ተሳታፊ እናቶችን በብዙ ያደክማል።
ጊዚያቸውንም ያባክናል።በመሆኑም በእናቶች ጉልበት አይዘለቅም።በዚህ ላይ ዘመኑ ጭስ አልባ የምግብ ማብሰያ ቴክኖሎጂዎች የሞላበት ነው።በመሆኑም የክፍለ ከተማው ስንቅ ዝግጅት ማስጀመሪያ እናቶች ፍቅራቸውንና ዝግጁነታቸውን ለሠራዊቱ የሚያሳዩበት ነው።በመሆኑም ስንቅ ዝግጅት ሥራው በአፍሪካ ደረጃ ባለና ደህንነቱና ጥራቱ በተጠበቀ ዘመናዊና በኤሌክትሪክ የሚሠራ፣ማብሰያ፣መፈተጊያና መቁያ ላላቸው ድርጅቶች ሊሰጥና በሁለት ሳምንት ሊጠናቀቅ ታስቧል።
እኛም በዚህ መልኩና ጊዜ እንኳን 100 ፤500 ኩንታልም ስንቅ ማዘጋጀት ይቻላልና የእንስቶቹ የፌስ ቡክ ስንቅ ዝግጅት ተሳትፎ ተበረታቶ ይቀጥል እንላለን።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2014