ሶሪያ ለምን ፈራረሰች? የመን ለምን የረሃብና የጦርነት ማዕከል ሆነች? ሊቢያ ለምን የጎበዝ አለቆች መፈንጫ ሆነች ? የሚል ጥያቄ ሲነሳ በተቀናጀ መልኩ ሲካሄድ የነበረ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን የሐሰት ዘገባና ፕሮፖጋንዳ የሚል ምላሽ አብሮ ይነሳል።
እነዚህ አገራትና መገናኛ ብዙሃን በተለይ ወራሪውና አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከፈፀመ በኋላ መንግሥት የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ መጀመሩን ተከትሎ ሙሉ ትኩረታቸውን ኢትዮጵያ ላይ አድርገዋል።
በተለይ ባለፉት ሳምንታት የተለየና አዲስ እንግዳ አካሄድን በመከተልና ከተለያየ አቅጣጫ በተቀነባበረ መልኩ የሐሰት ዘገባን በማራገብ ዓለም ኢትዮጵያን በተሳሳተ መንገድ እንዲገነዘብ የማስጨነቅ፣የመክሰስ፣የመወንጀል ዘመቻን ተያይዘውታል።
‹‹አዲስ አበባ ተከባለች›› ከሚለው አንስቶ በተከታታይ በቁጥር በርከት ያሉ የሐሰት ዘገባዎችን ሠርተዋል። ባልተለመደ መልኩም በአራት ቀናት ብቻ አምስት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን አስመልክቶ 72 ሐሰተኛ ዘገባዎችን አሰራጭተዋል።
ለመሆኑ መገናኛ ብዙሃኑ በአሁን ወቅት ለምን በዚህ መልክ ስሜታዊና ግልጽ ደጋፊ እየሆኑ መታየት ጀመሩ? ዓላማቸው ምንድነው? ከሙያዊ ስነምግባር አንፃር ተግባራቸው እንዴት ይቃኛል? የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ጦርነቱን በመመከት ረገድ ሥራቸው እንዴት ይገመገማል? ይህን ወቅት ለመሻገርስ ምን መድረግ ይኖርባታል? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ለተለያዩ ምሁራንና ባለሙያዎች ጥያቄ አቅርቧል።
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለብዙ ጊዜ የሚዲያ ሥራዎችን በመሥራት የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሠላም ሙሉጌታ እንደገለጸው፤ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች የሚያሰራጩት ዘገባ በእጅጉ በውሸት የተሞላ ከመሆኑም በተጨማሪ የሚሰጡት የአየር ሽፋንም በጣም የሰፋ ነው።
በተለይም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከነበረበት ቦታ ወደ ደሴና ሌሎች አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ ጉዳዩን ሆን ብለው ሲቀባበሉ መታየታቸውን የሚያስታውሰው ሰላም፣ ‹‹በተለይም በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ የተደረጉት ምርመራዎች ውጤት ምዕራባውያኑ እንደፈለጉት ባለመሆኑ እጅጉን አበሳጭቷቸዋል፣ ይህን ተከትሎም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በተቀናጀ መልኩ የውሸት ዜና ለመፈብረክ ተገደዋል›› ይላል።
በኢትዮጵያ ላይ የጀመሩት ሐሰተኛ ውንጀላና የተዛባ መረጃ ቅብብሎሽ ዓለም አቀፍ ማኀበረሰብን ለማሳሳትና መንግሥትን በአስገዳጅ ወደ ድርድር ለማስገባት ከማሰብ የመነጨ ስለመሆኑ የሚያመላክተው ጋዜጠኛው፣የሚዲያው ባለቤቶች፣አስተዳዳሪዎችና ተቋማትም የርዕዮተ ዓለም አገልጋዮች እንጂ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ማዕከል ያደረጉ እንዳልሆኑ ያሰምርበታል።
በዚህ እሳቤ የሚስማሙበት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህሩ አቶ በለው አንለይም፣ የጋዜጠኝነት ሙያ የገለልተኝነትና የሚዛናዊነት ሙያዊ መርሆችን መሰረት ያደረገና እውነትን በማፈላለግ ላይ የሚያተኩር ቢሆንም የምዕራባውያን ሚዲያዎች ከጋዜጠኝነት የሙያ መርህ ባፈነገጠ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ የተዛባ መረጃ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።
‹‹አዲስ አበባ ተከባለች፣ ህዝቡ ተረብሿል›› በማለት ከፍተኛ የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻ ቢነዙም መረጃው እውነት አለመሆኑን የራሳቸው ዜጎች ሳይቀር እያጋለጡ ስለመሆኑ የሚጠቁሙት መምህሩ፣ መገናኛ ብዙሃኑ የኢትዮጵያን እውነታ ወደ ጎን ትተው ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ላይ የተጠመዱት የእነሱን ይሁንታ ያላገኘ መንግሥት እንዲኖር ካለመፈለግ በመነጨ ነው›› ይላሉ። ወደ ራሱ ማንነት ወደ ራሱ ክብር መመለስ የሚፈልግን ማንኛውንም አገር ካለመፈለጋቸው የተነሳ ስለመሆኑም ያሰምሩበታል።
ሲኤን ኤን፣ቢቢሲ፣አልጀዚራ፣ፍራንስ 24፣ሮይተርስ የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት በበርካታ የትምህርት ተቋማት ለዘመናዊ ጋዜጠኝነት እንደ ማጣቀሻ የሚወሰዱ ተቋማት እንደነበሩ የሚያመላክቱት አቶ በለው፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ እየተከተሉት ባለው የሐሰት ዘገባ በርካታ ወገኖች ተቋማቱን መለስ ብለው እንዲመረምሯቸው ስለመገዳዳቸውም ይጠቁማሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሳምሶን መኮንንም ምዕራበውያን መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚሠራቸው ዘገባዎች ከጋዜጠኝነት መርህና ስነምግባር ጋር በግልጽ መራራቃቸውን እያስመለከቱ ስለመሆኑ ይስማሙበታል።
‹‹ዘገባዎቻቸውም የአገሮቻቸውን መንግሥታት ፍላጎትና ስሜት የሚያንፀባርቅ ነው፣ ከጀርባ የየአገራቱ እጅ በግልጽ ይታያል›› የሚሉት ዶክተር ሳምሶን፡ይህም መገናኛ ብዙሃኑ ከጋዜጠኝነት ሙያ ክብራና መርህ ይልቅ ግድ የሚሰጣቸውና የማይደራደሩት የአገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ማስከበር ላይ መሆኑን እንደሚያሳያ ይጠቁማሉ።
‹‹የውጭ መገናኛ ብዙሃኑ የአገሮቻቸውን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስጠብቁ ከሆነ የኢትዮጵያ ሚዲያም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስከብር መሆን አለበት›› የሚሉት ዶክተር ሳምሶን፣የአገሩን ህልውና እና ብሄራዊ ጥቅም የማያስከብር መገናኛ ብዙሃንም ትርጉም እንደሌለው አፅእኖት ይሠጡታል። በአሁን ወቅትም ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚሰራጭ የትኛውም መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚጠብቅና በሚያስከብር መልኩ መሥራት እንዳለበት ያሰምሩበታል።
እንደ ዶክተር ሳምሶን ገለጻ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት አገር አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስትገባ ወቅቱን የሚመጥን ሥራ በማከናወን አገራዊ አንድነትና አብሮነትን የሚያጠናክሩና ዜጎች ለአገራቸው እንዲነሳሱ አስተዋጽኦ በማድረግ ረገድ ድርብ ኃላፊነት አለባቸው።
ይሁንና ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃኖች ከዚህ በፊት ከተለመደው አሠራርና የአዘጋገብ ስልት ወጥተው ኢትዮጵያና ዜጎቿን ከገጠሙት ወቅታዊ ችግሮች ሊያሻግሩ በሚችሉ ዘገባዎች በማቅረብ ረገድ አስተዋፅኦአቸው በሚፈለገው ልክ እንዳልሆኑ ሲነገር ይደመጣል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣንም፣ በአሁን ወቅት የህዝብ ሚዲያዎች በአንፃራዊነት በአገራዊ ህልውናው የተሻሉ ሥራዎችን እያከናወኑ ቢሆንም አብዛኞቹ የግል መገናኛ ብዙሃን በአንጻሩ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተገንዝበው ለዚህም የሚመጥን ሥራ እየሠሩ እንዳልሆነ ከቀናት በፊት አሳውቋል።
ዶክተር ሳምሶን መኮንንም፣የአገርን ህልውና እና ብሄራዊ ጥቅም ለማስከብር ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተገንዝበው ለዚህ የሚመጥን ሥራ በመሥራት ረገድ መገናኛ ብዙሃን በሚፈለገው ቁመና ላይ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ።
እንደ ዶክተር ሳምሶን ገለጻም፣የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት በተለይም ወቅታዊና እለታዊ መርሃ ግብር መሰረት ባደረገ መልኩ የህዝብ አስተሳሰብ ማስተካከል ላይ ነው፣ታሳቢ አድርገው የሚሠሩትም የአገር ውስጥ ታዳሚና በአገር ውስጥ ቋንቋ ነው። ይህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን እየሆነ ነው የሚለውን ጠንቅቆ እንዳይረዳ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል።
በአሁን ወቅት ስለ ጦርነቱ የተዛባ አረዳድ የሚስተዋለው የውጭ መገናኛ ብዙሃኑ በሚሠሩት የሐሰት ፕሮፖጋንዳና ዘገባ ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ምዕራባውያኑን ታሳቢ ያደረጉና የሚመጥኑ የበሰሉ ሥራዎችን መሥራት ባለመቻል ነው። አጀንዳ ከመስጠት ይልቅ ተቀባይ በመሆንና አነሱን ተከትሎ ይህ እውነት ነው፤ ይህ ውሸት ነው እያሉ መቀጠል አሸናፊ አያደርግም።
በአሁን ወቅት የህዝብ ሚዲያዎች በአንፃራዊነት በአገራዊ ህልውናው የተሻሉ ሥራዎችን እያከናወኑ ቢሆንም የግል መገናኛ ብዙኃን ሚና በአንፃሩ ‹‹በጣም የሚያሳዝን›› ነው ሲሉ የሚገልጹት ዶክተር ሳምሶን፣ የአገር ህልዋና ጥያቄ ውስጥ በወደቀበትና አሳሳቢ በሆነበት በዚህ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ስፖርትና ፊልሞችን የሚያስኮመክሙ የግል መገናኛ ብዙኃን ማስተዋላቸውም ለተፈጠረባቸው ስሜት መነሻ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ምንም እንኳን ለንግድ የተቋቋሙ ቢሆንም የአገር ህልውና ጥያቄ ውስጥ በሚገባበት ወቅት እያንዳንዱ መገናኛ ብዙኃን ለጊዜው የሚሠራውን ቢዝነስ በመተው አገርን የማዳን ሥራ ላይ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም አፅእኖት ይሰጡታል።
‹‹ይህ ዓይነት ችግር የሚከሰተው ፈቃድ ሲሰጥ ነው›› የሚሉት ዶክተር ሳምሶን፣ችግሩን ለማስቀረት ለመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ ሲሰጣቸው የአገርን ህልውናና ብሄራዊ ጥቅም እንደሚያስጠብቁ እና እንደሚያስከብሩ የሚያስገድድ መስፈርትና ስምምነት ሊኖር እንደሚገባም ሳያመላክቱ አላለፉም።
‹‹የግል መገናኛ ብዙኃን ህጋዊ ብቻም ሳይሆን የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው ሊረዱት ይገባል፣ ምክንያቱም መገናኛ ብዙሃን የሚኖሩት አገር ስትኖር ነው›› የሚሉት ዶክተሩ፣ይህ እንዲሆን ለማድረግ ተቋማቱን የሚያቀናጅ፣ የሚያስተባብርና አቅጣጫ የሚያሳይ ሊኖር እንደሚገባና የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎትም ሆነ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በዚህ ረገድ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት፡
በጦርነት ወቅት ፕሮፖጋንዳና መረጃ እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን መሬት ላይ ከሚካሄደው ጦርነት በላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አላቸው። መገናኛ ብዙኃን አበርክቶ ግን በህዝብ የሚዲያ እውቀት ወይንም ንቃተ ህሊና ካልታገዘ የዜሮ ድምር እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። በተለይ የሐሰት ዘገባዎች ጀርባ ያለውን ስውር እጅ የሚገነዘብ ማህበረሰብ የግድ ይላል።
በዚህ ረገድ ሃሳባቸውን የሚያጋሩ ምሁራንም እንደሚያስረዱት ከሆነ ግን ፣የኢትዮጵያ ህዝብ የሚዲያ ንቃተ ህሊና አነስተኛ ነው። ይህን እሳቤ የሚያጠናክሩት፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር አንተነህ ጸጋዬም ‹‹እንደ አገር ትልቁ ችግር ሐሰተኛ መረጃን ሁሉ ትክክል አድርጎ የመቀበል ሁኔታ መኖሩ ነው። መረጃን የመገምገም፣የማገናዘብ ልምድ ባለመኖሩ ሐሰተኛ መረጃን በቀላሉ የመቀበል ሁኔታ ይስተዋላል›› ይላሉ።
አንድ ሰው ሚዲያን እንዴት ይረዳዋል የሚለው የራሱ መለኪያ እንዳለው የሚጠቁሙት ዶክተር ሳምሶንም፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያውያን የሚዲያ ንቃተ ህሊና በጣም ዝቅተኛ ነው። ከሚዲያ የሚመጣው መረጃ በአጠቃላይ እውነት ነው ብሎ መቀበል፣ ሳያረጋግጡ ማጋራት፣ ማመንና በቀላሉ መሰበር የሚታይበት ነው›› ይላሉ። ‹‹አዲስ አበባ ተከባለች በተባለበት የሐሰት ዘገባ ወቅት ህዝብ መረበሹና አንዳንዶችም ከተማ ለቀው እስከመውጣት መድረሳቸውን በዋቢነት ያቀርበዋል። የመንና ሶሪያ ለዚህ ደረጃ የደረሱት በሚዲያ ጦርነትና በህዝቡ ንቃተ ህሊና ማነስ መሆኑን የሚያስገነዝቡት ምሁሩ፣ በዚህ ረገድ ከፍተኛ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠይቅም ነው አፅእኖት የሰጡት።
የምዕራባውያኑን የሐሰት ዘገባ ጦርነት እንዴት እንቀልብሰው? ለሚለው ጥያቄም አስተያየት ሰጪዎቹ ምክረ ሃሳብ የሚሉት አላቸው። በተለይም የመገናኛ ብዙኃኑ ስውር ደባና ፍላጎትን አስቀድሞ መገንዘብ እንደሚገባ ያሰምሩበታል። ‹‹የግሉም ሆነ የህዝብ መገናኛ ብዙኃንም ወቅቱን የሚመጥን ሥራ መሥራት የግድ ይላቸዋል›› ይላሉ።
ዶክተር ሳምሶን እንደሚገለጹቱ ከሆነ፣ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተለያየ አስተሳሰብና የስነ ልቦና ውቅር ያለው ነው። ይህ እንደመሆኑም መገናኛ ብዙኃን ለአገር ውስጥ የሚሠራና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሠራው ዘገባ በየደረጃው የተለያየ ሊሆን ይገባል። ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ መረጃዎችን በፍጥነትና በተደጋጋሚ ተደራሽ ማድረግ ይገባል።
በተለይም ‹‹የሰሜኑ ጦርነት ቀጠናውን ጨምሮ ምን ዓይነት አንድምታ አለው፣ ኢትዮጵያ ለቀጠናው፣ ለአህጉሪቱ እንዲሁም ለዓለም ምን ያህል ወሳኝና አስፈላጊ ናት›› የሚሉና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ሊያውቃቸው ስለሚገቡ ዐበይት ጉዳዮችና አጀንዳዎችን በተቀናጀ መልኩ ማሰናዳት ያስፈልጋል።
ከሁሉ በላይ አጀንዳ ፈጣሪ እንጂ አጀንዳ ተቀባይ መሆን አይገባም። እነሱ የዘገቡት ልክ ነው ፣ልክ አይደለም የሚል ግብረ መልስ እየሰጡ መሄድ አግባብ አይደለም። ቀድሞ መረጃና አጀንዳዎችን መስጠት ያስፈልጋል። ወቅታዊ መድረኮችን መሰረት ያደረጉ ዘገባዎችን ከመሥራት ይልቅም ጥልቀት ያላቸውና ሁሉንም አቅጣጫ የሚያመላክቱ ትንታኔዎችን መሥራት የግድ ይላል። ይህን አቅም ለመገንባትም ጋዜጠኞችን ማሰልጠን መረሳት አይኖርበትም።
የዶክተር ሳምሶንን ሃሳብ የሚጋሩት አቶ በለውም፣ የሐሰት ዘመቻውን በማጋለጥ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እየሠሩት ያለውን ተግባር ማጠናከር እንዳለባቸው አፅእኖት ሰጥተውታል። ከዚህ ባሻገር ዘመቻውን በሚመጥን መልኩ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በሚገባቸው ቋንቋ ሰፊ የሆነ ትንታኔና ዘገባ በመሥራት ህዝቡን በሚገባ የማንቃት ሥራ መሥራት አለባቸው።
ባለፉት 27 ዓመታት ለምዕራቡ ዓለም ስለኢትዮጵያ የተሰጠው የተዛባ ሥዕል በመሆኑ ያንን ምስል መቀየርና አሁናዊ የኢትዮጵያን ገጽታን ማሳየት እንደሚጠበቅ ያስገነዘቡት ዶክተር አንተነህ ጸጋዬ በበኩላቸው፣ እንደ አገር አንድ የሚያደርግ አገራዊ ምስል ባጎለበትን ቁጥር ለማንኛውም የውጭ ተፅዕኖ ተጋላጭ የመሆን ዕድል ይጠባል፣ ውስጣችንን ማጽዳትና ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ማንነት በትውልዱ ላይ ማስረጽ ያስፈልጋልነው›› ነው ያሉት። መረጃን በአግባቡና በጊዜው ለህዝብ ማቅረብ ሥራ በተቀናጀ መንገድ መሥራትና ህዝቡም መረጃን የማጣራት ልምድ እንዲያዳብር መገናኛ ብዙኃን መሥራት እንዳለባቸው ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንዲሉ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑ ሁሉ ለአገራቸው ክብር በጋራ መቆምና መረባረብ የሚገባቸው ትክክለኛ ሰዓት አሁን ነው የሚለውም አስተያየት ሰጪዎቹ የጋራ ምክረ ሃሳብ ነው።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2014