መመሪያ ቁጥር 2 /2014
በሀገራችን ዘመናዊ የመታወቂያ አሰጣጥ ሥርዓት ያልተዘረጋ በመሆኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት መደበኛውን የመታወቂያ አሰጣጥ ሥርዓትን ለማስቀጠል አስቸጋሪ በመሆኑ መደበኛውን የመታወቂያ አሰጣጥ ሥርዓት ለጊዜው በማገድ ጊዜያዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወቂያ አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል የሚገኙ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በመደበኛው የመታወቂያ አሰጣጥ ሂደት መታወቂያ ያላገኙ በመሆኑ ለእነዚህ ዜጎች ጊዜያዊ መታወቂያ በመስጠት ሰላማዊውን ህብረተሰብ ከፀረ-ሰላም ቡድኖች ለመለየት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሆኖ በመገኘቱ፣
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀፅ 6(6) ላይ ለመታወቂያነት የሚያገለግሉ ሰነዶች የሌለው ሰው ይህን ጉዳይ በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ ዝርዝር የአፈፃጸም መመሪያ ባወጣ በሁለት ሳምንት ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኝ የቀበሌ፣ የወረዳ የፀጥታ እና አስተዳደር ፅሕፈት ቤት ወይም ፖሊስ ጣቢያ በመመዝገብ ጊዜያዊ የመታወቂያ ወረቀት የመያዝ ግዴታ እንዳለበት የተደነገገ በመሆኑና ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፣
በሃገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል በወጣ አዋጅ ቁጥር 5/2014 አንቀፅ 10/1/ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ይህን መመሪያ አውጥቷል።
ክፍል አንድ
ጠቅላላ ድንጋጌዎች
1. አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ “የጊዜያዊ መታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት መመሪያ ቁጥር 2/2014″ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፣
2. ትርጓሜ
በዚህ መመሪያ ውስጥ፡-
1) አዋጅ ማለት በሃገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 ነው፣
2) ጊዜያዊ መታወቂያ ማለት በዚህ መመሪያ መሰረት የሚሰጥ መታወቂያ ነው፣
3) ክልል ማለት በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 47 መሰረት የተቋቋመ ክልል ሲሆን፤ ለዚህ መመሪያ ዓላማ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ያካትታል፤
4) በአዋጁ ትርጉም የተሰጣቸው ቃላትና ሀረጎች ለዚህ መመሪያም ተፈፃሚነት አላቸው።
3. የተፈፃሚነት ወሰን
ይህ መመሪያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጸንቶ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ በየትኛውም የኢትዮጵያ ከተማ ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል።
ክፍል ሁለት
ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲወስዱ የማይገደዱ ሰዎች እና ስለ
ጊዜያዊ መታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት
4. ጠቅላላ
1) የነዋሪነት መታወቂያ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ ፓስፖርት ወይም ከእነዚህ ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሰነድ ያለው ሰው ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲያወጣ አይገደድም።
2) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀንቶ በሚቆይበት ወቅት መደበኛ መታወቂያ ማውጣትን አስመልክቶ የሚጣሉ ገደቦች፣ ክልከላዎች ወይም የሚተላለፉ ትዕዛዞች የመታወቂያ እድሳት ላይም ተፈፃሚ ይሆናሉ።
5. ተመጣጣኝ መታወቂያ ሰነዶች
የሚከተሉትን ሁኔታዎች ያሟሉ ሰዎች ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሰነድ እንዳላቸው ተቆጥረው ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲወሰዱ አይገደዱም።
1) በሚሠሩበት ተቋም ወይም ድርጅት የተሰጠ የሠራተኛነት መታወቂያ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች፣ ሕጋዊ ሰውነት ያለው የንግድ ድርጅት ሠራተኞች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሠራተኞች፣ ህጋዊ ሰውነት ያለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሠራተኞች፣
2) አግባብነት ካለው አካል የተሰጣቸው የማንነት መታወቂያ ያላቸው ስደተኞች፣
3) ህጋዊ እውቅና ካለው የትምህርት ተቋም የተማሪነት መታወቂያ ያላቸው ተማሪዎች።
6. ስለ መስፈርቶች
ማንኛውም ዕድሜው 18 ዓመት የሞላው ሰው የሚከተሉትን መስፈርቶች ካሟላ ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲሰጠው ማመልከት ይችላል፡-
1. የአዲስ አበባ ነዋሪ ስለመሆኑ ህጋዊ የመኖሪያ መታወቂያ ያለው እና በአካባቢው ነዋሪነት የሚታወቅ የቤተሰብ ኃላፊ ስለአመልካቹ ማንነት እና ሰላማዊነት ሙሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ ዋስ ሆኖ ለጊዜያዊ መታወቂያ የቀረበውን ማመልከቻ ከደገፈ፣ ወይም
2. አሁን ከሚኖርበት አካባቢ ውጪ ሌላ ቦታ ሲኖር የነበረ ሆኖ ከነበረበት ቦታ ሸኚ ወረቀት ማምጣት የሚችልና አሁን የሚኖርበት ቤት ህጋዊ ሰነድ ያለው ሆኖ የቤቱ ባለቤት ወይም ህጋዊ ወኪሉ ካስመዘገበው ወይም ዋስ ለመሆን ፍቃደኛ ከሆነ፤
3. በካምፕ፣ በማሰልጠኛ ወይም በአባላት የጋራ መኖሪያ ቤት የሚኖሩ የፖሊስ ሠራዊት ወይም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ቤተሰባቸውና ራሳቸው በሚኖሩበት ቤት ቁጥር አገልግሎቱን እንዲያገኙ ከሚመለከተው አካል ተፈቅዶ ደብዳቤ ከተፃፈላቸው፣
4. ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲሰጥ ጥያቄ በቀረበበት አካባቢ ነዋሪ የሆነ ባለትዳር ባል ወይም ሚስት ከሌላ ቦታ በሥራ ምክንያት የተዛወረ ከሆነና ስለመዘዋወሩ እና ህጋዊ ትዳር ስለመኖሩ በቂ ማስረጃ ካቀረበ፣
7. የጊዜያዊ መታወቂያ የጊዜ ቆይታ እና ስለሚይዛቸው መረጃዎች፡-
1. ጊዜያዊ መታወቂያ የሚሰጠው ለ6 ወር ሲሆን፤ መታወቂያውን የያዘው ሰው በየወሩ መታወቂያውን የወሰደበት ቦታ በመቅረብ ሪፖርት ማድረግና ማሳደስ ይኖርበታል፣
2. ጊዜያዊ መታወቂያ ላይ ግለሰቡ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ የተነሳው ፎቶ የሚለጠፍ ሆኖ በመታወቂያው ላይ የሚሰፍሩ መረጃዎች ይዘት መደበኛው መታወቂያ የሚይዛቸው መረጃዎች ይሆናሉ::
8. ጊዜያዊ መታወቂያ የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው አካላት
የሚከተሉት አካላት ጊዜያዊ መታወቂያ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው፡-
1) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ መዋቅር፣
2) በድሬዳዋ እና በክልሎች ደግሞ የፖሊስ መዋቅር።
9. ማንነትን ስለማረጋገጥ
ጊዜያዊ መታወቂያ ለመውሰድ የሚያመለክት ማንኛውም ግለሰብ ስለትክክለኛ ማንነቱ መታወቂያውን በሚወስድበት ቦታ በመንግሥት አካል በሚዘጋጅ ቅፅ ላይ የተመለከቱ ማንነትን ለማረጋገጥ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በመሙላትና ቃለ መሀላ በመፈጸም ያረጋግጣል።
10. የጊዜያዊ መታወቂያ አገልግሎት
በዚህ መመሪያ መሰረት የሚሰጥ ጊዜያዊ መታወቂያ መታወቂያውን የወሰደውን ሰው ማንነትን ከማረጋገጥ ውጪ መደበኛው የነዋሪነት መታወቂያ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ወይም መብቶች አያስገኝም።
ክፍል ሦስት
ግዴታዎችና የተከለከለ ተግባራት
11. ማህበራዊ ጉዳይን የሚመለከት ተግባርና ኃላፊነት ያለባቸው የመንግሥት ተቋማት ግዴታዎች
ማህበራዊ ጉዳይን በተመለከተ ኃላፊነት ያለባቸው የፌዴራልና የክልል የመንግሥት ተቋማት ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር ጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ ቋሚ አድራሻ እና ሥራ የሌላቸውንና ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በማደራጀት ወደ መጠለያ ወይም ጊዜያዊ መቆያ እንዲገቡ እና በዚያ ቦታ እንዲቆዩ ሊያደርጉ ይችላሉ።
12. ጊዜያዊ መታወቂያ የወሰደ ሰው እና የመታወቂያ ሰጪው አካል ግዴታዎች
1) ጊዜያዊ መታወቂያ የጠፋበት፣ የተበላሸበት ወይም በሌላ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ወይም በማናቸውም ምክንያት ከእጁ የወጣበት ማንኛውም ሰው ለፖሊስ በ24 ሰዓት ውስጥ ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነት አለበት፣
2) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 የተመለከተው ሁኔታ ሪፖርት ፖሊስ ተቋም በሚሰጠው ማረጋገጫ መሰረት ጊዜያዊ መታወቂያ የመስጠት ስልጣን የተሰጠው አካል፣ ምትክ ጊዜያዊ መታወቂያ ይሰጣል::
13. የተከለከሉ ተግባራት
የሚከተሉትን ተግባራት መፈጸም በአዋጁ እና ሌሎች ህጎች መሰረት የወንጀል ኃላፊነት ያስከትላል፡-
1) ጊዜያዊ መታወቂያ ለመውሰድ ሐሰተኛ መረጃ መስጠት፣
2) መስፈርቱን ለማያሟላ ሰው ጊዜያዊ መታወቂያ መስጠት፤
3) መስፈርቱን የማያሟላ ሰው ጊዜያዊ መታወቂያ እንዲሰጠው በማሰብ ማረጋገጫ ደብዳቤ መፃፍ ወይም ምስክር መሆን፣
4) ከአንድ በላይ ጊዜያዊ መታወቂያ ይዞ መገኘት።
ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
14. ተፈፃሚነት የሌላቸው መመሪያዎች ወይም ልማዳዊ አሠራሮች
ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረን ማንኛዉም መመሪያ ወይም የአሠራር ልምድ በዚህ መመሪያ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ይህ መመሪያ ጸንቶ በሚቆይበት ጊዜ ተፈፃሚነት አይኖረዉም።
15. መመሪያዉ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ መመሪያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል።
አዲስ አበባ ሕዳር 06 ቀን 2014 ዓ.ም
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ እዝ
አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2014