አዲስ አበባ፡- ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ደማቸውን አፍሰው የገነቧትን አገር የቀደመ ዝና እና ገናናነት ለማስመለስ መንግስትና ምሁራን እርስ በርስ ከመወቃቀስ ወጥተው በጥምረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያውያን በተለይም በአድዋ ጦርነት ላይ የፈፀሙት ድልን ተከትሎ በመላው አለም ያሉ ጥቁር ህዝቦች ከጭቆና ቀንበር መላቀቂያ ስልት በማድረግ «የኢትዮጵያዊነት መርህ»ን ይዘው ታግለዋል፡፡ ድልም ነስተዋል፡፡
አገሪቱ በነጮች ላይ ባሳየችው ጀግንነት ብቻ በስሟ ቤተክርስቲያን እስከ መክፈትና የሰንደቅ አላማቸውን ቀለም እስከመቀየር ደርሰዋል፡፡ ውሎ ሲያድር ግን ባለታሪኮቹ ህዝቦች ታሪካቸውን ለትውልድ ማቆየት ባለመቻላቸው ለዘመናት ውቅያኖስን ተሻግሮ የናኘው ስምና ዝና እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ ሃሰን እንደሚሉት፤ ዘመናትን ላስቆጠረው ኢትዮጵያዊ ገናናነት መደብዘዝ ዋነኛውን ሚና የተጫወቱት በተለያዩ ጊዜያት አገሪቱን የመሩት መንግስታትና ምሁራን ናቸው፡፡ በተለይም ምሁሩ ህብረተሰብ ትውልዱ የአባቶችን ትክክለኛ ታሪክ አውቆ በወኔ የአገሩን ልማትና ብልፅግና እንዲያስቀጥል ከማድረግ ይልቅ ልዩነቱን አጉልቶ የሚያይባቸውን የታሪክ ሰበዞች በመምዘዝ የአንድነት ቋንቋው እንዲደበላለቅና ያስተሳሰረው ገመድ እንዲላላ መንገድ ከፍተዋል፡፡
አገሪቱን በተለያዩ ዘመናት ሲመሩ የቆዩትም መንግስታትም በበኩላቸው የአገሪቱን እውነተኛ ታሪክ ወደ ጎን በመተው ስልጣናቸውን የሚያቆይላቸውን አጀንዳ ቀርፀው የትውልዱን አስተሰሰብ መበረዛቸውን ዶክተር አህመድ አስረድተዋል፡፡ይህም ለእርስበርስ ግጭትና ወደማያበራ የማንነት ቀውስ ውስጥ እንደከተተው አመልክተዋል፡፡ «ቀድሞ የነበረው ውስጣዊ ህብረ ብሄራዊነታችን መደብዘዝ ደግሞ ማንነቱን የዘነጋና የሌሎችን አገር አሻግሮ የሚመለከት ትውልድ እንዲፈጠር ከማድረጉም ባሻገር አገሪቱ ቀድማ ትታወቅበት የነበረበትን መልካም ስምና ዝና እንዲጠፋ አድርጓል» በማለት ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም መንግስትና የታሪክ ምሁራን እርስ በርስ በመናበብ ትውልዱን መታደግ ብሎም የአገራቸው የቀደመ ዝና በአለም አደባባይ ላይ እንዲመለስ መስራት እንደሚገባቸው ዶክተር አህመድ አስገንዝበዋል፡፡ « አንድን ትውልድ ለማዳን በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልም፤ በመሆኑም ለጥፋቱ አንዱ በሌላው ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ በአንድ ድምፅ ለአንዲት አገር ብልፅግና እና እድገት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል» ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና የታሪክ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶክተር ሳሙኤል ነጋሽ በበኩላቸው «የኢትዮጵያ የቀደመ የገናነት ታሪክ በፖለቲካ ምክንያት ስንፈልገው የምንጠቀምበት ሳንፈልገው የምንዘነጋው አድርገን ስንወስድ ኖረናል» ብለዋል፡፡ በተለይም የፖለቲካ መሪዎች የራሳቸውን አድዋ መፍጠር ባለመቻላቸው የአባቶቻቸውን ታሪክ ለማድነቅና ለማውሳት የማይፈልጉ በመሆናቸው ትውልዱ ታሪኩን ሳያውቅ እንዲኖር ያደረጉት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ስልጣን ላይ የነበረው መንግስት የታሪክ ትምህርትን ለራሱ ስልጣን ማራዘሚያ አድርጎ እሱ በሚመቸው መልኩ ብቻ በመቀየስ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ያደረገበት መንገድ ለአገሪቱ ዝና መደብዘዝ ትልቅ ሚና እንደነበረው አንስተዋል፡፡ በተለይም የታሪክ ምሁራንን በተለያየ መንገድ ጫና በማሳረፍ በገባቸውና ባወቁት ልክ ፅፈውና አስተምረው ትውልዱን እንዳያንፁ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
« አሁን ላይ እገሌ ይህንን አድርጓል፤ ወይም ደግሞ ይህንን ባለማድረጉ ትልቅነታችን ጠፍቷል ብሎ መካሰሱ አይበጀንም» ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፣ ከዚያ ይልቅም የወደፊቱን በማየት ከትናንት ስህተት መማርና ለለውጥ መነሳት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስትና ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ወቅትን እየጠበቁ ስለቀደሙት ጀግኖች ታሪክ ከመዘከር ባሻገር በየእለት ተእለት ስራቸው ውስጥ በማስገባት የአገሪቱ መልካም ስም ዳግም በአለም መድረክ እንዲነሳ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23/2011
ማህሌት አብዱል