ሰሞኑን በአሜሪካ የፌዴራሊስት ሃይሎች በሚል ሰባት ሰዎች በአሜሪካ ተሰባስበው በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸውን በማህበራዊ ሚዲያ አየሁ። ሰዎቹን ስመለከት በአንድ በኩል አሜሪካ የምትባለው ሃገር በዚህ ደረጃ የወረዱ ሰዎችን በጉያዋ ይዛ ቦታ ሰጥታ ማስተናገዷ እውን ዴሞክራሲ የምትለው ይህንን ያካትታል ማለት ነው? የሚል ጥያቄን ሲያጭርብኝ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የ27 አመትታ የአሸባሪው ሕወሓት የአገዛዝ ዘመን የነበሩ የምርጫ አሻንጉሊቶች ዛሬም በዚህ መልኩ ሕወሓትን ለማዳን አሜሪካ ላይ መገኘታቸው ቀልድና ቁምገር እንዲደበላለቅብኝ አደረገኝ። በሌላ በኩል ይህች አሜሪካ የምትባል ሃገር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለምን በዚህ ልክ መሯሯጥ ፈለገች የሚል ጥያቄን እንድጠይቅ አስገደደኝ። ለዚህ መልስ ባይኖረኝም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደረገች ያለው ተግባር ግን እጅግ አሳፋሪ መሆኑን ብዙዎች እየተገነዘቡ ይገኛሉ።
እነዚህ የፌዴራሊስት ሃይሎች ነን የሚሉ አካላት ከዚህ ቀደም ሕወሓት በመቀሌ ሰብስቦ ሲጫወትባቸው የነበሩ ሃይሎች ቅጥያ ናቸው። ልዩነቱ አሁን መቀሌ ላይ ለመሰብሰብ ባለመቻላቸው ወደሌላኛዋ ዋና ከተማቸው ዋሽንግተን ዲሲ መሄዳቸው ብቻ ነው። ይህ ስፍራ መቀሌን ስለሚያስታውሳቸው ተመራጭ ስፍራ የሆነላቸው ይመስላል።
በዚህ ቡድን ውስጥ የተሰባሰቡት ቡድኖች ብዙዎቹ ምናልባት ስልጣን ታገኛላችሁ ተብለው የተሰባሰቡ ካልሆኑ በስተቀር ከዚህ ቀደም ስለመንግስትነት አስበው የሚያውቁ ናቸው ለማት ይከብዳል። በድንገት አሜሪካ ስልጣን ልትሰጠን ትችላለች በሚል ከእንቅልፋቸው የባነኑ አሳፋሪዎች ናቸው። እነዚህ ሀይሎች በምን መስፈርት እንደተገናኙና ኣላማቸውም ምን እንደሆነ እንኳን የዚህ ፅሁፍ አቅራቢም እነሱም የሚያውቁት አይመስለኝም።
ነገር ግን ከነዚህ ሰዎች በስተጀርባ ያለውን የአሜሪካን ድርጊት እጅግ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪና በዚህ ዘመን ለዓለም ሰላም ዘብ እቆማለሁ ከምትል ትልቅ ሃገር የማይጠበቅ ተግባር ነው። ያም ሆነ ይህ ግን ሰሞኑን አሜሪካ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራች መሆኗ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በተለይ ሰሞኑን ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ተነስተው ይህንን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት እንደ ደራሽ ጎርፍ መሰባሰባቸው ለአሸባሪው ሕወሓት ሽብር፤ ለአሜሪካም ስጋት ሆኖባቸዋል።
ስለዚህ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸውን በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥለዋል። ለዚህ የቀረፁት ዘመቻ ደግሞ ሕወሓት እና ሸኔ ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሱ ነው፣ ባለስልጣኖች ከሃገር ሊወጡ ነው፤ የአሜሪካ ዜጎች ኢትዮጵያን ለቃችሁ ውጡ ወዘተ የሚሉ ዘመቻዎች በስፋት ተከፍተዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም የሽግግር መንግስት ለመመስረት የፌዴራሊስት ሃይሎች የሚባሉ ሃይሎችን ወደፊት በማምጣት እንዲታዩ ማድረግ እና ተደራደሩ በሚል በሌላ መልኩ ጫና ማሳደር ጀምረዋል።
ለመሆኑ አሜሪካ በዚህ ልክ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ላይ እንደ አዲስ የከፈተችው ዘመቻ መነሻ ምንድ ነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይህንን ፖለቲከኞች በተለያየ መንገድ ሊተነትኑት ይችላሉ። እኔ ግን ለዚህ መነሻ ብየ የማስቀምጠው ዋነኛ ምክንያት የቀኝ እጃቸው ሕወሓት እውነተኛ ሞቱን ሊሞት ከጫፍ መድረሱን ሲመለከቱ ከዚያ በፊት ለማዳን የሚደረግ ሩጫ ነው።
እንደሚታወቀው የአሜሪካ ሩጫ የጀመረው ገና በጦርነቱ ማግስት ቢሆንም የሰሞኑ ግን ለየት ያለና የተጠናከረ ነው። በተለይ አሸባሪው ሕወሓት በወሎ ግንባር የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመነሳት ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማውደም እየተንቀሳቀሱ ነው። ይህንን የተረዳው የአሸባሪው ቡድንም በቃልአቀባዩ ጌታቸው ረዳ አማካኝነት ስልታዊ ማፈግፈግ በሚል ከደሴና ኮምቦልቻ መውጣታቸውን ገልፀዋል።
(ጥቂት ቆይቶ የተናገረውን ቢውጠውም)። አሁን የተነሳው ህዝባዊ ማዕበል አሸባሪውን ቡድን እስከመጨረሻ ለመቅበር የሚያግደው አንዳችም ሃይል እንደሌለ ያሳያል። ስለዚህ ወያኔ ከዚህ በኋላ የሚያንሰራራበት እድል የጠበበ ነው። ስለዚህ ይህ ከመሆኑ በፊት ከሞት አፋፍ መመለስ የአሜሪካ ዋነኛ ፍላጎት ነው። ወዳጄ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶችን ልሰጥህ እችላለሁ። ጥቂቶችን እናንሳ።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን ባካሄዱት ጥናት አሜሪካና የምዕራባውያን ሚዲያዎች ለአንድ አመት ሲያወሩ የከረሙት ውሸት ሁሉ ተገልብጦ ታሪኩ ሌላ ሆኗል። ጦርነቱን የጀመረው አሸባሪው ሕወሓት ነው ከሚለው ጀምሮ ምዕራባውያን ሚዲያዎች መንግስት ረሃብን እንደጦር መሳርያ ተጠቅሟል የሚለውና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንደነበሩ ሪፖርቱ አጋልጧል። ይህ ደግሞ የምዕራባውያንን ፍርደ ገምድልነት እና የሃሰት ውንጀላ የሚያጋልጥ ነው።
ስለዚህ ይህ ከመሆኑ በፊት አሜሪካ ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ሪፖርቱ ሊቀርብ አንድ ቀን ሲቀረው ለኢትዮጵያ ሰጥታ የቆየችውን ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ የማስገባት እድል /አግዋ እድል/ ዘጋች። አስቡት ይህ ሆን ተብሎ ከሪፖርቱ ጋር የተደረገ የሩጫ እሽቅድምድም ነው።
አሜሪካ በዚህ ብቻ አላበቃችም። አሸባሪ ቡድኑ በደሴና ኮምቦልቻ የደረሰበትን ከፍተኛ ምት እና ከዚያ በኋላም ከኋላ እየመጣ ያለውን የህዝብ ማዕበል ሲመለከቱ አሸባሪው ሕወሓት የማዳን ዘመቻው በሌላም አቅጣጫ ቀጠለ። ለዚህ ሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ “ድርድር” የሚል ስልታዊ የማወናበጃ መንገድ ነው። በዚህ የተነሳ አሜሪካ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ሁኔታዎች ሁሉ በተለየ መልኩ ድርድር እንዲካሄድ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ ጀምራለች። ለዚህ ደግሞ በአንድ በኩል ተወካዩዋን ወደ አዲስ አበባ በመላክ እና የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በርካታ ሃገራት በዚህ ላይ እንዲረባረቡ በማድረግ ቡድኑ የሚድንበት መንገድ እያመቻቸች ትገኛለች።
የሚገርመው በኢትዮጵያ ጉዳይ አሉታዊ አቋም በመያዝ የሚታወቀው ይህ የአሜሪካ ተወካይ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጠው መግለጫ ለሽብር ቡድኑ ሃሳብ ሰንዝሯል። ሰውዬው በሰጠው አስተያየት በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ለድርድር ዝግጁ እንድትሆን የሚል ሃሳብ ሲኖረው በሌላ በኩል ደግሞ የሕወሓት እና የሸኔ ጦር ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን ግስጋሴ ያቁም የሚል የተጠና ንግግር አድርጓል። ሰውየው በዚህ ንግግሩ ለማሳየት የፈለገው ሕወሓትና ሸኔ ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሱ ነው፤ የሚያቆማቸው የለም የሚል መልዕክትም ለማስተላለፍ ነው። ይህ የስነልቦና ጫና ለማሳደር ታስቦ የተገለፀ ሃሳብ ነው።
አሜሪካ በዚህ ብቻ ሳታቆም ሰሞኑን ምንም ነገር በሌለበት እና የአሸባሪው ሕወሓት ሀይል ተመትቶ ከደሴም መውጣቱ እየታቀወቀ የአሜሪካ ዜጎች ኢትዮጵያን ለቃችሁ ውጡ የሚል ማስጠንቀቂያም አስተላልፋለች። እውን አሜሪካ ራሷ ለመዋጋት ፈልጋ ካልሆነ በስተቀር በዚህ ልክ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው ውጡ የሚለው ማስፈራሪያ የመጣው የሚለው መልስ የሌለው ጥያቄ ነው። አሜሪካ ዜጎቿን ከአፍጋኒታን ለማስወጣት በዚያ ልክ እስከመጨረሻው ድረስ እንዳልቆየች አሁን በዚህ መልኩ የሚደረገው ማስፈራሪያ የስነልቦና ጫና ለማሳደር እንደሆነ ግልጽ ነው።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በዚህ ልክ እልህ ውስጥ ለምን ገባች የሚለው ጥያቄ በግልፅ መልስ ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን ታሪክም እንደሚነግረን አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከዋለችው ውለታ ይልቅ በችግሯ ጊዜ ገሸሽ ስታደርጋት መኖሯን ማስታወስ ለዚህ መልስ ሊሆን ይችላል።
ከአርባ አመታት በፊት ሲያድባሬ በእብሪት ተነሳስቶ ኢትዮጵያን ሲወርና አዋሽ ድረስ ዘልቆ ሲገባ አሜሪካ ከሶማሊያ ጎን ነበረች። ዛሬ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ የሚገኘው አሸባሪው ሕወሓት ወደስልጣን ሲመጣም አሜሪካ እጇ ረጅም ነበር። ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ወርራ በያዘችበት በዚህ ወቅትም ቢሆን አንድም ቀን ስለኢትዮጵያ እውነታ ስትናገር አልተሰማችም። ግብጽ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ስትሞክር የአሜሪካ አቋም በግልፅ ለግብፅ የወገነ ነው።
ሌላም ሌላም፤አሁን እየተካሄደ ባለው ጦርነት እንኳ መንግስት የመከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ባስወጣበት ወቅት አጋጣሚውን ለሰላም ከመጠቀም ይልቅ ሕወሓት እንዲያንሰራራ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከዚያ በኋላም ቡድኑ በተለያዩ የአማራና የአፋር አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀማቸውን ጅምላ ጭፍጨፋዎች አሜሪካ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታ አልፋቸዋለች። ለምን፣ ምክንያቱም ለአሜሪካ ሚዛናዊ እይታ ቦታ የላቸውምና።
እውን አሜሪካ ለእውነትና ለፍትህ የቆመች ሃገር ናት? በታሪኳ ፍትህና አሜሪካ ምን ያህል አብረው ይሄዳሉ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። ነገር ግን አሜሪካ ከጥቅሟ እንጂ ከፍትህ ጋር ስትሰራ የታየችበት የዓለም ታሪክ ብዙም አይታይም። ለዚህ ጥቂት ማሳያዎችን ላንሳ።
አሜሪካ በአረቡ አለም አለኝ ከምትላቸው ወዳጆቿ ውስጥ ዋነኛዋ ሳውዲ አረቢያ ናት። ታዲያ ሳውዲ አረቢያ ለአሜሪካ ካላት ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አንጻር ጥፋቷ በአሜሪካ እንደጥፋት ሲቆጠር አይታይም። ለዚህ የቅርብ ጊዜውን የጋዜጠኛ ካሾጊ ግድያ ማንሳት ይቻላል። በዚህ ኢሰብአዊ ድርጊት አሜሪካ የውሾን ያነሳ ውሾ በሚል ዝምታ መምረጧ ይታወሳል። የእስራኤልና ፍልስጤም ህዝቦችም ልክ እንደማንኛውም ህዝብ እኩል የሰው ልጆች ናቸው። በነዚህ ሃገራት መካከል ያለው ውዝግብም ለአመታት የዘለቀ ነው። አሜሪካ ግን እነዚህ ሃይሎች ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከማድረግ ይልቅ ለአንድ ወገን ያደለ አካሄድ ስትከተል መኖሯን የዓለም ህዝብ ጭምር የሚያውቀው ነው።
በአፍሪካ ከሚገኙ ሃገራት ግብፅ በጸረ ዴሞክራሲ ተግባሮቿ ዓለም ያውቃታል። መንግስትን የሚቃወሙ ዜጎችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን በጅምላ በአደባባይ የምትረሽን ሃገር ናት። መፈንቅለ መንስግስትም ቢሆን ለዚያች ሃገር አዲስ አይደለም። ይሁን እንጂ አሜሪካ በሌሎች ሃገራት ላይ የምታነሳቸው የዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ለግብጽ አይነሳም። ለአሜሪካ ዋናው ጉዳይ ስትራቴጂክ አጋር መሆን ነው።
በሌላ በኩል አሜሪካ ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለግብጽ የወገነ አቋም በማራመድ ትታወቃለች። ግብጽ የታችኛው ተፋሰስ ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የውሃው ዋነኛ ምንጭ መሆኗን እያወቀች የጥቅም ይገባኛል ጥያቄን ስታነሳ አሜሪካ በዚህ መልኩ ለግብጽ መወገኗ አሳፋሪና ፍትህ ለአሜሪካ ምን ያህል የተዛባ እንደሆነ ያሳያል። በአንፃሩ አሜሪካ ወደሜክሲኮ የሚፈስ ወንዝ እንዳላት ይታወቃል። በዚህ ወንዝ ላይ አሜሪካ ያለከልካይ ስትጠቀም እንዴት የሚል ጥያቄ የሚያነሳ የለም።
ለመሆኑ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እንዲህ አይነት ጫና ስታሳድር እውን ለህዝቦቿ አስባ ነውን የሚል ጥያቄም ይነሳል። ለዚህ መልሱ አይደለም የሚል ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ልማት እና እድገት ሆኖ ሳለ አሜሪካ በኢትዮጵያ ከምታደርገው ኢንቨስመንት ይልቅ የፖለቲካ ጣልቃገብነቷ የጎላ ነው። በኢትዮጵያ በርካታ የስራ እድሎችን ከፈጠሩ የኢንቨስመንት ስራዎች ይልቅ በሰብአዊ እርዳታ ስም የሚያተራምሱ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ይበዛሉ። አሜሪካ ለድሃ ሃገራት ዳቦ የሚገኝበትን መንገድ ከማመላከት ይልቅ ዳቦ እየሰጡ ለዘላለም በእጅ አዙር መግዛት የሚለው አካሄዷ ይበልጥ ሚዛን ይደፋል።
ሰሞኑን ከአግዋ ጋር በተያያዘ የፈፀመችው ክልከላም አሜሪካ ተግባሯና ቃሏ የሚጣረሱ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው። በአግዋ ተጠቃሚው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። በተለይ ሴቶችና ወጣቶች ከዚህ እድል በብዙ መልኩ የሚጠቀሙ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ የተገለፀ እውነታ ነው። ታዲያ አሜሪካ ክልከላውን ስታደርግ የኢትዮጵያ ህዝብንም ጭምር የመጉዳት ዓላማ ይዛ መሆኑን መገመት አይከብድም።
በአጠቃላይ እነዚህና መሰል የአሜሪካ ጫናዎች ኢትዮጵያ ከገባችበት ጫና ለማውጣት ሳይሆን አጋጣሚውን በመጠቀም መንግስትን አፍርሶ ሌለ፤ ተላላኪ መንግስት ማቋቋም ነው። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን ለመንግስትነት ያዘጋጀቻቸው ሃይሎች ማሳያ ናቸው። በነዚህ ሃይሎች ኢትዮጵያን ለመበተን ወይስ ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር ለማላቀቅ? እነዚህ ሃይሎች ወደስልጣን ቢመጡስ ምን ያህል ኢትዮጵያ እንደሃገር መቀጠል ትችላለች። ይህ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው።
አሁን አሜሪካ የመጨረሻውን ኢትዮጵያ የሚለውን ስም የማጥፋትና ትንንሽ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራትን የመፍጠር ተልዕኮዋን ለማሳካት እየሰራች ትገኛለች። የአሜሪካ ዓላማ ከዚህ በኋላ ምንም ድምጽ የማይኖራቸው ትናንሽ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትን በመፍጠር ለግብጽ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። ከዚህም አልፎ በቀጣናው ላይ ምዕራባውያን እንደፈለጉ የሚፈነጩበት የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ዘመንን ማስፋት ነው።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት እና መላ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ምቹ አልሆኑም። ህዝቡ የሕወሓትን መሰሪ ተልዕኮና ተላላኪነት በመረዳቱ እነዚህን ሃይሎች ለማጥፋት ከዳር ዳር ተነቃንቋል። ሰሞኑን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የታየው የህዝብ ማዕበልም ለዚህ ማሳያ ነው። ይህ የህዝብ ማእበል ኢትዮጵያን የማቆም እና ወደከፍታ የመውሰድ ትልቅ ብቃት ያለው ነው። የውጭ ሃይሎች ሴራም ሆነ የአሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይመክናል።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2014