በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያን ሰቅዞ የያዛትን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት የተለያዩ ወገኖች በአማራጭ መፍትሔነት፣ የብሔራዊ መግባባት ወይም የብሔራዊ ዕርቅ ጥሪን ያቀርባሉ። እነዚህ የመፍትሔ አማራጮች በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተደጋግመው ይሰሙ እንጂ፣ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት የሚነሱ የግጭት መፍቻ አማራጮች ናቸው።
ብሔራዊ መግባባት (National Dialogue)፣ ወይም ብሔራዊ ዕርቅ (National Reconciliation) ተብለው በአማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴነት በስፋት ይቅረቡ እንጂ፣ በተለያዩ የዓለም አገሮች በተለያዩ ስያሜዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም መካከል እ.ኤ.አ. ከ1991 እስከ 1993 በደቡብ አፍሪካ የተካሄዱት ተመሳሳይ መድረኮች ብሔራዊ ጉባዔ ለዴሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪካ። የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር መድረክ የሚል ስያሜ ይዘው ከአፓርታይድ አገዛዝ የተላቀቀችው ደቡብ አፍሪካ “ሬንቦ ኔሽን” የተባለችበትን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንድታደርግ ረድተዋታል። በሌሎች አካባቢዎችም ብሔራዊ የሰላም ጉባዔ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ለግጭት መፍቻነት ጥቅም ላይ የዋለ አማራጭ ነው።
ከላይ የተገለጹትና ሌሎች የተለያዩ ስያሜዎች ለተለያዩ መድረኮች ይሰጡ እንጂ፣ ሁሉም ዓላማቸው ወይም ማሳካት የሚፈልጉት ግብ ዴሞክራሲያዊ ሽግግርን ወይም ልዩነቶችን አስታርቆ ስምምነት የተደረሰበት ፖለቲካዊ ፍኖተ ካርታን መተግበር፣ አልያም ሁሉም ወገኖች ከሞላ ጎደል ስምምነት የደረሱበትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈን ነው።
ብሔራዊ መግባባት ወይም ብሔራዊ ዕርቅ፣ አልያም የተለየ ስያሜ የተሰጣቸውን መድረኮች ዓላማ የሚጋጩ የፖለቲካ ፍላጎቶች ዙሪያ መግባባት ሳይችሉ ቀርተው የሚቋሰሉ ብዝኃነትን የተላበሱ ማኅበረሰቦች ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት እንዲጠቀሙበት ያለመም ነው። በተራዘመ ፖለቲካዊ ሽግግር አጣብቂኝ ውስጥ የወደቁ ማኅበረሰቦች፣ ከእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለማቋቋምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል የነደፏቸውን የተለያዩ ሥልቶች ለማስታረቅ፣ ከተራዘመ ግጭት መውጣት ያቃታቸው ማኅበረሰቦች ከአጣብቂኙ ለመውጣት፣ አልያም በአገራዊ የፖለቲካ ሪፎርም (ለውጥ) ዙርያ የሪፎርም አቀንቃኝና በፀረ ሪፎርም ጎራ ተሠልፈው ዴሞክራሲን በአገራቸው ለመተክል አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች መውጫ መፍትሔ ለመፈለግ የሚያካሂዱት መድረክ እንደሆነ ይታመናል።
ካለፉት አራት ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያን ሰቅዞ የያዛትን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት የተለያዩ ወገኖች ብሔራዊ መግባባትን፣ ወይም ብሔራዊ ዕርቅን እንደ ቁልፍ መፍትሔ አድርገው ይወተውታሉ። የቀድሞው ገዥ ፓርቲ በነበረበት ወቅትም ቢሆን እነዚህ የመፍትሔ አማራጮች እንዲተገበሩ የተለያዩ ውትወታዎች ተደርገዋል፤ ነገር ግን ሳይተገበሩ ቀርተዋል።
አሁን ካለንበት የፖለቲካ ሁኔታ ለመውጣት መፍትሔ የሚሆነው ብሔራዊ መግባባት ወይም ብሔራዊ ዕርቅ እንደሆነ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችና የፖለቲካ ልሂቃን እየጠየቁ ነው። ይህንን ያሳካል የተባለ ጉባኤም በያዝነው ሕዳር ወር ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ አካላት በተገኙበት ይካሄዳል ተብሎም ይጠበቃል።
እኛም ዴስቲኒ ኢትዮጵያ መስራችና አስተባባሪ እንዲሁም ማይንድ ወይም ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር ውጥን አባል ከሆኑቱ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ ስለ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ አመሰራረት ብሎም ዓላማው ትንሽ ይንገሩኝ፤
አቶ ንጉሡ፦ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ የዛሬ አራት ዓመት
ገደማ ጀምሮ አገር ውስጥ ያሉ 50 ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችን በአንድ ላይ አምጥቶ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ምን ልትሆን ትችላለች? የሚል ጥያቄ በመጠየቅ የተነሳ ሲሆን ይህም አንድ ዓመት በፈጀ ሂደት ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 20 ዓመታት አራት አይነት አማራጮች አሏት የሚል ሀሳብ አምጥተው እርሱን እንዴት ወደ መሬት እናውርደው በማለት የሚሰራ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን፦ አነሳሳችሁ ይህ ከሆነ 50ዎቹ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ኢትዮጵያን በ 2013 ዓ.ም ምን ትመስላለች አሉ?
አቶ ንጉሡ፦ በ2032 ዓ.ም ኢትዮጵያ ንጋት ሊሆንላት ይችላል። ሰባራ ወንበር ልትሆን ትችላለች። የፉክክር ቤት ልትሆን ትችላለች እንዲሁም አጼ በጉልበቱ አይነት ልትሆን ትችላለች የሚል ነገር ሰርተው ነው ያቀረቡት።
በመሆኑም ከእነዚህ ከቀረቡት አራት አማራጮች ውስጥ ንጋት የሚለው ለሁላችንም የተመቸ በመሆኑ ኢትዮጵያ ንጋቷ እንዲመጣ እንሰራለን በሚል ኃላፊነት ይዘው ወጥተዋል፤ ዴስቲኒ ኢትዮጵያም ስራውን የጀመረው በዚሁ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የኢትዮጵያን ንጋት ሁላችንም የምንመኘው ነው፤ ነገር ግን ይህ ንጋት እንዲመጣስ ምን ዓይነት አማራጮች ተቀምጠዋል?
አቶ ንጉሡ፦ አዎ፤ ንጋት በመጠባበቅ አይመጣም፤ ንጋት በስራ ነው የሚመጣው። በመሆኑም ይህ ንጋት እንዲመጣ ምን እናድርግ የሚለው ደግሞ የሁላችንም ጥያቄ ነበር። ንጋት እንዲመጣ እንግዲህ ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት መኖር አለባቸው፤ ሶስተኛው ደግሞ እንደ አገር
በጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር ያስፈልጋል፤ የሚል ነገር ነው የተጠቆመው። በመሆኑም ንጋት እንዲመጣ ካስፈለገ ትልቁ ቁልፍ ነገር ምክክር ስለሆነ አገራዊ ምክክር ብንጀምር ጥሩ ነው በሚል ከተለያዩ ሰባት ድርጅቶች ጋር በመሆን አገራዊ ምክክር ውጥን ጀመርን።
ስንጀምርም ዴስቲኒ ኢትዮጵያ። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ እንዲሁም ሰላም ሚኒስቴር ነበርን። በኋላ ደግሞ ሃሳቡ የተበታተነ እንዳይሆን የተቀናጀ ስራ ተሰርቶ ውጤት እንዲያመጣ ያግዛል በማለት በጉዳይ ላይ የሚሰሩ ሌሎች ድርጅቶች ተጋበዙ በዚህም አምስት ተመሳሳይ የሚሰሩ ድርጅቶች ተጨምረው እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በተለያየ ጊዜ በሚነሱ አለመግባባቶች ምክንያት አገራችን እስከ አሁንም ድረስ ከእርስ በእርስ ሽኩቻ ከፋ እስካለ ጦርነት ውስጥ ናትና እንደው ለዚህ ሁኔታ መፈጠር ዋናው ምክንያት ግን አለመነጋገራችን ብቻ ነው?
አቶ ንጉሡ፦ አለመነጋገራችን ብዙ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያን ታሪክ ወደኋላ ሄደን እንደምናውቀው የሃሳብ ልዩነቶችን ልንፈታ የሞከርንባቸው መንገዶች ሁሉም ሀይል የተቀላቀለባቸው ናቸው። አንዳንድ ጊዜ አንዱ መንግሥት ሌላውን በጦርነት አሸንፎ በሌላ ወቅት ደግሞ መንግሥት ገልብጣ እንዲሁም የነበረው ገዢ መደብ ሌሎቹን አስገብሮ ሌላ ጊዜ ደግሞ ችግር የለውም ሰላም ይሻለናል በማለት የተለያዩ መሪዎች ተፈራርቀውብናል። ነገር ግን እነዚህ ሁኔታዎች ችግሩን ከመፍታት ይልቅ እንዲያድር ለነገ እንዲተላለፍ ነው ያደረጉት ።
አሁን ላይ ሆነን የምንጣላባቸው ነገሮች ሁሉ እኮ የዛሬ 50 ዓመት ስንጣላባቸው የነበሩ ችግሮች ናቸው፤ ምክንያቱም ችግሮቹን እያፈናቸው ቆየን እንጂ እየፈታናቸው አልመጣንም። በመሆኑም ዛሬ ያለንባቸው ችግሮች ደግሞ ለነገ አድረው ሌላ ቁርሾ እንዳይፈጥሩብን የምንፈልግ ከሆነ ብቸኛው መንገድና እስከ አሁንም ያልሞከርነው ምክክር ብቻ ነው።
በመሆኑም እንደ አንድ አገር ልጆች ቁጭ ብለን በስነ ስርዓት ተመካክረን አናውቅም፤ እስከ አሁን የሚደረጉ ምክክሮችም አንድ አይነት የፖለቲካ አካሄድ ያላቸው ሰዎች ተሰብስበው ሊነጋገሩ ይችላሉ፤ ወይንም ደግሞ በሃይማኖት የሚመሳሰሉ ሰዎች ተሰብስበው በአገር ጉዳይ ላይ ሊማከሩ ይችላሉ እንጂ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች፣ የብሔር ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖቶች እንዳሉባት አገር ቁጭ ብለን የተነጋገርንበት ጊዜ የለም።
በነገራችን ላይ እኔ ሁሌም የሚያስደንቀኝና የሚያስደነግጠኝ ነገር ልንገርሽ ፤ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በሚመራበት ጊዜ ከአስር በላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኤርትራ ውስጥ ነበሩ፤ እና ሁሉም የነበረውን መንግሥት ለመጣል የሚታገሉም ናቸው። ግን እነዚህ ፓርቲዎች አንድም ቀን ቁጭ ብለው ለምንድን ነው የምንዋጋው? ብናሸንፍ ምንድን ነው የሚሆነው? የምንዋጋው መንግሥት ስልጣን ቢለቅ ምንድን ነው የምናደርገው? የእያንዳንዳችን ራዕይስ ምንድን ነው? ለኢትዮጵያስ ይስማማታል ወይ ?ካልተስማማትስ እንዴት ነው የምናስታርቀው የሚሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተመካክረው አያውቁም። ይህ በጣም ያስደነግጣል።
አሁን ላይም የምናደርጋቸው እያንዳንዱ ነገር ምክክር የጎደላቸው ናቸው። የኢትዮጵያን ያለፉትን አሁን ያሉትንም እንዲሁም ወደፊት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ታሳቢ ያደረጉ ምክክሮችን እያደረግን ብንመጣ ኖሮ ችግሮቻችንን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንኳን ባንችል እንቀንሳቸው ነበር። በመሰረቱ ሁሉም ነገር በንግግር ይፈታል ማለት ላይሆን ይችላል ምክንያቱም ሰላም በሁለት አካላት ተሳትፎ የሚጣ በመሆኑ ግን ደግሞ እንነጋገር የሚለው ነገር ወሳኝ ነው።
አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን ወክለው የሚንቀሳቀሱ አካላት ተገናኝተው መነጋገር አለባቸው፤ እዛ ውስጥ አልፈልግም ብሎ የሚያፈነግጥ ካለ ደግሞ ሌላ መንገድም ሊኖር ይችላል፤ መነጋገር ግን ብዙ ችግሮችን ይፈታል ለመነጋገር መፍቀድ ደግሞ ወሳኝ እርምጃ ነው።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎም ከላይ ጠቀስ አድርገውታል የዋሉ ያደሩ ችግሮቻችንን በንግግር አለመፍታታችን እዚህ አድርሶናል አሁንስ ለመነጋገር ዝግጁነታችን ምን ያህል ነው፤ እናንተስ በስራችሁ ላይ ምን ታዘባችሁ?
አቶ ንጉሡ፦ እውነት ለመናገር አሁን ላይ አገራችን ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የመመካከር ፍላጎት አለ፤ ምክንያቱም አሁን በዚህ ዘመን ሰዎች የትኛውንም ችግሮቻቸውን በመነጋገር ነው የሚፈቱት፤ ይህ ደግሞ እንኳን በከተማ በገጠሩም እየተለመደ የመጣ ነው። እንደ ማሳያ የጋሞ አዛውንቶች የሰሩትን ስራ ማስታወስ በቂ ነው። በመሆኑም እኛ ያልተጠቀምንባቸው ነገር ግን ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሉን። እነዚህን እሴቶቻችን በመንደር በቀበሌ በቤተሰብ ደረጃ እንደሚያገለግሉንና ችግርን ግጭትን እየፈታንባቸው ያሉ መንገዶች በአገር ደረጃ ባሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዘልቀው መግባት አልቻሉም።
ፖለቲካው ውስጥ ያለው ባህል የተለየ ከመሆኑም በላይ ግጭቶች ሲፈጠሩ እነሱን ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ ሃይል ብቻ መሆኑ ነው። ግን ይህም ሆነ አሁን እኛ እየሰራን በምናየው ነገር ብዙ አበረታች ነገሮች አሉት። ለምሳሌ የዴስቲኒ ኢትዮጵያን ስራ ስንሰራ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚወክሉ ሰዎች ያጋጥሙናል በተለይም ደግሞ ብዙ ልምድ ያላቸው ፖለቲከኞቻችን ተሰብስበው ሲነጋገሩ ስናይ አስደሳች ከመሆኑም በላይ ተስፋ ሰጪ ነው። የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ይህች ናት ብለው እኮ የሚፈልጓትን አገር አስቀምጠዋል፤ ምን ልትመስል እንደሚገባም በተወሰነ መልኩ አሳይተዋል። በኢኮኖሚ በማህበራዊ በፖለቲካ በዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት የሚለውን ሰርተዋል።
በመሆኑም አንድ ቦታ ተገናኝቶ ለመነጋገር የፈቀደ ለማዳመጥም ዝግ ስለማይሆን ይህ መደማመጥ ደግሞ የራሳችንን ችግር እንድናውቅ እኛም በሌሎች ጫማ ውስጥ ቆመን ሁኔታዎችን እንድንረዳ ይጠቅማል ፤ ይህንን ካላደረግን ግን አንድ ሰው የሚያራምደውን አመለካከት ሁልጊዜ የተሳሳተ ነው ብሎ ማሰብ እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ወደማለት መሄድ ያመጣል። በመሆኑም እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎች አንድላይ ተሰብስበው የሚስማሙበትን ነገር ለማሳየት ችለናል፤ ይህም ለእኛ በጣም አዲስ ነገር ነው። በመሆኑም ተስፋ አለን ለማለት ያስደፍራል።
በሌላ በኩል ደግሞ በምርጫ ወቅት ምርጫው እንዴት ነጻ ሰላማዊ ፍትሃዊ ሊሆን ይችላል? በማለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር አካሂደዋል፤ መጨረሻ ላይም ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ራሳቸው የተወሰኑ ችግሮቻችንን ፈተናል ያልተፈቱ ብዙ ችግሮች አሉን ግን ደግሞ የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን በሰላም እንዲጠናቀቅ እንፈልጋለን ብለው ነው ሰላማዊ ያደረጉት። በመሆኑም ቁጭ ብለን እስከተመካከርን ድረስ ማድረግ የሚቻልና የማይቻለውን እናውቃለን። ነገር ግን ዝም ብለን ሩቅ ሆንን ከመፍረድና አንድ ጎራ ይዘን ከመተጋተግ ቀረብ ብለን ችግሮቻችን ላይ በመመካከር መፍትሔ ማምጣት እንችላለን። በመሆኑም አንዳችን ሌላኛችንን የመረዳት ነገር ሊፈጠር ይገባል። ይህ ደግሞ በተወሰነ መልኩ መተማመን እንዲሁም ራስን በሌሎች ጫማ ውስጥ ከቶ ማየትን ይፈጥራል። አንዱ አንዱን እየተረዳ እየተማመንን ስንሄድ የሌላውን ህመም እያወቅን ይሄድና በመጨረሻም ወደጋራ ስምምነት የምንመጣ ይሆናል። ስለዚህ አንድ የሚያግባባን እርምጃ እንውሰድ ካልን ተነጋግረን ተግባብተን ተመካክረን ወደሚያግባባን ነገር መሄድ አለብን።
ሌላ በምክክር የመጣና ተስፋ የሚሰጥ ውጤት ልንገርሽ ፤ በእኛ አገር ከሚያለያዩን ነገሮች መካከል የታሪክ ትርክታችን አንዱ ነው። ይህንን ለማስተካከልም የታሪክ ምሁራንን ከአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች አሰባስበን ለአራት ቀናት አቆየናቸው በዚህም ያሉት ነገር ምን መሰለሽ ትንሽ ከተነጋገርንና ለቀጣዩ ንግግር መሰረት ከጣልን ይበቃናል ፤በዚህ አራት ቀን ውስጥም የታሪክ አረዳዳችንና አገላለጻችን የተለያየ ቢሆንም ማህበር መስርተን ችግሮቻችንን ሳይንሳዊ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንፍታ ብለው ተስማሙ ፤ ሌላው ከአስር ዓመት በላይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰጠው የመጀመሪያ ዓመት የታሪክ ትምህርት ቆሟል ለምን ቆመ እነሱ ራሳቸው ያልተግባቡባቸው የተወሰኑ አንቀጾች በመኖራቸው ነው፤ በዛ ስብሰባ ላይም አላግባባ ያሉንን አንቀጾች ቁጭ ብለን እንፈትሽ ብለው ተስማሙ በዚህም ጥልቅ ውይይት አደረጉ ፤አሁን አንቀጹ ተሻሽሎ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የታሪክ ትምህርት እንደገና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲሰጥ ሆኖ አሁን ላይ የተወሰኑ የትምህርት ተቋማት ጀምረዋል።
ከዚህ አንጻር ቁጭ ብለን በመነጋገር እንጠቀማለን እንጂ አንጎዳም፤ እስከ አሁን ድረስ እድል ያልሰጠነው ለምክክር ብቻ ነው። ሁሉንም ነገር አይተነዋል ከጥቅሙም ጉዳቱ እንደሚያመዝን ተረድተናል። በመሆኑም ለምክክር እድል እንስጥ።
አዲስ ዘመን፦ አንዳንድ አካላት ምክክር ከማን ጋር ማንስ ከማን ተጣልቶ ነው ብሔራዊ መግባባት የሚያስፈልገው የሚሉ አሉና እንደው እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ንጉሡ፦ አሁን ፀብ የሚባለው ነገር የመንደር ጥል አይደለም። እንግዲህ ከዚህ በላይ አገር እንዴት ሊጣላ ይችላል። የምናየውን መሸፈን ጥቅም የለውም ምክንያቱም አሁን ማህበራዊ ሚዲያው የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋም ሌላው ቢቀር እስከ ዛሬ ድረስ የመጣንበት የግጭት ሂደት አሁን ያለንበትን ሁኔታ ወደፊት ሊመጡ የሚችሉትን ሁሉ እያሳየን ነው። ቆም ብለን ማሰብ ከቻልን ተጣልተናል አልተግባባንም። እነዚህን ጉዳዮቻችንን የጸባችንን መንስኤዎች በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጠን መወያየት ካልቻልን “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” አይነት ነገር ነው የሚገጥመን።
እሺ ፀብ የለም ማን ከማን ጋር ነው የሚነጋገረው የሚሉ አካላትም እኮ ቆም ብለው ማየት ስላልፈለጉ እንጂ አሁን እየሆን ላለው ነገር መንስኤው እኮ አለመግባባታችን ነው። ባልተግባባንባቸው ነገሮች ላይ ደግሞ ቁጭ ብለን መወያየት አለመቻላችን ችግሮች እንዲሰፉ ብሎም ብሔር ከብሔረሰቦች በጥቅም በስልጣን በሀብት በርስት እንዲጣሉ አድርጓል፤ በመሆኑም ይህ ጉዳይ የፖለቲከኞቹ ብቻ አለመሆኑን በመረዳት ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የሚወክሉ አካላት በአንድ ላይ ተቀምጠው መወያየት ብሔራዊ መግባባት ላይ የምንደርስበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ አዎ እንግዲህ በዚህ መልኩ ብሔራዊ እርቅንና ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት በእናንተ በኩልም የታሰበ ነገር እንዳለ አውቃለሁና እስኪ ስለሱ ትንሽ ይንገሩን?
አቶ ንጉሡ፦ ይህ ውይይት ከበፊት ጀምሮ ሲገፋ ሲገፋ መጥቶ ነው እዚህ የደረሰው፤ እኛ ሕዳር ወር ላይ እናካሂደዋለን ብለን አስበናል፤ አገራዊው ሁኔታ ደግሞ በምን እንደሚያስኬደን አናውቅም።
አዲስ ዘመን፦ ሀገራችን አሁን ካለችበት ችግር ለመውጣት አንዱ መንገድ አንድነት ነው የሚሉ አሉ፤ በተቃራኒው ደግሞ ልዩነት የሚሰበክበት ሁኔታ ብዙ ነው፤ ከዚህ አንጻር አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ምን ያህል ፈታኝ ይሆናል ይላሉ?
አቶ ንጉሡ፦ እዚህ ላይ ምን መሰለሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉንን የተለያዩ ልዩ ልዩነቶች አቻችለን ተቻችለን ተደማምጠን ተከባብረን ተጠቃቅመን ተጋግዘን ነው አንድነታችንን የምንፈጥረው፤ አንድነት አንድ አካል በሌሎቹ ላይ ጭቆና ለማምጣት የሚጠቀምበት መሳሪያም ሊሆን አይገባም። አንድነት በትክክል በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ልዩነቶች እውቅና ሰጥቶ ጥያቄ ካላቸውም ጥያቄያቸውን አዳምጦ ደረጃ በደረጃ ምላሽ የሚያገኙበትን ሁኔታ እያበጀ የሚሄድ ሊሆን ይገባዋል።
እንዴት ተቻችለን መሄድ አለብን የሚለውን ቀመርም እየቀመሩ በውይይት የሚኬድበት እንጂ ይህ ነው አልያም ያ ነው የሚለው ነገር በበኩሌ ምቾት አይሰጠኝም። ዛሬ አንድነት አያስፈልገንም ተብሎ ሁሉም ወዳሻው ቢሄድ መሰረታዊ የሆኑት ጥያቄዎች ቡድኑ ውስጥ አይቀሩም ነገ ሌላ ቡድን በውስጡ ንዑስ ቡድኖችን ፈጥሮ ጥያቄው እየቀጠለ ይሄዳል፤ ይህ ሲሆን ደግሞ መከፋፈሉ እየሰፋ ይመጣል። ነገር ግን እኔ እንደሚመስለኝ ሊሆን የሚገባው የተለያዩ አስተሳሰቦች ማንነቶች ተቻችለው ሊኖሩ የሚችሉበትን ቀመር ተጋግዘን መስራት ነው የሚያስፈልገው።
እነዚህን የሚያለያዩንን ነገሮች ደፈር ብለን ይዘን መነጋገር መቻል አለብን። አለበለዚያ ግን ነገሩን እያሳደርን ለይስሙላም እያመንን የማንተገብረውን ቃል እየገባን ባስ ሲልም ነገሩን ከመጠን በላይ እየለጠጥነው ስንሄድ ነገሮች ከመስመር እየወጡ ይሄዳሉ።
አሁን እንደምናየውና ከታሪክም እንደተማርነው ቁጭ ብለን መነጋገር መቻል አለብን። እሺ የእነዚህ ቡድኖች ፍላጎት አስተሳሰብ ምንድን ነው? ምንድን ነው የጎደለባቸው ጥቅም? የሚለውን መነጋገር ከዛ አቅማችንን እየጨመርን መፍትሔ እያመጣን እንሄዳለን ለዚህ ግን መሰረቱ መነጋገር ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ጽንፍ የወጣ ብሔርተኝነት እየገነነ መጥቷል፤ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ብሔራዊ መግባባት የሚባለው ነገር ሊተገበር የሚችለው?
አቶ ንጉሡ ፦ በማንኛውም አገር ውስጥ ጫፍ የወጡ አመለካከቶች ሁሌም አይቀሩም፤ የፈለገ ጥያቄ ለመመለስ እንሞክር ቢባል ጫፍ ላይ የሚሆኑ አስተሳሰብ የያዙ ሰዎች አይጠፉም፤ የዳበረ ዴሞክራሲ አላቸው በሚባሉ አገራት እንኳን ይህ ሁኔታ አለ፤ እናም ማስቀረት አይቻልም፤ ግን ሰዎቹን ወደመሃል መሰብሰብ ይቻላል፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ በመመካከር ነው። በመሆኑም የተለያየ አቋም ያላቸውን ሰዎች አቀራርበን እንዲነጋገሩ ባደረግን ልክ ችግሩ የአቋም መሆኑ ይቀርና ወደ ጥቅም ተኮርነት ይቀየራል። ይህንን ጥቅምም ለማምጣት የሚቻለው በተከታታይ በሚደረጉ ምክክሮች ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን እያደረግን ያለነው የብሔራዊ መግባባትና የንግግር ሁኔታ ስኬታማ ቢሆን ወደፊት ምን አይነት ኢትዮጵያን ነው የምናየው?
አቶ ንጉሡ፦ ይህ ነገር ከተሳካ አንድ አካል ብቻ ሳይሆን ሁላችንም የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ እየገነባን እንሄዳለን። ይህ አገራዊ ምክክር የአንድ ቀን አውደ ጥናት ወይም የሳምንት ስራ አይደለም። በተከታታይ ዓመታትን ሊፈጅ የሚችል ሂደት ሲሆን በዚህ ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ፍላጎቶች ያሏቸው ቡድኖች ጥቅማቸው እየተከበረ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ እየመጣች ነው እያሉ እንዲሄዱ ያስፈልጋል።
አንዱ አካል ብቻ የሚፈልጋት ኢትዮጵያ እየተገነባች ለሌላኛው ሰው ደግሞ ኢትዮጵያ የሚለው ትርጉም እየጠፋበት መሄድ የለበትም። በመሆኑም ሁላችንም የምንፈልጋት አገራችን እየተፈጠረች መምጣት ይኖርባታል። ይህ ሲሆን ደግሞ ሰላማችን ተረጋግጦ የተረጋጋ ኑሮ መኖር እንጀምራለን። ያ ሰላማዊና የተረጋጋ ኑሮ ደግሞ አገራችን በግጭትና በአለመግባባት ምክንያት የምታጣውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አስቀርቶ ኢኮኖሚያችን በጨመረ ሁኔታ እያደገ ሄዶ ፍላጎቶቻችን እየተመለሱ የሚሄዱበት ጊዜ እንዲመጣ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ጦርነት ላይ ነው ያለነው፤ ይህ የጀመርነው አገራዊ የውይይት ሁኔታና ያስፈልገናል የምንለው ብሔራዊ መግባባት ምን ያህል ከችግሩ ያወጣናል?
አቶ ንጉሡ፦ አገራዊ ምክክር እስከ ዛሬ የገባንባቸው አሁን ያለንበትን እንዲሁም ወደፊት የሚፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ መከላከል ይችላል። አገራዊ ምክክር ያልሞከርነው ብቸኛ አማራጭ ነው ፤እናም መሞከር አለብን።
አዲስ ዘመን፦አገራዊ ምክክርም ሆነ ብሔራዊ መግባባት አለማቀፋዊ ተሞክሮው ምን ይመስላል?
አቶ ንጉሡ፦ አገራዊ ምክክር ተሞክሮ አንድ እርምጃ ወደፊት ያስኬዳቸው አሉ ፤ ያላለቀበት ሁኔታም እንዲ የከሸፈበትም አካባቢ አለ፤ ስለዚህ ተሞክሮው በጣም የተለያየ ነው። እኛ ግን ስላልሞከርነው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይቻልም፤ ነገር ግን የከሸፉባቸውንም ሆነ የተሳኩባቸውን ምክንያቶች ነቅሰን አውጥተን እዚህ እንዲሳካልን ምን ብናደርግ ጥሩ ነው የሚለውን አይተን እንድንወስን ይረዳናል።
በመሆኑም ለአገራዊ ምክክር እድል እንስጥ። እስከ ዛሬ ብዙ ነገሮችን ሞክረናል ያልሞከርነው ብቸኛ ነገር እርሱ ብቻ ስለሆነ ሁላችንም ወደጠረጴዛ ዙሪያ መጥተን በመመካከር የሚያጣሉንን የማያግባቡንን ነገሮች ለመፍታት ጥረት ብናደርግ የማንስማማባቸው ነገሮች ላይም እንዴት ተቻችለን መኖር እንችላለን የሚለውን ብናይ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ንጉሡ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/2014