የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥበበኛ ህዝብ ነው…ጥበቡ ይገርመኛል። ማስተዋሉ…ምሳሌው ያስደንቀኛል። ነገሮችን፣ አጋጣሚዎችን፣ ሁኔታዎችን በምሳሌአዊ አነጋገር ሲገልጽ ሳይንስን የሚያስንቅ ጥበብ አለው። ከዚህ ምሳሌአዊ ንግግሩ መካከል ለአሸባሪው ሕወሓት የሚመጥን አንድ አባባል መዘዝኩ፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል” የሚል አህያን ምሳሌ ያደረገ ድንቅ አባባል።
ይህ አባባል ለአህያና ላልተገባ ተግባሯ እንደተቀመረ ሁላችሁም የምታውቁት ሀቅ ነው። እኔም ለሕወሓትና ላልተገባ ተግባሯ ስጠቀምበት ሃሳቤን በትክክል ይገልጽልኛል ብዬ በማሰብ ነው። ሕወሓትን በአንድ ቃል ግለጽልኝ ብትሉኝ “አህያ” ብዬ ነበር የምመልስላችሁ። ከላይ ባቀረብነው የኢትዮጵያውያን ምሳሌአዊ አነጋገር ላይም አህያ ለሚመጣው ትውልድ ርህራሄን አጥታ ሰርዶ እንዳይበቅል፣ ግጦሽ እንዳይለማ የምታስብና አሁናዊ ራሷን ብቻ የምትሻ እንስሳ ሆና ቀርባለች።
በአህያ ልብ ውስጥ ሰውነት የለም፣ ለሌሎች ማሰብና ለሌሎች መኖር የለም፣ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ራስና የራስ ብቻ ነው ያለው። ይሄን እውነት ወደ አሸባሪው ሕወሓትና ወደ ግብረ አበሮቹ ስናመጣው የምናገኘውም ይህንኑ እውነታ ነው። ቡድኑ ልክ እንደ አህያና እንደ አስተሳሰቧ ነው። በማንነቱ ውስጥ ሰውኛ ባህሪ የለም። ለሚመጣው ትውልድም ሆነ ላለው ትውልድ የሚሆን ቅንጣት ርህራሄ ያልፈጠረበት ከግለኝነትና ከቡድንተኝነት እሳቤ ያልተላቀቀ እንስሳዊ ተፈጥሮ ያለው ቡድን ነው። በህዝብ ላብ፣ በወገን ዕንባ ራሱን ወልዶ ያሳደገ፤ በንፁሐን ስቃይ፣ በደጋጎች እንግልት የራሱን ቤት የሠራ አረመኔ ቡድን ነው።
ቡድኑ ሃያ ሰባት ዓመታት ሙሉ እንደ አህያ እያሰበና እያደረገ፣ አህያዋ የተናገረችውን እየተናገረ በአህያዊ አስተሳሰብ ውስጥ ተዘፍቆ ኖሯል። ሕዝብ የሌለበት፣ ታሪክና እውነት የመከኑበት፣ አብሮነትና እኩልነት የተረሳበት ግለኝነትና ኢፍትሐዊ የአንድ ወገን ተጠቃሚነት የነገሠበት አስተሳሰብ ይዞ ለራሱና ለራሱ ብቻ ኖሯል። ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ የቡድኑ የሃያ ሰባት ዓመታት የስልጣን ዘመን ከአህያና ከተረቷ ጋር ይመሳሰላል። እሱ ብቻ አይደለም። አሁን ላይ ሀገር ለማፍረስ ጫካ የገባው ይኸው አሸባሪ ቡድን ዛሬም ድረስ ከዚህ አስተሳሰብ አለመውጣቱን ስመለከት የተረቱ ባለቤት መሆኑ ያንስበት እነደሆነ እንጅ የሚበዛበት አይደለም።
“እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አለች አህያ የሚለው ተረት ሕወሓትን በደንብ ስለሚገልጸው፤ “እኔ ከሞትኩ ሀገር ትጥፋ አለች ሕወሓት” በሚል ቢስተካከል ደስ ይለኛል። ምክንያቱም አሁን ላይ እኔ ካልመራሁ ሀገር ትጥፋ በሚል ፈሊጥ እየተንቀሳቀሰች ያለችው እሷው ራሷ ሕወሓት ስለሆነች። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ሕወሓትን ትላንትናም ዛሬም ገላጭ አባባል ነው። ትላንትና ሕወሓት ማለት የሀገርና የታሪክ የትውልድም ጠንቅ ነበር። ባልነበረ ታሪክ፣ ባልነበረ ድራማ የትውልድን ታሪክ አበላሽቷል። ለዘመናት እንደ ድርና ማግ የተቋጠረ ኢትዮጵያዊነትን አላልቷል።
በዚህም በአባቶቻችን የእውነትና የሀቅ ተጋድሎ የተወረሰን የጋራ መልክ አደብዝዟል። በሕወሓት የስልጣን ዘመን ማር የሌለው ቀፎ ነበርን…ማራችንን በልቶ፣ ማራችንን ለባዕድ ሰጥቶ ቀፎ ብቻ አድርጎን ነበር። በሕወሓት የስልጣን ዘመን እንጀራ የሌለው ሌማት ነበርን። እንጀራችንን እርሱ ብቻ በጉልበት በልቶ ባዶ ሌማት አድርጎን ነበር። በሕወሓት የስልጣን ዘመን እርሱ እንጅ እኛ የምንተነፍስበትና የፀሐይ ብርሃን የምንመለከትበት በታፈነ ቤት ውስጥ የምንኖር መስኮት አልባ ቤትም ነበርን። ታዲያ ይሄ ቡድን እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አለ ካልተባለ ማን ሊባል ይችላል? አሁንም እያየነው ያለነው ይሄንን ነው። አሸባሪው ሕወሓት እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም እኔና ለእኔ ብቻ በሚል ሰብዓዊነት ባልፈጠረበት እንሰሳዊ ባህሪው ሀገር በማውደም ላይ ይገኛል። ዛሬም በሕወሓት የግፍ በትር ያልተመታ ኢትዮጵያዊ የለም። ዛሬም እንደትላንቱ በሕወሓት የግፍና የጭካኔ ጥርስ ተይዘው የሚያለቅሱ ብዙ ናቸው። ዛሬም እንደ ትላንቱ በመራር ስቃይ ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ናቸው። አህያዊ የግለኝነት አባዜ የተጠናወተው ይሄ ቡድን እኔ ከሞትኩ ሀገርና ትውልድ የራሳቸው ጉዳይ በሚል እሳቤ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው። እንደዛ ባይሆንማ በንፁሐን ሞትና እንግልት ትርፉን አያሰላም ነበር።
እንደዛ ባይሆንማ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማየት ከሚሹት ጋር ተባብሮና ተፋቅሮ ይሠራና ይኖር ነበር። እንደዛ ባይሆንማ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ሰይጣናዊ የረከሰ እሳቤ ለጥፋት አይነሳም ነበር። ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ሰው መሆን ያቃተው ሕወሓት የትላንቱ የሕዝብ ስቃይ ሳይበቃው ዛሬም በስቃይ ፈጣሪነቱና በሕዝብ ገዳይነቱ እንደቀጠለበት ነው። ይሄ ቡድን ዓላማው ምንድነው? ከእኔነት የዘለለ እሳቤን እንዴት መፍጠር አቃተው? ሰው እንዴት ሀገሩን በማጥፋትና ወገኑን በማሰቃየት ደስታን ያገኛል?
በዓለም ታሪክ አምርሮ የሚጠላትን ሀገር የመራ ብቸኛው ቡድን ከሃዲው የሕወሓት ቡድን ነው። ሕወሓት ኢትዮጵያን የሚወዳት ቢሆን ኖሮ በዚህ ልክ ባልጎዳት፣ መከራዋንም ባላበዛው፣ እንድትጠፋም እንዲህ በግልጽ ዕቅድ ይዞ ያለ ዕረፍት ባልሠራ ነበር እላለሁ። ሕወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ቢወደው ኖሮ በዚህ ልክ እንዲህ ባላሰቃየው ነበር እላለሁ። ከመጀመሪያ የስልጣን ዘመኑ አንስቶ እስከአሁን ድረስ ሀገራችን በዚህ ቡድን ክፉኛ እየተሰቃየች ነው። ኢትዮጵያ ለሕወሓት ምኑም ናት። ታጥቆና ከአማጺያን ጋር ተቧድኖ ጥቅሙን የሚያስጠብቅባት እንጂ የመቶ ሃያ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እናት አትመስለውም።
ከብዙኃኑ በተለየ እርሱ ላይ የበቀለ አውሬያዊ ማንነቱን የሚደብቅባት ገመናውን የሚሸፍንባት የሐሰትና የክፋት መሸሸጊያ የግል ጓዳው እንጂ የመቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ መተኪያ የሌላት ውድ እናት፣ የደምና የአጥንት መስዋዕትነትን በከፈሉ ልጆቿ ለዘመናት ነፃነቷን ሳታስነካ በክብር የኖረች ዛሬም ለእውነትና ለፍትህ ልጆቿ ሕይወታቸውን የሚሰጡላት አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ ሃገር አትመስለውም። ሕወሓት ኢትዮጵያን እንዲህ ነው የሚያያት…እንደዚህም ነው ሲያያትት የኖረው። እናም ይሄን ቡድን መታገል አለብን። ይሄን ቡድን ከነአስተሳሰቡ፣ ከነክፋቱ፣ ከነፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለሙ መቅበር ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል እላለሁ።
ሀገር መውደድ በተግባር የሚገለጽ ነው። ሀገር በመውደድ ውስጥ እኔነት የለም። ሀገር በመውደድ ውስጥ በጎ ሃሳብ እንጂ እንደ አህያ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚል እኩይ ቃል አይነገርም። ለሀገር የሚለፉ እነርሱ የተባረኩ ናቸው። ለሀገር የሚለፉ አንድ ቀን በትውልዱ እንደሚከብሩ ታሪክ ያስተምረናል። አባቶቻችን ለሀገርና ለነፃነት በከፈሉት ዋጋ እያመሰገንናቸው ነው። በዓድዋና በአንባላጌ፣ በካራማራና፣ በኦጋዴን ለሀገርና ለታሪካቸው ሲሉ በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ትውልድ እየዘከራቸው ነው።
እንደ ሕወሓት ያሉ በሀገርና በታሪክ ላይ መጥፎ አሻራ ያስቀመጡ እነሱም በትውልድ የሚወገዙበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ኢትዮጵያን የነኩ፣ ያስነኩ ሁሉ ሳይቀጡ አይቀሩም። ታሪክ የሚነግረን ይሄንን ነው። አሁን ተራው የሕወሓት ነው…ኢትዮጵያን ነክቷልና፣ በህዝቦቿ ላይ ግፍ ፈጽሟልና ሳይቀጣ አይቀርም።
ሀገር መልካም ነፍስ ትሻለች። ሀገር መልካም ልብ ግድ ይላታል። መልካም ነፍሶች ለሌላው የሚሆን ደስታ እንጂ ስቃይ የላቸውም። መልካም ልቦች ለሌሎች የሚሆን እውነት እንጂ ሐሰት የለባቸውም። አሁን ጊዜው በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የምናሻግርበት ነው። ከእኔነት ወጥተን ወደ ህዝባዊነት የምንሸጋገርበት የተሀድሶ ምዕራፍ ነው። አሁን ጊዜው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የምንልበት ሳይሆን በኔ መኖር ሌሎች እንዲኖሩ የምፈቅድበት የምንልበት ጊዜ ነው።
አሁን ጊዜው በእኛ ፍቅር፣ በእኛ አንድነት፣ በእኛ ሕብረት የልጆቻችንን ኢትዮጵያ የምንገነባበት እንጂ እንደ ሕወሓት በራስ ወዳድነት ሀገርና ታሪክ የምናወድምበት አይደለም። አሁን ጊዜው ለውጥ ከናፈቁ ሕዝቦች ጋር ወደ ፊት የምንልበት እንጂ ከሀዲዎች በነገሩን የሐሰት ትርክትና ወሬ ተጠምደን ሰላም የምናጣበት አይደለም። ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን ክብር ይሄን ጊዜ የምንጠቀምበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ነን።
ይሄ ጊዜ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየተፋለምን ስለ አንድነትና ስለአብሮነት የምናወራበት ነው። ይሄ ጊዜ ከአሸባሪው ሕወሓት አስተሳሰብ ተላቀን መልካም ሀገርና መልካም ትውልድ የምንገነባበት ብርሃናማ ማለዳ ነው። ይሄ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ ኢትዮጵያን የምናገለግልበት፣ ህዝባችንን የምንጠቅምበት የመነሳት ጊዜ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል እሳቤው ብዙ ተጉዞ ሀገራችንን አራቁቷታል። ህዝባችንን ባዶ አድርጎታል። ታሪክ አበላሽቷል። ሕወሓት ከፍጥረቱ ጀምሮ ኢትዮጵያዊ አይደለም። ቢሆን ኖሮ ሀገሬ ናት ብሎ ቢያስብ ኖሮ በዚህ አስተሳሰብ ባልተጓዘ ነበር። ከሃምሳ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላም ከዚህ ከለእኔ ብቻ አስተሳሰቡ አልተላቀቀም። ዛሬም በጭካኔ ላይ ነው። ዛሬም ሕወሓት በንፁሐን ሞትና ስቃይ ትርፉን በማስላት ላይ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሃያ ሰባት ዓመታት በዚህና በመሳሰሉት ጎጂና ትርፍ በሌላቸው ለፖለቲካ ትርፍ ብቻ በሚቀመሩ የውሸት ፈጠራዎች ስትመራ ሰንብታለች። አንዳቸውም ግን ከጉዳት ባለፈ ትርፍ አልነበራቸውም።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ርካሽና ውዳቂ እሳቤ ስር ነበረች። በፖለቲካ ቀበኞቹም ሆነ በወቅቱ የስርዐት አራማጆች የተጠቀመችው አንዳች ነገር የለም። ኢትዮጵያ አዲስ መሪ፣ አዲስ አስተሳሰብ እንደሚያስፈልጋት አላወቀም። ህዝብ አዲስዛሬ፣ አዲስ ነገ እንዳለው አልደረሰበትም። ዓለምና የሰው ልጅ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንዳሉ ዘንግቶታል። በተመሳሳይ ርምጃ እዛው እየረገጠ የሚኖር ቆሞ ቀር ቡድን ነው። ይሄ ቡድን ለዚህ ትውልድ አይመጥነውም።
ስለሆነም አዲስ አስተሳሰብ ልንገነባ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ከሕወሓት የወረስነውን አውዳሚና ኋላቀር አሮጌ ማንነታችንን መሻር አለብን። አዲስ ሃሳብ ከሌለን አዲስ ነገር አይኖረንም፣ የጥንቱን ስርዓት አራማጅ ነው የምንሆነው። የሀገራችን የኋላ ታሪክ ደግሞ ሕወሓትና አስተሳሰቡ ነው። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለው የሕወሓት አስተሳሰብ ነው የኋላ ታሪካችንና አሮጌው ማንነታችን። እኛ የዛሬዎቹ ግን ሕዝብ የሚጠቅም፣ ሃገር የሚገነባ፣ ትውልድን በመልካምነትና በጀግንነት የሚያንጽ አዲስ አስተሳሰብ ልንፈጥር ይገባናል። ከሁሉ አስቀድመን አስተሳሰባችንን መቀየር ይኖርብናል።
ይህንንም ነገ ለምትፈጠረው ሀገርና ትውልድ የሚሆን በሥራ የተፈተነ መልካምና አወዳሽ ሕዝባዊ ስነ ቃል በመፍጠር መጀመር እንችላለን። ትውልድን የሚያስከፋ ግለኝነት የነገሠበት ክፋትን የሚያስተምር ሳይሆን ትውልድን ለመልካም ሥራና ለአኩሪ ጀግንነትና ክብር የሚያነሳሳ አባባል በበጎ ሥራዎቻችን በኩል መፍጠር ይኖርብናል። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚለውን አውዳሚውንና ኋላቀሩን የሕወሓት መመሪያ “ትውልድ ይቀጥል፣ እኔ ካለፍኩ ጀግና ይፈጠር” በሚል አዲስ መሪ አባባል መቀየር ይጠበቅብናል። “በኔ መኖር ሌሎች ይኑሩ፣ በኔ ሰውነት ሌሎች ያትርፉ” የሚል አዲስ አስተሳሰብ መገንባት ይኖርብናል። ሁላችንም በዚህ እውነት ውስጥ ሆነን ማሰብና መኖር ይጠብቅብናል። ሁላችንም ለዚህ እውነት ተገዢ መሆን ይገባናል።
አሁን ያለው በለውጥ መንፈስ የተገለጸው ትውልድ በፍቅርና በእውነት ሀገሩን ለመገንባት መዶሻና ሚስማር የያዘ ትውልድ ነውና። ይሄ ትውልድ በመተቃቀፍና በመተጋገዝ አዲስ ታሪክ ሊሠራ የተሰናዳ ትውልድ ነውና ጊዜው ኢትዮጵያን የምንፈጥርበት እንጂ በአሮጌ እሳቤ የምንራመድበት አይደለምና አዲስ አስተሳሰብ በመፍጠር ለሁሉም የምትመች እኩልነትና ፍትሐዊነት የሰፈነባት አዲስ አገር መገንባት ይጠበቅበታል። አገር የምትጠፋውም የምትፈጠረውም በአስተሳሰብ ነውና።
ይሄ እንዲሆን ግን ከሁሉ አስቀድመን የምንጊዜም የሀገራችን ጠላት የሆነውን የሕወሓት ኃይል ማውደም ይኖርብናል። ምክንያቱም አሸባሪው ሕወሓት እስካለ ደረስ መልካም ሀገርና መልካም ትውልድ መፍጠር የማይታሰብ፤ ቢታሰብ እንኳን ዋጋ የሚያስከፍል ተግዳሮት ይሆንብናልና።
ለዚህም አንዳችን እየሠራን አንዳችን ጠባቂ በመሆን፣ አንዳችን እየለፋን አንዳችን ዳር ቆሞ ተመልካች በመሆን ሳይሆን ሁላችንም የሚጠበቅብንን ማድረግና ኃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት መቻል ይጠበቅብናል። በሀገር ጉዳይ ሁላችንም ያገባናልና… የሀገር ጉዳይ የመንግሥት ብቻ አይደለም፣ ሁላችንም ለሀገራችን ያገባናልና! በሀገር ጉዳይ ላይ የማይመለከተው የለምና! ሁላችንም ስለሀገራችን ይመለከተናል። ሁላችንም ስለሕዝባችን ያገባናል። እንደዛ ሲሆን የሃገርና የሕዝብ ፀር፣ የሁላችንም ቀንደኛ ጠላት የሆነውን፣ ሊያጠፋን የተነሳውን ከሃዲውን ሕወሓት ከእነ አስተሳሰቡ አጥፍተን የምናልማትንና የምንመኛትን ለሁላችንም የምትመች አዲሲቷን ፍትሐዊት ኢትዮጵያ ዕውን ማድረግ እንችላለን።
የበትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/2014