በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሓ.ት) በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ምዕራባውያን መንግሥታትና የመገናኛ ብዙኃን ተቋሞቻቸው በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩት ያለው መረን የለቀቀ ኢ-ፍትሐዊ ጫና የእውነትን፣ የሉዓላዊነትን፣ የዓለም አቀፍ ትብብርንና የፍትሕን መርሆች የጣሰ ስለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎችን መቁጠር ይቻላል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ መከላከያ ሠራዊትን ከትግራይ ካስወጣ በኋላ አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት አማራና አፋር ክልሎችን በመውረር አሰቃቂ ግድያዎችን እንዲሁም የንብረት ውድመትና ዝርፊያ ፈፅሟል፤ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ ለረሀብና ለበሽታ ዳርጓል። ቡድኑ ይህን ሁሉ ግፍ እየፈፀመም እነዚህ ምዕራባውያን መንግሥታትና ተቋማት ውግንናቸውን ለዚሁ ቡድን አድርገዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተስተዋሉ ያሉት የእነዚህ አካላት ተፅዕኖዎች ከመገናኛ ብዙኃን የውንጀላ ዘመቻዎች የተሻገሩ ሆነዋል። የማዕቀብ ማስፈራሪያዎችንና የብድርና እርዳታ ክልከላዎችን በአማራጭነት ለመጠቀም እየዛቱ ነው። በሌላ በኩል አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ አገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ እያሳሰቡ ነው። ‹‹ … አማፂያኑ አዲስ አበባን ስለከበቡ የከተማዋ ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል … ›› የሚል ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ወሬ በማራገብ በከተማዋ የሚኖሩ የውጭ አገራት ዜጎችን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያውያንን እያሸበሩ ነው።
CNN የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ያደረገው ደግሞ ከሁሉም የተለየና እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው። ጣቢያው ከወራት በፊት ከሌላ ጽሑፍ ጋር ተያይዞ የተለጠፈን ፎቶ በመውሰድ ‹‹የአማፂያኑ ወታደሮች በአዲስ አበባ ዙሪያ ይታያሉ›› ብሎ ዜና መስራቱ ከማስገረም አልፎ በጣም የሚያስቅም ነው። ምንም እንኳ የምዕራብ መገናኛ ብዙኃን የየመንግሥቶቻቸውን አጀንዳ አስፈፃሚዎችና ገንዘብ ለከፈላቸው ሁሉ ጯሂ እንደሆኑ ባይካድም አንድ ‹‹አክቲቪስት›› እንኳ የማይሰራውን ስህተት መፈፀማቸው በጣም ግራ ያጋባል። ከሁሉም በላይ መሰል ስህተቶች በCNN ተሰርተው መታየታቸው በእጅጉ ያስገርማል።
እነዚህ መንግሥታትና ተቋማት ከእውነት የራቁ ነገሮችን እያወሩ ጫና የሚፈጥሩባቸው ምክንያቶች አሏቸው። ከእነዚህም መካከል አንዱ ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር በሚደረገው ውጊያ ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ እንዳያደርግ በማዘናጋትና ተስፋ በማስቆረጥ የእነዚህ መንግሥታት ሸሪኮች የሆኑት አሸባሪዎች ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ለማመቻቸት ነው። ይህ ድርጊታቸው ደግሞ የሌሎች አገራትን ሉዓላዊነት ከማያከብረው የብሔራዊ ጥቅማቸው እሳቤ ይመነጫል።
የሕግ የማስከበር እርምጃው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለጉዳዩ የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ነው። ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ (እንዲኖረው) ከማድረጉ ባሻገር የኢትዮጵያ ጠላቶች ‹‹ኢትዮጵያን ለመበታተን ከዚህ የተሻለ ጊዜ/እድል አናገኝም›› ብለው ታጥቀው እንዲነሱና በረጅም ጊዜ ታሪኳ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን፤ ከኃይል ይልቅ ንግግርን ለማስቀደም እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ትብብርንና ወንድማማችነትን የሚያሰፍኑ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲመሰረቱና እንዲጠነክሩ ባላት ቁርጠኛ አቋም የምትታወቀው ኢትዮጵያ ስሟ እንዲጠለሽ ምክንያት ሆኗል።
አሜሪካና አጋሮቿ ፖለቲካዊ ትርፋቸውን አስልተው ከአሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት ጎን መቆማቸው ብዙም የሚያስገርም እንዳልሆነ ይታወቃል። ይህ ፖለቲካዊ ትርፍን ያገናዘበ እሳቤ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ዳርጓታል። የውሸት መረጃዎች እውነተኛ ተደርገው ተቆጥረው አገሪቱ ከገጽታ ግንባታ ጀምሮ በሌሎች ዘርፈ ብዙ መስኮች ቀላል የማይባሉ ኪሳራዎችን እንድታስተናግድም ተገዳለች።
በሕግ ማስከበር እርምጃው ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ተበታትኖ ለሞት፣ ለምርኮና ለሽሽት የተዳረገውን የወዳጃቸውን የቡድኑን ውድቀት አምኖ መቀበል ያቃታቸው ብዙ ምዕራባውያን መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ ጋዜጠኞች፣ ተንታኝ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተብዬዎች ለትዝብት የዳረጉ ዘመቻዎችን በኢትዮጵያ ላይ ከፍተው ቆይተዋል። ‹‹ውሻ በበላበት ይጮሃል›› እንዲሉ አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት የኢትዮጵያ አድራጊ ፈጣሪ በሆነበት ወቅት የኢትዮጵያን ሀብት እንዳሻቸው እንዲዘርፉት የፈቀደላቸውና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘረፈው ገንዘብ እየመዥረጠ ያጎረሳቸው መንግሥታት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች (ውለታቸውን ለመመለስ አልያም ወዳጃቸውን ከሞት አስነስተው በድጋሚ ኢትዮጵያን ለመዝረፍ በማሰብ) ሐሰተኛና የጥላቻ መረጃዎችን፣ ወገንተኛ መግለጫዎችን እንዲሁም አሳፋሪ የክህደት ሪፖርቶችን በማሰራጨት ላይ ተጠም ደዋል።
አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ባሉ አጋሮቹ በኩል አገሪቱ ልትበታተን እንደሆነ የሚያውጁ በርካታ የውሸት መረጃዎች እንዲሰራጩ አድርጓል። እነዚህን መረጃዎች ያዳመጡና የተመለከቱ ብዙ የውጭ አገራት ሰዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ መረጃዎቹን እንደወረዱ በመቀበል እንዲሁም ቡድኑ ‹‹ጥቅማችንን ያስጠብቅልናል›› ከሚለው እሳቤያቸው አንፃር ከእውነት የራቀ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ተስተውለዋል።
በሌላ በኩል አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፣ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተማራማሪ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ወዳጆችን አፍርቷል። እነዚህ ሰዎች ያልተደረገውን ነገር እንደተደረገ አድርገው የ‹‹በሬ ወለደ›› ውሸት በማሰራጨት ወዳጃቸውን ከሞት አትርፈው ወደ መንበሩ ለመመለስ ሲታትሩ ከርመዋል።
እነዚህ መገናኛ ብዙኃንና ‹‹የሰብዓዊ መብት ተሟጋች›› የሚባሉ ‹‹አክቲቪስቶች›› በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከሕ.ወ.ሓ.ት ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ፀብ አለን›› የሚሉ፣ ራሳቸውን አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ዲፕሎማት፤ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፤ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተመራማሪ ብለው የሾሙና በዚሁ ጭምብል የሚንቀሳቀሱ ጥራዝ ነጠቅ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አምባሳደሮች ናቸው።
የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች እጅግ አሳዛኝም አሳፋሪም ናቸው። የአገራችን ሰው ‹‹ነጭ ውሸት›› እንደሚለው ዓይነት መረጃ እያሰራጩ ነው። የእነዚህ ‹‹መገናኛ ብዙኃን›› የሐሰት ፕሮፓጋንዳና ውንጀላ ጠቅለል ያለ ምክንያት ‹‹አፍቅሮተ- ሕወሓት›› ወይም ‹‹ፀረ-ኢትዮጵያዊነት›› ነው።
ምዕራባውያን መንግሥታትና ተቋሞቻቸው (መገናኛ ብዙኃኑን ጨምሮ) መርጦ አልቃሽ/ወገንተኛ ብቻ አይደሉም፤ውሸታሞችም ናቸው። ያልተደረገውን ነገር እንደተደረገ፤ ያልተባለውን ነገር እንደተባለ አድርገው ዜና በመስራትም የተካኑ የውሸት ቋቶች ናቸው። ‹‹የጋዜጠኝነት መርህ ፈጣሪዎች ነን›› ብለው የሚመፃደቁለት ወሬያቸው ከንቱ ቀረርቶና አስመሳይነት እንጂ እንደሚጮሁለት የእውነት መግለጫ አይደለም።
በእርግጥ ለምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን፣ መንግሥታትና ተቋማት ‹‹እውነት›› ማለት ብሔራዊ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ነው። የሌሎች አገራት ዜጎች የመብት ጥሰት፣ ረሀብ፣ አፈናና ግድያ ጉዳያቸው እንዳልሆነ ደግመን ደጋግመን አይተናል። ይህን ሴረኛ ስልታቸውን በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና በደርግ መንግሥታት ዘመንም ሰርተውበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት እንዲሁም የውጭ መንግሥታት የራሳቸው ዓላማ አላቸው። እነዚህ አካላት በሌሎች አገራት የሚፈጠሩ ክስተቶችን የሚመለከቱትና ብያኔ የሚሰጡት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ሁኔታም የሚመዝኑት ዓላማቸውንና ጥቅማቸውን መሠረት አድርገው ነው። ምዕራባውያን አገራትም ሆኑ ለመንግሥታቱ ቅርብ የሆኑት መገናኛ ብዙኃን ሰብዓዊነት፣ እውነት፣ የጋዜጠኝነት መርህ … የሚባሉትን ነገሮች ፈፅሞ አያውቋቸውም። ለእነዚህ አካላት ሰብዓዊነት፣ እውነት፣ የጋዜጠኝነት መርህ … ማለት የተቋማቸውና የመንግሥቶቻቸው ጥቅምና አቋም እንጂ በመርህ የሚነገሩት የጽንሰ ሃሳቦቹ ትክክለኛ ትርጉም አይደለም።
ከዚህ ቀደም የነበሩትን ብንረሳቸው እንኳ ያለፉት ጥቂት ሳምንታት የሰብዓዊነት፣ የጋዜጠኝነት መርህና የእውነት ጠበቃ እንደሆኑ የሚያወሩት ምዕራባውያን ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና መንግሥታት ከሰብዓዊነት፣ ከእውነትና ከጋዜጠኝነት መርሆች ጋር ፈፅሞ እንደማይተዋወቁና ዓይናቸውን በጨው ያጠቡ ከሃዲዎች፣ ውሸታሞችና ወገንተኞች እንደሆኑ በግልጽ ያረጋገጥንባቸው ወቅቶች ናቸው።
ምዕራባውያን መንግሥታትና ተቋሞቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥሩትን ጫና አጠናክረው መቀጠላቸው አይቀርም። ስለሆነም እያንዳንዱን ጉዳይ በብልሃትና በጽናት መያዝ ይገባል። እየታየ ያለው የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መረን የለቀቀ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ የዓለም ፖለቲካን፣ በተለይም ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን፣ የመረዳት ችሎታችንንና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያለን አቅም ያመላከተ በመሆኑ ጉዳዩ የሁሉንም አገር ወዳድ ወገን አስቸኳይ ተሳትፎና ትጋት ይፈልጋል! ከሁሉም በላይ አስተማማኙ መፍትሔ ደግሞ በተባበረ አንድነትና በቆራጥ አመራር ጦርነቱን በድል ማጠናቀቅ ብቻ ነው።
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/2014