ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ደህና ናችሁ? ትምህርቱስ እንዴት ይዟችኋል፣ እያሸነፋችሁት ነው፣ ወይስ እሱ እያሸነፋችሁ? አይ፣ ጨዋታው በእናንተ መሪነት እንደሚጠናቀቅ የታወቀ ነውና ምንም አያሳስብም።
ልጆች፣ ትምህርት ቤት ከተከፈተ’ኮ ትናንትና ልክ አንድ ወሩ፤ ጥቅምት 2 አይደል የተከፈተው? አቤት ቀኑ እንዴት ይሮጣል?? በዚህ አይነት እኮ ምንም ሳናስበው ሰኔም ከተፍ ሊል ነው ማለት ነው። ኦኦኦ … ልጆች ጊዜው እንዴት እንደሚሮጥ አያችሁ አይደል? አዎ፣ በጣም ይበራል። ስለዚህ ሁሉንም የትምህርት ነገር ከወዲሁ መጀመር፣ ጀምሮም ጠበቅ አድርጎ መያዝ ይሻላል። አይሻልም ልጆች?
ሰኔ ለተማሪዎች ልዩ ነው፤ የትምህርት ቤት መዝጊያ ጊዜ ነው። የማለፍ ብስራት፣ የመውደቅ መርዶ የሚሰማበት ወር ነው። ለሁለት ወርም ቢሆን፣ ከጓደኛሞች የመለያያ ጊዜ ስለሆን ቅር የምንሰኝበት ጊዜ ወዘተ … ነው። በመሆኑም “ሰኔ” ሲባል ብዙ ነገር ትዝ ይለናል።
ልጆች ዛሬ የምንነጋገረው ሰኔ ደርሶብን ሳያበሳጨን እኛ ከወዲሁ ተዘጋጅተን ሰኔን በደስታ እንድንቀበለው ስለ ማድረግ ነው። አዎ ልጆች፣ ስለ ጥናት ነው ዛሬ የምናወራው፤ ስለ አጠናን ዘዴ።
ልጆች መቸም በትምህርት ውጤታማ የመሆኛው ቁልፍ ተግባር ጥናት መሆኑን ታውቃላችሁ አይደል? በጣም ጥሩ፣ በትምህርት ውጤታማ የመሆኛው ቁልፍ ተግባር ጥናት ነው።
እናንተ ጎበዝ ስለሆናችሁ የጥናትን ጥቅም በሚገባ ታውቁታላችሁ። ጥናት “የአጠናን ዘዴ” የሚባል አሰራር እንዳለውም ታውቃላችሁ አይደል ልጆች? በጣም ጥሩ ልጆች፣ እኔም ለማስታወስ ያህል ለዛሬ “በጥናት ወቅት ሊደረጉ የሚገባቸው”ን ክንውኖች ይዤላችሁ ቀርቤአለሁና ተከታተሉኝ።
ልጆች በማንኛውን ተግባር ተግባሩን ለማከናወን የመጀመሪያው ጉዳይ ዝግጁነት ነው። አይደለም እንዴ? አዎ “ዝግጁነት” ነው!!! እናንተም በመጀመሪያ ደረጃ እራሳችሁን ለጥናት ዝግጁ ማድረግ አለባችሁ። ዝግጁነት ደግሞ ለጥናት አስፈላጊ የሆኑትን ቁሶች ሁሉ ዝግጁ፣ የጥናት አካባቢን ምቹ ከማድረግና አእምሮን ማዘጋጀትን ሁሉ ስለሚያካትት በዚህ መልኩ ለጥናት ትዘጋጃላችሁ ማለት ነው።
ልጆች፣ መዘጋጀት (ዝግጅት) ተለዋጭ እቅዶችን ሁሉ እንደሚመለከት ከዚህ በፊት ተነጋግረናል እንዴ? ካልተነጋገርን ዛሬ በመጠኑ እነግራችሁና ሌላ ጊዜ ደግሞ በሚገባ እንነጋገርበታለን።
ልጆች ዝግጅት በተለዋጭ የሚከናወኑ ተግባራትን ሁሉ ይመለከታል። እንደምታውቁት አብዛኛው ነገር አስተማማኝ አይደለም። ለምሳሌ መብራት ሊጠፋ ይችላል። ታዲያ ትተኛላችህ? ያ ደግሞ አይሆንም። ስለዚህ መብራት ቢጠፋ መብራትን ሊተካ የሚችል ሌላ የሚበራ ነገር (ለምሳሌ ሻማ) ማዘጋጀት አለባችሁ። ኮምፒውተር ቢበላሽ፣ ስክሪፕቶ አልጽፍም ቢል ወዘተ እነዚህ ሁሉ ተለዋጭ የሚፈልጉ ናቸውና “ዝግጅት” ስንል እነዚህንም ማሰብ ያስፈልጋል ለማለት ነው። እሺ ልጆች!!!
ልጆች ልብ በሉ፤ ሁሌም ቢሆን የምታጠኑበት ስፍራ ምቾት ሊሰጣችሁና ትኩረት ለማድረግ የሚረዳችሁ ሊሆን ይገባል። ከጥናት ጋር አብረው ከማይሄዱ ነገሮች ሁሉ መራቅ እንደሚገባ አስተማሪያችሁ እንደሚነግሯችሁ እርግጠኛ ነኝ። በዛ መሰረት ለማጥናት ጥረት አድርጉ።
ሌላው ደግሞ በእቅድ መመራት ነው። ይሄንን ታውቃላችሁ አይደል ልጆች? እኔም አንድ ጊዜ በዚሁ ቦታ ላይ ጽፌላችሁ ነበር እኮ? አስታወሳችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች፣ በጣም ጥሩ!!!
አያችሁ ልጆች ለማንኛውም ነገር “እቅድ” ያስፈልጋል። የትኛው መጀመሪያ መሆን እንዳለበት፣ ቀጥሎ ደግሞ ሂሳብ ነው ወይስ እንግሊዝኛ? እነዚህን በሚገባ በመለየት በእቅድ ማጥናት፣ በእቅድ መስራት፣ በእቅድ መመራት አለባችሁ። ይህንን ካደረጋችሁ ሰኔ ሲመጣ የማለፍን ብስራት እንጂ የመውደቅን መርዶ አትሰሙም፤ እሺ ልጆች።
ከዚህ በፊት ስለ ልምድ ሲወራ ሰምታችኋል? ወይም ተጽፎ አንብባችኋል? ጥሩ፤ አንድን ተግባር በሚገባ ለማከናወን ጥሩ ወይም የካበተ ልምድ ያስፈልጋል። “ልምድ” ደግሞ የሚዳብረው ከእለት ተእለት ተግባር ነው። በመሆኑም ልጆች ማጥናትን፣ ማንበብንና መጻፍን፤ ያልገባችሁን መጠየቅን፣ የገባችሁን መመለስን እና የመሳሰሉትን ተግባራት ማከናወንን ልምዳችሁ ለማድረግ ሞክሩ። ይህን ካደረጋችሁ፣ በቃ እናንተ ጎበዝ ተማሪ ናችሁ ማለት ነውና በጣም ደስ ይላል።
ሌላውና የማጥናት ፍላጎታችሁን የሚያድሰውና ለማጥናት ጉልበት የሚሰጣችሁ ነገር ቢኖር “እረፍት” ነው። ለትኩረትም ሆነ ለመንፈስ እድሳት አጭር እረፍት መውሰድ ጥቅም አለው። ልጆች በየመሀሉ፣ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ አጠር ያለ እረፍት ማድረግን አትርሱ።
ሰአት፣ ቀን መቁጠሪያና የመሳሰሉትም አጠገባችሁ ቢኖሩ ይጠቅማችኋልና በጣም ጥሩ ነው። ለእንቅልፍ የሚያመቻቹ ነገሮችን አትጠቀሙ።
በመጨረሻ ልነግራችሁ የምፈልገው “ዝርዝር የስራ እቅድ” (check list የምትሉት ማለቴ ነው) ሊኖራችሁ የሚገባ መሆኑን ነው። አዎ፣ ይህ ቀላል የሚመስል ግን ደግሞ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው ልጆች። በመጀመሪያ ልትሠሯቸው የሚገቡትን መሠራት ባለባቸው ቅደም ተከተላቸው መሰረት ፃፏቸው። በምትሰሩበት ወቅት ደግሞ “እሰራቸዋለሁ” ካላችኋቸው መካከል የሰራችኋቸውን (ያጠናቀቃችሁትን) ከፊት ለፊቱ ምልክት (የ”ራይት” ምልክትም ሊሆን ይችላል) አድርጉባቸው። በኋላ የተሰራውን ካልተሰራው፤ የቀረም ካለ ለመለየትና እንደገና ለመስራት ይጠቅማችኋልና ይህን ማድረግ እንዳትረሱ። እሺ ልጆች። የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች!!!
ልጆች እነዚህንና ሌሎች ለጥናት የሚያገለግሉ ተግባራትን ካከናወናችሁ ጎበዝ ተማሪ ከመሆናችሁም በላይ ሰኔ ላይ ከማለፍም ባለፈ ተሸላሚ ትሆናላችሁና በርቱ ልጆች። ለማለፉም ሆነ ለመሸለሙ ደግሞ ስራው መጀመር ያለበት ከአሁን ጀምሮ ነውና እንዳትዘናጉ።
ሳምንት በሌላ ርእስ እንገናኛለን፤ መልካም የትምህርትና መማር ሳምንት ልጆች!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 5/2014