ሕይወት የወደቁትን እያነሱ ያዘኑትን እያጽናኑ ከምንዱባን ጋር፣ ከተናቁት ጎን መቆም ነው። ተስፋ ካጡት ጋር ሕብረት ፈጥሮ መጓዝ ነው። ያኔ ሃሳባችን እውን ይሆናል፤ ያቀድነው ይሳካል። ያኔ የምንፈልገው ነገር የእኛ ሆኖ እናገኘዋለንም። ብዙዎቻችን በዓለም ታሪክ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ የሌለን በሌሎች ታላቅነት ውስጥ ተደብቀን ያለን ስለሆንን ነው። እናም ሕይወት ማለት ዋጋችንን፣ ጸጋችንን አውቀን ለሌሎች ማሳወቅ ስንችልና እነርሱ ሲኖሩበት የሚታይ ነው።
ሕይወት ለምን ሰው እንደሆንን የምንረዳበትም ነው። ምክንያቱም ሰውነቱን ያልተረዳ ሰው ለራሱም ሆነ ለአገሩ የሚፈጥረው አንዳች ጥቅም የለም። እናም መኖር መተንፈስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ነፍስ መዝራት እንደሆነ አውቆ ሕይወትን ማጣጣም ያስፈልጋል። ይህንን እያደረጉ ያሉ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በርካታ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ለዛሬ የ‹‹ሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ ያደረግናቸው ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው አንዱ ሲሆኑ፤ ስኬታቸውን የሚለኩት አገራቸውን በጠቀሙበት ልክ ነው። ስኬታችን መልካምነት ውስጥ ያለ ስንዴም እንደሆነ ያምናሉና ያንን በማድረጋቸው ብዙዎች እንዲከተሏቸው መንገድ የጠረጉና አርአያነታቸውን ያስቀጠሉም ናቸው። እናም ይህንን ተሞክሯቸውን ትቃርሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።
የአገር ልጅነት
በእነፕሮፌሰር ቤት የአገር ልጅነት የሚታየው እንደ ምግብና መጠጥ ነው። አገር ከሌለች ባንዲራ ከወደቀች መኖሪያም መብያም የለም ተብሎ መናገር ብቻ ሳይሆን መኖርም ግድ ነው። ስለ አገር ተደጋግሞ ይወሳል፤ ስለባንዲራ ክብር የሁልጊዜ የመክፈቻ መዝሙራቸው ነው። እናም በአደጉበት የልጅነት ሁኔታ ውስጥ ይህንን እየተረዱና እየኖሩት ነው ያሳለፉት። ለዚህ ደግሞ መሰረት የሆናቸው አባትና እናታቸው እንደሆኑ ያስረዳሉ። አባት አገረ ገዢ ከመሆናቸውም በላይ በሕግ ትምህርት የታወቁ ሲሆኑ፤ ጣሊያን ዘምተው የመጡ ናቸው። በዚያ ላይ እርሳቸው የተወለዱበት ጊዜ ጣሊያን ከተባረረ 15 ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ እንደ አዲስ የአገራቸውን ጀግንነት መስማት ችለዋል።
ወሬው ሁሉ ራሷን ያስከበረች አገር፣ ነጭን የረታች አገር የሚለው ነበር። ስለዚህም ተወልደው በአደጉባት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በምትገኘው ደብረብርሃን ከተማ ይህ ድምጽ ለእርሳቸው ወኔን ያላበሳቸውና ጀግኖችን እንዲያከብሩ፣ አገራቸውንም እንዲወዱ ጽናትን የሰጣቸው እንደሆነ ይናገራሉ። በተመሳሳይ እናታቸው በየቀኑ የሚነግሯቸው የድል አድራጊነት ዜናም ከአገር ውጭ ማን ይመረጣል እንዲሉ አድርጓቸዋል። ውጭ አገር ሄደው ብዙ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ትተው የመጡትም ከዚህ የአስተዳደግ ግንባታ አንጻር እንደሆነም ያስታውሳሉ።
ፕሮፌሰር ዳንኤል በ1948 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን፤ በአባታቸው ሥራ ምክንያት አንድ ቦታ ላይ እድገታቸውን ማድረግ ያልቻሉ ናቸው። በዚህም ወለጋ ውስጥ የምትገኘው ሆሮ ጉዱሩን ጨምሮ ደብረብርሃን፣ ደብረሲና የእርሳቸው የልጅነት የእድገት ቦታ ናቸው። ብዙ ትዝታዎችን የሰነቁባቸው ቦታዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። በተለይ ወለጋ ላይ የተለየ ባህልና አኗኗር በመኖሩ ያንን እንዲለምዱ እድል የሰጣቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ስለዚህም ሆሮ ጉዱሩ የቋንቋ ቤቴ፣ የባህል ትምህርት ቤቴ፤ ጓደኞችን የሰጠችኝ መልካም ርስቴ ነበረችም ይላሉ።
እንግዳችን ከልጅነት ትዝታዎቻቸው ብዙ ነገሮችን የሚያስታውሱ ቢሆንም መቼም አይረሱኝም የሚሏቸው ግን ጥቂቶች ናቸው። የመጀመሪያው ማሕበረሰቡ ልጅን የሚያሳድግበት ሁኔታ ነው። በተለይም የአገር ፍቅር ላይ የሚሰሩት ሥራ ዛሬ ጭምር ማንም የሚያቆም ነው። ምክንያቱም በአገሩ የማይደራደር ትውልድ ፈጥረዋል። ክፍፍልም ቢሆን እንዲኖረው አላደረጉም። አንድ ልጅ የወለደው ብቻ ሳይሆን ኃላፊነቱ የሁሉም ነው። ይህ ደግሞ አንተ የእከሌ ዘር እንዳይል አድርጎታል። ጓደኝነቱም ያለ ልዩነት ሆኖ የቀጠለው ለዚህ ነው።
ቀደም ሲል የነበረ ጓደኝነት ዛሬም ድረስ የሚፈርስ አይደለም። አሁን በአለው ብሔርተኝነትም ውስጥ አይካተትም። ብሔርተኝነት የሚለውን ሃሳብም ለመደገፍ በጣም ይቸገራል። ወንድማማችነት እንጂ ጠላትነት ለእርሱ እንደማይጠቅመውም ስለሚያውቅ ኢትዮጵያዊነትን ያስቀድማል። ስለዚህም በዚያን ወቅት የነበረ ልጅነት አንድነት ምግቡና መጠለያው እንደሆነ የሚያምን ነው። በዚህም መቼም ብቻዬን የሚሉት ነገር እንዳይኖር አድርጓቸዋል።
ፕሮፌሰር ዳንኤል ሌላው ከልጅነታቸው የሚወዱትና አረሳውም የሚሉት ነገር የጀግንነት ታሪክ እየሰሙ ማደጋቸውን ነው። በዚህም ሰው በተለይም የአገሪቱን የጸጥታ ኃይል አጥብቀው እንዲወዱ ሆነዋል። ከመምህርነት ቀጥሎ የሚመኙት ሙያም ወታደር እንዲሆን ያደረገው ይህ መሆኑን አይዘነጉትም። በእርግጥ ለዚህ መሰረታቸው አባታቸው እንደሆኑ ያስረዳሉ። እርሳቸው የጣሊያን ዘማች ብቻ ሳይሆኑ የአገር ጠበቃም ናቸው። በዚህም ታሪክና ጀግንነት እንዲሁም አገር ወዳድነት ከልቦናቸው እንዲሰርጽና እንዳይጠፋ አድርገዋቸዋል። ሁልጊዜም እንደአባታቸው የአገር መከታ መሆን እንፈዲፈልጉ የሚያደርግ ስሜት የተፈጠረባቸውም ለዚህ ነው።
በልጅነታቸው የታህሳስ ግርግር ሳይቀር ልዩ ትዝታ የጣለባቸው ባለታሪካችን፤ በአውሮፕላን የተበተነው ወረቀትን አይተው የአካባቢው ሰዎች እነዚህ የሚበትኑት የአገር ከሀዲዎች ናቸው ሲሉ ሰምተው ከወረቀቱ እኩል እነርሱን ለማግኘትና ለመግደል የተሯሯጡትን መቼም አይረሱትም።
ፕሮፌሰር ዳንኤል ከስፖርት ጨዋታዎች ሁሉ የሚወዱት እግር ኳስ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜያቸውንም በዚያ ያሳልፋሉ። ከዚያ በተረፈ በቤት ውስጥ እያንዳንዱ ነገር በሰዓት የሚከናወን ስለነበር ጥናት ላይ ብዙ ይቆያሉ። የሚነሱትም በጠዋት ነው። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ እናታቸው ናቸው። እርሳቸው ዳዊት ደጋሚ ስለሆኑ በጠዋት ቀስቅሰዋቸው እንዲያጠኑ ያደርጓቸዋል። ይህ ደግሞ በትምህርታቸው ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ የደረጃ ተማሪ እንዲሆኑ አግዟቸዋል። የማንበብ ፍቅር እንዲኖራቸውም ረድቷቸዋል።
በባህሪያቸው ዝምተኛ እና እልኸኛ ናቸው። የእልሃቸው ምንጭ የጀመሩትን ከመጨረስ አኳያ ብቻም ላይ ይወሰናል። ሁልጊዜ ያሰቡትን ሳያሳኩ ወደኋላ አይሉም። ደጋግሞ መሞከርና መውደቅን ይወዱታል። በዚህም የአሰቡት ላይ ለመድረስ ችለዋል። መበለጥንም ቢሆን በፍጹም አይፈልጉትም። ስለዚህም ተወዳዳሪነታቸው በማሸነፍ እንዲጠናቀቅ ይፈልጋሉ፤ ይጠራሉም። ከዚህ ጋር ተያይዞም መምህራቸው ያላቸውን ለመተግበር ያደረጉት ነገር ዛሬ ድረስ ያስቃቸዋል። ይህም ሁሉም ነገር የሚሰራው ከአቶም ነው ሲላቸው ብልቃጥ አዘጋጅተው ሳርና ቁንዶ በርበሬን የመሰሉ በአካባቢው የሚያገኙዋቸውን እፅዋት ቀላቅለው ምንም አለማግኘታቸው ነው።
ከአጼ ዘርዓያቆብ እስከ ቱሪን
እንግዳችን የትምህርትን ሀሁ የጀመሩት በቄስ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ዳዊት መድገም ደርሰዋል። ትምህርቱን የወሰዱት በዚያው በትውልድ አካባቢያቸው ደብረሲና ላይ ሲሆን፤ ከየኔታ ገብረማርያም እግር ስር ቁጭ ብለው ነው። ከዚያ አባት ራቅ ወደአለ ቦታ ሲሄዱ የተቀረው ቤተሰብ ወደ ደብረብረሃን ከተማ ተመለሰ። በዚህም እርሳቸውም ሌላኛው የትምህርት ምዕራፋቸው ደብረብርሃን ላይ በአጼ ዘርዓያዕቆብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆነ። እስከ አምስተኛ ክፍል መጀመሪያ በትምህርት ቤቱ ቆይተዋል። አምስተኛ ክፍልን ያላጠናቀቁበት ምክንያት አባት ወደ ወለጋ ሻምቦ ሆሮ ጉዱሩ ወደ ምትባል ቦታ በመዛወራቸው የእርሳቸውም የትምህርት ጉዞ ወደዚያ በመሆኑ ነው። በዚህም ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሆነዋል።
አዲስ የሕይወት ምዕራፍን ያስጀመረኝና የመማር ጥቅሙን ያስረዳኝ ነው የሚሉትን ሌላኛው ትምህርት ቤታቸው ጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ 12ኛ ክፍል በዚያው በአዳሪ ተማሪነት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ይህንን ትምህርት ቤት ሕይወትን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ያስተማራቸው ብቻ ሳይሆን ነገን እንዴት ማየትም እንደሚቻል ያወቁበት እንደነበር ያነሳሉ። በምክንያትነት የሚጠቁሟቸውም ሦስት መሰረታዊ ነገሮችን ነው። የመጀመሪያው የሰዓትን ዋጋ ያወቁበት ሲሆን፤ እያንዳንዱ ተግባር በሰዓት የሚከናወንና ሰከንድ ማሳለፍ የማይቻልበት እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህንንም በማስረጃ ጭምር ያብራሩታል።
በዊንጌት ትምህርት ቤት የተለያየ ደውል በተለያየ ድምጽ አለ። በዚህም የምግቡን ብቻ ብናነሳ የመጀመሪያው ደውል ሲደወል ሰልፍ ውስጥ መግባት ግድ ነው። ከዚያ ሁለተኛው ደውል ሲደወል ምግብ ተጀምሮ መመገብ ውስጥ ይገባል። ይህንን ጊዜ የሌለ ሰው ሰልፍ ውስጥ መግባት አይችልም። ከዚያ በኋላ የሚመጣውን ተማሪ ተቆጣጣሪ አለቆች በወሰኑት ውሳኔ መሰረት የሚስተናገድ ይሆናል። እንደሁኔታው ቅጣት ተቀጥተው የሚበሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ብዙ ጊዜ ግን ረጅሙን ጊቢ ሁለት ጊዜ መሮጥ ዋናው ድካምና ባይበላስ የሚያስብል ነው። ነገር ግን ሙሉ ጾም መዋል አዳጋች ስለሚሆን የታዘዘን አለመፈጸም አይቻልም ይላሉ። ይህ ነገር ደግሞ በተደጋጋሚ ገጥሟቸው እንደሚያውቅ ያስታውሳሉ።
የሰዓት ጉዳይ በመብላትና አለመብላት ብቻ ሳይሆን በጥናትም እንዲሁ ይወሰናል። በፈተና በኩልም ብዙ ያሳጣን ነበር ይላሉ። ለዚህ አንድ ገጠመኛቸውን ያነሳሉ። ፈረንሳይኛ ፈተና ሲወስዱ ግማሹን እንደሠሩ ሰዓቱ አለቀ። በዚህም ከ20ው ዘጠኝ ነጥብ አምስት አገኙ። ስለዚህም በጣም አብሽቋቸው እንደነበር አይረሱትም። በዚያው ልክ የአገኙትን ጠቀሜታ መቼም አይዘነጉትም። ምክንያቱም ይቅርታ የሌለበት የሰዓት ጉዳይ ብዙ ነገር አስተምሯቸው አልፏልና።
ሁለተኛው ከትምህርት ቤቱ ተማርኩት የሚሉት ነገር በፕሮግራም መሥራትን ሲሆን፤ እያንዳንዱ ነገር ተግባራዊ ሲሆን በእቅድና በቅደም ተከተል ነው። እቅዱ ላይ ከሰፈረው ውጪ ምንም መከወን አይቻልም፤ አይፈቀድምም። በተለይም ትምህርታዊ ጉዳዮች ላይ ድርድር አይታወቅም። በዚህም ከጥናት ጀምሮ እስከ ሥራ የሚያከናውኑትን ተግባራት በፕሮግራም ይተገብራሉ። አሁንም የሥራ መርሃቸው አድርገው እየተገለገሉበት ይገኛል።
ሦስተኛው ተማርኩ ያሉን መውደቅ ቢኖርም ደጋግሞ መሞከርን ልምድ ማድረግን ነው። አሁን ድረስ ደጋግመው መሞከርን ልምዳቸው እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል። ውድድር ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው መሞከር አለበት። ከሞከረ ደግሞ ሁልጊዜ ስኬታማነት ሊኖረው አይችልምና ደጋግሞ ይወድቃል። ነገር ግን ተስፋ ካለው እንደሚነሳ ያምናል። ስለዚህም ስኬት ደጋግሞ ከመሞከርና ከመውደቅ በኋላ የሚመጣ እንደሆነ ይረዳል፤ ያደርገዋልም። እርሳቸውም የልቦና ውቅራቸውን በዚህ መልክ እንዲሠሩት መስመር ያስያዛቸው ይህ ትምህርት ቤት እንደሆነ ያስረዳሉ።
የዊንጌትን ውለታ በብዙ መልኩ የሚገልጹት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ የዚህ ትምህርት ቤት ቆይታቸው ሲጠናቀቅ በቀጥታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ነው የተቀላቀሉት። በዚያም ገብተው የመጀመሪያ ድጊሪያቸውን በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ተመርቀዋል። ከሁለት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ደግሞ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ጣሊያን አገር አመሩ። ‹‹ቱሪን ፖሊቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ›› ተብሎ በሚጠራ ትምህርት ቤትም ሁለተኛና ሦስተኛ ድጊሪያቸውን በኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ተከታተሉ። ከንድፈ ሃሳቡ ይልቅ የተግባር ትምህርት በስፋት በዚያው በጣሊያን አገር ላይ ስለሚሰጣቸውም በተመረቁበት የትምህርት መስክም በተለይም ኢንዱስትሪዎች ላይ ብዙ ልምድ ቀስመዋል።
የተለያዩ ሥልጠናዎችን በተለያዩ አገራት እየሄዱ ወስደዋልም። በአገራቸው ላይም ቢሆን ብዙ ሥልጠናዎችን በተለይም ከትምህርት መስካቸው ጋር
የሚገናኙትን እንዲያልፋቸው አይፈልጉም። ማስተማር በራሱ መማር ነው የሚሉት እንግዳችን፤ ሁልጊዜ በሥራ ላይ ቢሆኑም እየተማሩ እንዳሉ ይሰማቸዋልም። በሚሰሯቸው የምርምር ሥራዎችና ለትምህርት መማሪያነት በሚያዘጋጁዋቸው መማሪያ መጻሕፍት እንዲሁም በሚያነቧቸው መጻሕፍት አቅማቸውን ያጎለብታሉና ይህም የትምህርት ጉዟቸው እንደሆነ ያምናሉ።
ሥራን ማፍቀር
ወደ ሥራ ልምዳቸው ከመግባታችን በፊት የእርሳቸው ስብዕና ምን እንደሚመስል ከሥራ ወዳድነታቸው ጋር አያይዘው የሚያነሱትን ሃሳብ እንይ። ‹‹ለራሳችን እያሰብን ስለራሳችን ብቻ እየተጨነቅን በምንኖረው ሕይወት ውስጥ ስኬት አይኖርም። ስኬት የምትኖረው ለሌሎች ባሰብን ሰዓት፣ ለሌሎች መልካም በሆንን ቅጽበት ብቻ ነው›› እምነታቸው የሆነው ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ ሥራን ሲያነሱ ክፉ ሆነን፣ ሰርቀንና ቀምተን ወይም ደግሞ ባልተገባ መንገድ ሄደን የምንፈልገውን ሀብትና ዝና እንዲሁም ሥልጣንና ጌትነት ልናገኝ እንችላለን። ይህ ግን የላባችን ስላልሆነ በተለያየ መልኩ ዋጋ እንድንከፍልበት እንሆናለን ይላሉ።
ዘለዓለማዊ ደስታችን በላባችን እንጂ በሰው ችሮታ ሊሆን አይገባውም። እርሱ ጊዜያዊ ደስታን ከመስጠት አያልፍም። እንዲያውም መጥፊያችን ሊሆን ይችላል። ምክንያም በሳቃችን ማግስት ራሳችንን በከባድ ኀዘን ውስጥ ልናገኘው የምንችልበትን አጋጣሚ ይፈጥራል። ከእኛ ጋር ካለ ግን የእኛ ነውና ዘላለም አብሮን ይቀበራል። እናም ሰዎች ሥራን ሲወዱና ስኬታቸውን ሲያልሙ አብሮ ማደግን፤ ለአገር መሥራትን ማሰብ አለባቸው። ይህ ደግሞ ከዛሬ ቀጥሎ የሚመጣውን ነጋቸውን ያለምንም ተቀናቃኝ ያቀኑበታል፤ ያበሩበታልም ባይ ናቸው።
የእንግዳችን የሥራ ጅማሮ ያደረጉት የመጀመሪያ ዲጊሪያቸውን በሰሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ በኢንጅነሪንግ መምህርነት ያገለገሉበት ነው። ሁለት ዓመታትን መጀመሪያ ላይ አሳልፈውበታል። ከዚያ ከትምህርት መልስም እንዲያስተምሩበት ሆነዋል። በእርግጥ ይህ የመምህርነት ተግባራቸው ከመጀመሪያው የተለየ ነበር። ምክንያቱም የተመረቁበት የትምህርት መስክ ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ በመሆኑ በአገሪቱ የተለመደ ትምህርት ስላልነበር የተመረቁበትን ትምህርት ትተው ኢንዱስትሪያል ማኔጅመንት ኤንድ ኢንጅነሪንግ ኢኮኖሚክስ የሚባል የትምህርት መስክ ላይ እንዲያስተምሩ ተደርገዋል። ይሁንና ወደ ተማሩበት የትምህርት መስክ እያስጠጉ ነበር የሚያስተምሩት። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያታቸው መስኩ ለአገሪቱ እንደሚያስፈልግ ስለተረዱ ነው።
ዋናውን የተማሩበትን መስክ በዩኒቨርሲቲው ለማስጀመር ጎን ለጎን ማስተማሪያ መጻሕፍትን ያዘጋጁ የነበሩት ባለታሪካችን፤ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ደረጃ ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግን እንዲጀመር በማድረግ ደፋ ቀና ያሉ ናቸው። አስተማሪ ሳይኖረው ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ተቀብሎ ስለነበርም ቢያንስ በየ 15 ቀኑ እየተመላለሱ አስተምረዋል። የትምህርት መስኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲጊሪ እንዲጀመር አድርገዋልም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ባህርዳር መሄዳቸውን ጭምር ያስቀረላቸው እንደነበር ያነሳሉ። ምክንያቱም ብዙ የባህርዳር ተማሪዎች ሁለተኛ ዲጊሪያቸውን በዚህ በመከታተላቸው እነርሱ ተክተዋቸው እንዲያስተምሩ አግዟቸዋል።
ደካማ በሆንበት ጉዳይ ላይ ጠንክረን ካልሰራን ድልን አናገኝም የሚል እምነት ያላቸው እንግዳችን፤ ድክመትን አውቆ ጠንክሮ ካልተሰራ ስኬት ምኞት ብቻ ነው። ስለዚህም ለስኬታማነት መንደርደር ድክመትን ማወቅ ነው ይላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪግ ሦስተኛ ዲጊሪንም የማስጀመሩን ሥራ ወደማከናወኑ የገቡትም ለዚህ እንደሆነ ይናገራሉ። ምክንያቱም ሁለተኛና ሦስተኛ ዶጊሪ እያሉ ባያስተምሩና የተለያዩ የመማሪያ መጻሕፍትን ባያዘጋጁ ኖሮ በውጭ ተምረው የመጡት የትምህርት መስክ ውሃ ይበላው ነበር። በኢንዱስትሪው ዙሪያ የሚሠሩት ተግባራትም አይፈጠሩም ነበር። በዚህም የአገሪቱን ደካማ ጎን ከቅርብ ጀምረው ወደመሥራቱ ገቡ።
በአምስት ኪሎ ተማሪዎችን አስተምሮ ከማስመረቁም በላይ እንደ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ ካሉ ተቋማት ጋር በትብብር በመሥራት ለውጡ በፍጥነት እንዲመጣም አደረጉ። ይህ ደግሞ 42 ዓመታትን የዘለቀ ጉዞን በማስተማር ዙሪያ እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል።
እንግዳችን ሥራን በአገር ብቻ የሚወስኑ አይደሉም። ለዚህም ማሳያው ጣሊያን አገር ለትምህርት በሄዱበት እንኳን ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ከመሥራት አለመቆጠባቸው ነው። ጣሊያን ላይ ሆነው ያስተምራሉ፤ ልጆችን እንግሊዝኛ ያስጠናሉ። ከዚያም አለፍ ሲል ደግሞ በሚኖሩበት አካባቢ ፒዛ ቤት ነበርና ሠራተኞቹ ሲቀሩበት እንዲሠሩ ስለሚያደርጋቸው በማስተናገድ ሙያ ላይም ተሳትፈው ያውቃሉ። በትርፍ ጊዜያቸው ፋብሪካ ውስጥም ይሠሩ ነበር። ይህ ደግሞ ከአላቸው ብቃት አንጻር አትሂድ የፈለከውን ያህል እንክፈልህ ይሏቸው ነበር። ሆኖም የተሰጣቸው የአገር አደራ ስላለባቸው ማን እንደአገር ብለው ተመልሰው አገራቸውን ወደ ማገልገሉ ገቡ።
ሥራ ምርጫ ብቻ ሳይሆን ሌላ ልምድም መቅሰሚያ እንደሆነ የሚያስቡት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ በሥራቸው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን የተለያዩ የቦርድ አመራርነት ቦታዎችን በመያዝም በአገሪቱ ላይ ሰፊ ለውጥ እንዲታይ አስችለዋል። ከእነዚህ መካከል በሕወሓት እጅ ስር የነበሩና አይነኬ ተብለው የሚጠሩት እንዲሁም የአገሪቱን ሀብት ንብረት በብዙ ችግር ውስጥ የከተቱት እንደ ብረታብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽንንና የስኳር ኮርፖሬሽን ያሉ ተቋማት ውስጥ በመግባት ለውጡ ለውጥ እንዲመስል አድርገዋል። ብረታብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽንን በቦርድ ሰብሳቢነት ሲያገለግሉ፤ የስኳር ኮርፖሬሽንን ደግሞ በቦርድ አባልነት አገልግለውበታል። በዚህም ከገቡ ጀምሮ ብዙ ለውጦችም ማምጣት ችለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ውስጥ በቦርድ አባልነት ረጅም ዓመታትን በሥራ አሳልፈዋል። ከአስር ዓመት በላይ በኢትዮጵያ የደረጃዎች ምክር ቤት አባል በመሆንም አገልግለዋል። አሁንም በመስራት ላይ ይገኛሉ። በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከመስራችነት ጀምሮ በምህንድስና ዘርፉ ዛሬ ድረስ አስተዋጽጾ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ጠነሳሽና አሁንም በቦታው ላይ የሚፈለገውን ድጋፍ የሚያደርጉም ናቸው። በግሉ ኢኮኖሚ ላይም ሙያዊ አበርክቶ አላቸውም። ለአብነትም ኔካት ኢንጅነሪንግ ኮሌጅና ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ በብርሃን ባንክ ከባለድርሻነታቸው ባለፈ የባንኩ የመጀመሪያ ቦርድ ሰብሳቢ ነበሩም። በተጨማሪም በጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር ውስጥ የተተኪ አርበኛ አባል ናቸው። በተመሳሳይም በማሕበሩ ምክር ቤት ውስጥ በአባልነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
‹‹ሁለት ነገሮች ይቆጩኛል። የመጀመሪያው ታሪክን አለማወቄና አለማንበቤ ሲሆን፤ ሁለተኛው ከባላገር ከሚመጡ ሰዎች ጋር ቁጭ ብዬ አለማውራቴ ነው። ምክንያቱም ከእነርሱ ዘንድ የሚገኘው ስብዕና ብዙ ነገሮችን ይለውጣል።›› የሚሉት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ ይህንን ጥማቸውን ለማርካት ለአንባብያን የተለያዩ የመርጃ መጻሕፍትን ከማዘጋጀታቸው በላይ ለእውቀት የሚጠቅሙ እንደ እንሆ መንገድ … የሚል መጽሐፍ አይነት አዘጋጅተዋል። ከዚህ በተረፈ ፕሮፌሰሩ ቤታቸውም ገብተው አያርፉም። አምስት የንብ ቀፎዎችን በጊቢያቸው ውስጥ አኑረው በየዓመቱ ከራሳቸው አልፈው ለወዳጅ ዘመድ የሚተርፉበትን ሥራ ይሠራሉ። አትክልትና ፍራፍሬም ቢሆን ጊቢያቸው ሙሉ ነው። ስለዚህም በመስሪያ ቤት፣ በቤትም አትራፊ ሆነው ነው ኑሯቸውን የሚመሩት።
ሌላው ሥራቸውና እርሳቸውን በጣም ዛሬ ድረስ የሚያስደስታቸው ምንም እንኳን ፕሮግራሙ ቢቆምም አንድ የቴክኒክ ትምህርት ቤት መክፈታቸው ሲሆን፤ መንገድ ላይ ተቀምጠው የሚያዩዋቸውን ልጆች ለመሰብሰብ አስችሏቸዋል። ከመሰብሰብ አልፈው ተማሪዎቹ የራሳቸው ጌታ መሆን ስለቻሉ ውስጣቸው ይረካል። ተማሪን ማስተማር ብቻ ሳይሆን ለቁም ነገር ማብቃት ነው አስተማሪ የሚያስብለው። እናም እስካሁን ካደረኳቸው በበለጠ ይህንን ማድረጌ ውስጤን ሀሴት ይሞላዋልም ብለውናል።
በማንኛውም ጊዜ ለሚመጣ መንግሥት አንድ አይነት መልዕክት እንዳላቸው የሚናገሩት እንግዳችን፤ ማንኛውም መንግሥት ቢመጣ በአንድ ጀልባ ውስጥ ያደርገናል። ጀልባው ደግሞ እንክብካቤ ካልተደረገለት ይሸነቆራል። ከተሸነቆረ አብረን እንጠፋለን። ስለሆነም ተሸንቁሯል ብለን የምንተወው ነገር መኖር የለበትም። ራሳችንን ለማትረፍ ብለን ለጀልባዋ መኖር የበኩላችንን ማበርከት አለብን። ከዚህ አንጻር መንግሥትን የምንንከባከበውና የምናከብረው ለራሳችንና ለአገራችን ደሕንነት እንጂ ለእርሱ ሥልጣን ብለን አይደለም ባይ ናቸው።
ጀልባዋ የምትመሰለው በአገር ሲሆን፤ ይህቺ አገር የባለሥልጣናቱ ብቻ አይደለችም። እነከሌ ናቸው ይህንን ያደረጉት የሚባልባት ልትሆንም አትችልም። ካልተቀየሩ የሚለው እሳቤም አይሰራም። ከዚያ ይልቅ ከራስ የጀመረ ለውጥ በማሳየት አገር እንድታድግ ማድረጉ የእኛው እንደሆነ ማመንና መሥራት እንዳለብን ይናገራሉ። ኃላፊነት መቀበል የሚገባን ስለሠራነው ሳይሆን መሥራት ሲገባን ሳንሠራው ስለቀረነው ጭምር ነው። ከዚህ አንጻር ስለአገራችን የሚታየኝ አረንጓዴና ብሩህ ተስፋ ነውና እናስቀጥለው ይላሉ።
በስብሰባ መሪነታቸው አንቱታን ያተረፉት ባለታሪካችን፤ ማንም ባለሥልጣን ቢሆን ሰዓቱን ከጨረሰ አይታገሱትም። በምስጋና ብቻ ሲፈጅም ወደ ጉዳዩ እንዲገባ ይጠቁሙታል። ነገር ግን አሻፈረኝ ብሎ ሃሳቤን ካልጨረስኩ ካለ ያስቆሙታል። ይህ ደግሞ ብዙዎች በአርአያነት እንዲከተሏቸው አድርጓቸዋል። እርሳቸው ያሉበትን ስብሰባ ሁሉም ናፍቆ እንዲሰበሰብበት አድርገውታልም።
ውጤት እንጂ ክርክርና የማይጠቅሙ ወሬዎች በዚያ ቦታ ላይ እንዳይኖር በመደረጉ ስብሰባ የሚጠላ ሁሉ ስብሰባ ወዳድ ማድረግ እንደቻሉም የሚናገሩት እንግዳችን፤ ስለጮኸ ማንም ሰው መናገር የለበትም ብለው ያምናሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩና በተራ ሰራተኛው መካከል ልዩነት ሳይፈጥሩ በእኩል ደረጃ መስተናገድም ይገባዋል የሚሉና የሚተገብሩም ናቸው። ይህንን ሲያደርጉ ግን በጨዋ ደንብ ነው። ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ ብዙ ውሳኔ ለማስተላለፍና ቶሎ ውጤት ላይ ለመድረስ እንደሚያስችላቸውም አውግተውናል።
የሕይወት ፍልስፍና
እያንዳንዱ ልምድ በአንድ ጊዜ የሚመጣና የሚዳብር አይደለም። ፍላጎትና ተደጋጋሚ ሥራን ይጠይቃል። በተለይም ጊዜ ዋጋው በምንም የሚተመን አይደለም። ማንኛውም ሀብት ንብረት ቢጠፋ ለማግኘት ጊዜ ይፈጃል እንጂ ወደነበረበት መመለሱ አይቀርም። ጊዜ ግን ከአለፈ አለፈ ነው። ሳልሰራው እንጂ እሰራበታለሁ የሚባል አይደለም። የምንቆጭበት እንጂ የምንደሰትበትም ሊሆን አይችልም። እናም ለጊዜ የምንሰጠው ዋጋ ከሀብትም ከሥልጣንም በላይ መሆን አለበት የሚለው የመጀመሪያው አቋማቸው ነው።
ሌላው ፍልስፍናቸው የአንድ ሰው እድገት በአንድ ቀን የሚመጣ አይደለም የሚለው ሲሆን፤ ጊዜና አካባቢ እየለወጠ የሚያሳድገው በመሆኑ አካባቢን በመለወጥ ራስን ለውጥ ውስጥ ማካተትና አገርን ማሳደግ ይቻላል ብለው ያስባሉ። ውጪዎች የሚበልጡን የተቀየረ አዕምሮ ስላላቸው እንጂ በተፈጥሮ ስለታደሉ አይደለም። እኛ ደግሞ በተፈጥሮ ያገኘነው ብዙ ነገር ያለን ዜጎች በመሆናችን የአስተሳሰብ ለውጣችን ላይ እንደየዘመኑ እየዋጀን ብንመጣበት ማንም ሊደርስብን እንደማይችል ያምናሉ።
መልዕክት
የተማረው ማሕበረሰብ ከፊደል ባሻገር ስለአገሩ ጠንቅቆ የሚያውቅና ለአገሩ መሥራት የሚችል መሆን አለበት። ለሕዝቡና ለአገሩ ግድ ያለውና ሊደርስለት የሚገባ መሆንም ይጠበቅበታል። ስለሆነም የአዕምሮ መገዛትን ማስቆም ላይ መስራት ያስፈልጋል። ለዚህም ማሳያው ሀበሻ ሲሆን ለማመን እንቸገራለን። ፈረንጅ ግን ያንኑ ሲነግረን ትክክል እንደሆነ አምነን እንቀበለዋለን። እናም ይህንን ማስተካከል ከተማረው ዜጋ ይጠበቃል። ይህ ሲሆን ያለንን ምሁር መጠቀም እንችላለን፤ በመከባበርም አዲስ ነገሮችን መፍጠሩ ቀላል ይሆንልናል። ያን ጊዜ አገርን ወደማገልገሉ እንገባለን የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ሕዝብ ፈቅዶና ወዶ እንዲሁም ጊዜ ሰጥቶ የመረጠውን መሪን ማንም እየተነሳ ሲያቀለው ዝም ማለት የለበትም የሚለው ሲሆን፤ ከራሱ የጀመረ የማክበር ባህሪን ሊያሳይ ይገባል ይላሉ። እንደ አሜሪካ አይነት የአገር ጠላት ይህንን የሚያደርጉት መንግሥቱን ስለናቁ ሳይሆን ሕዝቡን ስለናቁ ነው። የራሳቸውን መንግሥትም ማስቀመጥ ስላልቻሉ ነው። እናም ማሕበረሰቡ ይህንን ተረድቶ መሪውንና አገሩን መደገፍ ላይ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን የኖርንበት ባህላችን ነው። አንድነታችን ኃይላችን እንደሆነ በአድዋ አይተነዋል። አሁንም ሁሉንም ለማሳፈር የምንችለው ዳግማዊ አድዋን በሕብረታችን ስንፈጥረው ነውና ሥጋ የሚበላው ወደ ሹሮ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሱሪ የሚለብሰው በቁምጣ እየሄደ ለወንድምና እህቶቹ መድረስ አለበት። የአገር አለኝታነቱን በሚችለው ሁሉ የሚያሳይበት ሰዓት ላይ ነውና ጊዜው እንዲሄድ አይፍቀድ ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ። መልዕከታቸው እውን ይሁን እያልን እኛም አበቃን። ሰላም፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ኅዳር 5/2014