በሽታዎችን መርምሮ ውጤታቸውን ለማግኘት ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግበአቶች ያስፈልጋሉ፡፡ የሰው ልጅ ያለበት በሽታ የሚታወቀውና መድኃኒት የሚታዘዝለትም በነዚሁ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶች አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ መሳሪያዎች ወሳኝ የህክምና ግበአቶች ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡
እነዚህ የበሽታ መመርመሪያ ግበአቶች ያላቸውን ጠቀሜታ ያህል ታዲያ በመንግሥትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ተደርጎባቸው ሲሰራ አይታይም፡፡ አብዛኛዎቹ ግበአቶችም የሚገቡት ከውጪ ሀገራት ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱን በየአመቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እያስወጣት ይገኛል፡፡
ከዚህ አኳያ ሀገሪቱ ያለባትን ክፍተት ለመሙላትና እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማርካት ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ፍላጎት እያቀረበ ያለውና በዚሁ ዘርፍም ከኢትዮጵያም ሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚው ዘ ኒው ሚሊኒየም ወርልድ ሜዲካል ዲቫይስ ማኒዩፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተጠቃሽ ነው፡፡
አቶ ተሾመ በየነ የዘ ኒው ሚሊኒየም ወርልድ ሜዲካል ዲቫይስ ማኒዩፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ቀደም ሲል ኩባንያው ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን ከውጪ ሀገራት በማስመጣት ለሀገር ውስጥ ገበያ ያቀርብ ነበር፡፡ ይሁንና ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ግብአቶቹን በሀገር ውስጥ ሲያመርት ቆይቷል፡፡ ባለፈው አመት ደግሞ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ቦታ ተሰጥቶት እነዚህኑ ግብአቶችን እያመረተ ይገኛል፡፡
ኩባንያው ሙሉ በሙሉ ከውጪ ሀገር የሚገቡትን ጥሬ እቃዎች ወደ 60 ከመቶ ዝቅ በማድረግና የሀገር ውስጥ ግበአቶችን 40 ከመቶ በመጠቀም ምርቶቹን አምርቶ ለገበያ እያረበ ሲሆን ከአንድ አመት በፊት የተወሰኑ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶች አካላትን በማምረት ውጤታማ መሆን ችሏል፡፡
ሆኖም መጀመሪያ ላይ እነዚህ ምርቶች በአብዛኛው ከውጪ ሀገር የሚገቡ በመሆናቸውና በትስስርም የሚሰሩ እንደመሆኑ ምርቶቹን አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ሂደት ከፍተኛ ችግር አጋጥሞት ነበር፡፡ ቀስ በቅስ ግን ወደገበያው ዘልቆ በመግባት ምርቶቹን በአብዛኛው ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ፣ በአስመጪነት ለተሰማሩ የግል ድርጅቶችና የንግድ ድርጅቶች እያቀረበ ይገኛል፡፡
በ46 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ስራውን የጀመረው ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 50 ሰራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ የሚገኝ ሲሆን በዚሁ የሰው ሃይሉ በአመት 137 ሚሊዮን 800 ሺ የመመርመሪያ ግብአት የማምረት አቅም አለው፡፡ ይህም መንግሥት የሚፈልገውን ምርት በበቂ ሁኔታ ለማሟላት ያስችለዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚው እንደሚሉት፤ ኩባንያው በአሁኑ ግዜ እያመረታቸው የሚገኙ ምርቶች አራት ሲሆኑ እነዚህም HCG /የእርግዝና መመርመሪያ መሳሪያ/፣ URS/ አስር የተለያዩ በሽታዎችን የሚገልፅ/፣ H.payroly Ag/ የጨጓራ መመርመሪያ/፣ እና H.payroia Ab / በደም የሚወሰድ ምርመራ/ ናቸው፡፡ በሂደት ላይ የሚገኙ የተለያዩ በሽታዎች መመርመሪያ መሳሪያ ግበአቶችም አሉት፡፡ ምርቶቹንም ከውጪ ከሚገባው ምርት ባነሰ ዋጋ ለገበያ ያቀርባል፡፡ እነዚህኑ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለመንግሥትም ሆነ ለግል ተቋማት የማቅረብ አቅምም ገንብቷል፡፡
ኩባንያው የአስር አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን በአቅዱ መሰረት በአምስት አመት ውስጥ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎች ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ እቅዱ ሲሳካም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት መንግሥት ለዘርፉ የሚያወጣውን የውጪ ምንዛሬ እንደሚያስቀር ተስፋ አሳድሯል፡፡ ምርቶቹንም ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘትም ውጥን ይዟል፡፡
ይህም በተለይ ኢትዮጵያ ከ AGOA ውጪ መሆኗ አይቀሬ ከሆነ የሀገር ውስጥ አምራቾች በመንግሥት በኩል ማበረታቻ ተደርጎላቸው ምርቶቻውን ወደተለያዩ የውጪ ሀገራት ሊልኩ የሚችሉበት እድል የሚመቻች ከሆነ ኩባንያውም በተመሳሳይ ምርቶቹን ወደውጪ ሀገራት በመላክ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የማስገኘት ውጥን አለው፡፡
ለዚህም ኩባንያው ምርቶቹን በስፋት ለማምረትና በተለይ ደግሞ የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ለማምረትና ወደውጪ ሀገር ለመላክ የሚያስችለውን ህንፃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በቅርቡ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ አስቀምጧል፡፡ ይህንኑ ግንባታም በሁለት ደረጃ ለማከናወን ከ509 ሚሊዮን ብር በላይ መድቧል፡፡
ግንባታውን አጠናቆ ወደማምረት ሲሸጋገርም ኩባንያው 495 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል በመፍጠር በዚሁ የሰው ሃይል በአመት ከ500 ሚሊዮን በላይ ፈጣን የበሽታ የመመርመሪያ ግብአቶችን የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህን ሥራ ሲሰራም በቀጣይ በአለም ገበያ በመግባትና የባዮቴክኖሎጂ ገበያን መሰረት አድርጎ እንደሀገር ትልቅ የገቢ ምንጭ ለመሆን ነው፡፡
በአሁኑ ግዜም ኩባንያው ሃምሳ ሰራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ የሚገኝ ሲሆን በዚሁ የሰው ሃይል በአመት 137 ሚሊዮን 800 ሺ ፈጣን የበሽታ የመመርመሪያ ግብአቶችን የማምረት አቅም አለው፡፡ በዚህ አቅሙም ኩባንያው መንግሥት የሚፈልገውን ግብአት ማቅረብ ይችላል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ኩባንያው በዚህ ዘርፍ ከኢትዮጵያም ሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ እንደመሆኑ መጠንና የግበብአቶቹን አስፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡ እነዚህ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ መሳሪያዎች እጅግ አስፈላጊና ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚወጣባቸው በመሆናቸው መንግሥት እነዚህ ግብአቶቹ በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱ ኩባንያውንም ሆነ በቀጣይ በዚሁ ግበአት ማምረት ስራ ላይ የሚሰማሩ ድርጅቶችን መደገፍ ይኖርበታል፡፡
ኩባንያው በባዮ-ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያም ሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ከመሆኑ አኳያም በተለይ ኢትዮጵያ በዚሁ ዘርፍ ራሷን እንድትችል ትልቅ ራእይና ግብ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዱካን ደበበ በኢቲቪ አራት መአዘን የዜና ሰአት ከሰሞኑ በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ 24 የሚሆኑ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚገኙና ሰባቱ የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የAGOA ውሳኔ በብዙ መልኩ እነዚህን የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች በብዙ መልኩ ተፅእኖ እንደማያሳድርባቸውም ገልፀዋል፡፡ በተለይ በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙና 120 የሚደርሱ የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች አብዛኛውን ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ፍላጎት የሚያቀርቡ በመሆናቸው ከ AGOA ጋር የሚያይዛቸው ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለም ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልል መንግሥታት የሚተዳደሩ የተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ከ AGOA ጋር በተመሳሳይ ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌላቸው ተፅእኖው አነስተኛ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አብራርተዋል።
ከ AGOA ጋር በተያያዘ እየተነሱ ያሉት ኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል ባስገነባቸው አስራ ሶስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ከአስራ ሶስቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አስሩ በጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት ላይ አተኩረው የሚሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከ100 በላይ ባለሀብት እንዳላቸውና ትላልቅ ኩባንያዎች እንደሚገኙባቸውም አብራርተዋል፡፡ የAGOA ውሳኔ ተፅእኖ የሚያሳድረውም በነዚሁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
AGOA ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ ገብተው እንዲያለሙ አንድ አማራጭ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ባለሀብቶች AGOAን ተጠቅመው ሙሉ በሙሉ ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ የሚልኩ፣ AGOA የማይመለከታቸውና ምሮቶቻቸውን ወደ አሜሪካ የማይልኩና ገበያ መር በሆነ ሁኔታ ምርቶቻቸውን የሚልኩ እንዳሉም አብራርተዋል፡፡ ይህ ውሳኔ ተፅእኖ ሊያሳድር የሚችለው ደግሞ የአሜሪካ ገበያ መሰረት አድርገው ምርቻቸውን የሚልኩትን ብቻ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስረድተዋል፡፡
ይሁንና AGOA ከታክስ ነፃ እድል ከመሆኑ አኳያ ኩባንያዎቹ ታክስ ጭምር ከፍለው ለአሜሪካ ገበያ ምርቶቻውን የሚያቀርቡበት አማራጭ በመኖሩ ፈፅሞ የተዘጋ እድል እንደሌለም አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አንድም ሰራተኛ በኩባንያዎቹ ምርት መቀነስና ሥራ መዘጋት ምክንያት AGOA ተፅእኖ እንዳይኖር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያን ከ AGOA ወይም ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ የማስገባት እድል ውጪ የማድረግ ውሳኔ ከፈረንጆቹ ጥር ወር 2021 ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ መንግሥት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ምርቶቻቸውን ወደ ሌሎች ውጪ ሀገራት በመላክ የውጪ ምንዛሬ እንዲያገስኙ ማበረታቻ ያደርጋል ተብሎም ይታሰባል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/2014