ኢትዮጵያ ቡና በዋናነት የምታመርተው ለዓለም ገበያ በማቅረብ ለውጭ ምንዛሪ ማግኛነት ቢሆንም ከምርቱ ከ 40 እስከ 45 በመቶ የሚሆነው ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚውል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ያመለክታል። ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበው ቡና መብዛት መልካም አጋጣሚ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የምጣኔ ሀብት ዘርፍ ተመራማሪ አቶ መሀመድ በሽር፤ ሀገሪቱ ቡናን በብዛት ለአገር ውስጥ ፍጆታ መጠቀሟ ቡና አምራች ከሆኑ አገራት ለየት እንደሚያደርጋት ይጠቅሱና ይህ ግን ወደ ውጭ አገር በሚላከው ምርትም ሆነ ኢኮኖሚውን ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም፡፡
የአገር ውስጥ ፍላጎት ከመጨመሩ በላይ ሀገሪቱን ሊያሳስባት የሚገባው የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ መዋዥቁ ነው ይላሉ፡፡ የዛሬ 10 እና 15 ዓመት የነበረው የቡና መሸጫ ዋጋ አይነት ዛሬ እንደሌለ በመጥቀስም፣ ‹‹ይህ ምናልባት በኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ ያሳርፍ ይሆናል እንጂ ቡና በብዛት በአገር ውስጥ መጠጣቱ የሚያሳስብና ኢኮኖሚውንም ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም›› ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹ከገቢ አንጻር ምናልባት ቡናው አገር ውስጥ መሸጡ ልዩነት ባይኖረውም አገሪቱ ታዳጊ ከመሆኗ እንዲሁም ለረጅም ዓመታት የውጭ ምንዛሪ ማግኛዋ ሆኖ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ ጉዳት የሚያስከትል ሊመስል ይችላል›› የሚሉት አቶ መሀመድ፣ ይህም ቢሆን አሁን ባለው የንግድ ሰንሰለት የአገር ውስጡ ፍላጎት በምንም መልኩ የውጪውን እንደማይገፋም ያመለክታሉ፡፡ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያትም ቡና ወደ ውጭ የሚላከው በህጋዊ መንገድ በምርት ገበያ በኩል የጥራት ደረጃው ተረጋግጦና ደረጃ ወጥቶለት መሆኑን ነው።
‹‹አንዳንድ ጊዜ የወጪ ንግዱን ትተነው የአገር ውስጥ ፍላጎትን እንደ መልካም አጋጣሚ መውሰዱ እንደ ቻይና ከመሆን ያድናል›› ያሉት አቶ መሀመድ « የቻይና እና የአሜሪካ የንግድ ባለሃብቶችም የግብር እፎይታ በመሰጠት፣ ምርቶቻቸው ደንበኞቻቸው ዘንድ እንዲደርሱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ከምርቶቻቸው ጋር የሚወዳደሩና ወደ ሃገር ውስጥ በሚገቡ የውጪ ምርቶች ላይ ከፍ ያለ ቀረጥ በመጣልና በተለያዩ መንገዶች የሃገር ውስጥ ምርቶች ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ ጆንሴ ይመክራሉ፡፡
የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ዋና አስተዳዳሪና የምጣኔ ሃብት ባለሞያው አቶ ክቡር ገና እንደሚሉት፤የሃገር ውስጥ ምርት ተፈላጊነትን ለማሳደግ የምርቱን ተፈላጊነት፣ ጥራቱንና ዋጋውን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ የሃገር ውስጥ ምርቶችን ፍላጎት ካማሳደግም ባሻገር የምርቱን አቅርቦት ለመጨመር በቂ ካፒታል ፣መሬትና የሰው ሃይል ማሟላትም ይገባል፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ተከታትለው የሚወጡና በሃገር ውስጥ ምርት ንግድ የተሰማሩ ወጣቶች በበቂ ሁኔታ እውቀት መያዛቸውም ሊፈተሽ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
እንደ አቶ ክቡር ገለፃ የሃገር ውስጥ አምራቾች ምርቶቻቸው በዋጋም በጥራትም በሸማቾች ዘንድ ተፈላጊ ሆነው የጥሬ እቃ እጥረት ወይም የማምረቻ ማሽን ችግር ቢያጋጥማቸው በመንግሥት በኩል ብድር ተመቻችቶ ምርቶቻቸውን በብዛት እንዲያመርቱ ድጋፍ ሊደርግላቸው ይገባል፡፡
ለአምራቾች እንቅፋት የሆኑ ደንብና መመሪያዎችን ማንሳት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰው፣መንግሥት በሃገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ጉዳቱና ጥቅሙን በማየት አምራቾች ቢያንስ ከውጪ ሃገር ብድር የሚገኝበትን መንገድ መንግሥት ማመቻቸት ይኖርበታል ይላሉ፡፡
የሃገር ውስጥ አምራቾች ምርቶቻቸውን ለገበያ በሚያወጡበት ጊዜ ከውጪ ሃገር ከሚመጡ ምርቶች ጋር መወዳደር ሳይችሉ ሲቀሩ ምርቶቻቸውን ለመሸጥ እንሚቸገሩ ጠቅሰው፣በዚህ ወቅት የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ነው አቶ ክቡር የሚናገሩት፡፡ የሃገሪቱን አቅም ለመገንባት ሲባል ከውጪ የሚመጡ እቃዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንዲሁም አምራቾች በተለያዩ ምክንያቶች ማምረታቸውን እንዳያቆሙ ስራቸውን ለማስፋፋትና በጥራት ለማቅረብ የሚያስችላቸውን የሰው ሃይል ስልጠና፣ የካፒታልና፣ ሌሎችም የቴክኖሎጂ ድጋፎችን በመንግሥት በኩል ማድረግ እንደሚገባ አቶ ክቡር ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የንግድ ትርኢትና ኩነት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ባዝግናወርቅ ወልደመድህን ‹‹የሃገር ውስጥ ምርቶች በርካታ ተጠቃሚ እንዲኖራቸው ካስፈለገ በሸማቱ ላይ ያለው የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡››ይላሉ፡፡
ዳይሬክተሯ የሃገሪቱ የንግድ ማህበረሰብ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲሸጋገር ትልቅ የቅስቃሳ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅም ጠቅሰው፣ነጋዴው ኅብረተሰብ በንግዱ ዘርፍ የሚያተርፈውን ያህል ከዛም በላይ በኢንዱስትሪ ሴክተሩ ሊያተርፍ እንደሚችል የማስተማር፣ የማሳወቅናመረጃዎችን የማቅረብ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ፡፡
ምክር ቤቱ፣ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ፣የመገናኛ ብዙኃን ከመንግሥት ጋር በመሆን ተከታታይነት ያለው የቅስቀሳ ሥራ መስራት እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ፡፡
አምራቾች ምርቶቻቸው በሸማቾች ዘንድ የበለጠ ተፈላጊ እንዲሆኑ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን አለባቸው የሚሉት ዳይሬክተሯ፤በዋጋና በጥራት የተሻሉ ምርቶችን ይዘው ቢቀርቡ ምርቶቻቸው የመሸጥ እድላቸው እንደሚሰፋ ያመለክታሉ፡፡ በሌላውም ሴክተር በተለይም በግብርና ምርት ማቀነባበር ላይ በእሴት ሰንሰለት ትልቅ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ፣የንግድ ማኅበረሰቡን ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲያዘነብል መረጃዎችን መስጠት እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡
በሀገሪቱ በትልልቅ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች እንዲሁም በጎዳናና በአዳባባዮች ላይ በሚዘጋጁ የንግድ ትርኢቶች ‹‹በሀገሬ ምርት እኮራለሁ››የሚሉ የአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ ምርቶችን በማህበራት አማካኝነት ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህም የሃገር ውስጥ ምርቶችን ለኅብረተሰቡ እንዲተዋወቁና ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል፡፡በንግድና የዘርፍ ምክር ቤት ኣማካኝነት ፖሊሲዎችን በመቅረፅና የቅስቀሳ ስራዎችን በመስራት ለንግዱ ማኅበረሰብ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሃገር ውስጥ ምርቶች ተቀባይነት እንዲኖራቸው ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
የሃገር ውስጥ ምርቶችን በቀጣይ ጥራት፣ዋጋና አቅርቦታቸውን ማሻሻል የሚቻል ከሆነ ተፈላጊነታቸውን ማሳደግ ይቻላል፡፡ በተለይም የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ሰፋፊ የማስተዋወቅና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ከተሰሩ የምርቶቹን ተፈላጊነት ይበልጥ ማሳደግ ይቻላል፡፡
በመንግሥት በኩልም ለአምራቾች ስልጠናዎችን መስጠት፣ የሃገር ውስጥ ምርቶች በውጪ ሃገር ምርቶች እንዳይዋጡ ከለላ ማድረግ፣ የምርቶችን አቅርቦት ለመጨመር በቂ ካፒታል፣መሬትና የሰው ሃይል ማሟላት፣ ለአምራቾች እንቅፋት የሆኑ ደንብና መመሪያዎችን ማንሳት ብሎም ከውጪ የሚመጡ እቃዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚቻል ከሆነ የምርቶቹን ተፈላጊነት ማሳደግ ያስችላል፡፡
እፀገነት አክሊሉ