የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም በመስቀል አደባባይ ተገኝተው ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡በተለይም ምዕራባውያን የሚያደርጉትን ጫና እና ሚዲያዎቻቸው የከፈቱትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ አውግዘዋል፡፡
በዚህ ሰልፍ ላይ በርካታ ወጣቶች ታድመዋል፡፡ወጣቶቹ የአሸባሪውን ቡድን ከልክ ያለፈ ኢሰብአዊ ድርጊትና የሀገር ክህደት፤ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩትን ጫና እያወገዙ ቁጣቸውን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከውጭና ከውስጥ ተቀናጅተው የሚሰሩ ኃይሎችን አደብ ማስገዛት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በላይ ወጣቱ ትውልድ አባቶቹ የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ያስረከቡትን ሀገር እርሱም ለመጪው ትውልድ ክብሯን አስጠብቆ የማስተላለፍ ሀገራዊ ግዴታ እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ለዚህም የመንግሥትን ጥሪ ተቀብሎ ሀገርን ከአደጋ መታደግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገራቸው ወጣቶች የሰጡትን አስተያየትና በእለቱ ለወጣቱ መልዕክት ያስተላለፉ የክብር እንግዶችን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
ወጣት ናሆም ኢሳያስ ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ፣ ኮልፌ ክፍለ ከተማ ነው፡፡የድጋፍ ሰልፉ ላይ ለመሳተፍ ማልዶ ወደ መስቀል አደባባይ መምጣቱን ይናገራል፡፡ወጣት ናሆሙ ኢትዮጵያን አሁን ከገጠማት ፈታና መታደግ የሚቻለው ሁሉም አንድ ሆኖ ሲቆም እንደሆነ ይገልጻል፡፡ከመቼውም በላይ ኢትዮጵያ ልጆቿን የምትፈልግበት ጊዜ ላይ እንደምትገኝ የሚገልጸው ናሆም፤ እያንዳንዱ ወጣት የእናት ሀገሩን ጥሪ ተቀብሎ የአባቶቹን አኩሪ ገድል በመድገም የሀገሩን ሉዓላዊነት ማስከበር ይጠበቅበታል ይላል፡፡
ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ተቀናጅተው ሊያፈርሷት እየሠሩ መሆኑን የተናገረው ናሆም፤ ወጣቱ አንድነቱን አጠናክሮ ጠላቶቿን ሊመክት ይገባል ብሏል፡፡እስከ ህይወት መስዋዕትነት ዋጋ ለመክፈል ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ገልጿል፡፡
ከሰሞኑ የኢትዮጵያን መንግሥት ስም ለማጠልሸት የተከፈተው የሚዲያ ዘመቻ እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ብሎ ሲያደራጅ መመልከቱ እንዳናደደው ተናግሯል፡፡ይህም ምእራባውያን በህዝብ የተመረጠ መንግሥትን አስወግደው አሻንጉሊት መንግሥት ሊያስቀምጡ መቋመጣቸውን የሚያሳይ ነው ብሏል፡፡
በተለይም ዓለማቀፍ ሚዲያዎች የሚያሰራጩት ከተራ የፌስ ቡክ ወሬ ያልዘለለ ሀሰተኛ መረጃ የአለም ማህበረሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝና ህዝብን ለማሸበር ጭምር ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡እንደ ናሆም አስተያየት መንግሥት በተለይም በዲጂታል ወያኔ የሚሰራጩትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች ከነአካቴው ለማጥፋት ለጊዜው የፌስ ቡክ አገልግሎትን ቢያቋርጥ የተሻለ መሆኑን ይናገራል፡፡
አዲስ የተመሰረተው መንግሥት የእድገትና የብልጽግና ራዕይ ይዞ መልካም ጅምሮችን እንዳሳየ የተናገረው ናሆም፤ ወጣቱ ከመንግሥት ጎን በመቆም የሀገሩን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ከአባቶቹ የተረከባትን ሀገር ከነሙሉ ክብሯ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ እንዳለበት ተናግሯል፡፡ለዚህም ወጣቱ ተደራጅቶ አካባቢውን ከመጠበቅ ጀምሮ መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ግዴታ ሊወጣ ይገባል ይላል፡፡
በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ከተማዋን ለማሸበር የተዘጋጁ ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጿል፡፡የእያንዳንዱን ሰው እንቅስቃሴ በንቃት መከታተልና መረጃዎችን ለሚመለከተው የጸጥታ አካል ማቅረብ ከወጣቱ የሚጠበቅ አንዱ ጉዳይ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ሌላዋ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ያገኘናት ወጣት ራህመት ማሬ ትባላለች፡፡ የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ነዋሪ ነች፡፡ ኢትዮጵያውያን የፍርሃት ታሪክ የለንም በሚል ንግግሯን ትጀምራለች፡፡አባቶቻችን ያለምንም ፍርሃት የነፍስ ዋጋ ከፍለው በክብር ያቆዩልንን ሀገር እኛም የነፍስ ዋጋ ከፍለን ለመጪው ትውልድ እናስረክባለን እንጂ አይናችን እያየ ኢትዮጵያ አትፈርስም ብላለች፡፡
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን 27 ዓመት ሙሉ የፈጸመው በደል አልበቃ ብሎት ዛሬም ጦርነት አውጆ ሀገሩን ይወጋል፤ ከውጭ ኃይሎች ጋር ተመሳጥሮ ያስወጋል ያለችው ራህመት ወጣቱ ይህንን ሴራ ለመቀልበስ ዘምቶ ደሙን በማፍሰስና ህይወቱን በመስጠት ሀገሩን ሊታደግ ይገባል ትላለች፡፡እርሷን ጨምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወጣት ጥሪውን ተቀብሎ ለሀገሩ የሚደርስላት አሁን እንደሆነ አጥብቃ ትናገራለች፡፡
ወጣቱ በግንባርም ይሁን በከተሞች አካባቢ የሰርጎ ገቦችን ጥቃት በመከላከል ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል በላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅበታል ብላለች፡፡
ሁሉም ነገር ከሀገር ሰላም እና ደህንነት አይበልጥም ያለችው ወጣቷ ሰርቶ ለመኖርም ይሁን ተምሮ አንድ ደረጃ ላይ ለመድረስ ወይም ትዳር መስርቶ መኖር የሚቻለው ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ሀገር ስትኖር እንደሆነ ገልጻለች፡፡በግንባር የሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንቅልፍ ካቆሙ ዓመት ማስቆጠራቸውን የተናገረችው ራህመት፤ በዚህ ወቅት ሃሳቡን ጥሎ የሚተኛ ወጣት ሊኖር አይገባም ትላለች፡፡
በዕለቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ካደረጉት ከፍተኛ ኃላፊዎች የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አንዷ ናቸው፡፡በንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬ ማልደን በመስቀል አደባባይ የተገኘነው ኢትዮጵያ ሀገራችን ላደረገችልን ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ሀገር ሰላም ከሌላት እኛ ሰላም የለንም፡፡ሀገር ከተደፈረች ህዝቦቿ ይደፈራሉ፡፡የሀገር ሉዓላዊነት ቀይ መስመሩ ከታለፈ ነጻነት፣ ፍትሐዊነትና ከብር አይኖረንም›› ብለዋል፡፡
የሀገርን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት ለማስከበር የዛሬውም ትውልድ ቆራጥ እንደሆነ የገለጹት ክብርት ከንቲባዋ፤ ይህን ለውጥ በማምጣት ሂደት ወጣቱ ዋጋ መክፈሉን አስታውሰዋል፡፡
ከባለፉት ሦስት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ወጣቶች ኢፍትሐዊነትን፣ ጭቆናን፣ በብሔር ማንነት የሚደረግ ልዩነትን አንደግፍም፤ አንሸከምም፤ በጋራ ሆነን ሀገራችንን መለወጥ እንሻለን ብለው ትግል አድርገዋል ብለዋል፡፡ከስናይፐር፣ ከድሽቃና ከመድፍ ፊት ቆመው ለውጥ ማምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡በርካታ ወጣቶች መስዋዕትነት ከፍለው የነጻነት ቀንን እንዳመጡ ገልጸዋል፡፡ይህንን በመስዋዕትነት የተገኘ ነጻነት ሊነጥቅ የሚፈልግ ማንኛውንም ኃይል ወጣቱ አሁንም የተለመደ ትግሉን በማድረግ ሊመክት ይገባል ብለዋል፡፡
የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ትናንት ያደረገው ጥፋት ሳያንሰው ዛሬ የለውጥ ምዕራፍ በጀመርንበት ማግስት እኩልነትን አልቀበል ብሎ ጦርነት መክፈቱን ጠቅሰዋል፡፡ የሕወሓት አሸባሪ ቡድን የሚጋልባቸው መሰሎቹም ይህንኑ ሊያስፈጽሙ ተነስተዋል፡፡እነዚህን የሀገር ውስጥ ጠላቶቻችንን የሚጋልቧቸውም በቀደምት አባቶቻችን ዘመን ኢትዮጵያን ቅኝ መግዛት አምሯቸው ያልተሳካላቸው የውጭ ኃይሎች መሆናቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የአድዋ ልጆች መሆናችንን ታሳቢ በማድረግ በጋራ ከቆምን የፈለገውን ያህል ቢረባረቡ ሀገራችንን ማፈራረስ አይችሉም ብለዋል፡፡አሸባሪው ሕወሓት ትናንት በድብቅ ሲሠራ የነበረውን ዛሬ ይፋ አውጥቶ ኢትዮጵያን አፈራርሼ ሀገረ ትግራይን እመሰርታለሁ ብሎ መነሳቱን ጠቅሰዋል፡፡
የዲሞክራሲ መምህር እኛ ነን ባዮቹ ምዕራባውያንም አሻንጉሊት መንግሥት ካላስቀመጥንላችሁ በስተቀር እናንተ ለመረጣችሁት መንግሥት እውቅና አንሰጥም በማለት የአሸባሪውን ቡድን ጥፋት ከማውገዝ ይልቅ መንግሥት ላይ ጫና ማድረግን አጠናክረዋል፤ ይህም አይሳካላቸውም ብለዋል፡፡
ሚዲያዎቻቸው ለአንድ ዓመት ሳይታክቱ የኢትዮጵያን ስም በማጠልሸት ያልተደረገውን ተደረገ እያሉ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ ሲያደርጉ መክረማቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ፤ በተለይም ከሰሞኑ የአዲስ አበባን ህዝብ ለማሸበር ‹‹አዲስ አበባ በታጣቂዎች ተከባለች›› እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ የተከበበችው በድንቅ ህዝቦቿ እና በሚጠብቋት ወጣቶቿ በመሆኑ ምኞታቸው አይሳካም ብለዋል፡፡‹‹አድዋ›› ነጻነት፤ ‹‹አጎዋ›› ግን እርዳታ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ የአድዋ ልጆች ስለሆንን ከእርዳታና ብድር የሚበልጥብን ነጻነታችን ነው ብለዋል፡፡ወጣቱ ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ በተሰማራበት ሁሉ ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባው ክብርት ከንቲባዋ አሳስበዋል፡፡በተለይም የሀገሩን የጸጥታና ሰላም ጉዳይ በንቃት እንዲከታተልና ለእናት ሀገሩም ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ማንኛውም ሰው በሀገሩ ጉዳይ የሚሰስተው ህይወት፣ ጉልበት፣ ገንዘብና ጊዜ ሊኖር አይገባም ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ጀግኖች አሏት፤ ዛሬም የእኛ ትውልድ ጀግና ነው ›› ያሉት ከንቲባዋ፤ በዱር በገደሉ ህይወታቸውን እየሰጡን ያሉ ወጣት ጀግና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በድል ላይ ድል እያስመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ከአባቶቻችን ጀግንነትን እንጂ ባርነትን አልወረስንም ያሉት ከንቲባዋ፤ ወጣቱ ነገ ዛሬ ሳይል ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል፤ እንዲዘምት ጥሪ አቀርበዋል፡፡ጎን ለጎንም ሁሉም ወጣት የከተማውን ሰላም በመጠበቅ ሀገር አፍራሾችን ምንም አይነት መፈናፈኛ እንዳያገኙ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡
የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካይ አቶ አበበ ሙሉጌታ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የፖለቲካም ይሁን ማንኛውም የሃሳብ ልዩነት ከሀገር በታች እንደሆነ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን ከገጠማት ችግር ለማዳን ሁሉም ዜጋ ልዩነቱን ወደ ጎን ትቶ በጋራ ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡
ከውስጣችን የወጡና የውክልና ጦርነት የሚያካሂዱ በባንዳነት አባዜ የተለከፉ፤ ሀገራችንን ለማተራመስ ቢሞክሩም በተባበረ ክንዳችን እንደቁሳቸዋለን፤ አሳፍረን እንመልሳቸዋለን ብለዋል፡፡አንድነትን ማጠናከር ጠላትን ለመመከት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ያሉት አቶ አበበ፤ ሀገራችንን ለመታደግ ውድ ህይወታችንን ጭምር መስጠት ያስፈልገናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ ወርደን እንሰራለን ያሉት አሸባሪዎች ወደ መረጡት መኖሪያቸው ልከን የጋራ ሀገራችንን መገንባት አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡ያሰቡትን ሀገር የማፈራረስ ሥራ እንዳያሳኩም አስቀድመን ልንመክታቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማዳን ያለምንም የርዕዮተ ዓለምና የሃሳብ ልዩነት ወደ ክብሯ ማማ ላይ ለማስቀመጥ እጅ ለእጅ ተያይዘን ራሳችንን ለሀገራችን ለመስጠት መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ክብራችን ኢትዮጵያ ናት ያሉት አቶ አበበ፤ ሉዓላዊነቷ እንዳይደፈር እንደአባቶቻችን ቀድመን በመሞት እናስከብራታለን ብለዋል፡፡ማንኛውም የፖለቲካ አመራር በየትኛውም እርከን ያለ ሁሉ ለአንድ ህዝቡና ለአንዲት ሀገሩ ግንባር ቀደም ሆኖ ዋጋ መክፍል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
መሥራት የሚችል እጅ ይዘን፤ ማብቀል የሚችል መሬት እያለን ማንም በጥቅም እየደለለ ክብራችንን እንዲዋርድ እድል አንሰጠውም ብለዋል፡፡ወጣቱ የሀገሩን ጉዳይ በንቃት እየተከታተለ ጥሪ በተደረገለት ቦታ ሁሉ በመሰለፍ የሀገሩን ሉዓላዊነት ማስከበር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
እየተደረገ ያለው የውክልና ጦርነት እንደሆነ ተረድተናል ያሉት አቶ አበበ፤ አያቶቻችን ላሳፈሯቸው ኃይሎች ተላላኪ የሆኑ የባንዳ ልጆችና የፋሺስት ጉዳይ አስፈጻሚዎችን እናሳፍራቸዋለን፤ የምናስደፍረው ሉዓላዊነትም አይኖርም ብለዋል፡፡
ሀገራችን በእጃችን ላይ ያለች እንቁላል ነች፤ እንዳትወድቅብን አጥብቀን ልንይዛት ያስፈልጋል፡፡በመላው የሀገራችን ወጣቶች ትግል የመጣውን የነጻነት እስትንፋስ ለመዝጋት የሚፈልጉ ኃይሎችን እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንመክታቸው ይገባል፡፡ኢትዮጵያን ከነ ሙሉ ክብሯ ለማቆየት፤ የውስጥንም የውጭንም ጥቃቶች መክቶ ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የዚህ ትውልድ አደራ እና ኃላፊነት ነው፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3 /2014