ሰሞኑን በአሜሪካ የፌዴራሊስት ኃይሎች በሚል ጥቂት ሰዎች በአሜሪካ ተሰባስበው በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ አየሁ። ሰዎቹን ስመለከት በአንድ በኩል አሜሪካ የምትባለው አገር በዚህ ደረጃ የወረዱ ሰዎችን በጉያዋ ይዛ ቦታ ሰጥታ ማስተናገዷ እውን ዴሞክራሲ የምትለው ይህንን ያካትታል ማለት ነው? የሚል ጥያቄን ሲያጭርብኝ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የ27 ዓመታት የአሸባሪው ሕወሓት የአገዛዝ ዘመን የነበሩ የምርጫ አሻንጉሊቶች ዛሬም በዚህ መልኩ ሕወሓትን ለማዳን አሜሪካ ላይ መገኘታቸው ቀልድና ቁምገር እንዲደበላለቅብኝ አደረገኝ። በሌላ በኩል ይህች አሜሪካ የምትባል አገር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለምን በዚህ ልክ መሯሯጥ ፈለገች የሚል ጥያቄን እንድጠይቅ አስገደደኝ። ለዚህ መልስ ባይኖረኝም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደረገች ያለው ተግባር ግን እጅግ አሳፋሪ መሆኑን ብዙዎች እየተገነዘቡ ይገኛሉ።
እነዚህ የፌዴራሊስት ኃይሎች ነን የሚሉ አካላት ከዚህ ቀደም ሕወሓት በመቀሌ ሰብስቦ ሲጫወትባቸው የነበሩ ኃይሎች ቅጥያ ናቸው። ልዩነቱ አሁን መቀሌ ላይ ለመሰብሰብ ባለመቻላቸው ወደሌላኛዋ ዋና ከተማቸው ዋሽንግተን ዲሲ መሄዳቸው ብቻ ነው። ይህ ስፍራ መቀሌን ስለሚያስታውሳቸው ተመራጭ ስፍራ የሆነላቸው ይመስላል።
በዚህ ቡድን ውስጥ የተሰባሰቡት ቡድኖች ብዙዎቹ ምናልባት ሥልጣን ታገኛላችሁ ተብለው የተሰባሰቡ ካልሆኑ በስተቀር ከዚህ ቀደም ስለመንግሥትነት አስበው የሚያውቁ ናቸው ልማት ይከብዳል። በድንገት አሜሪካ ሥልጣን ልትሰጠን ትችላለች በሚል ከእንቅልፋቸው የባነኑ አሳፋሪዎች ናቸው። እዚህ ኃይሎች በምን መስፈርት እንደተገናኙና ዓላማቸውም ምን እንደሆነ እንኳን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እነሱም የሚያውቁት አይመስለኝም።
ነገር ግን ከነዚህ ሰዎች በስተጀርባ ያለውን የአሜሪካን ድርጊት እጅግ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪና በዚህ ዘመን ለዓለም ሰላም ዘብ እቆማለሁ ከምትል ትልቅ አገር የማይጠበቅ ተግባር ነው። ያም ሆነ ይህ ግን ሰሞኑን አሜሪካ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራች መሆኗ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በተለይ ሰሞኑን ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ተነስተው ይህንን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት እንደ ደራሽ ጎርፍ መሰባሰባቸው ለአሸባሪው ሕወሓት ሽብር፤ ለአሜሪካም ስጋት ሆኖባቸዋል። ስለዚህ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻቸውን በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥለዋል። ለዚህ የቀረፁት ዘመቻ ደግሞ ሕወሓት እና ሸኔ ወደአዲስ አበባ እየገሰገሱ ነው፣ ባለሥልጣኖች ከአገር ሊወጡ ነው፤ የአሜሪካ ዜጎች ኢትዮጵያን ለቃችሁ ውጡ ወዘተ የሚሉ ዘመቻዎች በስፋት ተከፍተዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም የሽግግር መንግሥት ለመመስረት የፌዴራሊስት ኃይሎች የሚባሉ ኃይሎችን ወደፊት በማምጣት እንዲታዩ ማድረግ እና ተደራደሩ በሚል በሌላ መልኩ ጫና ማሳደር ጀምረዋል።
ለመሆኑ አሜሪካ በዚህ ልክ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ላይ እንደ አዲስ የከፈተችው ዘመቻ መነሻ ምንድነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይህንን ፖለቲከኞች በተለያየ መንገድ ሊተነትኑት ይችላሉ። እኔ ግን ለዚህ መነሻ ብዬ የማስቀምጠው ዋነኛ ምክንያት የቀኝ እጃቸው ሕወሓት እውነተኛ ሞቱን ሊሞት ከጫፍ መድረሱን ሲመለከቱ ከዚያ በፊት ለማዳን የሚደረግ ሩጫ ነው።
እንደሚታወቀው የአሜሪካ ሩጫ የጀመረው ገና በጦርነቱ ማግስት ቢሆንም የሰሞኑ ግን ለየት ያለና የተጠናከረ ነው። በተለይ አሸባሪው ሕወሓት በወሎ ግንባር የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመነሳት ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማውደም እየተንቀሳቀሱ ነው። ይህንን የተረዳው የአሸባሪው ቡድንም በቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ አማካኝነት ስልታዊ ማፈግፈግ በሚል ከደሴና ኮምቦልቻ መውጣታቸውን ገልፀዋል። (ጥቂት ቆይቶ የተናገረውን ቢውጠውም)። አሁን የተነሳው ሕዝባዊ ማዕበል አሸባሪውን ቡድን እስከመጨረሻ ለመቅበር የሚያግደው አንዳችም ኃይል እንደሌለ ያሳያል። ስለዚህ ወያኔ ከዚህ በኋላ የሚያንሰራራበት እድል የጠበበ ነው። ስለዚህ ይህ ከመሆኑ በፊት ከሞት አፋፍ መመለስ የአሜሪካ ዋነኛ ፍላጎት ነው። ወዳጄ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶችን ልሰጥህ እችላለሁ። ጥቂቶችን እናንሳ።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን ባካሄዱት ጥናት አሜሪካና የምዕራባውያን ሚዲያዎች ለአንድ ዓመት ሲያወሩ የከረሙት ውሸት ሁሉ ተገልብጦ ታሪኩ ሌላ ሆኗል። ጦርነቱን የጀመረው አሸባሪው ሕወሓት ነው ከሚለው ጀምሮ ምዕራባውያን ሚዲያዎች መንግሥት ረሃብን እንደጦር መሳሪያ ተጠቅሟል የሚለውና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች የውሽት ፕሮፖጋንዳ እንደነበሩ ሪፖርቱ አጋልጧል። ይህ ደግሞ የምዕራባውያንን ፍርደ ገምድልነት እና የሐሰት ውንጀላ የሚያጋልጥ ነው።
ስለዚህ ይህ ከመሆኑ በፊት አሜሪካ ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ሪፖርቱ ሊቀርብ አንድ ቀን ሲቀረው ለኢትዮጵያ ሰጥታ የቆየችውን ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ የማስገባት እድል /አግዋ እድል/ ዘጋች። አስቡት ይህ ሆን ተብሎ ከሪፖርቱ ጋር የተደረገ የሩጫ እሽቅድምድም ነው።
አሜሪካ በዚህ ብቻ አላበቃችም። አሸባሪ ቡድኑ በደሴና ኮምቦልቻ የደረሰበትን ከፍተኛ ምት እና ከዚያ በኋላም ከኋላ እየመጣ ያለውን የሕዝብ ማዕበል ሲመለከቱ አሸባሪው ሕወሓት የማዳን ዘመቻው በሌላም አቅጣጫ ቀጠለ። ለዚህ ሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ “ድርድር” የሚል ስልታዊ የማወናበጃ መንገድ ነው። በዚህ የተነሳ አሜሪካ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ሁኔታዎች ሁሉ በተለየ መልኩ ድርድር እንዲካሄድ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ ጀምራለች። ለዚህ ደግሞ በአንድ በኩል ተወካዩዋን ወደአዲስ አበባ በመላክ እና የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በርካታ አገራት በዚህ ላይ እንዲረባረቡ በማድረግ ቡድኑ የሚድንበት መንገድ እያመቻቸች ትገኛለች።
የሚገርመው በኢትዮጵያ ጉዳይ አሉታዊ አቋም በመያዝ የሚታወቀው ይህ የአሜሪካ ተወካይ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጠው መግለጫ ለሽብር ቡድኑ ሃሳብ ሰንዝሯል። ሰውዬው በሰጠው አስተያየት በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ለድርድር ዝግጁ እንድትሆን የሚል ሃሳብ ሲኖረው በሌላ በኩል ደግሞ የሕወሓት እና የሸኔ ጦር ወደአዲስ አበባ የሚያደርገውን ግስጋሴ ያቁም የሚል የተጠና ንግግር አድርጓል። ሰውየው በዚህ ንግግሩ ለማሳየት የፈለገው ሕወሓትና ሸኔ ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሱ ነው፤ የሚያቆማቸው የለም የሚል መልዕክትም ለማስተላለፍ ነው። ይህ የስነልቦና ጫና ለማሳደር ታስቦ የተገለፀ ሃሳብ ነው።
አሜሪካ በዚህ ብቻ ሳታቆም ሰሞኑን ምንም ነገር በሌለበት እና የአሸባሪው ሕወሓት ኃይል ተመትቶ ከደሴም መውጣቱ እየታወቀ የአሜሪካ ዜጎች ኢትዮጵያን ለቃችሁ ውጡ የሚል ማስጠንቀቂያም አስተላልፋለች። እውን አሜሪካ ራሷ ለመዋጋት ፈልጋ ካልሆነ በስተቀር በዚህ መልክ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው ውጡ የሚለው ማስፈራሪያ የመጣው የሚለው መልስ የሌለው ጥያቄ ነው። አሜሪካ ዜጎቿን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት በዚያ ልክ እስከመጨረሻው ድረስ እንዳልቆየች አሁን በዚህ መልኩ የሚደረገው ማስፈራሪያ የስነልቦና ጫና ለማሳደር እንደሆነ ግልጽ ነው።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በዚህ ልክ እልህ ውስጥ ለምን ገባች የሚለው ጥያቄ በግልፅ መልስ ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን ታሪክም እንደሚነግረን አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከዋለችው ውለታ ይልቅ በችግሯ ጊዜ ገሸሽ ስታደርጋት መኖሯን ማስታወስ ለዚህ መልስ ሊሆን ይችላል።
ከአርባ ዓመታት በፊት ሲያድባሬ በእብሪት ተነሳስቶ ኢትዮጵያን ሲወርና አዋሽ ድረስ ዘልቆ ሲገባ አሜሪካ ከሶማሊያ ጎን ነበረች። ዛሬ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ የሚገኘው አሸባሪው ሕወሓት ወደስልጣን ሲመጣም አሜሪካ እጇ ረጅም ነበር። ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ወራ በያዘችበት በዚህ ወቅትም ቢሆን አንድም ቀን ስለኢትዮጵያ እውነታ ስትናገር አልተሰማችም። ግብጽ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ስትሞክር የአሜሪካ አቋም በግልፅ ለግብፅ የወገነ ነው። ሌላም ሌላም፤
አሁን እየተካሄደ ባለው ጦርነት እንኳ መንግሥት የመከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ባስወጣበት ወቅት አጋጣሚውን ለሰላም ከመጠቀም ይልቅ ሕወሓት እንዲያንሰራራ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከዚያ በኋላም ቡድኑ በተለያዩ የአማራና የአፋር አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀማቸውን ጅምላ ጭፍጨፋዎች አሜሪካ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታ አልፋቸዋለች። ለምን፣ ምክንያትም ለአሜሪካ ሚዛናዊ እይታ ቦታ የላቸውምና።
እውን አሜሪካ ለእውነትና ለፍትህ የቆመች አገር ናት? በታሪኳ ፍትሕና አሜሪካ ምን ያህል አብረው ይሄዳሉ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። ነገር ግን አሜሪካ ከጥቅሟ እንጂ ከፍትሕ ጋር ስትሰራ የታየችበት የዓለም ታሪክ ብዙም አይታይም። ለዚህ ጥቂት ማሳያዎችን ላንሳ።
አሜሪካ በአረቡ ዓለም አለኝ ከምትላቸው ወዳጆቿ ውስጥ ዋነኛዋ ሳዑዲ አረቢያ ናት። ታዲያ ሳዑዲ አረቢያ ለአሜሪካ ካላት ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አንጻር ጥፋቷ በአሜሪካ እንደጥፋት ሲቆጠር አይታይም። ለዚህ የቅርብ ጊዜውን የጋዜጠኛ ካሾጊ ግድያ ማንሳት ይቻላል። በዚህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አሜሪካ የውሾን ያነሳ ውሾ በሚል ዝምታ መምረጧ ይታወሳል። የእስራኤልና ፍልስጤም ሕዝቦችም ልክ እንደማንኛውም ሕዝብ እኩል የሰው ልጆች ናቸው። በነዚህ አገራት መካከል ያለው ውዝግብም ለዓመታት የዘለቀ ነው። አሜሪካ ግን እነዚህ ኃይሎች ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከማድረግ ይልቅ ለአንድ ወገን ያደለ አካሄድ ስትከተል መኖሯን የዓለም ሕዝብ ጭምር የሚያውቀው ነው።
በአፍሪካ ከሚገኙ አገራት ግብፅ በጸረ ዴሞክራሲ ተግባሮቿ ዓለም ያውቋታል። መንግሥትን የሚቃወሙ ዜጎችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን በጅምላ በአደባባይ የምትረሽን አገር ናት። መፈንቅለ መንግሥትም ቢሆን ለዚያች አገር አዲስ አይደለም። ይሁን እንጂ አሜሪካ በሌሎች አገራት ላይ የምታነሳቸው የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ለግብጽ አይነሳም። ለአሜሪካ ዋናው ጉዳይ ስትራቴጂክ አጋር መሆን ነው።
በሌላ በኩል አሜሪካ ከዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለግብጽ የወገኑ አቋም በማራመድ ትታወቃለች። ግብጽ የታችኛው ተፋሰስ፣ኢትዮጵያ ደግሞ የውሃው ዋነኛ ምንጭ መሆኗን እያወቀች የጥቅም ይገባኛል ጥያቄን ስታነሳ አሜሪካ በዚህ መልኩ ለግብጽ መወገኗ አሳፋሪና ፍትህ ለአሜሪካ ምን ያህል የተዛባ እንደሆነ ያሳያል። በአንፃሩ አሜሪካ ወደሜክሲኮ የሚፈስ ወንዝ እንዳላት ይታወቃል። በዚህ ወንዝ ላይ አሜሪካ ያለከልካይ ስትጠቀም እንዴት የሚል ጥያቄ የሚያነሳ የለም።
ለመሆኑ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እንዲህ አይነት ጫና ስታሳድር እውን ለሕዝቦቿ አስባ ነውን የሚል ጥያቄም ይነሳል። ለዚህ መልሱ አይደለም የሚል ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ልማት እና እድገት ሆኖ ሳለ አሜሪካ በኢትዮጵያ ከምታደርገው ኢንቨስመንት ይልቅ የፖለቲካ ጣልቃገብነቷ የጎላ ነው። በኢትዮጵያ በርካታ የሥራ እድሎችን ከፈጠሩ የኢንቨስመንት ሥራዎች ይልቅ በሰብዓዊ እርዳታ ስም የሚያተራምሱ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ይበዛሉ። ለአሜሪካ ለድሃ አገራት ዳቦ የሚገኝበትን መንገድ ከማመላከት ይልቅ ዳቦ እየሰጡ ለዘላለም በእጅ አዙር መግዛት የሚለው አካሄዷ ይበልጥ ሚዛን ይደፋል።
ሰሞኑን ከአግዋ ጋር በተያያዘ የፈፀመችው ክልከላም አሜሪካ ተግባሯና ቃሏ የሚጣረሱ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው። በአግዋ ተጠቃሚው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በተለይ ሴቶችና ወጣቶች ከዚህ እድል በብዙ መልኩ የሚጠቀሙ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ የተገለፀ እውነታ ነው። ታዲያ አሜሪካ ክልከላውን ስታደርግ የኢትዮጵያ ሕዝብንም ጭምር የመጉዳት ዓላማ ይዛ መሆኑን መገመት አይከብድም።
በአጠቃላይ እነዚህና መሰል የአሜሪካ ጫናዎች ኢትዮጵያ ከገባችበት ጫና ለማውጣት ሳይሆን አጋጣሚውን በመጠቀም መንግሥትን አፍርሶ ሌላ፤ ተላላኪ መንግሥት ማቋቋም ነው። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን ለመንግሥትነት ያዘጋጀቻቸው ኃይሎች ማሳያ ናቸው። በነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለመበተን ወይስ ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር ለማላቀቅ? እነዚህ ኃይሎች ወደስልጣን ቢመጡስ ምን ያህል ኢትዮጵያ እንደአገር መቀጠል ትችላለች። ይህ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው።
አሁን አሜሪካ የመጨረሻውን ኢትዮጵያ የሚለውን ስም የማጥፋትና ትንንሽ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን የመፍጠር ተልዕኮዋን ለማሳካት እየሰራች ትገኛለች። የአሜሪካ ዓላማ ከዚህ በኋላ ምንም ድምጽ የማይኖራው ትናንሽ የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በመፍጠር ለግብጽ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። ከዚህም አልፎ በቀጣናው ላይ ምዕራባውያን እንደፈለጉ የሚፈነጩበት የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ዘመንን ማስፋት ነው።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት እና መላ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ምቹ አልሆኑም። ሕዝቡ የሕወሓትን መሰሪ ተልዕኮና ተላላኪነት በመረዳቱ እነዚህን ኃይሎች ለማጥፋት ከዳር ዳር ተነቃንቋል። ሰሞኑን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የታየው የሕዝብ ማዕበልም ለዚህ ማሳያ ነው። ይህ የሕዝብ ማዕበል ኢትዮጵያን የማቆም እና ወደከፍታ የመውሰድ ትልቅ ብቃት ያለው ነው። የውጭ ኃይሎች ሴራም ሆነ የአሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይመክናል።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3 /2014