የሰዎች ሰብዓዊ መብቶች ይጠበቁ ዘንድ አገራት የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጋሉ። ከእነዚህ ጥረቶቻቸው መካከል ደግሞ በአገራቸው ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየተከታተለ እርማት እንዲወሰድ የሚያደርግ ተቋም ማዋቀር ግንባር ቀደሙ ነው። ኢትዮጵያም እንደ አገር የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ብላ ተቋም መስርታ ወደ ስራ ከገባች ብዙ ጊዜያት ቢሆናትም ተቋሙ ያን ያህል ነፍስ ዘርቶ የተበዳይ እንባ አብሷል ለማለት ግን አያስደፍርም። ባለፉት ሶሰት ዓመታት ይህ ተቋም ገለልተኛ፣ ነጻና ተዓማኒ ሆኖ እንዲሰራ በተደረጉ ከፍተኛ ጥረቶች የብርሃን ጭላንጭል የምትመስል ተስፋን የምታጭር ሥራ በተለያዩ ጊዜያት እየሠራም አሳይቷል።
አሁንም በተለይም አገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የሰብዓዊ መብት አጠባበቁ ምን ይመስላል? በማለት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ጋር በጣምራ ጥናት አድርጎ ውጤቱም ይፋ ሆኗል። ይህ ጥናት በተለይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሰዎች ሰብዓዊ መብት በምን ያህል ደረጃ ተገፏል? ወደፊትስ ምን መሆን አለበት የሚለውን እንዳካተተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ነግረውናል። ዶክተር ዳንኤል በቀለን በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ቃለ ምልልስ አድርገንላቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዊ መብት አያያዝ በተለይም ከለውጡ በኋላ ያለውን እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ዳንኤል፦ በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የፖለቲካ አካሄድ ከመጣበት ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ በብዙ ተስፋና በጎ እርምጃዎች የተጀመረ ነው። ለዚህም ማሳያዎቹ ከዚህ ቀደም የነበሩ ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ እንቅፋት የሆኑ ሕጎች የተሻሻሉበት አዳዲስ ተቋማት የማደራጀት፣ የነበሩትን የማጠናከር ሥራ የተጀመረበት፣ የፖለቲካ ምህዳሩ የተከፈተበት፣ የፖለቲካ እስረኞች የተፈቱበት እና የሚዲያ ነጻነት የተከበረበት ከመሆኑ አንጸፃር የሚያበረታታ እርምጃ እንደነበር ይታወቃል።
በሌላ በኩል ደግሞ የራሱ የሆኑ ብዙ ተግዳሮቶችን ይዞ መምጣቱም የሚካድ አይሆንም። ለምሳሌ አዲስ የተፈጠረው የፖለቲካ ምህዳር ወይም ከነጻነቱ ጋር አብረው ተያይዘው የመጡ ችግሮች እንዲሁም በአገራችን ላይ ለረጅም ጊዜ የነበረው ስር የሰደደ የፖለቲካ ቀውስ መፍትሔ ያላገኘ በመሆኑ ወደ ግጭት በማምራቱና ግጭቱንም ተከትሎ በጣም ብዙ የሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ የገባንበት ነው። በመሆኑም በአንድ በኩል ብዙ በጎ እርምጃዎች ነበሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ገጥመዋል፤ ከእነዚህ ፈተናዎች አሁንም አልወጣንም። ይህ የረጅም ጊዜ ሥራን የሚጠይቅ ነው። ጅምሩ አበረታች ቢሆንም ሰብዓዊ መብትን በማስከበር በኩል ገና ረጅም ስራ እንደሚቀረን ያሳያል።
አዲስ ዘመን ፦ በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተውን ጦርነት በማስመልከት እናንተም ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን የሰራችሁትን ሪፖርት በቅርቡ አውጥታችኋልና ጥናቱ እንዴት ተከናወነ? ተዓማኒነቱስ ምን ያህል ነው?
ዶክተር ዳንኤል፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ጋር በጣምራ ሲያካሂዱ የነበሩት ጥናት ነው። ይህ ጣምራ ሥራ በዋናነት ያስፈለገው በተለይም በትግራይ ክልል ጋር በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ተነስተው የነበሩ የሰብዓዊ መብት ችግሮችን ነጻ፣ ገለልተኛና ታዓማኒ በሆነ ሁኔታ ማጣራትና ግኝቶቹን ማወቅ የመፍትሔ፤ ሃሳብንም ማቅረብ ስለሚያስፈልግ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤትን በጋራ ስራውን እንድንሰራ ጠይቀናቸው የኢትዮጵያ መንግሥትም የጣምራ ስራው እንዲካሄድ ፍቃደኛ በመሆኑ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የጣምራ ምርመራ ስራ ተካሂዷል።
በዓይነቱ የመጀመሪያ ያልኩት በአንድ አገር ውስጥ ባለ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋምና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቅ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ጋር በዚህ ደረጃ የጣምራ ምርመራ ሲካሄድ የመጀመሪያው በመሆኑ ነው። ይህ ዓይነቱ ስራ የመጀመሪያው እንደመሆኑም ስራውን ለማከናወን የተለያዩ ችግሮች አጋጥመው ነበር፤ የዚህ አይነት የጣምራ ስራ ሊካሄድ አይገባም የሚሉም ነበሩ፤ እነሱ ስራው በጣምራ መሰራቱ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ መብት ተቋም እንደ ነጻ ተቋም ሊቆጠር አይገባም የሚል መከራከሪያ ነበር ያነሱት፤ ነገር ግን በዚህ ሥራ ላይ የተሳተፈው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት እንዲሁም በርካታ የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት የዚህ አይነቱን የጣምራ ምርመራ ለማካሄድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነጻና ገለልተኛ ነው፤ ብለው ተዓማኒነት በማግኘቱ ኮሚሽኑም በጣምራ ምርመራው ላይ እንዲሳተፍ ተደርጎ ረጅም ጊዜ ከወሰደ የምርመራ ስራ በኋላ ውጤቱ ወጥቷል።
አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ግን የጣምራ የምርመራ ሥራው ሂደት ምን ይመስል እንደነበር ቢገልጹልን?
ዶክተር ዳንኤል፦ የምርመራ ሥራው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው ሲሠራ የቆየው ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደዚህ አይነት ምርመራዎች የሚካሄዱበትን ዜዴዎች በመጠቀም በሃላፊነት ስሜት የተሠራ ነው። ይህንንም እኔ ከምናገረው በላይ የሥራውን ውጤት፣ የተቋማቱን ገለልተኝነትና ነጻነት በማየት መገመት ይቻላል። በሌላ በኩልም ይህ የጣምራ ምርመራ ያስገኘው ውጤት ከታወቀ በኋላም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነትንም ያገኘ ሆኗል። በሥራው ላይ የተሳተፉት 16ቱም አገራት ውጤቱን ተቀብለው በጋራ ባወጡት መግለጫ ሥራው ትክክለኛና ነጻ መሆኑን ገልጸው በችግሩ ላይ የተሳተፉ ወገኖች በሙሉ ምክረ ሃሳቡን ተግባራዊ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል። ከእነዚህ አገራት በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ የምክር ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎችም አባል አገራት ሪፖርቱን እንደ ሃሳብ መነሻ አድርገው በማቅረብና በመወያየት ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በመሆኑም ይህ ሪፖርት በእነዚህ ሁሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች ስለ ገለልተኝነቱ በሙያ ብቃት የተሰራ ስለመሆኑ ትክክለኛ ሥራም ስለመሆኑ እንደ ማረጋገጫ ሊወሰድ የሚችል ነገር ነው ፤ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ማንኛውም አንባቢ ሪፖርቱን በማንበብ የተሠራበትን መንገድ በማየት ለማረጋገጥ ይችላል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ሪፖርቱ በገለጹት ልክ ተቀባይነት እንዲያገኝ በጥናታችሁ ያካተታችኋቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ምን ነበሩ? ግኝቶቹስ?
ዶክተር ዳንኤል፦ ይህንን የምርመራ ሥራ ስናካሂድ በመጀመሪያ ሊያካትት የሚገባውን ፍሬ ጉዳዮች የት አካባቢ ቢሆን ይሻላል ፤ሊመራበት የሚገባ የምርመራ ስልት ምን ይሁን የሚለውን አይተናል፣ በዚህም መረጃ እንዴት ይሰበሰባል፣ ይተነተናል፣ ከሕግ ጋር ያለው ተዛምዶ እንዴት ይገመገማል፣ የሚሰበሰቡት ማስረጃዎች በምን ዓይነት መስፈርት ይመዘናሉ ፣ በየአካባቢው ተከሰቱ የተባሉትን ችግሮች ያላቸው የተያያዥነት ጸባይ በምን ዓይነት ዘዴ ይታያል፣ የሚለውን የመቀመር ሥራ ቀዳሚው ነበር።
ይህንን እንግዲህ በኮሚሽናችን ውስጥ የራሳችንን ስልት ማሰብ ማዘጋጀት ጀምረንም ስለነበር እሱን የማሳደግ በተጨማሪ ግን የተባበሩት መንግሥታት ለረጅም ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ መሰል ምርመራዎች የዳበረ ልምድ ስለነበነረው ያንንም መሰረት አድርገን ለዚህ ስራ አግባብነት ያለው የምርመራ ስልት በማውጣት ተጠቅመናል።
በሌላ በኩልም፣ ሥራውን የምንመራበትን መርሆዎች ለምሳሌ የነጻነት፣ የገለልተኛነት፣ ሥነ ምግባር የመከተል፣ በተጎዱ ሰዎች ላይ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ የመጠንቀቅ፣ የሚባሉትን መርሆዎች መሰረት አድርገንና የምርመራ ስልት አውጥተን ከሁለቱም ድርጅቶች እኩል ቁጥር ያላቸውና ለሥራው ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች አውጣጥተን ሌሎች ድጋፍ ሰጪዎችንም ከሁለቱም ተቋማት እንዲሳተፉ አድርገን ነው ወደምርመራ የገባነው።
የምርመራ ሥራውም የተጀመረው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ ተፈጽመውባቸዋል ወደተባሉት አካባቢዎች በመድረስ የተጎዱ ሰዎችን ቤተሰቦች፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች፣ የህክምና ባለሙያዎችን፣ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችን፣ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮችንና ሌሎችንም የመረጃ ምንጮች በማነጋገር መረጃ የመሰብሰብ ሥራ ተከናውኗል። በነገራችን ላይ በቃለ መጠይቅ ከሚሰበሰበው መረጃ በተጨማሪ የሰነድ፣ የፎቶግራፍ፣ የተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ)፣ እንዲሁም በዓይን እይታ የሚሰበሰቡ መረጃዎች አሉ። እነዚህን ሁሉ በማሰባሰብና በማጠናቀር ሁለታችንም በአንድነት ባደረግነው ትንተና እንዲሁም ከሕግ ጋር አዛምደን በሰራነው ሥራ መሰረት የደረስንበትን ድምዳሜዎችና ምክረ ሃሳቦች ይፋ አድርገናል።
በጠቅላላው በግጭቱ ላይ ተሳታፊ በነበሩ ሁሉም ወገኖች ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመ መሆኑንና እነዚህም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ፣ የጦር ወንጀል ሊባል የሚችል እንደሆነ ይዘረዝራል። በእነዚህ ስር የተፈጸሙት ልዩ ልዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምን ምን እንደሆኑ ያመለክታል። በዚህ ጥሰት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ብለን የለየናቸውም በግጭቱ ያሉትን ሁሉንም ወገኖች ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የተፈጸመው ድርጊት የጦር ወንጀል ሳይሆን የዘር ማጥፋት መሆኑን የሚያሳይ መረጃ አላገኛችሁም ? ብዙዎች የማይካድራውን ጭፍጨፋ ብቻ እንኳን በማንሳት ዘር ተኮር ነው ይላሉና ይህንን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ዳንኤል፦ ሪፖርቱ ላይ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች እንግዲህ የትግራይ ግጭት ከተከሰተ በኋላ የሆኑ ነገሮች የዘር ማጥፋት መልክ ያላቸው ናቸው ሲሉ ይሰማል፤ እኔም እሰማለሁ ፤ ነገር ግን የዘር ማጥፋት ወንጀል ምን ማለት ነው? የህግ ጽንሰ ሃሳቡስ ምን ይላል ? በሌላ በኩል ደግሞ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያቋቁሙት የህግና የፍሬ ነገር ምንድን ናቸው ? የሚለውን ጠንቅቆ ካለማወቅ የመነጨ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚባለው በአንድ በኩል የህግ ጽንሰ ሃሳብ ሲሆን በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ህጉ ውስጥ የተካተተ ነው።
በመሆኑም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት ሊሟሉ የሚገባቸው የህግና የፍሬ ነገር ጉዳዮች አሉ ማለት ነው፤ ከዚህ የተነሳ ይህንን ጽንሰ ሃሳብ ምንነቱን በትክክል ካለመረዳትና በማህበረሰቡ ውስጥ ስለጉዳዩ ካለ የተሳሳተ አረዳድ የሚመነጭ አስተያየት ይመስለኛል።
የተሳሳተ አረዳድ ማለት እንግዲህ አንድ ጥቃት ሃይማኖት፣ ብሔር እንዲሁም ዘር ተኮር ሆኖ ሲታይ ጥቃቱን በማህበረሰብ መደበኛ አረዳድ ከነዚህ ውስጥ አንዱን ያሟላ ወይም ሰዎች በዘራቸው በብሔራቸው ምክንያት ተገለዋል ብሎ የማሰብና የመገንዘብ ሁኔታ ነው። ይህ ፍጹም የተሳሳተ አረዳድ ነው፤ ምክንያቱም አንድ ጥቃት ዘር፣ ሃይማኖት ወይም ብሔር ተኮር ስለሆነ ብቻ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊባል ስለማይችል። በዓለም አቀፍ ህጉ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊያስብሉ የሚችሉ በጣም ዘርዘር ያሉ መስፈርቶችም አሉ።
አዲስ ዘመን ፦ እናንተ በምርመራችሁ ወቅት እነዚህን መስፈርቶች ተጠቅማችኋል?
ዶክተር ዳንኤል፦ እኛ በምርመራችን ወቅት ያደረግነው ነገር በጦርነቱ ተከስተው ያገኘናቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሙሉ ከነዛ መስፈርቶች አንጻር ነው እንዲመዘኑ ያደረግነው። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ማይካድራ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ነው ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ በትግራይ እየሆነ ያለው የዘር ማጥፋት ነውም ይላሉ፤ ነገር ግን እኛ የመረመርነው ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር ነው። በዚህም ያገኘነው ውጤት ችግሩ ብሔር ተኮር መሆኑን ነው። ይህ ሁኔታ ከዓለም አቀፉ ሕግ አንጻር ትርጉሙ የሚወድቀው በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ወይም የጦር ወንጀል እንጂ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከሚባለው ጋር የሚዛመድ ሆኖ አላገኘነውም።
እዚህ ላይ ግልጽ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተብለው የሚታወቁት በጣም የተወሰኑ ጉዳዮች ናቸው። ነገር ግን ሰዎች በተለምዶ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር የሆነን ጥቃት በሙሉ በዛ መነጽር ስለሚመለከቱት ነው እንጂ የዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነና ጥብቅ የሕግና የፍሬ ነገር መስፈርቶች ያሉት ነው። በመሆኑም እኛም በተደጋጋሚ እያስረዳን ነው፤ ቀስ በቀስም ግንዛቤው እየጨመረ ይመጣል ብለን እናስባለን።
ሌላው ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባን ነገር በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሳይፈጸም ተፈጽሟል ብሎ ማለት ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል። በነገራችን ላይ የተፈጸመው ወንጀል የዘር ማጥፋት ባይሆንም ቅሉ ቀላል ግን አይደለም፤ ከፍተኛ የሆነ የግፍና የጭካኔ ሁኔታ የታየባቸውም ነገሮች አሉ።
አዲስ ዘመን፦ አንድ ወንጀል አንድን ብሔር ነጥሎ ማጥቃቱ በራሱ ግን የዘር ማጥፋት ወንጀል አያሰኘውም ?
ዶክተር ዳንኤል፦ የተፈጸመው ወንጀል በአንድ ብሔር ላይ ማጠንጠኑ ብቻውን የዘር ማጥፋት ወንጀል አያሰኘውም። ምክንያቱም የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚባለውን ከሚያቋቁሙት የሕግና የፍሬ ነገር አንዱ በወንጀል ተግባሩ ላይ የተሳተፉት ሰዎች ጥቃቱን የፈጸሙት የዛን ብሔር ሰዎች በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት ሆን ብለው አስበው ተዘጋጅተው አቅደው የፈጸሙት ተግባር መሆኑን ማስረዳትና ማረጋገጥ ሲቻል ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የተፈጸመው ወንጀል ዓላማው ምንድን ነው ለምሳሌ የዛ ብሔር ሰዎች በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት ነወይ? የሚለው ከፍተኛ ትኩረት ሊያገኝ የሚገባው ነው። ይህ ወንጀል ከሌሎች የወንጀል አይነቶች የሚለይበትን ነገር በምሳሌ ላስረዳሽ፤ ለምሳሌ የአንቺን ቦርሳ አንድ ሰው ነጥቆሽ ሮጠ፤ የዚህን ሰው ጥፋትና ወንጀል ለማረጋገጥ መስረቁን በማስረጃ ማቅረብ ብቻ በቂ ነው። የአንቺን ቦርሳ የሰረቀበትን ሃሳብ ማረጋገጥ አያስፈልግም። በመሆኑም መስረቁን የሚያስረዳ ማስረጃ ቀርቦ የስርቆት ወይም የንጥቂያ ወንጀል መፈጸሙን ማረጋገጥ ይቻላል። አንዳንድ ወንጀሎች ግን ከጸባያቸው አንጻር ድርጊቱን ብቻ ሳይሆን ሃሳብንም ማረጋገጥ ይፈልጋሉ ፤ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚባለው ነው። በመሆኑም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት ሊረጋገጥ ከሚያስፈልገው ነገር አንዱ በድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉ የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሁሉ በዛ ብሔር ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያነሳሳቸው ጥላቻ ነው። ከአካባቢው እንዲወጡ ለማድረግ ነው የሚለው ዓላማው መታወቅ አለበት። በመሆኑም የወንጀሉ መነሻ ሃሳብ እስካልታወቀ ድረስ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት አይቻልም።
ነገር ግን በሲቪል ሰዎች ላይ ዘራቸውን ሃይማኖታቸውን መሰረት በማድረግ ግድያ ከተፈጸመ ምንም እንኳን የዘር ማጥፋት ወንጀል ባይባልም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው ተብሎ ይተረጎማል።
አዲስ ዘመን፦ እንግዲህ ይህ ምርመራ በጣምራ የተከናወነ ስለመሆኑ ገልጸዋልና ይህ ለምን አስፈለገ?
ዶክተር ዳንኤል፦ በጣምራ ምርመራውን ማድረግ ካስፈለገበት ምክንያት ዋናው በግጭቱ ውስጥ በሰዎች ላይ የደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምን ያህል መሆኑን ለመረዳትና ለማረጋገጥ ነው። ምክንያቱም ግጭቱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የመገናኛ ብዙሃንና ተቋማቶቻቸው እንዲሁም ደግሞ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን የሚደግፉ አክቲቪስቶችና ደጋፊዎች ስለ ግጭቱ አነሳስ እንዲሁም ተፈጸመ ስለሚባሉት ነገሮች የተለያዩ ዘገባዎችን ሲያወጡ ቆይተዋል ፤ በዚህ ደግሞ እውነቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል። በመሆኑም የዚህ አይነት ነጻና ገለልተኛ ምርመራ ማድረግ ያስፈለገው እውነቱን ከሀሰቱ ለመለየት ነው።
በመሆኑም የምርመራ ሥራው በጣም ጊዜ ተወስዶ በዚህ አይነቱ ሥራ የካበተ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ተደግፎ እንዲሁም በብዙ አገሮች ላይ ጥቅም ላይ በዋሉ የመመርመሪያ ዘዴዎች ተደግፎ ቦታው ላይ ተሄዶ በመሠራቱ እውነቱ እንዲታወቅ አድርጓል።
በመሆኑም በቀጣይ የችግሩን ምንጭ ለማጥናት ተጨማሪ ሥራን ለመስራት የሚፈልጉ አካላት ቢመጡ ይህ የጥናት ውጤት የመጀመሪያ ማስረጃቸው ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም እስከ አሁን ስንሰማው የነበረው መረጃ በተለያዩ ምክንያቶች ለአንድ ወገን ያደላ ስለነበር።
አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ ከዚህ ቀደም ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግሥት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞበታል የሚል ተደጋጋሚ ዘገባ ነበርና ይህንን ያጠራል ማለት ይቻላል?
ዶክተር ዳንኤል፦ አዎ ያጠራል። እኛ በዚህ ምርመራ ልናረጋግጥ የቻልነው በእርዳታ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ተገቢ ያልሆነ የማደናቀፍ ሥራ የነበረ ቢሆንም ይህ የማደናቀፍ ተግባር ግን የአንድ ወገን ሳይሆን በግጭቱ በተሳተፉ ሁለቱም ወገኖች በኩል ይፈጸም እንደነበር ነው። በሌላ በኩልም እርዳታ ሰጪዎቹን፣ ተረጂዎቹን በቦታው ላይ በመሆን አነጋግረን ለመረዳት እንደቻልነው ለእርዳታ አሰጣጡ እንቅፋት የሆነው የጦርነቱ ሁኔታ፣ የጸጥታው መደፍረስ መሆኑን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የጦርነቱ ተሳታፊዎች ከጦር አካሄዱ አንጻር በግላቸው የሚያደርጉት ቁጥጥር እንዲሁም ቅጽበታዊ የሆኑ ጦርነቶች የመንገድ መዘጋት በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ተግዳሮት ፈጥረው የነበሩ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።
ከዚህ ውጪ ግን ሲዘገብ በነበረው መልክ የኢትዮጵያ መንግሥት ሆን ብሎ አስቦ አቅዶ እርዳታ ሊያገኙ የሚገባቸውን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርሳቸው በማድረግ የጦር ስልት ማድረጉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላገኘንም። ይህ ደግሞ በጥናቱ የተሳተፍን ሁለታችንም የሰበሰብነው መረጃ ያረጋገጠልንና የደረስንበት መደምደሚያ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ሪፖርት መረጃን ከማጥራት ባሻገር እንደ አገር የሚጠቅመን ነገር ምንድን ነው?
ዶክተር ዳንኤል፦ ሪፖርቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ነው። ምንም እንኳን በዚህ ሪፖርት ሁሉም እውነት፣ ታሪክ ሙሉ በሙሉ ተሸፍኗል ባይባልም በጠቅላላው ግን የሰብዓዊ መብት ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር አሳማኝ ማስረጃ አግኝተናል፤ በዚህም እውነቱን ማውጣት አስችሏል።
ሌላው ደግሞ በግጭቱ ውስጥ የበርካታ ሲቪል ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ በሴቶች ፣በህጻናት፣ በወንዶች፣ በወጣቶች ላይ በጣም በሚያሳዝን መልኩ ወሲባዊ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፤ በመሆኑም በጥፋቱ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎችም ለጥፋታቸው ተጠያቂነታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ የጥናቱ ዓላማም ይኸው ነው።
ሪፖርቱ መሰራቱ ደግሞ በግጭቱ ምክንያት የተለያዩ ችግሮችን ያስተናገዱ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም በመሆኑ እነዚህ ሰዎች የጉዳታቸው መጠን ታውቆ ወደ ህይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ ሪፖርት እንደ አገር የሚያግዘን ነገር ወደፊትም መሰል ችግር ውስጥ እንዳንገባ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ምንድን ናቸው? የሚለውን ለማወቅ ነው። በአገራችን በተደጋጋሚ እያየን ላለነው ችግር የስር ምክንያቱን ለማጥናትም ያግዛል። ሪፖርቱን ያዘጋጀነው አካላትም ተስፋ የምናደርገው ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለን ነው።
ለነገሩ አሁን ላይ አንዳንድ ምልክቶችም ማየት ጀምረናል። ለአብነት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክርት ቤት በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት ባደረገበት ወቅት የምክር ቤቱ አባላትና እራሱ ምክር ቤቱ ሪፖርቱን መሰረት አድርገው የመፍትሔ ሃሳብ ሲያመነጩና በሪፖርቱ የቀረበው የመፍትሔ ሃሳብም ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ ሲያደርጉ ነበር።
አዲስ ዘመን፦ ሪፖርቱ የቀረበው ግጭቱ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ መከላከያ መቀሌን ለቆ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ነውና ከዚያ በኋላ ያሉት ጊዜያትስ በምን ሁኔታ ነው የሚታዩት?
ዶክተር ዳንኤል፦ አዎ ሪፖርቱ ግጭቱ ከተከሰተበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ 2013 ዓም ነው። የጣምራ ስራው ሲታሰብ የነበረው ነገር ሪፖርቱን እስካጠናቀቅንበት ጊዜ ድረስ እንሄዳለን የሚል ነበር፤ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት መቀሌን ለቆ ከወጣ በኋላ በአካባቢው የነበረው ሁኔታ ይህንን ለማድረግ አስቻይ አልሆነም። ከዚህ የተነሳ ደግሞ የምርመራውን ሁኔታ የጊዜ ገደብ ማበጀት አስፈለገ። በዚህም እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ሆነ። ነገር ግን ከዛ በኋላ የነበሩት ጉዳዮች ሊመረመሩ አይገባም ወይም ምርመራ አልተደረገባቸውም ማለት አይደለም። እንደውም ሁለታችንም ያለውን ሁኔታ በየተቋሞቻችን ምርመራ ማድረግ ቀጥለናል። ግኝቶቻችንና የደረስንበትን የመፍትሔ ሃሳብም የአሁኑን ሪፖርት ባቀረብንበት መልኩ ወደፊት የምንገልጸው እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተደጋጋሚ ሪፖርቶቹን ሲያወጣ በተለይም የሽብር ቡድኑ እያደረጋቸው ያሉ ነገሮችን ወደ ጎን በመተው መንግሥት ላይ ብቻ ጫና በማሳደር ላይ ነው የሚሉ ወገኖች አሉና እንደው እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ዳንኤል፦ እንግዲህ ስራችን ግኝታችን ሪፖርታችን ድምዳሜዎቻችን ከትችት በላይ ናቸው ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን ትችቱ ምክንያታዊና በትክክለኛ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ከሆኑ ለሥራችን ጥሩ ግብዓት ነውና እንቀበለዋለን። ግን አንዳንድ ጊዜ የምንሰማቸው ትችቶች ምክንያታዊ ያልሆኑና በማስረጃ ላይ ያልተመሰረቱ ይሆናሉ፤ እኛም በዛ ትዝብት እንወስዳለን።
በሌላ በኩል ደግሞ ማንኛውም ሰው የመሰለውን የመናገር አቋም የመያዝና የመተቸት መብቱንም እናከብራለን፤ እዚህ ላይ ግን ልብ እንዲባል የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ነጻ ፣ገለልተኛ ፣ ተዓማኒ ሥራ የሚሠራ ተቋም መሆኑ ተረጋግጧል ተቀባይነትም አግኝቷል። ኮሚሽኑ የሚሰጣቸው ምክረ ሃሳቦችም ተቀባይነት እንዲያገኙ በሥራ ላይ እንዲውሉ ብዙ የዓለም አቀፍ መሪዎችና ተቋማትም ውይይት ያደርጉባቸውል፤ እነሱም ይናገሯቸዋል።
በመሆኑም ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ የተዓማኒ መረጃ ምክረ ሃሳብና ሙያዊ አስተያየት ምንጭ መሆኑ በአገር ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃም በደንብ እየተረጋገጠ የመጣ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ጥሩ እርምጃ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የሰዎች ሰብዓዊ መብቶች ከሚጣሱባቸው ክስተቶች አንዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነውና አሁን ደግሞ እኛም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ነን፤ ኮሚሽኑም ሰሞኑን ያወጣው ማሳሰቢያ አለ፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ዳንኤል፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተወሰኑ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ገደብ ይጥላል፤ ግዴታዎችንም ያስቀምጣል፤ ይህ ደግሞ ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ አንጻር ስጋት የሚፈጥር ነው። እኛን በጣም ያሳስበናል፤ በተለይም የሰዎች ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ አዋጁና አፈጻጸሙም ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ እንዲሆን በቅርበት እየተከታተልን ነው። በመሆኑም ያለንን አቅም ሁሉ በመጠቀም አፈጻጸሙ በሰብዓዊ መርሆዎች ዙሪያ እየተፈጸመ መሆኑን የቅርብ ክትትል እንዲሁም አስፈጻሚ አካላቱን የማገዝ ተግባር እያከናወንን ነው።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቀድሞ ከምናውቀው ተለይቷል? ገለልተኛና ነጻስ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ዳንኤል፦ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ በነበረን የፖለቲካ ታሪክ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ብቻ ሳይሆን ብዙ መንግሥታዊ ተቋማት ከመንግሥት ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ውጪ ሆነው መስራት የማይችሉበት ሁኔታ ነው የነበረው። አሁን ግን የተጀመረው በተለይም ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ የሚጠበቁ ተቋማት በመንግሥት ስራ አስፈጻሚ ተጽዕኖ ነጻ ሆነው ሙያና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ተዓማኒ ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።
እነዚህ ተቋማት ደግሞ በጣም ያስፈልጉናል። ይህንን ለመፍጠር ሰፊ ጥረት እያደረግን ነው። ሥራው ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም። እኔም ጓደኞቼም የሚያበረታታን ደግሞ በዚህ ሁለት ዓመት እንኳን በጣም ተስፋ ሰጪ ነገሮችን አይተናል። በዚሁ ከቀጠልን ደግሞ ለረጅም ጊዜ ጠንካራ ሆኖ የሚቆም ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ድምጽ የሚሆን ጠንካራ ኮሚሽን እንገነባለን ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ እጅግ በጣም እናመሰግናለን።
ዶክተር ዳንኤል ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሕዳር 2/2014