አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በአሁን ወቅት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር ነፍስ እንዳላወቀ ሕፃን ልጅ በሞግዚት አስተዳደር የማስተዳደርና የመጠበቅ ህልማቸውን ለማሳካት እየተውተረተሩ ናቸው። ”የሚበላኝን አሞራ ሲዞረኝ ነው የማውቀው” እንደሚባለው ከቅኝ ግዛት መንፈስ ያልተላቀቁ እነዚህ አገራት ስሜትና ፍላጎታቸውን ለማሳካትም የጥፋት ክንዳቸውን በመገናኛ ብዙኃን በኩል እየሰነዘሩ ናቸው።
እነዚህ አገራት በአሁን ወቅትም ኢትዮጵያ ላይ ግልፅ የሚዲያ ጦርነት ከፍተዋል። ሌላው ዓለም ኢትዮጵያን በተሳሳተ መንገድ እንዲገነዘብ የተቀነባበረ መልኩ ዘመቻ ጀምረዋል። ከተለያየ አቅጣጫ ኢትዮጵያን ማስጨነቅ፣ መክሰስ፣ ማሸማቀቅና መወንጀልን ተያይዘውታል።
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ በመግባት የአገሪቱን የውስጥ ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግ እየጣሩ ነው። በአሸባሪው ሕውሓት በኩል የውክልና ጦርነት ውስጥም ገብተዋል። በሽብርተኛው ሕውሓት በኩል አገር የመበተን ትግልና ትንቅንቅ ገጥመዋል።
የዓለም የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጠበቃና አርአያ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቀምጡት ምዕራባውያንና መገናኛ ብዙኃን የሽብር ቡድኑ የእብደት ተግባርና ጥፋት ለመናገር እየተናነቃቸው ነው። ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋና አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሰምተው እንዳልሰማ፣ አይተው እንዳላዩ ፣ገብቷቸው እንዳልገባቸው ሲሆኑም እያስተዋልን እንገኛለን።
አሸባሪው ቡድን የጭካኔ ድርጊት ከማውገዝ ይልቅም በሰብዓዊነት ስም ለአሸባሪው ቡድን መተላለፊያ ኮሪደር ስለሚከፈትበት መንገድ ብዙ ሲጨነቁና ሲደክሙ እያየናቸው ነው። ለፖለቲካ ሸሪኮቻቸው ሲሉ ኢ-ሰብዓዊነትን እንደሚያበረታቱ እያሳዩን ይገኛሉ።
ትላንት በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በአፍጋኒስታንና በሊቢያ ያደረጉትን ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ምድር ለመድገም ጥረት እያደረጉ ነው።መሬት ላይ መሆን ያልቻለውን በመገናኛ ብዙኃን በኩል እየሞከሩት ይገኛሉ። በተለይ ሲ ኤን ኤን፣ ቢቢሲና አልጀዚራ የተሰኙ የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያን በተመለከተ የከፋ ጥቁር ፕሮፖጋንዳ ውስጥ ናቸው።
ይህ የተቀናጀ የመገናኛ ብዙኃኑ ድካም እንዲሁ የመጣ አይደለም። የሽብርተኛው ቡድን እንዲሁ ወጥቶ መቅረትና ወጥቶና ተበትኖ መተንፈሻ ቀዳዳ ማጣት የፈጠረባቸው ጭንቀት ድምር ውጤት ነው። ቡድኑ ላይ ነፍስ ለመዝራት የሚደረግ ልዩ ተልዕኮ አካል ነው።
የመገናኛ ብዙኃኑ ዘመቻ በተለይ ባለፉት ሳምንታት የተለየና አዲስ እንግዳ አካሄድ እየተከተለ ይገኛል። በተለይ ሲኤን ኤን ባልተለመደ ሁኔታ በኢትዮጵያ ጉዳይ በቀን ሰባትና ስምንት ዘገባዎች ሲሰራም አይተነዋል። ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርጓል። በዚህ ወቅትም ከጋዜጠኝነት መርሕና ሥነ ምግባር ጋር በግልፅ እንደተጣላ አሳይቷል።
በጋዜጠኝነት ዓለም አቀፍ ተሸላሚ የሆነችው ሊንዳ ሬይ (Linda Rey)ቀደም ሲል በራሷ አንደበት እንዳለችው “መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች የግል ሃሳብና ፍላጎትን የሚያስተጋቡ አይደሉም። ሙያውን የሚያከብር፣ ለዘርፉ ክብር ያለውና በሥራው ኃላፊነት የሚሰማው ጋዜጠኛም የራሱን አስተሳሰብ ከሚያስተላልፈው ዘገባ ነጥሎ የሚያቀርብ ነው”።
በጋዜጠኝነት መርሕ እና ሥነምግባር ከአድሎ መንጻት የሁሉ መሠረትና ማጠንጠኛ ነው። በቃለ ምልልስ ወቅት አንድ ጥያቄ አቅራቢ ጋዜጠኛ Interviewer አድሎአዊ በሚመስል መልኩ ስሜታዊነት የታከለበት ጥያቄን ማቅረብ የሙያው ሥነምግባር የሚፈቅደው አይደለም። ጥያቄ ለሚያቀርብለት ተጠያቂ /Interviewee/ እንግዳ ክብር መስጠት እጅጉን ወሳኝ ነው። ሃሳቡን ሳይጨርስ ማቋረጥ ፈፅሞ አይገባም።
ሲኤን ኤን በአንፃሩ በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ የጋዜጠኝነት መርሕና ሥነ ምግባር በግልፅ ጥሶ አሳይቶናል። በተንሸዋረረ አድሎአዊ እይታ ከጥያቄ ይልቅ ፍረጃዎችን ሲያዥጎደጉድ፣ ኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን የሐሰት ዘገባ ለመሸፋፈን ሲጥር ታይታል።
በእያንዳንዱ ጥያቄዎች ለአሸባሪው ቡድን ሕወሓት ያደላ አቋም እንዳለው በግልፅ አሳይቷል። መንግሥት የሰራቸውን መልካም ሥራዎች እንዳይሰሙ፣ አሸባሪው ሕውሓት የሚያደርሰው ጭፍጨፋ ለዓለም እንዳይታይና እንዳይሰማ የቢልለኔ /የእንግዳዋን/ ምላሽ ማቋረጥን ጨምሮ ግልፅ አፈና ሲያደርግ ተስተውሏል።
ተግባሩ እጅጉን የሚያበሳጭና ቃለ ምልልሱን እስከማቋረጥ የሚያስወስን ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም በአንፃሩ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ በመስጠት ኢትዮጵያና ሕዝብን አኩርተዋል።በዓለም አቀፍ አደባባይ ታላቅ ገድል ፈጽማለች።
አገራዊ እውነታውን ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ለማሳየት የሄደችበት የትዕግስት መንገድ፤ እንደ አገር እውነታችን በዓለም አቀፍ አደባባይ የተሻለ ስፍራ እንዲያገኝ ያስቻለ ነው። የተገኘውን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ያስቻለ ነው።
በቃለ ምልልሱም ሲ.ኤን.ኤን ከሙያዊ ሥነ ምግባርና ከዓለም አቀፉ የሚዲያ አሠራር ሕግ ባፈነገጠ መንገድ ለአንድ ወገን የሚያጋድሉ አድሏዊ ብሎም ሆን ተብለው የተቀነባበሩ የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር እየሠራ ስለመሆኑ በተጨባጭ ማየት ተችሏል።
ቢልለኔ በተጠናና በታቀደ መንገድ ሲ.ኤን.ኤን በኢትዮጵያና በሕዝብ በተመረጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሰነዘራቸውን የምዕራባውያኑን ሴራ ያነገቡ በመርዝ የተቀቡ የቃላት ጦሮችንም በሚገባ በመመከት ትክክለኛውንና እውነተኛውን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና አቋም የዓለም ሕዝብ እንዲያውቅ በሚያስችል መንገድ በጨዋ ደንብ ምላሽ ሰጥታለች ።ይህ አይነት የአደባባይ ተጋድሎ በሌሎችም የኢትዮጵያ ዜጎችና ወዳጆች መደገም ያለበት አኩሪ ገድል ነው።
በርግጥ የምዕራብ ዓለም መገናኛ ብዙኃን በአሁን ወቅት ለምን በዚህ መልክ ስሜታዊና ግልፅ ደጋፊ እየሆኑ መታየት ጀመሩ የሚለውን ጥያቄ መቃኘት ያስፈልጋል። ለዚህ ጥያቄ መልሱ አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ይህም ኢትዮጵያን እንደ አገር እንዳትቀጥል የማድረግ ሴራ ነው።ተግባራቸውም አጎንባሽ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ የማስቀመጥ ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸውና አድሎአዊና ምንጊዜም ለአፍሪካዊ የሚቆም ብሎም ነፃነቱን የሚያስጠብቅ መሪና መንግሥት ሲፈጠር ማየት እንደማይፈልጉ ምስክር የሚሆን ነው።
ጥልቁ እውነት ጠላቶች እንቅልፍ አጥተው ሌት ተቀን ቢዶልቱም ኢትዮጵያና ሕዝቧ የቆሙበት የእውነትና የአንድነት አለት ጠንካራ በመሆኑ ዓላማቸውን ማስፈፀም አለመቻላቸውን ነው። በአሁን ወቅትም ኢትዮጵያውያን ለነጻነትና ሰላም በምንም ዋጋ የማይቀይሩት ሕይወታቸው ለመስጠት እንደማይሰስቱ እያስመሰከሩ ይገኛል።
በቀጣይም የመገናኛ ብዙኃኑ ሚዛን የሳቱ ሕልሞች በኢትዮጵያውያን ትብብርና ፅናት እየከሸፈ እንደሚቀጥል ጥርጥር የለውም። ይሑንና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለእውነት ለነፃነትና ለአትንኩኝ ባይነት የሚያደርጉት ፍልሚያ ይበልጡን መቀጠል ይኖርበታል።
ተፅዕኖአቸውን ተጋፍጠው በፅናት የቆሙ አገራትም ምሳሌዎቻችን ሊሆኑ ይችላሉ። ኢራንና ቱርክ ላይ ያልተወረወረባቸው ድንጋይ የለም። ይሑንና የሚወረወርባቸው ድንጋይ ሰብስበው የፀና ግንብ መገንባት ችለዋል። ከመፍረክረክ ይልቅ ጠንካራ ሆነው ከፍ ብለው ታይተዋል። ጠላቶቻቸውን አሳፍረዋል። አንበርክከዋል። ኢትዮጵያም ይህንኑ ታሪክ በማድረግ ጠላቶቻችን በማሳፈር ወደ ከፍታዋ የመመለሷ እውነታ የነገ ታሪካችን አካል መሆኑ የማይቀር ነው ።
እንደ አገር አሁን ያጋጠመንን ችግር ለመሻገር ከበፊቱ በተሻለ መልኩ እጃችንን ልንሰብስብ ይገባናል። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር› እንዲሉ እኛ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የምናምነው ሁሉ ለአገራችን ክብር እና ሞገስ እንዲሁም ብልጽግና በጋራ መረባረብ ይኖርብናል።
አሁን የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን የከፈቱብን ጥቁር ፕሮፖጋንዳ ሕዝባችንንና ሠራዊቱን በስነ ልቦና ዘመቻ ለመፍታት መሆኑን በአግባቡ መረዳት፤ ውሸታቸውን ሰምቶ ከመደናገጥ መቆጠብ ያስፈልጋል። ይህ በማድረግም በየዘመናቱ የተነሱ ጠላቶቿን በሕዝቦቿ አንድነትና የጋራ ክንድ እያሳፈረች ዘመናትን የተሻገረችውና ለጥቁሮች የነፃነት ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያን፣ ዛሬም እንደ ትላንቱ ከገጠማት ወቅታዊ ፈተና በብቃት ማሻገር ይቻላል።
ለዚህም እንደ ቢልለኔ አይነት በዓለም አቀፍ አደባባይ ስለ አገር በጽናት፣ በጀግንነትና በልበሙሉነት የሚሞግቱ ጀግኖችን በብዛት መፍጠር ይገባናል ።ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ ባለው አቅምና እውቀት ሰልፉን መቀላቀል ይኖርበታል ።ወቅቱ ጀግኖች የሚፈጠሩበት በመሆኑ ሁሉም ለአገሩ ጀግና ሆኖ በታሪክ ስፍራ ለማግኘት ይህንን አጋጣሚ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል ።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም