በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከጥቅምት 20 እስከ ጥቅምት 30/2014ዓ.ም የተካሄደው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት(ሴካፋ) ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ውድድር ትናንት ተጠናቋል። ኢትዮጵያም አስተናጋጇን አገር በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት ሦስት ለሁለት በመርታት የውድድሩ ቻምፒዮን ሆናለች፡፡
ያልተጠበቀ ውጤት በተመዘገበበት ጨዋታ ዩጋንዳ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ለዜሮ እየመራች ወደ እረፍት ያመራች ሲሆን፤ የሉሲዎቹ ተተኪዎች በሁለተኛው አጋማሽ በሜዳዋ የተጫወተችውን ዩጋንዳን ውጤት ቀልብሰው ቻምፒዮን ይሆናሉ የሚል ግምት አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ በዩጋንዳ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ጭምር የተደነቀ እንቅስቃሴ ያደረጉት የሉሲዎቹ ተተኪዎች ከሁለት ለዜሮ መመራት ተነስተው በሁለተኛው አጋማሽ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ዋንጫውን ለመሳም በቅተዋል፡፡ ረድኤት አስረሳኸኝ በ52ኛው ደቂቃ፣ አሪያት ኦዶንግ 80ኛው ደቂቃና ቱሪስት ለማ በ85ኛው ደቂቃ ግቦቹን ለኢትዮጵያ አስቆጥረዋል።
ይህም ከሁለት ሳምንት በፊት ዋናው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን(ሉሲዎቹ) ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በዩጋንዳ አቻቸው በአበበ ቢቂላ ስቴድየም በመለያ ምት ተሸንፈው ከውድድሩ የወጡበትን የሚያስቆጭ አጋጣሚ ያካካሰ ክስተት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ የውድድሩ ቻምፒዮን በመሆን ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ስትሆን ዩጋንዳና ታንዛኒያ የብርና የነሐሴ ሜዳሊያ በማጥለቅ ውድድሩን ቋጭተዋል፡፡
የዘንድሮው ውድድር ላይ ጥቂት አገራት ብቻ እንደመሳተፋቸው የውድድሩ ይዘት አሸናፊውን ለመለየት በምድብ ጨዋታዎች ሳይሆን አገራቱ በአምስቱ ጨዋታዎች በሰበሰቡት ነጥብ መሰረት ሆኗል። በዚህም ኢትዮጵያ ከትናንቱ ጨዋታ በፊት በአራቱ ጨዋታዎች ሙሉ አስራ ሁለት ነጥብ ሰብስባና አስራ አምስት ግቦችን አስቆጥራ እንዲሁም አንድ ተቆጥሮባት ቻምፒዮኑን ለመለየት ትናንት ለተካሄደው ወሳኝ ፍልሚያ ደርሳለች።
አስተናጋጇ ዩጋንዳ በበኩሏ በተመሳሳይ በአራቱም ጨዋታ አስራ ሁለት ነጥብ ሰብስባ ሃያ ግቦችን በማስቆጠር አንድም ጊዜ መረቧን ሳታስደፍር ኢትዮጵያን በስድስት ግብ በልጣ ቻምፒዮኑ ለሚለይበት ወሳኝ ጨዋታ ደርሳለች። ይህም ዩጋንዳ ቻምፒዮን ለመሆን ከትናንቱ ጨዋታ የአቻ ውጤት በቂዋ ሲሆን ኢትዮጵያ በአንጻሩ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆና ነበር ወደ ሜዳ የገባችው።
ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ በዋናው ብሔራዊ ቡድን ተመርጠው የተጫወቱተጨዋቾችን ያስመረጡ ሲሆን ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች ሁለት ሁለት ተጫዋቾች በቋሚ አስተላለፍ ውስጥ ማካተት ችለዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እየተመራ በመጀመሪያው ጨዋታ ኢትዮጵያ ጅቡቲን ሰባት ለ ዜሮ በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ የቻለች ሲሆን፣ በጨዋታው ረድኤት አስረሳኸኝ ሶስት ግቦችን አስቆጥራ ሐትሪክ ስትሰራ፣ ቱሪስት ለማ ሁለት ግቦችን፣ እፀገነት ግርማና ቤተልሔም በቀለ አንድ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። በሁለተኛው ጨዋታውም ከኤርትራ አቻው ጋር ያደረገውን ጨዋታ ሰፊ በሆነ የአምስት ለዜሮ ውጤት ማሸነፍችሏል።
በጅቡቲው ጨዋታ ሶስት ግቦችን ያስቆጠረችው ረድኤት አስረሳኸኝ ኤርትራ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፋለች። ቱሪስት ለማ፣ መሳይ ተመስገንና ብዙየሁ ታደሰ አንድ አንድ ግቦችን ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ሆነዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ሶስተኛ ጨዋታውን ከታንዛኒያ አቻው ጋር አድርጎ ሶስተኛ ድሉን ሲያስመዘግብ መሳይ ተመስገንና ንቦኝ የን ግቦችን አስቆጥረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከትናንቱ ጨዋታ በፊት በውድድሩ ብቸኛውን ግብ ያስተናገደውም በዚህ ጨዋታ ነበር። የዋንጫ ተፋላሚ መሆን የቻለውም ባለፈው ቅዳሜ ቡሩንዲን በአሪያት ኦዶንግ ብቸኛ ግብ አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት ረቶ ነው።
በዘንድሮው የሴካፋ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ውድድር አዘጋጇ ዩጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲና ቡሩንዲ የተሳተፉ ስድስት አገራት ሲሆኑ፤ ውድድሩ ባለፈው ነሐሴ ሊካሄድ ታስቦ እንደተራዘመ ይታወሳል። ይህ ውድድር ለመጨረሻ ጊዜ እኤአ 2019 ላይ በዩጋንዳ አዘጋጅነት ተካሂዶ ታንዛኒያ ኬንያን በፍጻሜ ጨዋታ አሸንፋ ዋንጫ ማንሳቷ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተካፋይ ሲሆን፤ የዩጋንዳ አቻው ለሁለተኛ ጊዜ ነው ተሳታፊ የሆነው። ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች በቀጣይ ወር በደቡብ አፍሪካ ለሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ ለማለፍ ባደረጉት ጨዋታ ተጋጣሚያቸው ላይ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ያሸነፉ ሲሆን ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ችለዋል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴት ብሔራዊ ቡድን በሴካፋው ከትናንቱ ጨዋታ በፊት 15 ግቦችን በማስቆጠር ከዩጋንዳ አቻው ቀጥሎ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ ብሔራዊ ቡድን ሲሆን አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ የብሔራዊ ቡድኑ የመከላከልም ይሁን የማጥቃት ጥንካሬ የሚያሳይ ነው ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 1/2014