ምላሱና ነፍሱ የተበከለው እኩይ ቡድን፤
በረሀ ተወልዶ በበረሀ አስተሳሰብ የጎለመሰው አሸባሪው ሕወሓት ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት ሲቆምር የኖረውና ዛሬም ድረስ እየቆመረ ያለው እዚያው በረሀ ውስጥ የተለማመደውን የሴራ ፖለቲካ ስለመሆኑ ተግባሩ ምስክር ነው። ይህ ቡድን በአንድ ቦታ ተተክሎ የቆመ ግዑዝ የሰብዓዊያን ሐውልቶች ስብስብ ሲሆን አብዛኞቹ አባላቱም ዓይን እያላቸው የማያዩ፣ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙና አንደበት እያላቸው የማይናገሩ አቅመ ቢስ “ጣዖታት” ናቸው።
ባይሆንማ ኖሮ “አደብ ግዙ!”፣ ከማንጋፋው የሕዝብ ማዕበል ጋር መላተሙ ይቅርብን፣ ያለ ዓላማ የምናስጨርሰው ነፍስ “ለኩነኔ እንዳይዳርገንም እንጠንቀቅ” በማለት ቀልባቸውን ሰብስበው መሪዎቻቸውን በገሰጹ ነበር መቼስ ምኞት አይከለከልም አይደል፤ እነርሱ ሊሞክሩት የማይችሉትን ሃሳብ ብናዋጣላቸው በተንኮል የሰከረው አእምሯቸው በትዕቢት እንደማይገነፍል ተስፋ እናደርጋለን።
ይህ ቡድን ነባር ታሪኩ እንዳለ ሆኖ አሁን እያስተዋልን ያለነው ተግባሩ እንደሚመሰክረው ከተበከለው ምላሱና በደም ከጨቀየው ነፍሱ ውስጥ ሲመነጭ የኖረውና እየመነጨ ያለው የጥፋቱ ክርፋት የክፋቱን ጥግ በሚገባ የሚያሳይ ነው ይህንን እውነታ ለመረዳት ያለፉትን ድርጊቶቹንና በአሁኑ ወቅትም እየፈጸማቸው ያሉትን ሰይጣናዊ ተግባራቱን ብቻ መለስ ብሎ በማየት ሐቁን ማረጋገጥ ይቻላል።
በፕሮፖጋንዳው እየተነሰነሰ ያለው መርዝ ዞሮ ዞሮ ቡድኑን ራሱንና “እወክለዋለሁ” የሚለውን ሕዝብ እንደምን እንደሚበክልና “የስራይ-ፖለቲካው” ጥንስስ ከትውልድ ትውልድ እያመረቀዘ እንደሚኖር አልተረዳውም ለማለት ያዳግታልበሕዝቡ መካከል የተዘራውና ሥር የሰደደው ደዌ ይፈወስ ቢባል እንኳን ሰንኮፉ በቀላሉ ተነቅሎ እንደማይወጣ ያለመጠርጠሩ ቡድኑን እንመራለን የሚሉት ጥቂት ግለሰቦች ምን ያህል የአስተሳሰብ ድኩማን እንደሆኑና አርቆ ለማሰብም ልበ ስውራን መሆናቸው በሚገባ እየተስተዋለ ነው።
“የምንደሰኩረው የምንመራውን ሕዝብ እምነትና አመለካከት ወክለን ነው” እየተባለ ባልተገራ አንደበት፣ ባልሰከነ ሰብዕናና በዘቀጠ የቋንቋ አጠቃቀም ከአፈ ቀላጤዎቹ እየተሰነዘሩ ካሉት የፕሮፖጋንዳ አስኳል ሃሳቦች መካከል “ሂሳብ እናወራርዳለን” የሚለው ትርክትና ዛቻ በቀዳሚነት ይጠቀሳል“ሂሳቡን” ቀድሞ ከማን ጋር እንደሚያወራርዱ፣ ቀጥሎ ወደዬት እንደሚሸጋገሩና ሠልሰውም ከማን ጋር እንደሚጋፈጡ በግልጽ ቋንቋ መናገር ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ምክንያቱና ምንነቱ ተብራርቶ እንዲገለጽልን ያልተፈለገው “ይህ ያልተወራረደ ሂሳብ ጉዳይ” የስሌቱ ቀመር፣ ዓይነቱና ተመኑ ምን ያህል እንደሆነ የገለጹልን በተዳፈሩበት የወረራ ድርጊታቸው አማካይነት ነው“ሾላ በድፍኑ” እንዲሉ “ያልተወራረደ” የሚባለው የታሪክም ይሁን የነበር እውነታዎችን የፈጠራ ዕዳ የኢትዮጵያ ሕዝብ “የሾላውን ፍሬ” ፈልቅቆ በውስጡ የታጀሉትን “ትላትል ሃሳቦች” ቀደም ብሎ ምንነታቸውን ስለተረዳ እጅግም አልተጨነቀበትምአልገባቸው ከሆነ ይግባቸውእንዳልገባቸው ለመምሰል ልባቸውን የሚያደነድኑ ከሆነም እየቀመሱ ያሉት በትር ጭርሱኑ ወደ ትቢያ ለውጧቸው መታሰቢያው መቃብራቸው ላይ ይቆምላቸዋልነፍሳቸው ደግሞ “እስከ ሲኦል ድረስም ቢሆን እንጦሮጦስ እንወርዳለን” ብለው ወደ ተመኙት ሰይጣናዊ ግዛት ይላክላቸዋል።
ይልቅዬ ያልተወራረዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነታዎች፤ ሕወሓት ይሉት የስግብግቦች፣ የጨካኞችና የቂመኞች ቡድን የኢትዮጵያን ሕዝብ በውሸቱ ያራደና ግራ ያጋባ መስሎት ዛሬ “በእምበር ተጋዳላይ” ዘፈን አጅቦ የሚያስተጋባው ፕሮፓጋንዳ ነገ የቀብሩ ማስፈጸሚያ ሙሾ እንደሚሆን የገባው አይመስልምገብቶት ከሆነም እያዜመ ያለው ከጣዕረ ሞቱ ጋር እየተላፋ ይመስላል።
ለሦስት አሥርተ ዓመታት ያህል የኢትዮጵያን ሀብት እየጋጠ ሲፈነጭ መኖሩ ለቡድኑና ለጀሌዎቹ ቁብ አልሰጣቸውምበአደባባይና በግላጭ የእኔ የሚላቸውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተጠቃሚ ጋሻ ጃግሬዎቹን እያሳበጠ ሲያደልባቸው እንደኖረ የተዘነጋ መስሎት ከሆነም ተሳስቷል ከኪዮስክ እስከ ባንክ፣ ከልማት ብድር እስከ ርዳታ ርጥባን ለአገሪቱ የሚመጣው የገንዘብ ፍሰት ለቡድኑና የእርሱ ብቻ በሆኑት የኪስ ቻናል አማካይነት ሲፈስ መኖሩ የተረሳ ከመሰለው ተሳስቷል ያልገባን መስሎት ከሆነም የጅልነቱ ጥግ ማሳያ ስለሆነ መልሳችን “ትዝብት ውረስ!” ይሆናል ዜጎችን በቋንቋ፣ በብሔርና በድንበር እያናከሰ የሚፈሰውን ደም በዋንጫ ሲጎነጭ መኖሩ እንኳንስ መከራው የወደቀበት የዛሬው ትውልድ ይቅርና መፃኢው ትውልድና ታሪክም በጭራሽ ሊዘነጉት የሚችሉት ዓይነት “እርም” እንዳልሆነ ሊገነዘበው ይገባል።
የጭካኔ አራራውን በግላጭና በአደባባይ ሲያረካ የኖረባቸው የኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶቹ አሻራ ከመደብዘዝ ይልቅ በደማቁ እየታተመ እንዳለም ቢያውቀው አይከፋም ይህ አረመኔ ቡድን ከሰማይ በታችና ከምድር በላይ የፈጸማቸው የግፍ ዓይነቶች በዓይነት፣ በባህርይና በአተገባበርም ከአሁን ቀደም በሌሎች አገራት ታሪኮች ውስጥ ስለመፈጸማቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ቡድኑ ባለፉት ሦስት ዓመታትና በተለይም ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ያሉትን ክህደቶችና የግፍ ጭካኔዎች ዘንግቶት ከሆነ በጥቂቱ እናስታውሰው ለሉዓላዊነታችን ክብርና በተለይም ለትግራይ ክልል የመከላከያ ሠራዊታችን ለፈጸማቸው የጀግንነትና የሰብዓዊነት አገልግሎቱ የተከፈለው ዋጋ ምን ነበር? በየትኛውስ አገር መሰል ግፍ ተፈጽሞ በምን የሕግ አንቀጽ ተዳኘ? እንኳስ መሰል ግፎች ቀርተው አንድም ተቀራራቢ ታሪክ በዓለማችን የየትኛውም አህጉር ተፈጽሞ ስለማያውቅ የየአገሩ የፍትሕ ሥርዓት አስፈጻሚዎች የወንጀለኛ መቅጫና መቀጣጫ አንቀጽ አልቀመሩለትምወደፊት መነሻ የሚሆናቸውን ተሞክሮ የሚያመሳክሩት ወንጀለኝነት ብቻውን ከማይገልጸው ከዚህ ቡድን ድርጊት ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን።
ቀደም ሲል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች፤ ዛሬ ደግሞ በጠራራ ፀሐይ ይህ ግፈኛ ቡድን በወረራቸው በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የጨፈጨፋቸው ዜጎች ደም ቢሰፈር ምን ያህል ሊትር ሊወጣው ይችላል? የፈሰሰው የንጹሐን እምባስ የጋሎኑ ስሌት ምን ያህል ይሆናል? ያወደመው የግለሰቦች ንብረት፣ የዘረፈው የሕዝብና የአገር ሀብትስ መጠኑና ተመኑ ስንት ነው? የመከራው ጫና ያለርህራሄ ወድቆባቸው የተደፈሩት፣ የተኮላሹትና ለሥነልቦና ቀውስ ተዳርገው ወደ ፀባዖት የቃተቱት ዜጎች የጭንቀት ኡኡታ በኦዲዮ ዴሲቢል ቢለካ ስንት ዩኒት ይቆጠርለታል? ከቤት ንብረታቸው፣ ከቀዬና ከሠፈራቸው፣ ከባህልና ከእምነታቸው ተፈናቅለው ተንከራታች የሆኑ ዜጎች ቁጥር በእርግጡ ምን ያህል ነው? በወረራው ምክንያት ሳይታረስ ጦም ያደረው መሬትና መመረት የሚገባው አዝመራ ልኬትና መጠን በምን መስፈርት ቢገለጽ እውነቱ በይፋ ሊታወቅ ይችላል?
የአሸባሪው ቡድን አፈ ቀላጤዎችና ብረት ነክሰው ከሕዝብ ጋር እየተፋለሙ ያሉት የወንበዴዎቹ ጀሌዎች “ሂሳብ እናወራርዳለን” ብለው የሚፎክሩት እነዚህን መሰል የጥፋት ጀብዱ አደባባይ ይዘው ለመከራከር ከሆነ በእርግጥም “ትክክል ናቸው።” የኢትዮጵያ ሕዝብ አደባባይ ላይ ቆሞ በአንድ ድምጽ ለመፋረድ ዐይኑን ሳያሽ ፈቃደኛነቱን ሊገልጽላቸው ይችላልየሚወራረደው የሂሳብ ድምር ግን የእነርሱን ጠብመንጃ አፍ ለማዘጋትና የአንዳንድ ዓለም አቀፍ አሽቃባጭ መሪዎችን፣ የአዞ እምባ የሚያፈሱትን ያገባናል ባዮችና የመርዘኛ ፕሮፖጋንዳቸው ዋነኛ መነስነሻ የሆኑትን ሚዲያዎች ለማስደሰት ሳይሆን ቡድኑንና እኩይ ዓላማውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰንኮፉንና ዕጩን ቀብሮ ለመገላገል መሆኑን በሚገባ ሊገነዘቡት ይገባል።
ስለዚህም ነው ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር ዳር ሆ ብሎ በመትመም አደባባዮችን የሞላውከአገሬ በፊት እኔ ልቅደም በማለት ለፍልሚያው እየተሽቀዳደመ ያለውም ስለዚሁ ነው። ከሕዝባዊ ሠራዊት ጋር እየተላተመ ያለው ወራሪ ይልቅስ የመቀበሪያውን ጉድጓድ ቶሎ ቶሎ ምሶ ቢገላገል ስለሚበጀው “አማካሪዎች” ነን ባዮቹ አገራትና የዓለም አቀፍ ሚዲያ አካላት “የሐውልቱን መታሰቢያ” ቶሎ ቶሎ አንጸው ቢያቆሙለት የተሻለ ይሆናል። የዚህ እኩይ ቡድን የመጨረሻ መደምደሚያ “ሞት ላይቀርለት ይሁዳ ምክንያት ሆነበት” ይሉትን ብሂል ያስታውሰናል።
“ላግባሽ ያለ ላያገባሽ፤ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ፤”
ይህ አሸባሪ የጥፋት ቡድን ክህደት የህልውናው የደም ሥር፣ ጭካኔው የማንነቱ መታወቂያ፣ ዘራፊነቱ የተቆራኘው ባህል ስለመሆኑ ተደጋግሞ ሲጠቀስ ኖሯል። ይሉኝታ ይሉት ነገር ጭራሽ ያልዞረበት ስለመሆኑም ድርጊቱ አፍ አውጥቶ አዋጅ ያስተጋባል“ግፋ በለው” እያሉ በግላጭና በድብቅ የሚያንደረድሩት አገራትና ቡድኖች ለምን ዓላማ እንደሚጋልቡበት እንኳን አለማወቁ የመሪዎቹን መታወር ፍንትው አድርጎ ያሳያል“ልበ እውሩ የሚመራው ሠራዊትም መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ውጤቱን እያየን ነው።
“ላግባሽ ያለ ላያገባሽ…” እንዲል ብሂላችን፤ ከሩቅና ከቅርብ እየሆኑ “ከሕዝብ ማዕበል ጋር እንዲጋፈጥ” ሰባራ ጀልባ የሚያቀርቡለት አካላት ነገ በውድቀቱ እንደሚክዱትና “የት እናውቅህና” እንደሚሉት ያለመገንዘቡ ለቡድኑ ልበ-ቅልነት ጥሩ ማሳያ ነው። የእኔ የሚላቸውና በተለያዩ የዓለም ክፍል ያሉት “የሩቅ አገራት ቁራዎቹም” በራሳቸው የጠብ ደጋሾች እየፈረሰ ያለው “የሕዝባቸው ጎጆ” ደንታ ሳይሰጣቸው የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ መንጫጫታቸው ፋይዳ እንደሌውና ምንም የጎላ ለውጥ እንደማያመጣ ቢመራቸውም እንደ ዕንቆቆ እየተጋቱት ነውእነርሱ በበጋ ወራት በባህር ዳርቻዎች፣ በክረምት ወራት ደግሞ በማሞቂያ ማሽኖች “ነፍስና ሥጋቸውን እየተንከባከቡ” ምስኪኑና አዙሮ ለማየት አቅም የሌለው ወገናቸው ሞትን ተጋፍጦ እንዲዋደቅ እንደ አጋሰስ “በቀረርቶ እያጀገኑ ያሳብዱታል።”
የትግራይ ሕዝብም ቢሆን ቆም ብሎ እውነታውን ለመመርመር መንፈሱን ያረጋጋ አይመስልም። አልፎም ተርፎም ወራሪውን ኃይል እየመረቀ ለዘረፋና ለውድመት መላኩ ለምንና በምን ምክንያት እንደሆነ ይጠፋዋል ብሎ ለማመን በእጅጉ ያዳግታል“ሂሳብ ላወራርድ ነው!” ብሎ ጦር ሰብቆ ወደ ሰላማዊ ክልሎች ሲተም “ጽና! ለምን ምክንያት?” ብሎ ለመጠየቅ ያለመድፈሩም እጅጉን ያስተዛዝባል።
ቀድመን የጠየቅነውን የመነሻ ጥያቄ በመደም ደሚያችን ላይ ደግመን እናስታውስ አሸባሪው ቡድን “ሂሳብ ላወራርድ ነው ብሎ” ለወረራ የዘመተው ከማንና ለምን ጉዳይ ነው? ሀገር በማፈራረስ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብሎ አስቦ ከሆነ በረሀ ላይ አምጦ የወለደው የመነሻ ማኒፌስቶውም ይሁን በመንግሥትነት መንበር ላይ እያለ ሲጎነጉን የኖረው ሴራ እንደ ከሸፈና እንደመከነ ሊረዳ ይገባል። ይህቺ የዛሬዋ ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ አንገት ደፍታ “እህህ!” የምትል እንዳልሆነም ይረዳውሕዝቡም አንጀቱ እያረረ “ተው ቻለው ሆዴ” እያለ እንደማያንጎራጉር አጥብቆ ይገንዘብ።
የታሪክ ሂሳብ ለማወራረድ ከሆነ ሽንፈቱን አይችለውም የታሪክ መዛግብቱ የተገለጡ ዕለት ብዙ እባጮች እያመረቀዙ ስለሚሸቱ የቡድኑ መሪዎችም ሆኑ “ተማርን ባይ የትግራይ ልሂቃን” ደግመው ደጋግመው ቢያስቡበትና ሕዝቡን ለመከራ ባይዳርጉት ይበጃል። አሸባሪው ቡድን የተሰጠውን የምህረት ጸጋ ገፍቶ በመጣል ያንኮታኮተው “የመሰናበቻው ጣዕረ ሞት ጥሪ በል በል ብሎት ነው።” ኢትዮጵያ ታግሳና ልቧን አስፍታ እየተወጋችና እየተዘበተባት መስቀሏን ተሸክማ የምትጓዝበትን የጎልጎታ ጉዞ በቃኝ ብላ ካቆመች ሰነባብቷል።
የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህ የይሁዳ ውላጅ ቡድን ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ መቀጣጫ ማድረግ ብቻ ነውሕዝቧም ከዚህ በኋላ ደም መጣጩ የወያኔ ትኋን እንደማይሰለጥንበት ተማምሎ ጨክኗል“ሞት ላይቀር አሟሟቴን አሳምርልኝ” የሚባልበት ዕድልም አብቅቷልስለዚህም ወያኔ አወራርደዋለሁ ያለው ታሪክ በራሱ ውርደት እየተጠናቀቀ ስለሆነ አገሬ በቅርቡ የድል ብሥራት አብስራ በልጆቿ የድል ዜማ ልትደምቅ ዋዜማው ላይ ነች።
ድል ለሕዝባችን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 1/2014