በአሜሪካ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ላለንበት ስልጡን ዘመን የማይመጥን አንድ ነውር ሥርዓት አለ፤ እርሱም በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት ነው። ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ለዘመናት በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለፈች ሀገር ናት። በዚህ የከሸፈና የተበላሸ አስተሳሰብ የብዙ አገራትን እድልና ራዕይ አምክናለች። የዛሬ ሥልጣኔዋና ዘመናዊነቷም በዚህ ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት የተገኘ ነው። አሜሪካን በተመለከተ ብዙዎች የማያውቁት አንድ ምስጢር አለ።
በእርግጥ ስረ መሰረቷን ለመረመረ ሰው ብዙ ድብቅ ሴራዎችን ማወቅ ይቻለዋል። አሁን ላይ አገረ አሜሪካ በቀጥተኛና እውነትነት በተላበሰ አካሄድ ካገኘችው የሥልጣኔና የብልጽግና ትርፍ ይልቅ በሌሎች አገር ጣልቃ ገብታ ያገኘችው ትርፍ ይበልጣል ባይ ነኝ። ትርፎቿ በሌሎች አገራት ውድቀትና ጉስቁልና የተገኙ ናቸው። እድገትና ሥልጣኔዋ ሌሎች አገራትን በማስራብና በማስጨነቅ ያጋበሰችው ነው። ሃይሏና ጥንካሬዋ ከሌሎች አገራት የወሰደችው በትረ አሮን ነው።
የዛሬ ሁሉ ነገሯ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ጨዋ መስላ በመግባት ያጋበሰችው የሴራ ትርፍ ነው። አሁን ላይ አሜሪካና አሜሪካውያን ስልጡን አላዋቂዎች ናቸው እላለሁ። ስር በሰደደ የእኔነት መንፈስ የድሃ አገራትን ሰላምና እርምጃ በማደናቀፍ የበላይነታቸውን ለማስቀጠል የሚታትሩ አገርና ህዝቦች ናቸው።
ዛሬ ላይ አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን አፍቅራ የምትሰቃየውም ለዚህ ነው። እኔ በግሌ የአሸባሪው ሕወሓትና የአሜሪካ ፍቅር ያስደንቀኛል። የክፋት ፍቅር ሲያስደንቀኝ ይሄ የመጀመሪያዬ ነው። ምናለ ለመልካም ነገር እንዲህ ቢፋቀሩ እያልኩ … ምን ነበር አገርና ሕዝብን ከችግር ለማውጣት ቢዋደዱ እያልኩ እገረማለሁ … መቋጫ የሌለው ግርምት … ፍቅር ቅዱስ ነገር እንደሆነ ነበር የማውቀው።
የሁለቱን ፍቅር ስመለከት ግን ሰይጣናዊ ፍቅርም እንዳለ ለማወቅ ቻልኩኝ። እንዳልኩትም የሁለቱ ፍቅር ሰይጣናዊ ፍቅር ነው። ‹‹ምክንያት›› ካላችሁኝ እንዲህ እላችኋለሁ። በሁለቱም ልብ ውስጥ ክፋት እንጂ መልካምነት የለም። ውሸት እንጂ ሀቅ የለም። ነፍሶቻቸው የተፈላለጉት ለሌሎች መከራ ነው። እኔ የማውቀው ፍቅር የሰው ልጅ ለመልካም ነገር ሲወዳጅና ሲፋቀር ነው። እኔ የማውቀው ፍቅር አንዱ የሌላውን ስቃይ ሲሰቃይ ነው። በእነርሱ ውስጥ ግን ይሄ የለም።
ከትናንት እስከዛሬ አገር ለማፍረስ የተፋቀሩ ናቸው። ከትናንት እስከዛሬ ሕዝብ ለማስጨነቅ የተዋደዱ ናቸው። ዘመናቸውን ሙሉ ለክፋት የተባበሩና ከሃጢያት የተቃቀፉ ናቸው። እንዲህ አይነት ፍቅር ታውቃላችሁ? እኔ አላውቅም፤ እርግጠኛ ነኝ እናንተም አታውቁም። እኔ የማውቀው እናንተም የምታውቁት ፍቅር ለሌላው የመኖርን ፍቅር ነው። ፍቅር ለሌሎች መኖር..ለሌሎች መጎሳቆል.. ለሌሎችመልፋት ነው። የእነዚህ ጥንድ ቡድን ፍቅር ግን በሌሎች ደም መኖር፣ በሌሎች ላብ መበልጸግ፣ በሌሎች እንባ ቤታቸውን መስራት ነው።
አሜሪካ ለአሸባሪው ሕወሓት ያላት ፍቅር ይገርመኛል…አንዳንዴ ምናለ እውነት የናፈቀውን፣ ፍትህ የሚፈልገውን ኢትዮጵያን ሕዝብ ላመል ብታፈቅረው እላለሁ። ሰላም ርቆት፣ ድህነት ደቁሶት በቀን ሶስት ጊዜ መብላት ያቃተውንና ለውጥ የሚፈልገውን ማሕበረሰብ ብታየውም እላለሁ።
አሜሪካን ሳስብ የሰብዓዊነት ጥጉ ይጠፋኛል። ሰው የመሆን ትርጉሙ ይሰወርብኛል። አንዲት ሃያል አገር አንድን ወንበዴና ሸረኛ ቡድን አፍቅራ እውነት በናፈቀው ሕዝብ ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆና ሳይ እውነት የት ሄደ እላለሁ። በመግደል የኖረን አንድ ሰውበላ ቡድን አይዞህ እላለሁ እያለች ስታቅራራ ሳይ እውነት ትጎድፍብኛለች። ፍትህ ትሰወርብኛለች።
አንድን ሲሰርቅና ሲዋሽ ሲያወናብድም የኖረን ከሀዲ ቡድን በመደገፍ አጀግና ፍትህ የራቀው ድሃ ሕዝብ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ስትሰናዳ ሳይ እውነት፣ እምነት፣ ፍትህና ሰብዓዊነት እንጦሮጦስ ይወርዱብኛል። አንድን የአገርና የሕዝብ ጠላት የሆነን አሸባሪ ቡድን ወደ ሥልጣን ለማምጣት መንከራተቷን ሳይ እግዜር የለም እንዴ እላለሁ። በድሃ ሕዝብ ላይ የእግዜር ዝምታ ያስጨንቀኛል። የጥጋበኛን እብሪት አይቶ ዝም የሚለው ፈጣሪ ትዕግስቱን አልደርስበት እላለሁ። በሕወሓትና በአሜሪካ የክፋት ፍቅር ኢትዮጵያ ስታለቅስ፣ ሕዝቦቿ ሲጎሳቆሉ ሳይ ምናለ እግዜርን በሆንኩ እላለሁ… አሜሪካንን ድምጥሟጧን ላጠፋት… እንደ ኖህ ዘመን ውሃ ላወርድባት… ለዘመናት በሰው ልጅ ላይ ላደረሰችው በደል የእጇን ልሰጣት እመኛለሁ።
የአሜሪካ ነገረ ሥራ ሁሉ ሰይጣናዊ ነው። በየትኛውም የእውቀት ሚዛን ብትመዝኑት አሸባሪው ሕወሓት የሚፈቀር ቡድን አይደለም። ብዙዎችን የገደለ፣ ብዙዎችን ያሳደደ፣ ብዙዎችን ያሰቃየ ቡድን ምኑ ይፈቀራል? አገር ሊያፈርስ፣ ታሪክ ሊያበላሽ ጫካ የገባ ቡድን ምን መልካም ሥብዕና አለውና ነው የሚወደደው? የትኛው ነፍስና ስጋ፣ የትኛው ልብና አእምሮ ነው በሕወሓት ፍቅር የሚወድቀው?
አሜሪካ ዓለም ላይ ብቸኛዋ ራስ ወዳድ ሀገር ትመስለኛለች። ደግሞም ናት! በእሷ የራስ ወዳድነት በትር ያልተመታ አገር የለም። የሰላም አለቃ መስላ መታየት ልማዷ ነው። አዛኝና ሩህሩህ መስላ መቅረብ ትችልበታለች፤ ፍጻሜዋ ግን እንደነገርኳችሁ ነው… ሰይጣናዊ! በየመንና በሶርያ እኩይ አሻራዋ አለ፤ በሊቢያና በላይበሪያ የክፋት እጇ አለ። የሰሞኑ የአፍጋኒስታን መከራ እንኳን በዚችው ራስ ወዳድ አገር የተፈጠረ ነው።
ዛሬ ላይ የአሸባሪው ሕወሓት ወደ ሥልጣን መመለስ ከአሜሪካና ከጥቂት ጠላት አገራት በቀር የሚጠቅመው የለም። የሕወሓት ቡድን ለአሜሪካ እጅግ የተመቸ ቡድን ነው። ይሄን ደግሞ ሁላችሁም የምታውቁት ሀቅ ነው። ባሳለፍናቸው 27 ዓመታት ውስጥ የባከኑ የማንነት ጥያቄዎቻችን ከዚህ እውነት ውስጥ የመነጩ ናቸው።
በነዚህ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በአሜሪካ መንግሥት ስትተዳደር እንደነበር ነው የማስበው።
ለስሙ መንግሥትና ሕገመንግሥት ያላት አገር ትሁን እንጂ ከሀዲው ሕወሓት ማንነታችንን ለባዕድ አገር ሸጦ የራሱን የፖለቲካ ትርፍ ሲቃርም ነበር። የዛሬው የአሜሪካ እዬዬ፣ የባይደን ያዙኝ ልቀቁኝ ምስጢሩ ይኸው ነው። ትናንትና በእኛ ብዙ አትርፋለች። በድሃ አገራት መከራና ጉስቁልና የራሷን ቤት ስትሞላ ነበር። ይሄን ሁሉ መደላድል የፈጠረላት ደግሞ የሕወሓት ቡድን ነበር። አሜሪካ ራሷን ለማቆም የማትፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። ሰይጣን አገር ቢኖረው ከሰይጣን ጋር ወዳጅነትን ፈጥራ ከሰይጣን የምትሰርቀው ብዙ ክፋትና ብዙ ሃጢያት ይኖራት ነበር።
አሁን አሁን በጣልቃ ገብነቷ ካተረፈችው ይልቅ የከሰረችው እየበዛ ነው። ምክንያቱም የትኛውም የዓለም አገር አሜሪካ ማለት ምን ማለት እንደሆነች በደንብ አውቋል። ሸሯና ተንኮሏ ሳይታወቅ ብዙ አገራትን ጎድታለች። ብዙዎችን ከታሪካቸው፣ ከባህልና ልማዳቸው አራቁታለች። ብዙዎችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የአስተሳሰብ ጥቅም አሳጥታለች። ሃይሏንና ኢኮኖሚዋን በመጠቀም ብዙዎችን ብዙ ነገር አድርጋለች።
በእኛም አገር እየሆነ ያለው ይሄ ነው። ግን ከረፈደ ነው፤ ምንም እንደማታመጣ ባወቅንበት ሰሞን መሆኑ እሷን እንጂ እኛን አይጎዳንም። እንደ ልማዷ የበግ ለምድ ለብሳ ተንኮል ያነገበ ስውር ዓላማዋን ለማስፈጸም ደፋ ቀና እያለች ነው። ነፍሰ በላውን የሕወሓት ቡድን አፍቅራ ጨርቋን ከጣለች ሰነባብታለች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ በብዙ ነገር ላይ የበረታበት ሰሞን ላይ ነው። የማንንም ጣልቃ ገብነት የሚቀበልበት ሥርዓት የለውም። አሁን ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት እየተጋ ነው። የአሜሪካ ቅጥረኛ የሆነው የሕወሓት ቡድን ዳግም ወደ ሥልጣን እንዲመጣ አይፈልግም። የአሜሪካንም ሴራ አውቆት ‹‹ለማያውቁሽ ታጠኚ›› በሏት።
አሜሪካ አሸባሪውን ሕወሓትን ያፈቀረችበም ምክንያት ለሁላችሁም ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንዳሻት የሚያደርጋት ሃይል ሕወሓት ብቻ ነው። ከሕወሓት ውጪ ጥቅሟን የሚያስከብርላት፣ ከሕወሓት ውጪ ቀይ ምንጣፍ የሚያነጥፍላት አሸርጋጅ ቡድን ስለሌለ ነው ዛሬ በፍቅሩ ስክር ብላ ከለውጡ መንግሥት ጋር ሆድና ጀርባ የሆነችው። እንደ ሕወሓት ለአሜሪካ የሚመችና አሜሪካውያንን የሚያዘባንን ቡድን በታሪክ የለም።
ከሕወሓት ጋር በጋራ የጠነሰሷቸው በርካታ የተንኮል ሴራዎች አላቸው በዚህና በመሳሰሉት የሕወሓትን ወደ ሥልጣን መመለስ አሜሪካ ትፈልገዋለች። ግን ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው። ሕወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪክ ሆኗል። ለዚህም ነው በሞቱ ዋዜማ ጥቁር ለብሳ ያየናት።
ራስ ወዳድነት መጨረሻው የት ጋ ነው? ሌሎችን እያስጨነቁ መክበር የነፍስ እርባና ይኖረው ይሆን? አሸበሪውን ሕወሓትንና አሜሪካን ጠይቁልኝ! አበቃሁ። ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 1/2014