ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የጥቃት እጁን ካሳረፈ በኋላ ልክ በዛሬዋ ዕለት ጥቅምት 30 ቀን ደግሞ ሳምሪን በሚል ስም የተደራጁ የትግራይ ወጣቶች ደቡብ ምዕራብ ትግራይ ማይካድራ ከተማ የሚኖሩ ከ1000 በላይ የአማራ ብሄር ተወላጆችን በግፍ ሲጨፈጭፍ ማደሩን የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሠመኮ) እንዳስታወቀ የማይዘነጋ ነው። በዚህ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በአካባቢው የሠፈረው የትግራይ ሚሊሺያና የክልሉ ፖሊስ በጭፍጨፋው ላይ ተባባሪ ነበሩ። ይህም የሕወሓትን ሴራ እና ተንኮል በግልጽ የሚያሳይ ነው።
የአሸባሪው ሕወሓት አሳፋሪው ግፉ በዚህ ሳያበቃ ሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ በአፋር ክልል ጋሊኮማ ላይ 100 ህፃናትን ጨምሮ 250 የሚሆኑ ንፁሃንን ነፍስ ማጥፋቱም የሚታወስ ነው። ይህ በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የተፈተመው ግልጽ የዘር ማጥፋት ተግባር ነው። ከዚያም ልክ በወሩ ነሀሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ከ200 በላይ ሰዎችና ብዛት ያለቸው ከብቶች ተጨፍጭፈዋል። ሰብሎችም ተቃጥለዋል።
የሕወሓት ግፍ በዚህ አያበቃም፤ ከአምስት ቀን በኋላም ጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ይህ አሸባሪ ቡድን ቆቦ ላይ ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ ከ600 በላይ የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ ንጹሃን ሰዎችን በግፍ ገድሏል። በቅርቡም መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ኮምቦልቻ ከተማ ላይ በ100 ወጣቶች ላይ ተመሳሳይ የግፍ ግድያ ፈጽሟል።
ለአብነት እነዚህን ጠቀስን እንጂ በአሸባሪው ሕወሓት ስፖንሰር አድራጊነት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስቃይና እንግልት ተዳርገዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮምያ ክልል ሸኔ በተባለ አሸባሪ ኃይል የተደረገው ብሄርን መሰረት ያደረገ የዘር ጭፍጨፋ ሆን ተብሎ የታቀደበት ሲሆን የሕወሓት ሽብርተኛ ቡድን ንጹኃን ዜጎች ሲገደሉ ቀንደኛ አስተባባሪ ነበር።
ይህ የሕወሓት ቡድን እየሰራ ያለው ወንጀል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ አሳዛኝ የሆነ ክስተት ነው። በቤንሻንጉል ክልልም የእዚህ አሸባሪ ቡድን ፈፃሚዎች ሕፃናትን ደፍረው በስለት ቆራርጠዋል፣ እናቶች አንገታቸው ተቆርጧል፣ ቤት ተዘግቶባቸው ከነቤታቸው ብዙዎች በእሳት እንዲቃጠሉ ተደርገዋል፣
በርግጥ ሕወሓት ከተመሰረተበት ቀን ጀምሮ በስውር እጁ የንጹሃንን ደም በከንቱ ሲያፈስና ለሞት ሲዳርግ 27 ዓመታትን በማን አለብኝነት በሥልጣን ላይ እንዳሻው ሲፈነጭ ቆይቷል። በ1983 ዓ.ም ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ አስቀድሞ በአማፂነት ይንቀሳቀስ የነበረው አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረም በኋላ አምባገነናዊ አመራሩን በይፋ ሲያራምደው የነበረ መሆኑም መረጃዎች ያስረዳሉ።
ከጽንሱ በደም የተነከረው የሕወሓት የግፍ እጅ በሕዝብ ላይ ያለው ጥላቻ ወደ አጥንት ውስጥ ዘልቆ የገባ መሆኑ እነዚህ የዘር ጭፍጨፋዎች፣ መፈናቀሎች፣ እንዲሁም ግፍና በደሎች ማሳያ ናቸው ሊባል ይችላል። የሕወሓት ሽብርተኛው ቡድን አገራዊ ያልሆነ የዘር ማጥፋት ስትራቴጂን መከተሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ አሳፋሪ ተግባር ነው። በዚሁ አሸባሪ ቡድን አቀናባሪነት ንጹኃን ሰዎች ራሳቸውን እንኳን መከላከል በማይችሉበት ደረጃ በውድቅት ሌሊት ግድያ ተፈጽሞባቸዋል፤ ቤታቸው ውስጥ ተቃጥለዋል፤ በአሰቃቂ ሁኔታ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል።
በአጠቃላይ ሕወሓት በእነዚህ ግፍና በደሎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሙሉ በሙሉ ተቆራርጧል። በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥነ ልቦና ዝግጅት በማድረግ በዘር ማጥፋት ወንጀል የተጠመቀውን አሸባሪ የሕወሓት ቡድን በቃህ ሊለው ይገባል። በዚህ ቡድን የተከሰቱ እጅግ ሰቅጣጭ የሆኑ ወንጀሎችና ግፎች አሁን በኋላ ግን ዳግመኛ በኢትዮጵያ ምድር ሊከሰቱም ሆነ ሊታዩ አይገባም!
አዲስ ዘመን ኅዳር 1/2014