የሃይማኖት ተቋማት ለሠላም መስፈን ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ሊሠሩ ይገባል !

ሠላምን በማስፈን እና በማጽናት ሂደት ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት የማይተካ አስተዋፅዖ አላቸው። ትውልዶችን በሞራልና በሥነ ምግባር በማነጽ ለራሳቸው፣ ለማኅበረሰባቸው እና ለሀገራቸው ሠላም አቅም በመሆን ሊያገለግሉ እንደሚችሉ በእጅጉ ይታመናል። ለዘመናት ሲሆን የነበረው እውነታም ይህንኑ የሚያጸና ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የየትኛውም ሃይማኖት አስተምሕሮ ሠላምን መሠረት ያደረገ እና የሚያጸና ነው። ግለሰቦች ከራሳቸውና ከማኅበረሰባቸው ጋር ያላቸውን የዕለት ተዕለት መስተጋብር ሠላማዊ እንዲሆን የሚያስችሉ ማኅበራዊ እሴቶችን ማጎልበት፣ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር የሁሉም ሃይማኖቶች የጋራ መገለጫ መሆኑም ይታወቃል።

የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴቶችን እንዲሁም ማኅበራዊ ትስስሮችን በማጠናከር በሠላም ግንባታውም ሆነ፣ በዜጎች መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ መከፋፈሎችን በማስወገድና ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት በማምጣት፣ ሀገረ መንግሥትን በማጽናት ሂደትም የሃይማኖት ተቋማት ተልዕኮ ከፍ ይላል።

ይህንን እውነታ ታሳቢ በማድረግም የሃይማኖት ተቋማት በየትኛውም ጊዜ እና ሁኔታ ውስጥ ሆነው ስለሠላም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማታቸው ተለምዷል። ችግሮችን ወይም አለመግባባቶችን በሠላማዊ መንገድ በውይይት እና በይቅርታ የመፍታት መንገድን በማስተማር በማኅበረሰብ ውስጥ ሠላም እንዲጸና አብዝተው ይተጋሉ።

ይህ ትጋታቸው በቀደሙት ዘመናትም ሆነ ዛሬ በዓለም አቀፍ፤ በሀገር አቀፍ እንዲሁም በማኅበረሰብ ደረጃ የሠላም እሴቶች ጸንተው ለመቆማቸው በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። በቀጣይ ለሚኖረውም የሰው ልጅ ሠላም ትልቅ አቅም ሆነው እንደሚያገለግሉም ይታመናል ።

በተለይም ባለንበት ዘመን የጽንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብ አብሮ በመኖር ላይ የተደቀነ ዓለም አቀፍ ስጋት ወይም አደጋ እየሆነ በመጣበት ሁኔታ፣ የሃይማኖት ተቋማት የጽንፈኝነትና የመከፋፈል ሀሳብን ለመቋቋም ትልቅ ጉልበት እንደሚሆኑ፤ ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት እንደሚኖራቸው ይገመታል።

በሃይማኖቶች መካካል መቻቻልን ከማጎልበት ጀምሮ፣ የሠላም እሴቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማጠናከር፣ ዓለም አሁን ላይ እያጋጠማት ካለው የሠላም እጦት ወጥታ የተረጋጋች እንድትሆን ተቋማቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ።

ራስ ወዳድነት እና ኢ-ፍትሐዊነት፤ ጽንፈኝነትና አሸባሪነት ለዓለም ሠላም እና ሁለንተናዊ እድገት ዋነኛ ፈተና እየሆኑ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ የሃይማኖት ተቋማት ራሳቸውን ከችግሩ አርቀው የመፍትሔው አካል መሆን፤ ችግሮች በሠላማዊ መንገድ በውይይት እና በድርድር የሚፈቱባቸውን መንገዶች ማመቻቸትና ማመላከት በሚኖርባቸው ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሚገኙ ተገንዝበው አጥብቀው ሊሠሩም ይገባል።

ለሠላም እና ለሠላም እሴቶች የተገዛ ትውልድ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ያላቸውን ትልቅ ሚና በአግባቡ መወጣት፣ የሕዝቦችን በሠላም አብሮ የመኖርና የመከባበር እሴቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል፣ እሴቶቹ ተጠብቀው ለትውልዶች እንዲተላለፉ ያላቸውን የማይተካ ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

የሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ ሠላም በመሆኑ ሠላም በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ፣ በሀገር አቀፍ፣ ከዛም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰፍን ለማድረግም የሃይማኖት ተቋማት ለዚህ የሚሆን በቂ ዝግጁነት በመፍጠር ተጨባጭ ተግባር ማከናወን አለባቸው። ከሠላም ጋር ካላቸው የጠበቀ ቁርኝት አኳያም፤ በሃይማኖታዊ አስተምሕሮታቸው ለሠላም ቀጣይነት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ፣ ይህንን የሚሸከም ተቋማዊ ምሕዳር ሊፈጥሩም ይገባል።

ለሁለንተናዊ ዓለም አቀፋዊ ሠላም መስፈን፤ የየትኛውም ሃይማኖት ተቋም ተከታይ ምዕመን፣ ራሱን የሠላም ሐዋርያ እድርጎ መንቀሳቀስ የሚያስችለውን ግለሰባዊ ማንነት መገንባት የሚያስችል ተቋማዊ ዝግጁነት በመፍጠር በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ የሃይማኖት ተቋማቱ አሁናዊ ዋንኛ ተልዕኮ መሆንም ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You