የትራንስፖርት ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ አማራጭ መፍትሄዎችን መተግበር ይገባል !

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች መኖራቸው ይታወቃል። በሀገሪቱ ያለው የተሽከርካሪ ብዛት ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በጎረቤታችን ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ብቻ ያለው የተሽከርካሪ ብዛት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ካለው የተሽከርካሪ ቁጥር በላይ ነው።

በኢትዮጵያ አብዛኛው ተሽከርካሪ የግልና በጣት የሚቆጠር ሰው የመጫን አቅም ያላቸው በመሆናቸው በተለይ በሥራ ሰዓት መውጫና መግቢያ ላይ የሚታየው የትራንስፖርት እጥረት እጅግ አሰልቺ እና የሚያማርር አድርጎታል። በከተማው ካለው የተሽከርካሪ ቁጥር ማነስ ጋር ተዳምሮም የመኪኖቹ እድሜ ጠገብ መሆን ደግሞ ሀገሪቱን ለተደራራቢ ወጪዎች ዳርገዋታል። የትራንስፖርት ፍሰቱ በተቀራራቢ ሰዓት መሆኑ በትራንስፖርቱ ላይ ጫናን አሳድሯል።

በአንድ በኩል ኅብረተሰቡ በቂ ትራንስፖርት አግኝቶ መድረስ የሚፈልግበት ቦታ በሰዓቱ እየደረሰ አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ እድሜ ጠገብ መኪናዎች የነዳጅ ፍጆታቸውም ከፍተኛ ነው። የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ባለበት ፣ የመኪና መለዋወጫ ወጪም ሰማይ በደረሰበት በዚህ ወቅት ሀገሪቱን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ዳርጓታል። እንዲሁም ያረጁ መኪኖች መብዛት ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ የሚፈጥረው ተጽዕኖም የላቀ ነው።

በሀገሪቱ ካሉት ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹ በአዲስ አበባ የሚገኙ ቢሆንም ዛሬም ድረስ የትራንስፖርት እጥረት በከተማዋ አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ይነሳል። በመሆኑም መንግሥት በከተማው የሚታየውን የትራንስፖርት እጥረት ለመፍታት ለመንግሥት ሠራተኞች የፐብሊክ ትራንስፖርት፣ ለተማሪዎች የተማሪ ሰርቪስ ለሌሎችም የከተማው ነዋሪዎች ቁጥሩ በርከት ያለ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት በማቅረብ ችግሩን ለመቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ሆኖም ችግሩ ሊቀረፍ ስላልቻለ ሌሎች የግል ሠራተኞች ፣ ነጋዴዎች ፣ ተማሪዎች እና ሌሎችም በሚፈልጉት ሰዓት ወዳሰቡበት ቦታ ለመድረስ ፈተና ሆኖባቸዋል። ከቤታቸው ማልደው ወጥተውም ጊዜያቸውን ትራንስፖርት በመጠበቅ ለማባከን ተገድደዋል። በመሆኑም በትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የትራንስፖርት ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ አማራጭ መፍትሄዎችን መፈለግ የግድ ይላል።

ይሄውም በአንድ ጊዜ በቁጥር በርከት ያሉ ሰዎችን ማጓጓዝ የሚችሉ የሕዝብ ትራንስፖርት ማብዛት ፣ የቀላል ባቡር አገልግሎትን ማስፋፋት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የነዳጅ ወጪን በማስቀረት የካርቦን ልቀትን በመቆጣጠር ለማይበገር የአየር ንብረት አስተዋጽኦ የሚያደርገውን በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የሕዝብ ትራንስፖርትን ማስፋፋት ያስፈልጋል።

ይህም አንድም ሀገሪቱን ለነዳጅ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን፣ የአየር ብክለትን መቆጣጠር እንዲሁም ዓለም የደረሰበትንና በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠቃሚ ለመሆን ያግዛል። ይህም አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ያሰፋሉ። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ በተለይም ለእኛ ሀገር ጠቀሜታቸው ጉልህ ነው። በመሆኑም ዛሬ በአነስተኛ ደረጃ የተጀመረውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባትና በሀገር ውስጥ የመገጣጠም ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።

የነዳጅ ዋጋ መጨመር ያደጉትንም ሆኑ ታዳጊ ሀገራትን አማራጭ የትራንስፖርት ዘርፎችን እንዲያማትሩ እያስገደዳቸው ይገኛል። ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ነው። ቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በብዛት በመጠቀም ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛለች። ኢትዮጵያም የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እና በሀገር ውስጥም የመገጣጠም ሥራ እንዲሠራ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን አድርጋለች። ይህንን ዕድል በመጠቀም ጥቂትም ቢሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በመግባት ላይ ናቸው።

በትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የትራንስፖርት ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ጋራዦች፣ የባትሪ መሙያ ጣቢያዎች ፣ የባትሪ መሸጫ መደብሮችን ጎን ለጎን ማስፋትና ተጠቃሚውንም መለዋወጫዎችን እንደልብ አገኝ ይሆን? ከሚል ስጋት መታደግ ያስፈልጋል።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከጃፓኑ ዶዳይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጋር በኢትዮጵያ ዘላቂና አመቺ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል። ትብብሩ በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሞተር ብስክሌቶችን በስፋት ማቅረብ፤ የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ኤሌክትሪከ ተኮር ተሽከርካሪዎች ለመቀየር መሆኑ ተገልጿል።

ኩባንያው በቀጣይ በ12 ወራት ውስጥ እስከ 100 የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎችን በመትከል፤ የአጠቃቀም መረጃ በመሰብሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቋል። በሦስት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ ለሚገኙ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ተደራሽ የማድረግ ዓላማ አለው። አስተማማኝ የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎችን እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሠረተ ልማቶችን በማቅረብ የኢትዮጵያን የከተማ ትራንስፖርት ገጽታ ለመለወጥ ያለመ ነው። በመሆኑም ትብብሩ በፍጥነት ወደ ተግባር ሊቀየር ይገባል።

አሁን የሚታየውን የትራንስፖርት እጥረትን መፍታት የሚቻለው አማራጭና አዋጭ የትራንስፖርት አቅርቦቶችን በመወጠንና ፈጥኖ ወደሥራ በመግባት በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል የትራንስፖርት ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ አማራጭ መፍትሄዎችን ማጠናከርና ማስፋት ላይ አተኩሮ መሥራት ይገባዋል!

አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You