የቤኑና መንደር የለውጡ ሌላው ትሩፋት ነው!

ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከፍተኛ አቅም ካላቸው ሀገራት መካከል ትመደባለች ፤ ተስማሚ የአየር ጸባይ ፤ ውብ መልካምድር፤ የብዙ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ልዩ ልዩ ባህሎች መገኛ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤትም መሆኗም ይህን ያመላክታል።

የቀደምት ሥልጣኔ እና የረጀም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ያላትና የብዙዎችን ቀልብ የሚስቡ የታሪክ ትርክቶች ባለቤት ነች ፤ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶችን ቀድማ ማስተናገድ የቻለች ፤ የእምነት ተቋማቱ ምእመናንም ተቻችለው እና ተስማምተው ለዘመናት አብረው የኖሩባት ፤ ዛሬም የሚኖሩባት ሀገር ነች ።

ይሁንና እነዚህን ለቱሪዝም እንዱስትሪው ትልቅ አቅም የሆኑ ሀብቶችን አውቃ እና አልምታ በአግባቡ መጠቀም ሳትችል ኖራለች። ይህንን እውነታ ለመቀየር የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ማግስት ጀምሮ ሰፊ ጥረት አድርጓል፤ በዚህም አስደማሚ ተጨባጭ ውጤቶችንም ማስመዝገብ ችሏል።

የቱሪዝሙን ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ አድገት እንደ አንድ ስትራቴጂክ አቅም አድርጎ በፖሊሲ ደረጃ የወሰደው መንግሥት ፤ በዘርፉ ያለውን ሀብት “ማወቅ ፣ ማልማት እና መጠበቅ” በሚል መሪቃል ወደ ሥራ በመግባት ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ገልጦ ማሳየት በሚያስችል ትልቅ መነቃቃት ላይ ይገኛል፡፡

ለዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የእንጦጦ ፣ የአንድነት እና የወዳጅነት ፓርክን በአዲስ አበባ ፤ ከአዲስ አበባ ውጪም የጎርጎራ ፣ የወንጪ ፣ በኮይሻ ፕሮጀክት የሀላላ ኬላና የዝሆን ዳና ሎጅ ፓርኮችንና ሪዞርቶችን በአጭር ጊዜ በጥራት ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡበትን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል። በገበታ ለትውልድ ደግሞ በተለያዩ ክልሎች ሌሎች ተመሳሳይ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡

የእነዚህ ፓርኮች ግንባታ ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም እና ሀገሪቱ ከቱሪስቶች የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ የሚቻል ሲሆን፣ ለበርካታ ዜጎች አዲስ የሥራ እድል መፍጠርም ተችሏል፡፡ የሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች በማስፋት ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የተሻለ አበርክቶ እንዲኖረው ትልቅ አቅም መፍጠር እየቻለ ነው።

ግንባታዎቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች በዘርፉ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የተሻለ መመነቃቃት የሚፈጥሩ ፤ ሕዝቡም አጠገቡ ያሉ ትኩረት ሳይሰጣቸው የኖሩ ሀገራዊ ሀብቶች ለምተው ሀገር እና ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉ ተጨባጭ ተሞክሮ እየቀሰመባቸው ያሉ ናቸው።

ከትናንት በስቲያ በግሉ ዘርፍ እና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግሥት ትብብር ተገንብቶ ለምረቃ የበቃው የቤኑና መንደር የዚሁ እውነታ ሌላኛው ማሳያ ሲሆን፣ በዘርፉ የተመዘገበ ሌላ ትልቅ ሀገራዊ ስኬት እንዲሁም የይቻላል ሀገራዊ መነቃቃታችን መገለጫም ነው ።

መንደሩ በአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ አካባቢ በሰቃ ሀይቅ ዳርቻ የተመሠረተ ሲሆን፣ እጅግ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎች፣ አዳራሽ፣ ሲኒማ ቤት፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ስፓና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችሉ ግንባታዎች የተካሄዱለትም ነው፡፡

የሌማት ትሩፋት አንዱ ሥራ የሆነው የፍራፍሬ ልማት የተካተተበት መሆኑም፣ ግብርናን ከቱሪዝም መዳረሻ ጋር ለማስተሳሰር ትምህርት የሚወሰድበት ያደርገዋል። ባህላዊ የኪነ-ህንጻ ጥበብን ከዘመናዊ ግንባታ ጋር አቀናጅቶ የያዘ፤ ለአካባቢው ተጨማሪ የቱሪዝም አቅም የፈጠረ ውብ መዳረሻ ነው።

ግንባታው ከሁሉም በላይ በጣም አስቸጋሪ የሆነውን የአካባቢውን የአየር ሁኔታና መልክዓ ምድር በመቋቋም እውን መደረጉ፤ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ሀገርን በትጋት መለወጥ እንደሚቻል ትምህርት ሰጥቷል፤ በቀጣይ ለሚገነቡ ተመሳሳይ ፕሮጀክት የይቻላል መንፈስን ያጎለብታል።

በመንግሥት በኩል ሀገራዊ የቱሪዝም አቅሞችን አውቆ ለማልማት የሚደረገው ጥረት እና እየተመዘገበ ያለው ተጨባጭ ውጤት ፤ ለዘርፉ ተገበውን ትኩረት ሰጥቶ ከግሉ ዘርፍ ጋር ተባብሮ መንቀሳቀስ ከተቻለ፤ ከዘርፉ ሀገር እና ሕዝብ ገና ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ በተጨባጭ ያሳየ ፤ የለውጡ አንዱ ትሩፋት ነው ።

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም

Recommended For You