በተለያዩ ጊዜያት እንደ ሀገር ያጋጠመን የሰላም እጦት በታሪካችን ባልተለመደ መልኩ ብዙ ዋጋ እንድንከፍል አስገድዶናል። የሀገርን ሕልውና አደጋ ውስጥ በመክተት ተመልሰን የግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል። ለታሪካዊ ጠላቶችችን እና ለኛ በጎ ለማይመኙ የውጪ ኃይሎች እንደ መልካም አጋጣሚ ሆኖ ፈትኖናል።
በዜጎች የበዛ የሕይወት መስዋእትነት፤ መላውን ሕዝብ ከዳር አስከዳር በብዙ ተስፋ ያነሳሳውን ለውጥ እና ለውጡ የተገዛበትን አስተሳሰብ ገና ከጅምሩ ለማምከን በውስጥ እና በውጪ ኃይሎች የተቀናጀ ርብርብ የተጀመረው ሀገር እና ሕዝብን ሰላም የመንሳት እንቅስቃሴ ዛሬም መላውን ሕዝባችንን እየፈተነው ይገኛል።
በኃይል ላይ የተመሰረተው፤ በዘመናት አንደ ሀገር የከፋ ዋጋ ሲያስከፍለን የቆየው አሮጌው የፖለቲካ ባህላችን፤ ባህሉ በፈጠረው አስተሳሰብ የተገሩት የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን፤ ዛሬም ኃይልን የስልጣን ምንጭ አድርገው ማየታቸው፤ በዚህም ልባቸው መደንደኑ ለችግሩ መፈጠር መሰረታዊ ምክንያት ሆኗል።
ይህንኑ አሮጌ አስተሳሰብ እምቢ የሚል የማኅበረሰብ ንቃተ ህሊና መፍጠር አለመቻላችን፤ እነዚህ የፖለቲካ ልሂቃን ባልተገባ መንገድ ሀገርን መልሰው ወደ ግጭት አዙሪት መክተት እንዲችሉ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯላቸዋል። ሀገር እና ሕዝብ ጊዜ ባለፈበት አስተሳሰባቸው ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል።
ሕዝብን በሕዝብ ላይ፤ ሕዝብን በመንግስት ላይ የሚያነሳሱ የተዛቡ ትርክቶችን በመፍጠር፤ ለውጡን የራሱ አድርጎ በብዙ ተስፋ የተነቃቃው ሕዝባችን፤ ከለውጥ ተስፋው ለማለያየት ብዙ ለፍተዋል። የሀገርን ሕልውና አደጋ ውስጥ በከተተ መንገድ ስልጣንን በኃይል፣ በሁከትን እና በግርግር ለመያዝ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል።
በዚህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለሞት እና ለአካል ጉድለት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ፤ ከፍተኛ መጠን ያለው የሀገር ሀብት ለውድመት ተዳርጓል። ጦርነት እና ግጭቶች በፈጠሩት ጫና ብዛት ያላቸው ዜጎች ለተለያዩ የስነልቦና ችግሮች ተጋልጠዋል።
ችግሩ ዛሬም በአማራ ክልል፤ የክልሉን ነዋሪዎች የለት ተዕለት ሕይወት ከመፈታተን አልፎ ሀገር በሚረከቡ ትውልዶች ላይ ሁለንተናዊ ጥፋት እያስከተለ ነው። በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች ክልሉን የግጭት ማዕከል በማድረግ በብዙ ልፋት እና ሀብት የተገነቡ መሰረተ ልማቶች እንዲወድሙ አድርገዋል።
አጠቃላይ የሆነውን የክልሉን ነዋሪ ሕይወት ችግር ውስጥ በመክተት፤ በሰላም ወጥቶ የሚገባበትን፤ ማኅበራዊ መስተጋብሮቹን በሰላም የሚከውንበትን ዕድል አሳጥቶታል፤ ለሞት፣ለስደት፣ ለእገታ እና ለከፉ ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ ዳርገውታል። ቋንቋውን በሚናገሩ፣ ከማኅበረሰበዊ ማንነታቸው በተጣሉ በእነዚህ የጥፋት ኃይሎች /የገዛ ልጆቹ በታሪክ ሆኖ በማያውቅ መልኩ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል ሆኗል።
የክልሉን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነጻነት እንዲያጣ በማድረግ፣ ነገዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ዛሬዎቹም ትርጉም አልባ እንዲሆኑ፤ ትናንቶችን ናፋቂ በማድረግ፤ የለውጡ ዋዜማ ተስፋው እና ሕልሙ እንዲደበዝዝ አድርገዋል።
ሀገር ተረካቢ የሆነው ትውልድ ሀገር የሚረከብበትን አቅም እንዳይገነባ ትምህርት ቤቶችን ከመዝጋት ጀምሮ፤ የመማር ማስተማሩን ሂደት በመቃወም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይገኙ አድርገዋል፤ መምህራንን በአደባባይ በመግደል በትውልዱ ላይ ያላቸውን የጥፋት ተልዕኮ በተጨባጭ አሳይተዋል።
መንግስት በየወቅቱ የሚያቀርበውን የሰላም ጥሪ እንደ አቅመቢስነት በማየት፤ በተዛቡ ትርክቶች እና መሰረት አልባ ፕሮፓጋንዳዎች ፤ ያልሆኑትን የሆኑ እስኪመስላቸው ድረስ፤ ትርጉም በሌለው ፉከራ እና ቀረርቶ አስተው የክልሉን ሕዝብ ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል።
በጽንፈኛ አስተሳሰቦች ሰለባ ከሆኑ ዲያስፖራዎች፤ ጊዜ ካለፈባቸው ፖለቲከኞች፤ ሁሌም ከመቃወም የዘለለ የፖለቲካ ተሳትፎ ከሌላቸው የፖለቲካ ልሂቃን እና የዩቲውብ የግጭት ነጋዴዎች ጋር በመሆንም፤ የታሪካዊ ጠላቶቻችን አጀንዳ ተሸካሚዎች በመሆን አካባቢውን የግጭት ቀጠና አድርገውታል።
እነዚህን ኃይሎች አደብ በማስገዛትና የተገዙበትን የተሳሳተ/ጽንፈኛ አስተሳሰብ ለዘለቄታው በማረም የክልሉን ሰላም ለመመለስ በክልል ደረጃ ““ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄዱ ያሉ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንሶች ከሁሉም በላይ የክልሉን ሕዝብ ከተሳሳቱ ትርክቶች እና ትርክቶቹ ከፈጠሯቸው ውዥንብሮች እና የሰላም እጦቶች መታደግ የሚያስችሉ ናቸው።
በተለይም ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደደውን የክልሉ ሕዝብ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም፤ ክልሉን ከጽንፈኛ የጥፋት ኃይሎች ለማጽዳት ለሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው። የክልሉ ሕዝብ አብዝቶ የሚመኘውን ሰላም እና ልማት እውን ለማድረግም አስተዋጽኦአቸው የላቀ ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም