ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በመም በመካከለኛና ረጅም እርቀት ውድድሮች ውጤታማ ከመሆንም አልፈው የዓለም ክብረወሰኖችንም በመሰባበር ይታወቃሉ፡፡ የመም ውድድሮች ቁጥር መቀነስን ተከትሎም አትሌቶቹ በጎዳና ላይ ውድድሮች ዳግም ውጤታማነታቸውን እያስመሰከሩ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሚካሄዱ የጎዳና ላይ ሩጫዎች የሚያሻሽሉት ክብረወሰንና የሚያስመዘግቡት ፈጣን ሰዓትም ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተለያዩ የዓለም አገራት በስፖርት ቤተሰቡ ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸው የጎዳና ላይ ውድድሮች እንደተለመደው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ውጤታማነታቸውን ማስመስከር ችለዋል፡፡
በፈረንሳይ ሊል በተካሄደ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዳዊት ስዩም የዓለም ክብረወሰን ባለቤት መሆን ችላለች፡፡
አትሌቷ ክብረወሰን በመስበር የግሏ ማድረግ የቻለችው በ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ሲሆን፤ ርቀቱን ለማጠናቀቅም 14:41 የሆነ ሰዓት ፈጅቶባታል፡፡ በ1 ሺ500 ሜትር ርቀት በመወዳደር ዝና ያገኘችው አትሌት ዳዊት ከውድድር እርቃ ብትቆይም ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ፊቷን አዙራ በክብረወሰን ደምቃለች፡፡ በኬንያዊቷ አትሌት ቢትሪስ ኪፕኮይች ተይዞ የቆየውን የርቀቱን ክብረወሰን በሁለት ሰከንዶች ለማሻሻልም ችላለች፡፡
ጠንካራ ፉክክር ባስተናገደው የጎዳና ላይ ውድድር በመጨረሻው ኪሎ ሜትር አትሌት ዳዊት በፍጥነት ተስፈንጥራ በመውጣት ተፎካካሪዎቿን አስከትላ መግባት ችላለች፡፡ ኬንያዊቷ አትሌት ኖራህ ጄሩቶ 14:43 በሆነ ሰዓት በመግባት ሁለተኛ ስትሆን፤ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መስከረም ማሞ 14:55 በሆነ ሰዓት በሶስተኝበት ውድድሩን አጠናቃለች፡፡
በወንዶች ተመሳሳይ ውድድርም በ5ሺ ሜትር የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ የሆነው አትሌት በሪሁ አረጋዊ አሸናፊ ሆኗል፡፡ በሪሁ በውድድሩ አሸናፊ ሊሆን የቻለው ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ሲሆን፤ በርቀቱ ቀድሞ ከተመዘገበው የዓለም ክብረወሰን በአንድ ሰከንድ ብቻ የዘገየ ሆኗል፡፡ በሪሁ የገባበት ሰዓት 12:52 ሆኖ ሲመዘገብ፤ ኡጋንዳዊው አትሌት ሆሴ ኪፕላጋት ደግሞ 13:25 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኗል፡፡ ብርቱ ተፎካካሪ የነበረው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ያሲን ሃጂም አራት ሰከንዶች በመዘግየት ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል፡፡
በሊል የተካሄደው የጎዳና ላይ ውድድር የ10 ኪሎ ሜትር ፉክክር ያስተናገደ ሲሆን፤ በወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጪምዴሳ ደበሌ እና አደለደለው ማሞ አንደኛና ሁለተኛ ሆነው
አጠናቀዋል፡፡ በሴቶች አበራሽ ምንሰዎ አራተኛ በመሆን ውድድሯን ፈጽማለች፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ በስፖርት ቤተሰቡ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ያለው የኒውዮርክ ማራቶን ሲሆን፣ ከዓለም ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ ነው፡፡
በዚህ ውድድር ላይ በርቀቱ ሁለተኛው ፈጣን አትሌት የሆነው ጀግናው ቀነኒሳ በቀለ ተሳታፊ መሆኑን ተከትሎ የስፖርት ቤተሰቡ በትኩረት ሲከታተለው ቆይቷል፡፡ በመም የረጅም እርቀት እንዲሁም በአገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ የነገሰው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የዓለም ክብረወሰንን ለመስበር የቀሩትን ሴኮንዶች በበርሊን እንደሚያሻሽል ቢጠበቅም አልተሳካለትም ነበር፡፡
ይህንንም ተከትሎ በኒውዮርክ ማራቶን ሌላኛውን ሙከራውን ያደርጋል በሚል ቢገመትም፤ አትሌቱ 2፡12፡52 በሆነ ሰዓት ስድስተኛ በመሆን አጠናቋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ በሴቶች በኩል የተሳተፈችው አትሌት አባበል የሻነህ ደግሞ 2፡22፡52 በሆነ ሰዓት በመግባት ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
በስፔን በተካሄደው እውቁ የስፔን ማራቶንም በሴቶች በኩል ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ከአንድ እስከ አራት ባለው ደረጃ ተከታትለው በመግባት አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡ 2፡23፡53 የሆነ ሰዓት ያስመዘገበችው ታዱ ተሾመ ቀዳሚ ስትሆን፤ መሰረት ጎላ፣ መሰረት በለጠ እና በቀለች ጉደታ ደግሞ እስከ አራት ያለውን ስፍራ ይዘዋል፡፡
በፖርቹጋል ዋና ከተማ በሚካሄደው የፖርቶ ማራቶንም በሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ገብተዋል፡፡ እጅግ ተቀራራቢ በሆነ ሰዓት የሮጡት ቅድሳን አለማ፣ ሸዋረግ አለነ፣ ሞቱ መገርሳ፣ ፈይኔ ገመዳ እና መሰለች ጸጋዬ የበላይነቱን የያዙ አትሌቶች ናቸው፡፡ በወንዶች በኩል ደግሞ አስናቀ ዱብሪ ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽሟል፡፡
በስዊዘርላንድ በተደረገው የጄኔቭ 20ኪሎ ሜትር ውድድር ታደሰ አብረሃም በወንዶች ሁለተኛ ሲሆን፤ በሴቶች ደግሞ ሄለን በቀለ አሸናፊ ሆናለች፡፡ በጣሊያን የግማሽ ማራቶን ውድድርም በወንዶች ዳምጤ ኳሹ አንደኛ እንዲሁም መሰረት እንግዱ እና አስመራወርቅ በቀለ በሴቶች አንደኛና ሁለተኛ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2014