በዓለማችን እንደ ወንዶች ብዙ ባይሆኑም ሴቶችም በምርምሩ መስክ ይሳተፋሉ። ለአብነትም እስከ 2021 (እኤአ) መጨረሻ ድረስ ወደ ጠፈር ከተጓዙት 550 አስትሮኖቶች (የጠፈር ተመራማሪዎች) መካከል የሴቶቹ ቁጥር 65 ብቻ እንደነበር “አል-ዐይን” የተሰኘው የመረጃ ምንጭ ይገልፃል።
ምንም እንኳን ብዙ ሴቶች በምርምሩ መስክ የመሰማራት ፍላጎት ቢኖራቸውም እንደ ወንዶች ሲሳካላቸው አይታይም። የዚህ አቢይ ምክንያት ደግሞ በሴትነታቸው የሚደርስባቸው ተፅዕኖ እንደሆነ ብዙዎቹ ሴቶች ሲናገሩ ይደመጣል። ይሁን እንጂ በዘርፉ ሴቶች የሉም ማለት ግን አይደለም፤ ሞልተዋል።
በጠፈር ምርምሩ የጎላ ተሳትፎ ካደረጉት መካከል በአረቡ ዓለም የመጀመሪያዋ ሴት ተመራማሪ የሆነችውን ኖራ አል ማትሮሺን፤ ከሥነ-ፈለክ ተመራማሪዎች መካከልም ደግሞ ዶ/ር ክሌይ ፔይኒን መጥቀስ ይቻላል።
እንግሊዝ ውስጥ የተወለደችው የሥነ-ፈለክ ተመራማሪዋ ዶክተር ክሌይ ፔይኒ በመስኩ አምስት መጽሐፎችን በማሳተም በርካታ ሽልማቶችን አግኝታለች። ለዚህ ሁሉ ያበቋት የምርምር ሥራዎቿ ሲሆኑ በተለይም ክዋክብት የተወለዱበትን፣ የሚኖሩበትን፣ የሚሰማሩበትን፣ የሚሞቱባቸውን መንገዶች ወዘተ በመወሰን ረገድ በጥናትና ምርምር ሥራዋ የተጫወተችው ታላቅ ሚና ነው። ሆኖም እዚህ ለመድረስ የተጓዘችበትን መንገድ ሴትነቷ በብርቱ ፈትኗታል።
ለወንድ የሥነ-ፈለክ ተመራማሪዎች የሚሰጠው ከፍተኛ ክብርና ውዳሴ ለእሷ ተነፍጓታል። በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ክዋክብትን ካጠናቀቀች በኋላ አስትሮኖሚን መማር ብትፈልግም በሴትነቷ ምክንያት አልቻለችም።
በዚህ ምክንያትም ከተወለደችበት እንግሊዝ ወደ አሜሪካ ሄዳ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ለመሥራትና ለመማር ተገደደች። በዩኒቨርሲቲው በምትሰራበት ወቅት ይሰጣት የነበረው ደሞዝ በጣም አነስተኛ ነበር። ሌላው ቀርቶ የምታስተምራቸው የትምህርት አይነቶች እንኳን የኮርስ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ አልነበሩም።
ክሌይ በጾታዋ ምክንያት የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ ተቋቁማ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ራድክሊፍ ኮሌጅ (Radcliffe College) በስነ መለኮት የዶክተሬት ዲግሪዋን ማግኘት ችላለች። ኢትዮጵያ ውስጥም አብዛኞቹ ሴቶች ለቁም ነገር የሚደርሱት የክሌይን አይነት ፈተናዎች አልፈው እንደሆነ ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ይቻላል። ከእነዚህም አንዷ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጽጌ ከተማ ናቸው።
መግቢያችንን ስለ ሴት ተመራማሪዎች ማድረጋችን የዛሬው ጽሑፋችን በሴት ተመራማሪዋ ረዳት ፕሮፌሰር ጽጌ ከተማ ላይ ለማትኮር አስበን ነው።
‹‹ሴትነት በራሱ ተጽዕኖ ነው›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሯ በከፍተኛ ትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱና በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል። ተወልደው ያደጉት በአርሲ ዞን በምትገኝ ዲክሲስ በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። ቤተሰቦቻቸው የተማሩ ባይሆኑም “ለትምህርት ዋጋ ይሰጣሉ” ከሚባሉት የሚመደቡ ናቸው።
ተባባሪ ፕሮፌሰሯ እንዳጫወቱን ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወላጆቻቸው በአካባቢው በነበረ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገቧቸው። በትምህርት ቤቱ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በመማር ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው አርሲ ውስጥ በሚገኝ «ሮቤ ዲዳ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት» ዘመድ ጋር በመቀመጥ ተማሩ። በ1988 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን ወሰዱ።
እስከ ፒኤች.ዲ የትምህርት እርከን ድረስ ሊያደርሳቸው የቻለውን፤ ከፍተኛ ትምህርት የጀመሩበትን ሁኔታ ከሥራ ሕይወታቸው ጋር በማስተሳሰር አጫውተውናል።
በወቅቱ ያመጡት ነጥብ በዲፕሎማ ደረጃ የሚያስገባ ነበር። በመሆኑም መምህራን ኮሌጅ ተመድበው የዲፕሎማ ትምህርታቸውን በመደበኛው መርሐ ግብር ለሁለት ዓመታት ተከታትለው ተመረቁ። በጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም በቴክኒካል ረዳትነት በመቀጠር ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ጀመሩ። ለሦስት ዓመታት ከሠሩ በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የመከታተል ዕድልን አገኙ። በባዮሎጂ የትምህርት ዘርፍም ተመረቁ። በመቀጠልም “የማስተርስ ዲግሪዬን የመማር ዕድል አገኘሁ» ይላሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እ᎐ኤ᎐አ በ2008 በሥነ-ሕይወት ክፍል በባዮ ሜዲካል ሳይንስ አጠናቀቁ። ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰውም ማገልገል ቀጠሉ። እ.ኤ.አ በ2011 የፒኤች.ዲ (ሦስተኛ ዲግሪ) ዕድል አገኙ። ትምህርቱን የጀመሩት በአጋጣሚ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ቢሆንም ያለ ድጋፍ አገር ውስጥ መማር ከባድ ስለነበረ በዚህ መሐል የተለያዩ ነፃ የትምህርት ዕድሎችን መሞከር ነበረባቸው። ሙሉ የምርምርና የትምህርት ወጪያቸውን በሸፈኑላቸውና ከተለያዩ አገራት ባገኙት ድጋፍ ተጠቅመው ትምህርታቸውን ለመከታተል በቁ። በ«ዳዲንግ ካንትሪ ስኮላርሽፕ» ነፃ የትምህርት እድል መሰረት የፒኤች.ዲ ትምህርታቸውን ለሁለት ዓመት እንዲከታተሉ ድጋፍ ተደረገላቸው።
ቀጥሎም «ላውሪ ዩኔስኮ ሪጅናል ፌሎሽፕ» ለሚባለውና በአፍሪካ ላሉ፤ በተለይ የዶክትሬት ትምህርታቸውን ለሚማሩ ወጣት ተመራማሪዎች ድጋፍ ለሚያደርግ ተቋም አመለከቱ። ከ300 አመልካቾች ውስጥ ከአፍሪካ ከተመረጡት አስር አመልካቾች ውስጥ አንዷ በመሆንም ተመረጡ። «ለምርምር ስራዬ 20ሺ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አደረጉልኝና ያለምንም ችግር የፒኤች.ዲ ትምህርት ሥራዬን አጠናቀቅኩ» ብለውናል።
በ2008 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ተመራቂ ሆኑ። በተለያዩ ጊዜያት ከሃያ በላይ የምርምር ሥራዎችን በታዋቂ ዓለም ዓቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፤ የተለያዩ የደረጃ ዕድገቶችንም አግኝተውበታል። የረዳት ፕሮፌሰርነቱም ማዕረግ የተገኘው በእነዚሁ ሥራዎች አማካኝነት ነው።
ወደ አመራርነት የመጡበትን እንዳወጉንም በጅማ ዩኒቨርሲቲ በኮሌጅ ደረጃ የምርምርና የድህረ ምረቃ መርሐ ግብርን በማስተባበር ነው። በዚህ ቦታ ላይ እየሠሩ እያለ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታ ሲወጣ እንደማንኛውም ሰው አመለከቱና ፈተናውን አልፈው ተመደቡ። በውድድሩ በርካታ ወንዶችና አንዲት ሴት አብረዋቸው እንደነበሩም ያስታውሳሉ። ቢሆንም ከሁሉም እሳቸው በመመረጣቸው ወደ ኃላፊነቱ መምጣት ችለዋል። ወደዚህ የመጡት አብረው በርካታ የጎንዮሽ ሥራዎችን እየሰሩ በመቆየትም ጭምር ነበር።
«ሴት ነኝ፣ እናት ነኝ፤ ልጆች አሉኝ›› ሲሉም ሶስቱንም ዲግሪ ሲማሩ በየመሐሉ ሦስት ልጆች መውለዳቸውን፤ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን እነዚህን ልጆች የመንከባከብ፣ የማሳደግና የማስተማር ኃላፊነት እንደ ነበረባቸውም አውግተውናል። አሁን ያሉበት ደረጃ መድረስ የቻሉት ጎን ለጎን በቤት ውስጥ ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ሁሉ እየተወጡ ነው።
ፕሮፌሰር ጽጌ ከተማ እንደሚሉት ሴት ሆኖ ወደ አመራርነት ሲመጣ ያለውን ጫና ለመናገር ይከብዳል። ሴትነት በራሱ ተጽዕኖ ነው። ሴቷ በማኅበረሰብ ውስጥ ምን ያህል ዋጋ እንዳላት፣ የማኅበረሰቡ አመለካከት ምን እንደሚመስል ለማንኛውም ሰው ግልጽ ነው። “ይችላሉ ወይ?” የሚለው ራሱ ጥያቄ የሚሆንበት ሁኔታ መኖሩም አያጠራጥርም።
ይህ የማኅበረሰቡ፣ አብረው የሚሰሩት፣ አብረው የሚኖሩት ሰዎች አመለካከት እንዳለ ሆኖ፤ ተደራራቢ ኃላፊነቶች መኖራቸው በማናቸውም ሴቶች ሥራቸውን በትክክልና በሚፈለገው አቅም መወጣት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ምክንያቱም ቤት አለ፣ ልጅ አለ፣ ሌሎች ተጨማሪ ኃላፊነቶች ስላሉ ሴቷ በሀሳብ ቡዙ ቦታ ተበታትና ነው የምትኖርና የምትመራው። ይሄ ሸክም በራሱ ብቻዋን ለመወጣት ይከብዳታል።
ወደ ኋላ ዞር ብለው እንዳወጉን ወላጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ቢልኳቸውና በትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ እንደማንኛውም ወላጅ የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ ቢያደርጉላቸውም የተማሩ ባለመሆናቸው በትምህርት በኩል የሚያደርጉላቸው ድጋፍ እንብዛም አልነበረም። ብዙውን በራሳቸው ጥረት ነበር የተወጡት።
ነገር ግን በጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሰሩት መምህር ባለቤታቸው በእሳቸው አለመኖር ምክንያት በቤት ውስጥ የሚፈጠረውን ክፍተት በሙሉ በመሙላት እጅግ በጣም አግዘዋቸዋል። በትምህርታቸውም እንዲሁ። እንደውም የባለቤታቸው እርዳታ ባይኖር እዚህ መድረስ እንደማይችሉም ነው ያጫወቱን። «የኛን ሥራ ተክቶ የሚሰራ መሆን ባይኖርበትም ለእኛ ለሴቶች ሁኔታዎች እንዳይከብዱን በሀሳብ የሚረዳ፣ በርቺ፣ ጠንክሪ የሚል ሰው ከጎናችን መኖር አለበት» ሲሉም ለጾታ አጋሮቻቸው ምክር ይለግሳሉ።
እንደ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጽጌ ከተማ አስተያየት ሴቶች ብዙ የለውጥ ሂደቶችን ማለፍ ይኖርባቸዋል። ዛሬ በዛሬ የሴቶችን ሸክም ሊያቃልልና የተሻለ ሁኔታ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ዕምነት የላቸውም። የወንድና የሴት የሥራ ክፍፍል ባይኖር፣ ሴቶች የወንዶችን ሥራ መሸፈን እንደሚችሉ ወንዶች በተወሰነ ደረጃ እንኳን የሴቶችን ሥራ ቢሸፍኑላቸው ሸክሙን ሊያቃልል ይችላል ብለውም ያስባሉ።
‹‹ሸክማቸውን መረዳት በራሱ ከመርዳት በላይ ነው›› ይላሉም። በመሆኑም መሸፈን እንኳን ከአቅማቸው በላይ ቢሆን ችግራቸውን ቢረዱ መልካም መሆኑንም ይጠቅሳሉ። አንድ ሰው ሥራን መስራት የሚችለው አእምሮው ነፃ ሲሆን ነው። ነፃ ለመሆን በተለይ ለሴት ቤተሰብና ባል ወሳኝ ናቸው ብለው ያምናሉ። በተፅዕኖ ውስጥ የሆነ ሰው ምንም መሥራትና መፍጠር አይችልም። በመሆኑም ወደ ፊት ምን አልባት ነገሮች ሊሻሻሉ መቻላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ቢያንስ ወንዶች ባይረዷቸው እንኳን አሁን ላሉበት ደረጃ ለሴቶች ትልቅ ዋጋ እንዳለው ያሰምሩበታል።
ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንዴት እንደሚያዩትና ሴቶችን በማምጣት ጥረቱ እሳቸው ያላቸውን አቋም አስመልክተው እንዳጫወቱን ከሆነ ሴቶች ወደ አመራርነት መምጣታቸውን ይደግፋሉ። መምጣትም አለብን ብለው ያምናሉ። ከመጡ በኋላ እንዲቆዩ በሥልጠናም ሆነ በሌላ መንገድ አቅማቸውን በመገንባትና ክፍተታቸውን በመሙላት ማብቃት አስፈላጊ እንደሆነም ይመክራሉ። ሴቶች በዚህ በኩል እርስ በእርስ መተጋገዝ እንደሚገባቸውም ያስገነዝባሉ።
ወደ አመራርነት ከመምጣታቸው በፊት ትኩረታቸው ሴቶችን በምርምር ማብቃት እንደነበረም አውግተውናል። እንደሳቸው ሁሉ በምርምሩ መስክ የመሳተፉ ፍላጎት ያላቸው እጅግ ብዙ ሴቶች አሉ። ነገር ግን ሴትነት በራሱ ያሉት ተግዳሮቶች የልባቸውን በማድረስ ለስኬት የማያበቃበት ጊዜ ብዙ ነው። ከዚህ አኳያም ወደ አመራርነት በመጡ በአምስት ወራት ውስጥ ሴቶች በምርምር ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን፣ ይህ ክፍተት ሊፈጠር የቻለበትን ምክንያት ከሌሎች በተቋሙ ካሉ ሴት አመራሮች ጋር መለየታቸውንም አጫውተውናል። ሴቶች እንዴት ወደ ምርምር ተግባር መግባት እንደሚችሉ የሚያግዛቸውን የአቅም ግንባታ ሥራም በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውንም ነግረውናል።
እንዲሁም፣ ሴቷ በራሷ እሠራዋለሁ፣ አደርገዋለሁ፣ እችለዋለሁ የሚል ቁርጠኝነት ተነሽነት እንዲሁም የልብ ፍላጎት ካላት መሥራት የምትፈልገውን የምርምር ሥራ ከመሥራት የሚያግዳት እንደሌለም ነው ያወጉን። በተለይ ሴት ተመራማሪዎችን በገንዘብ፣ በሀሳብ፣ በቁሳቁስና በተለያዩ ነገሮች መደገፍ እንደሚገባም ምክራቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ለግሰዋል።
ከጓደኛ ጀምሮ ቤተሰብ፣ መምህራን፣ የትምህርት ተቋማትና ማኅበረሰቡ ከደጋፊዎቹ መካተት አለባቸውም ባይ ናቸው። እኛም ሴቶች በጾታቸው ምክንያት ምንም ዓይነት ልዩነት ቢደረግባቸውም እንደ ፕሮፌሰር ጽጌ ለስኬት የማይበቁበት ምንም አይነት ምክንያት የለምና ከዓላማቸው ዝንፍ ማለት እንደ ሌለባቸው በማሳሰብ የዛሬ ጽሑፋችንን አሳረግን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2014