በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ሥልጣን ዘመን እኤአ 2000 ላይ የተጠነሰሰው ‹‹አፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት/ አጎዋ››የአፍሪካ አገራት የተመረጡ አንዳንድ ምርቶች ከቀረጥና ከኮታ ነጻ ወደ አሜሪካ እንዲልኩ የሚያስችል የሕግ ድንጋጌ ነው።
ኢትዮጵያም የአጎዋ የንግድ ችሮታ ከተሰጣቸው አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ላለፉት ሃያ ዓመታት በተለይም የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርትን ከቀረጥ ነፃ ለአሜሪካ ገበያ ስታቀርብ ቆይታለች፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ በዚሁ እድል ወደ አሜሪካ ኤክስፖርት ከተደረጉ ምርቶች 300 ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር ማግኘቷም ይነገራል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣በኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረጉ አምራቾች በኩል 230 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ተጠቃሚ ናቸው፡፡በአጎዋ ትስስር ካላቸው ፋብሪካዎችና ምርቶች ጋር በተገናኘ ከ85 ሺህ በላይ ዜጎች ተቀጥረው ይሰራሉ።ከእነዚህም ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት እናቶችና ወጣት ሴቶች ናቸው።
በአሜሪካ መንግሥት እሳቤ አገራት በማዕቀፉ የተመረጡ ምርቶችን ከቀረጥና ከኮታ ነጻ ለማቅረብ አጎዋ በድንጋጌው ላይ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች ማሟላት የግድ ይላቸዋል፡፡የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን ለኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ፣በመንግሥት አስተዳደሩ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ማሳተፍ፤ የሕግ የበላይነትን መቀበልና ማስከበር፤ የኢንዱስትሪ ሠራተኞች መብቶችን ማስከበር እንዲሁም መሠረታዊ የሆኑ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስክበር የሚሉት ይገኙበታል፡፡
መሰል የመመዘኛ መስፈርቶችን በማሟላት ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት አዲስ ምዕራፍን የሚከፍቱ ዘርፈ ብዙ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ የለውጥ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በሕወሓት ዘመን ከነበረው በተለየና በላቀ መልኩ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢያዊ ሁኔታውን ለኢንቨስተሮች ክፍት አድርጓል።
መንግሥት ለግል ዘርፉ ተሳትፎ በቂና አስተማማኝ ቦታ በመስጠት ቀደም ሲል ዝግ የነበሩ ዘርፎችን ለኢንቨስትመንት ክፍት አድርጓል።አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተፈጻሚ አድርጓል፡፡ የሠራተኞችን መብት ለማስከበር ሰርቷል፡፡የሲቪል ማኅበራት በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ተሳተፎ በማሳደግ ረገድ እንዲሁም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የተሻለ የፖለቲካ ምህዳር ፈጥሯል፡፡
መሰል እርምጃዎች የኢትዮጵያን የአጎዋ አባልነት ቢያጠናክሩ እንጂ የሚያሳስቡ ተደርገው አይወሰዱም፡፡ ይሁንና በሰሜኑ በኩል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ቅድመ ሁኔታ አላሟላችም በሚል የንግድ ችሮታውን እንዳታገኝ በተለይ በአሸባሪው የሕወሓት ጋሻ ጃግሬዎች ሲነሳ ቆይቷል፡፡
መንግሥትም ኢትዮጵያ ከአጎዋ ከገበያ እድል ብትቀነስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለው ማኅበረሰብ በተለይም ሴቶች ቀጥተኛ ተጎጂ እንደሚሆኑ በመግለጽ እውነታውን ለማስረዳት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይሁንና የጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ በአጎዋ ተጠቃሚነት ዝርዝር ውስጥ የሚያስቀጥላት አይደለም በማለት ከገበያው እንድትታቀብ መወሰኑን ከቀናት በፊት ይፋ አድርጋል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም፣ውሳኔው በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ጦርነትና ሰብዓዊ መብት ጋር የማይያያዝ፣አድሏዊና መንግሥት የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ መሆኑን አሳውቃል፡፡
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት ዝርዝር መታገድ ምን ጉዳት አለው?የውሳኔው ዓላማስ ምን ይሆን? ውሳኔውን ለመቀልበስ ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ይኖርባታል?የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት የተለያዩ ምሑራንን አነጋግሯል፡፡
አስተያየት የሰጡ ምሑራንም፣ አሜሪካ የራሷን ፍላጎት ለማሳካት ኢትዮጵያ ከአጎዋ ዕድል እንዳትጠቀም ማገዷ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥልና ቀደም ሲል በአገሪቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አማካኝነት ለዜጎች ተፈጥረው የነበሩ የሥራ እድሎችን እንደሚጎዳም አስረድተዋል፡፡
ውሳኔው የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጉዳት፣ለማዳከምና ኢትዮጵያን ለማበርከክ ያለመና ፖለቲካዊ ፍላጎት ያለው ስለመሆኑም ይጠቁማሉ፡፡ አስቀድሞም አጎዋ ፖለቲካዊ ስለመሆኑም አገራት አባል ለመሆን ሊያሟላቸው የሚገባቸውን መስፈርቶች መመልከት ብቻ በቂ ስለመሆኑ ያነሳሉ፡፡
በእርግጥም አጎዋ ለአንዳንድ አገራት ኢኮኖሚ መጎልበት በአንድ በኩል ሲወደስ፣በሌላ በኩል ደግሞ የዕድሉ ተጠቃሚ አገራትን በመምረጥና በማስቀጠል ረገድ እጅግ ጠባብ በሆነ መስፈርቱ እንዲሁም የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ስውር በትር እስኪባል ድረስ ለፖለቲካ አድሎአዊነት ምቹ በመሆኑ በርካታ ትችት ይጎርፍበታል፡፡
በተለይም በአድሏዊና በቀፍዳጅ አንቀጾቹም ይታማል፡፡ ከሌሎች የገበያ እድሎች ጋር ሲነፃፀርም ተጠቃሚዎችን መምረጫ መስፈርቱ ፖለቲካዊ አድሎ ያለበትና ጊዜያዊ የፖለቲካ ወዳጅነትና የአገራት መሪዎች እሺታዊነት ብሎም የፖለቲካዊ ተንበርካኪነትን ያማከለ ነው ተብሎ በእጅጉ ይተቻል፡፡
በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን የሚያጋሩ ምሑራን እንደሚገልፁትም፣የአጎዋ የችሮታ መስፈርቱ አንድ ሀገር ሉዓላዊነቷን ተጠቅማ የምትቀርጻቸው ፖሊሲዎች በአሜሪካን የብሔራዊ ደህንነት ወይም የውጭ ፖሊሲ ጉዳይ ታሳቢ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ
ነው፡፡ የአገራት የንግድም ሆነ የፖለቲካ ፖሊሲ ለአሜሪካ ተመራጭና ለባለሀብቶቻችንም ተስማሚና በተፈለገ ጊዜ የሚጠመዝዙት እንዲሆን የተቀመረ ነው፡፡
አገራት ለአሜሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት እንቅፋቶችን የሚሆኑ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ሥርዓታቸውን የሕግ፣ የፖሊሲና የስትራቴጂ ማነቆዎች በማንኛውም መንገድ ማስወገድ ወይም በሂደት ማቅለል እንዲሁም በራቸውን በሰፊው መክፈት እንደሚኖርባቸውም ጫና ያሳድራል፡፡የእድሉ ተጠቃሚ አገራት በማናቸውም የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔዎች ላይ ተቃውሞ የማቅረብ፣ለተወሰዱ እርምጃዎች ተመላሽ ክርክር የማድረግ ምንም አይነት መብት እንደሌላቸው ጫና የሚያሳድር መሆኑም በእጅጉ ያስተቸዋል፡፡
ይህን እሳቤ በሚያጠናክር መልኩ የአሜሪካ ውሳኔ ከጀርባውም ግልጽ የፖለቲካ አጀንዳን ያነገበ ስለመሆኑ የሚስማሙበት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህር ዶክተር ሞላ አለማየሁ፣‹‹የአሜሪካ ችሮታዎች በአብዛኛው ከቅንነት ሳይሆን አገራት በተዘዋዋሪ ተንበርካኪ ማድረግን ታሳቢ ያደረጉና የእጅ መጠምዘዣ ናቸው››ይላሉ፡፡
አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ያስተላለፈችው የአጎዋ ክልከላ ውሳኔ ከወቅታዊው ጦርነት ጋር ተይይዞ የሰብአዊ መብት ተጥሷል በሚል የመጣ ነው ቢባልም፣በጉዳዩ ላይ በተባበሩት መንግሥታትና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተካሄደው ጥናት በአንፃሩ የሚባለው ሁሉ ሐሰት መሆኑን ይፋ ስለማድረጉ የሚያስታውሱት ዶክተሩ፣‹‹ይህ በሆነበት የአሜሪካ ውሳኔ፣በእውነተኛና በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ሐቅን ታሳቢ ያላደረገና በመንግሥት የተሰሩ ሥራዎችን በአግባቡ ያላገናዘበ እንደሆነ በግልፅ ያሳያል›› ይላሉ፡፡
አሜሪካኖቹ የመረጃ እጥረት አለባቸው ለማለት ባያስደፍርም ውሳኔው ሆን ተብሎ የግል ጥቅምን ማስጠበቅን ዓላማው ያደረገና የተቀነባበረ መሆኑን የሚጠቁሙት ዶክተር ሞላ፣ ከጀርባውም ግልጽ የፖለቲካ አጀንዳን ያነገበ ስለመሆኑ ከዚህ በላይ ማስረጃ መጥቀስ እንደማያስፈልግ አፅእኖት ይሠጡታል፡፡
የዶክተር ሞላን ሃሳብ የሚጋሩት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ እምቢአለ በየነም፣አጎዋ የአሜሪካ የፖለቲካ ጥቅም ማስከበሪያ ነው፣በተለይም የእድሉ ተጠቃሚ የሆኑ አገራትን በቁጥጥር ስራ የማድረጊያ ስልት ነው››ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ላይ የተጣለው ውሳኔም ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው፣የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ዓለም አቀፋዊ ባሕሪ ለማላበስና ስሟን ለማጥፋት የታለመ ስለመሆኑም የሚገልፁት ምሑሩ፣ አጎዋ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካም ጥቅም እንደነበረው በማስታወስ ውሳኔው ከሁሉም በላይ የሁለቱን አገራት ከ120 በላይ ዓመታት ያስቆጠረ ግንኙነት የሚጎዳ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
ውሳኔው ፖለቲካዊ ፍላጎትና ያነገበና ሉዓላዊነትን የሚዳፈር እንደመሆኑም ኢትዮጵያ ጥቅሟን አሳልፋ መስጠት እንደሌለባት የሚያስጠነቅቁ አንዳንድ ምሑራንም፣ከገበያው የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት አነስተኛ መሆኑንም ዋቢ በማድረግ ይህ በቀላሉ እንዳንትንበረከክ ከፍተኛ አቅም እንደሚሆናት ያስረዳሉ፡፡
በእርግጥም መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ኢትዮጵያ እንደሌሎች አገራት አጎዋን አልተጠቀመችበትም፡፡ ለዚህ ኬንያን መጥቀስ ይቻላል፡፡ከኬንያ ወደ አሜሪካ ያለው ኤክስፖርት ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ኤክስፖርት የምታደርገው በአንፃሩ ከ300 ሚሊዮን ዶላር የተሻገረ አይደለም፡፡
አንዳንድ ምርቶቿ ለአብነትም ቡናን ብንወስድ ቡና ላይ ቀረጥ ስለሌለ ድሮም ቢሆን የቡና ኤክስፖርት በአጎዋ ተጠቃሚ ነው ብሎ ለመናገር ይቸግራል፡፡በዋነኛነት አጎዋ የሚመለከተው የአልባሳት ዘርፍና የቆዳና ቆዳ ውጤቶችን ነው ፡፡ ይህም ወትሮም ቢሆን ‹‹ኢትዮጵያ በአጎዋ በሁሉ ረገድ ተጠቅማለች ለማለት አያስደፍርም ይላሉ፡፡
አንዳንዶች በአንፃሩ አነስተኛም ይሁን ግዙፍ ማንኛውም የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ቀላል የማይባል ተጽዕኖ ያሳድራል፣በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ይበልጥ ፈታኝ ሊሆን ይችላል።ይሁንና ጉዳቱን ለመቋቋም ምን ይደረግ የሚለው ላይ ማተኮር አዋጭ ነው››ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ጫንን መሠረት ባደረጉ መሰል ማዕቀቦች እጅ መስጠትና መንበርከክ ፈፅሞ እንደማያስፈልግና ይልቁንም እንደ እድል መጠቀም ለላቀ ለውጥ መነሻ ማድረግ እንደሚገባ የሚጠቁሙ ምሑራን ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ የዚህ እሳቤ አራማጆች እንሚያስረዱትም፣በዓለም ላይ በኢኮኖሚ ማዕቀብ ውስጥ ያለፉ ብዙ አገራት አሉ። ማዕቀቡ ያደበዘዛቸው እንዳሉ ሁሉ ከፍ ያደረጋቸውም አሉ። ኢትዮጵያም ዝቅ ከማለት ይልቅ ከፍ የማለት እድሉ አላት፡፡
በዚህ እሳቤ የሚስማሙት ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚገልፁትም፣ በዓለም ላይ አንድ ነገር ሲከሰት ሙሉ በሙሉ መጥፎ፣ አልያም ሙሉ በሙሉ ጥሩ ሆኖ አይደለም፡፡አሉታዊም አዎንታዊም ጎኖች
ይኖሩታል፡፡ አንዳንድ ማዕቀቦችም አገራት ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዲገነቡ ምክንያት ይሆናቸዋል፡፡ ቱርክ፣ ኢራንና ኩባ የመሳሰሉ አገራትም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡
‹‹እንደ እነዚህ አገራት ሁሉ ኢትዮጵያም የተወሰነባትን የአጎዋ ውሳኔ ወደ አዎንታ መለወጥ ትችላለች›› የሚሉት ዶክተሩ፣ለዚህ ደግሞ በተለይም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ፣ የተለያዩ አማራጭ ገበያዎችን መቃኘት ተደራዳሪ ምርት በማቅረብ ረገድ ጥራትን ታሳቢ ማድረግ እንደሚጠበቅባት ነው ያመላከቱት፡፡
አብዛኞቹ በአሜሪካ ማዕቀብ የታገዱ አገራት‹‹የዜጎች አንድነትና በራስ መተማመን ማዕቀቡ ለመቋቋም አስችሎናል››ሲሉ ይደመጣል፡፡ራሳቸውን ለማሻሻል የማእቀቡን ጉዳት በመቋቋም የተለያዩ መንገዶችን እንደተጠቀሙ ሲገልፁ ይደመጣል፡፡
ኢትዮጵያስ በዚህ ረገድ ምን ታድርግ ለሚለው ጥያቄ መልሳቸውን የሚያጋሩ ምሑራንም፣ መጀመሪያውኑ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድም ሆነ ኢኮኖሚ እድገቱ በአጎዋ ላይ ብቻ የተወሰነ ኢኮኖሚ ባለመሆኑ አማራጮችን ማየት እንደሚገባ ያሰምሩበታል፡፡
በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ደምመላሽ ሃብቴ፣ ‹‹ውሳኔው ኢትዮጵያን ተስፋ ሊያስቆርጥ አይገባም››ይላሉ፡፡ኢትዮጵያ በአጎዋ ንግድ ትስስር መቋረጥ ምክንያት የሚደርስባትን ችግር ለመቋቋም፣ከአሜሪካ ውጭ ባሉ አገራት አማራጭ የንግድ ትስስሯን ማስፋት እንዳለበት ነው ያመላከቱት፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ከሌሎች ቻይና፣ ሩሲያ ህንድና ሌሎች ወዳጅ አገራት ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ልታጎለብትና በተለይም በአፍሪካ ነጻ ገበያ ውስጥ ተሳትፎዋን ለማሳደግ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባታል››የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኽተስፋ(ዶክተር/፣በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በቀጣይም ከእርዳታና ከብድር አይኗን ለማንሳት ለአገር በቀል ኢኮኖሚ ትኩረት በመስጠት መሥራት እንዳለባትም ሳያመላክቱ አላለፉም፡፡
በእግጥም አሜሪካ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የምርት ተቀባይ አገር ብትሆንም አውሮፓና ጥቂት የእስያ አገራትም ተረካቢ መሆናቸውን ይታመናል፡፡ ይህ እንደመሆኑም አጎዋ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ የሚወስን አይሆንም፡፡የምርትና የተቀባይ አገራትን አማራጭ በማስፋት የፓርኮቹን ሥራ ማስቀጠልም ይቻላል፡፡ በተለይም በአገር ውስጥ ገበያ ተፈላጊነት ወዳላቸው ምርቶች ማተኮር አንደኛው አማራጭ ይሆናል፡፡
በዓለም ላይ ያሉ በርካታ ያደጉ አገራት የታዳጊ አገራትን ምጣኔ ሀብት ለማጎልበት እና በምላሹ ለዜጎቻቸው ምርት ለማቅረብ እንዲረዳቸው በርካታ የኮታና ቀረጥ ነፃ ዕድሎችን ይሰጣሉ።ለአብነትም ቱርክ፣ቻይና፣ህንድ፣ ኖርዌይ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ቺሊ፣ ታይላንድ፣አይስላንድ፣ደቡብ ኮሪያ፣ሞሮኮን የተለያዩ የታሪፍ ነፃ እድሎች ካመቻቹ አገራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡እነዚህን የቀረጥና ኮታ ነጻ የገበያ መግቢያ ዕድል አማራጮችን እንዴት እንደ አግባብነታቸው እንጠቀም ብሎ ማሰብ ይጠይቃል።
የገበያ አማራጮች ማስፋት የግድ ስለመሆኑ የሚስማሙበት ዶክተር ሞላ አለማየሁም፣ በተለይ አባካኝ የሆነውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈር ማስያዝና ኢኮኖሚውን መልሶ በሚጠቅም ስትራቴጂና ጊዜ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አፅዕኖት ሰጥተውታል፡፡
ይህን ማእቀብ ለመቋቋም፣በማዕቀብ ከደበዘዙት ሳይሆን ከፍ ካሉት አገራት ለመደመር የመንግሥት ሚና ከፍተኛ ፖሊሲዎችን በማውጣት፣አቅጣጫዎችን ለማሳየት፣ስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ ሕዝብም ከመንግሥት ጎን በመቆም በሁሉ ረገድ ተባባሪና ተደጋጋፊ መሆን፣በቁጭት ተነሳስቶ መሥራትና ምርትና ምርታማነትን ማጎልበት እንዳሚገባውም ሳያመላክቱ አላለፉም፡፡
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ እምቢአለ በየነ በበኩላቸው፣ኢትዮጵያ ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ እንደ ምክንያት የቀረበው ተገቢ ያልሆነና ፈፅሞ የተሳሳተ እንደሆነ ደጋግሞ ማስገንዘብም መረሳት እንደሌለበት ጠቁመዋል፡፡የማዕቀቡን ተፅዕኖ ለመቋቋም በተለይም ከታክስ ነጻ እድል ዘላለም ተጠቃሚ ሆኖ መዝለቅ ስለማይቻል ተወዳዳሪ ሆኖ ወደ ሌሎች የዓለም ገበያዎች መዝለቅን ታሳቢ ማድረግና ምርቶች በአገር ውስጥ ገበያ ገዢ የሚያገኙበትን እድል ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት፡፡
ከምሑራኑ የጋራ ምክረ ሃሳብ መረዳት እንደሚቻለው፣አማራጭ የገበያ ዕድል ማመቻቸት ወሳኝ ነው፡፡ አምራች ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆንና የአምራቾችን የማምረቻ ወጪ እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ በተለይ የሎጀስቲክ ወጪ፤ የኃይል አቅርቦቱን የማስተካከል ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ተወዳዳሪ ምርት በማቅረብና ወደ አሜሪካ ገበያም ቢሆን ታክስ በመክፈል ገበያውን መቀላቀል የሚችሉበት እድል ዝግ አለመሆኑን መዘንጋትም አያስፈልግም፡፡
በአፍሪካ አህጉር ክልላዊ የንግድና ምጣኔ-ሃብት ውህደት ላይ ማተኮር፣የወጪ ንግድ ምርቶች ስብጥር ብዝኃነትን ማስፋፋት፣ክልላዊ ኢንዱስትሪያላይዜሽን በማጠናከር የእሴት ሰንሰለቶችን እንዲተሳሰሩ ማድረግና ምርቶች ወደ ዓለም አቀፋዊ የእሴት ሰንሰለት እንዲገቡ በተገቢው ልክ ማስተዋወቅ ይገባል፡፡
‹‹አጎዋ›› ዘላቂ ስምምነት ሳይሆን በጊዜ ገደብ ጥቅም ላይ የሚውል ማትጊያ በመሆኑ መጠናቀቂያ ጊዜ
አለው፡፡ይህ ውሳኔ ተግባራዊ የሚደረገው በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ወይንም ከጥር ወር መጀመሪያ አንስቶ ነው፡፡የኢትዮጵያ መንግሥትም በቀጣይ ጊዜያት የአሜሪካ መንግሥት ጉዳዩን ዳግም እንዲያጤነውም ይጠይቃል፡፡ይሁንና በአጎዋ ሰበብ ሰጥቶ የሚቀበለው የህልውና ጉዳይ እንደማይኖር አስረግጧል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2014