እኛ ኢትዮጵያውያን የአሸባሪውን የሕወሓት መንግሥት በሕዝባዊ ትግል ከሥልጣን ካስወገድን ማግስት ጀምሮ ለመላው አፍሪካዊ አዲስ መነሳሳት የሚፈጥር ታሪካዊ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ገብተናል። ይህንንም ተከትሎ በተለይም ምዕራቡ ዓለም የተከፈተብን ጦርነት ሁለንተናዊ እየሆነ መምጣቱም የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ውሎ አድሯል።
አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ነጻነት ትግል ዋዜማ ጀምሮ በብዙ መስዋዕትነት ያለሙት እውነተኛ ነጻነት ሆነ ነጻነቱን ተከትሎ ተስፋ ያደረጉትን የብልጽግና ሕይወት ለመጨበጥ አልቻሉም። ከዛ ይልቅ አፍሪካውያኑን ከፍ ያሉ ዋጋ ያስከፈሉ የእርስበርስ ግጭቶችና ጦርነቶች ውስጥ ለማለፍ ተገደዋል። በዚህም ለነጻነታቸው የከፈሉት መስዋዕትነት ትርጉም የለሽ እስኪመስል የሆነበት እውነታ ተፈጥሯል።
በነጻነት ትግሉ ማግስት የነጻነት ትግሉ የፈጠረው የላቀ የተጋድሎ መነሳሳትና ተጋድሎው የፈጠረውን የአሸናፊነት መንፈስ መቀልበስ የማይቻል ደረጃ ላይ መድረሱን በተጨባጭ የተረዱት ቅኝ ገዥ ኃይሎችና ተባባሪዎቻቸው ብዙ ዋጋ የተከፈለበትን የነጻነት ትግል በአዲስ የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ መረብ በመጥለፍ ትግሉ እና በትግሉ የተከፈለው መስዋዕትነት የተሟላ ትርጉም እንዳይኖረው አድርገዋል።
ለዚህም በአንድ በኩል በትግሉ የተሰለፈውን ኃይል በመከፋፋል እና የውስጥ ተቃርኖዎችን በመፍጠር የነጻነት ኃይሉ የተነሳበትን ትልቁን ተልዕኮውን ዘንግቶ ልዩነቶችን ወደ ማስታረቅ ፤ አልያም በኃይል ወደ ማስወገድ ያልተገባ አማራጭ እንዲሄድ አድርገውታል ።
በሌላ በኩል ደግሞ ለእነሱ አዲስ የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት አቅም ሊሆኑ የሚችሉ ቡድኖችን ከመፍጠር አንስቶ ለቡድኖቹ ሁለንተናዊ ድጋፍ በመስጠት ወደ ሥልጣን እንዲመጡና በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ በማድረግ የነጻነት ትግሉን የተሟላ ትርጉም አሳጥተውታል።
ከዚህ የከፋው ደግሞ እነዚህን ኃይሎች በመጠቀም እውነተኛ የነጻነት ኃይሎች ላይ ሁለንተናዊ ጥቃቶችን በመሰንዘር ፤ትግሉ በቀጣይ ትውልዶች ውስጥ ወደ ትንሳኤ የሚመጣበት መንገድ በመዝጋት አፍሪካውያን ወደ ቀደመው የጨለማ ዘመን እንዲመለሱ አድርገዋል።
ቅኝ ገዥ ኃይሎችና ተባባሪዎቻቸው ከሁለንተናዊ ነጻነት ይልቅ ስለ ሥልጣንና የሥልጣን ዘመናቸው ብቻ የሚያስቡ መሪዎችን ከመፍጠር አንስቶ ከፍ ያለ ብሔራዊ አስተሳሰብና ሕዝባዊ መንፈስ ያላቸውን አፍሪካዊ መሪዎችን በማስወገድ ሴራዎች ተጠምደው ያለፉትን 70 ዓመታት አሳልፈዋል።
በዚህም አፍሪካውያን ከፍያለ የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት ባለቤት የመሆናቸውን ያህል እንኳን የዕለት እንጀራቸውን ማግኘት ተስኗቸው የጉስቁልናና የረሃብ ተምሳሌቶች የሆኑበትን ሕይወት እንዲመሩ ሆነዋል። ከሁሉም አሳዛኙ ደግሞ አፍሪካውያኑ ቀናቶቻችውን ለማሸነፍ ዓይኖቻቸውን ወደ ቀደሙት ጨካኝ ገዥዎቻቸው እንዲያነሱ መገደዳቸውና እነዚህን አካላት ለችግሮቻቸውም የመፍትሔ አካል አድርገው የማየታቸው እውነታ ነው።
በዚህ ሁሉ መሐል በኢትዮጵያ የዛሬ ሶስት ዓመት የተጀመረው ለውጥ ይህንን እውነታ በመቀልበስ ሂደት ውስጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንደሆነ ብዙዎች እየተስማሙበት ነው።መላውን አፍሪካዊ ለቀጣይ የተሟላ የነጻነት ትግል እንደሚያነሳሳ፤ ለአፍሪካውያን የዓድዋን ያህል ብርሀን ፈንጣቂ እንደሚሆንም ይታመናል።
ለውጡ የአፍሪካውያንን ነጻነት ምሉዕ ማድረግ የሚያስችል የብልጽግና አስተሳሰብ መሸከሙ፤ አስተሳሰቡ በአገር ውስጥ የፈጠረው መነቃቃት በራሱ፤ተምሳሌትነቱም በሌላ መልኩ ለለውጡ ኃይል ትልቅ ተግዳሮት ይዞበት መጥቷል።
ለውጡ ከተለመደው እና በዘመናት አፍሪካውያንን ዋጋ ካስከፈለው የተውሶና የሴራ አስተሳሰብ በመውጣት ራስን በአግባቡ ከመረዳትና በራስ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶች ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑ ደግሞ እውነታው የበለጠ ለምዕራቡ ዓለም የስጋት ምንጭ እንዲሆንና ትግላችንንም አፍሪካዊ ተልዕኮ የተሸከመ አድርጎታል።
ባለፈው ዘመን አባቶቻችን በዓድዋ ያደረጉት የአይበገሬነት ተጋድሎ በዘመኑ በቅኝ አገዛዝ የከፋ የጭቆና ቀንበር ውስጥ ላሉ ጥቁር ሕዝቦች የእንቢተኝነት መንፈስና የነጻነት መሻት ተጋድሎ ጮራ ፈንጣቂ እንደነበር ሁሉ አሁንም የጀመርነውን ለውጥና ለውጡ ይዞት የመጣው እልህ አስጨራሽ ትግል በአፍሪካውያን ላይ የተጫነን፤ አፍሪካውያን ራሳቸውን እንዳይሆኑ ያደረጋቸውን ዘመነኛውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመስበር ዳግም ጮራ ፈንጣቂ እንደሚሆን ይታመናል።
ብዙዎች እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት የገባንበት የህልውና ጦርነት ከአንድ ዳተኛ አሸባሪ ቡድን ጋር እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ፤ ከዚህም አልፈው የርስ በርስ ጦርነት አድርገው ለማየትም ይሞክራሉ። እውነታው ግን ከዚህ ከፍያለ ከምዕራባውያኑ የሴራ አስተሳሰብና ከዚህ የመነጨውን ቀንበር ለመስበር የሚደረግ ዘመኑ የጠየቀው የተጋድሎ ታሪክ ነው።
ከዚህም የተነሳም አብዛኛዎቹ የምዕራቡ አገራት መሪዎችና በነሱ የሚዘወሩ የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በለውጡ ኃይልና አስተሳሰብ ላይ የተጠናከረ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ በሐሰተኛ መረጃዎች እና ውዥንብሮችና ሳይቀር ዘመቻውን እየመሩ ይገኛል።
እኛ ግን አባቶቻችን በዓድዋ በከፈሉት ከፍ ያለ መስዋዕትነት ለእኛ የሚተርፍ የክብር ታሪክ እንዳስቀመጡልን ፤እኛም የጀመርነውን ለውጥ በስኬት በማጠናቀቅ ለመጪው ትውልድ ዳግማዊውን ዓድዋ በመስዋዕትነት ደማችን በመጻፍ እንደ አገር ታሪክ ሰሪነታችንን እናረጋግጣለን!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2014