ካለፈው ሳምንት የቀጠለ
የተወሰኑ የአራችን አትሌቲክስ ክብረወሰኖች ሳይሻሻሉና ሳይደፈሩ በጣም ሰንብተዋል። ለምሳሌ የ400 ሜትር ክብረወሰን ሜክሲኮ ኦሊምፒክ በአትሌት ተገኝ በዛብህ የተመሰረተ ነበር። እነሆ ዘንድሮ ሳይሻሻል 53ኛ ዓመቱን አከበረ። የሚገርመው በዚህ ውጤት ባለፈው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሚኒማውን (44.8 ሴ) አያሟላም! በአሎሎ ውርወራ የባሕር ኃይሉ ሳሙኤል ካሳዬ 15.98 ሜትር ክብረወሰን ሳይደፈር 45 ዓመት ሞላው።
የዲስከስ ውርወራ ክብረወሰን አሁንም በሳሙኤል ካሳዬ በ45.57 ሜትር የተያዘ ሲሆን ግማሽ ምዕተ ዓመት አለፈው። ሳይሰበሩ በጣም የቆዩት የዓለም አትሌቲክስ ክብረወሰኖች ከ22 ዓመት እስከ 34 ዓመት ደርሰዋል፡ ሆኖም ውጤታቸውን ስንመለከት እንዲህ መቆየታቸው አይገርምም፣ ምክንያቱም በጣም አስደናቂና ከፍተኛ ውጤቶች ስለሆኑ።
የአጭር ሩጫ፣ የውርወራና የዝላይ ድክመትን በአትሌቶች አቅም ውስንነት ማላከክ በጣም አሳፋሪ ነው። ይልቁኑ የአሰልጣኞች እውቀት ውስንነት ነው ውጤት አልባ ያደረገን። ለእነዚህ ስፖርቶች የጥንካሬ ልምምድ ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑ እየታወቀ በጣም ኋላቀር በሆነ አስተሳሰብ ጥንካሬና ኃይል የሚያስፈልጋቸው የሜዳ ተግባራት እንዳያድጉ የአሰልጣኞች የተሳሳተ አመለካከት ትልቅ ሚና አለው። የጡንቻ ድሮች ልዩነት የማያውቅ፣ የሃይል ጎዳናዎች ልዩነት ያልተገነዘበ አሰልጣኝ ምን ውጤት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል?
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ክብረወሰን ከጎሮቤት ኬኒያ ጋር ሲነፃፀር የአገራችን አትሌቲክስ ክብረወሰኖች ከፍተኛ ልዩነት ያሳያሉ። በ100 ሜትር የኛ ክብረወሰን 10፡61 ሲሆን ኬኒያ 10፡14 ደርሷል፤ በ200 ሜትር እኛ (በእጅ የተያዘ ያልፀደቀ ሰዓት 20፡7) የኤሌክትሪኩ 21፡74 ሲሆን ኬኒያ 20፡14፤ በ400 ሜትር የኛ 45፡41 የኬኒያ 44፡ 18 (በሙኒክ ኦሊምፒክ ኬኒያ በ4 በ400 ዱላ ቅብብል የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች፣ በነጠላ ነሐስ ሜዳልያ ተሸልማለች)፤ የ110 ሜትር መሰናክል የኛ 14፡73 የኬኒያ 13፡69፤ የከፍታ ዝላይ እኛ 2.10 ሜትር ኬኒያ 2.30 ሜትር (የአፍሪካ ክብረወሰን)፤ ርዝመት ዝላይ የኛ 7.58 ሜትር ኬኒያ 8.12፤ አሎሎ የኛ 15.98 የኬኒያ 18.19፤ ዲስከስ የኛ 45.57 የኬኒያ 56.08፤ በጦር ውርወራ የኛ 72 ሜትር ኬኒያ 92.72 ሜትር ደርሷል (በዓለም ቻምፒዮና የወርቅ፡ በኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ተሸልማለች)።
ለተሻሻለ ክብረወሰን የሚሰጥ ሽልማት አመለካከት መቀየር፣ አንደ ምክረሐሳብ የአትሌቲክሱን የወደፊት ዕጣ ፋንታ ሊለውጥ የሚችል ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ዓመታዊ ቻምፒዮና በሚካሄድበት ወቅት አትሌቶች በሚወዳደሩባቸው የሜዳ ተግባራት ክብረወሰን ሲያሻሽሉ ሽልማት ይበረከትላቸዋል። ይህ አካሄድ አትሌቶቹ ለወደፊት እንዲበረቱ ማነሳሳቱ አይካድም። ሆኖም ክብረወሰን ሲሰበር የሽልማቱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ለምን ተሻሽሎ ከአህጉሩ ሚኒማ ጋር አይታሰርም? የአህጉርን ሚኒማ የደረሰ ከፍተኛ ሽልማት ቢሰጠው ከዛ ቀጥሎ ከሚኒማ ያለው ቅርበት ወይንም ርቀት ተለክቶ ለምን ሌላ መስፈርት አይዘጋጅም?
ክለባትና ተወዳዳሪዎቹ ይህ መስፈርት መኖሩን ካወቁ በእርግጠኝነት ጥሩ መነሳሻ ፈጥሮባቸው አመርቂ ውጤት ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ አያጠራጥርም። ውጤቱን ላመጡት አሰልጣኞች ቢሸለሙ በአሰልጣኞች መካከል ጤነኛ ፉክክር ይፈጠራል፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ስፖርቱን እንደሚለውጥ አያጠራጥርም።
በኬኒያና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት ከፍተኛ የደረጃ ልዩነት ይታያል። የወንዶች የሜዳሊያ ድምር ስናነፃፅር ኢትዮጵያ ከኬኒያ መወዳደር ፈፅሞ አትችልም። አገራችን በ19 ቻምፒዮና ተሳትፎ ወቅት 24 የወርቅ፡23 የብርና 24 የነሐስ ሜዳሊያ ስትሰበስብ ጎሮቤታችን ኬኒያ በ20 ውድድሮች ተሳትፎ 89 ወርቅ፣ 71 ብርና በመጨረሻ 63 ነሐስ አግኝታለች።
ኬኒያ በወርቅ በ3.7 እጥፍ፡ በብር በ3 እጥፍ በመጨረሻም በነሐስ በ2.6 እጥፍ ትበልጠናለች። በእውነት የዲቪዚዮን ልዩነት እንዳለ በግልጽ ይታያል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከ5-10ሺ ሜትርና ማራቶን ላይ የሙጥኝ ብሎ ተጣብቋል። ኬኒያ ከአገራችን ተመጣጣኝ የኑሮ ደረጃ እያላት ቀስ በቀስ ረጅም ሩጫዎችን ሳትለቅ ወደ አጭር ሩጫ፣ ዝላይና ውርወራ ጣልቃ ገብታ ውጤታማ መሆን ጀምራለች። ውጤቶቻችን ስናመዛዝን በእውነቱ ከአንድ አፍሪካዊ አገር ጋር የምንወዳደር ሳይሆን ከአንድ ምራባዊ የበለፀገች አገር ጋር የምንፎካከር ነው የሚመስለው።
ኬኒያ የግል ሀብቷ አድርጋ የምትቆጥራቸው የአትሌቲክስ ውድድሮች አሉ፣ እነሱም 800፡ 1500ና 3000 ሜትር መሰናክል ናቸው:: ያመጡት ውጤት በራሱ ምስክር ነው። በ800 ሜትር ከተዘጋጁት 21 ወርቅ ሜዳሊዎች ኬኒያ 16 ወስዳለች፤ በ1500 ሜትር 14 ወርቅ አግኝታለች፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል 13 ወርቅ ወስዳለች። በመቶኛ ሲሰላ ከተመደቡት ጠቅላላ የሜዳሊያዎች ድምር በ800 ሜትር 76 %፣ በ1500 ሜትር 66% በመጨረሻም በ3ሺ ሜትር መሰናክል 62% ሜዳሊያዎችን ወስዳለች። በነዚህ 3 የሜዳ ተግባራት የ3 የተለያዩ ሜዳሊያዎች ድምር 189 ሲደርስ፣ ኬኒያ 91 አግኝታለች ይህም ከአጠቃላይ ከተመደቡት ሜዳሊያዎች 48% መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ እንደ ግል ንብረት የምትቆጥራቸው 5ና 10ሺ ሜትር ሩጫዎች ናቸው ተብሎ ይወራል። እያንዳንዱን ሩጫ ስንገመግም አገራችን በ21 ቻምፒዮና 6 ወርቅ ብቻ ነው ያገኘችው። ኬኒያ 12 ወስዳለች። በ10ሺ ሜትር 7 ወርቅ አግኝተናል፣ ጎሮቤታችን 8ቱን ወስዳለች። ታዲያ ይሄን እያየን እነዚህ ሩጫዎች የኛ የግል ንብረታችን ናቸው ብለን በሙሉ ልብ መናገር እንችላለን ወይ?
የወርቅ፡ የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችን ስንደምር ለ5ና 10ሺ ሜትር 126 ሜዳሊያዎች ተመድበዋል። አገራችን 36 ሜዳሊያ ስትወስድ ጎሮቤታችን ኬኒያ 53 ደርሳለች። የኛ የሜዳሊያ ድርሻ 28.5 % ሲሆን የኬኒያ 42 % ደርሷል። የ3ሺ ሜትር መሰናክል ከወሰድን አገራችን 2 ወርቅ፡ 2 ብርና 5 ነሐስ ሜዳሊያዎች አግኝታለች፡ ይህም 10 ሜዳሊያ ሲሆን ኬኒያ 13 ወርቅ፡13 ብርና 8 ነሐስ ወስዳለች፡ አጠቃላይ ድምሩ ደግሞ 34 ሜዳሊያ መሆኑ ነው። የኛ የ3ሺ ሜ መሰናክል የሜዳሊያ ድርሻ 16% ሲደርስ የኬኒያ ድርሻ 62 % ሆኗል።
ሳምንት ይቀጥላል…….
ዶ/ር ኤልያስ አቡሻክር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2014