አሸባሪ ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በታሪክ በደም በጨቀዩና በአዳፋ እጆቹ ለዘመናት በቀበሮ ጉድጓድ ሆኖ ሲጠብቀው የነበረውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረው ጥቃት እነሆ አንድ ዓመት ሞላው። ይህ ቀን ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለመታደግ ሲሉ ‹‹ሀ›› ብለው መሥዕዋት መክፈል የጀመሩበት ሲሆን አሸባሪ ህወሓት ደግሞ የተለመደ የክህደትና በደም የቆሸሸ ታሪኩን ዳግም የፃፈበት ቀን ነው።
‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል›› እንዲሉ፤ የፈፀመውን ጥፋቱን በመካድ የሀገር መከላከያ ሰራዊትንና የመላው ኢትዮጵውያንን በትር መቋቋም የተሳነው አሸባሪ ቡድን በትግራይ ላይ ጦርነት ተከፈተ ብሎ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እና ለዘመናት የኢትዮጵያን ሃብት በማራቆት በገንዘብ ሲደልላቸው ለነበሩትና ወዳጅ ለሚላቸው አካላት ለማሳወቅ ጥረት አድርጓል።
ታዲያ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ወንጀለኛ የህወሓት አባላትን የመያዝና ሃገርን የማዳን ጉዳይ እንጂ ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚደረግ ጦርነት አድርጎ መመልከት ተገቢ አለመሆኑን በማስረዳትና በተደጋጋሚ በማሳወቅ ወንጀለኞችን በማሳደድ ገሚሱን ለፍርድ በማቅረብ ገሚሱ ደግሞ የእጃቸው እየተሰጣቸው እስከመጨረሻው አሸልበዋል።
መንግስት አሸባሪውን ህወሓት በጦርነት በማሸነፍ መቐለ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላም ዜጎችን በማረጋጋት በሂደት ደግሞ የትግራይ አርሶ አደር በተረጋጋ ሁኔታ ወደ ግብርና ሥራው እንዲመለስ በማሰብ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም አዋጅ በማወጅ ክልሉን ጥሎ ቢወጣም አሸባሪ ህወሓት ጦርነትን ዳግም በመናፈቅ ወደ አዘቅት ታሪክ መመለሱ ይታወሳል። በዚህም ሳያበቃ በአማራ እና ትግራይ ክልል አጎራባች ወረዳዎችና ዞኖች በመስፋፋትና ወረራ በመፈፀም ህፃናትንና አዛውንቶችን መጨፍጨፍ፣ ቤትና ንብረት ማቃጠል፣ እንስሳትን መግደል እና የሀገር ሃብትን ማውደም መገለጫው አድርጎታል። ታዲያ በአሁኑ ወቅት ይህ አሸባሪ ቡድን አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣም መሆኑ ይታወቃል። በታሪክም ተወቃሽነት የሚድንበት ዕድል አላገኘም። በዛሬው ዕትማችን አሸባሪ ህወሓት አፈጣጠር፣ አመጣጥና እኩይ ባህሪያትን ከታሪክ አንጻር በመመዘን እንዲያቀርቡልን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪን ዶክተር ዳግማዊ ተስፋዬ እንግዳ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡-በኢትዮጵያ ታሪክ ሂደት ውስጥ የመሪዎች አመጣጥና ሂደቶችን እንዴት ይገነዘባሉ?
ዶክተር ዳግማዊ፡- የኢትዮጵያ ታሪክ ከ3000 ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ይመዘዛል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተለያዩ መንግስታዊ አስተዳደሮችና ሥርዓቶች ተፈራርቀዋል። እነዚህ ሂደቶችን አልፈው አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ከ1966 ዓ.ም ቀደም ብለው የነበሩት በአብዛኛው በአፄው ሥርዓት ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በዚህም ንጉሳዊ እና ዘውዳዊ ሥርዓቶች ነበሩ። በዚህም በራሱ ቀለም የቆየ ሲሆን ኢትዮጵያ ነፃነቷ ተከብሮ ቆይቷል። ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቿንም ስታስተናግድ ቆይታለች። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያ የቆየ፣ የጎለበተና ታሪክ ጠገብ የሀገረ መንግስት ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ነው። በዚህ ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶችን አስተናግዳለች። የተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጥቃቶችና ጫናዎችን በመቋቋም ብዙ ሂደቶችን ያለፈች ሀገር ናት። ኢትዮጵያ እነዚህን ሂደቶችን አልፋ ወደ ወታደራዊ ደርግ ሥርዓት ተሸጋግራ ነበር። በኋላ ደግሞ ከውስጥና ከውጭ በነበሩ ጥያቄዎችና ጫናዎች የተነሳ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ አዲስ ሥርዓት ለመዘርጋት ሞክሯል።
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያን በተለያዩ መንገዶች ለማስተዳደር የሞከረበት፣ በዚህ ጊዜ በርካታ ችግሮችና ተደራራቢ ፈተናዎች ክስተቶችና መልካም አጋጣሚዎችና ሁኔታዎችን አስተናግዷል። ይህ የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ አሁን ላሉትና ጎልቶ ለወጡት ችግሮችና ግጭቶች መነሻ ነው። ስለዚህ በታሪክ ቅብብሎሽ ውስጥ የምናየው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ምን ያህል የኢትዮጵያን ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር ያሳያል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መንግስት 3000 ዓመት በላይ ታሪክ እንዳላት ሀገር ዘመናዊ ኢትዮጵያን መገንባት ተችሏል?
ዶክተር ዳግማዊ፡- ዘመናዊ ኢትዮጵያ አንፃራዊ ቃል ነው። ምክንያቱም በወቅቱ የተነሱ ሰዎችና አስተሳሰቦችን መቃኘት ይገባል። ለምሣሌ ወደ ኋላ ስንመለከት አክሱም በዘመኑ በጣም የገነነ የሀገረ መንግስት ሥርዓት ነበረ። በአክሱም ዘመነ መንግስት አክሱም የምትባል ሀገር አልነበረችም። አሜሪካ የተመሰረተችው በ1492 ክርስቶፈር ኮሎምቦስ የሚባል መርከበኛ በአሰሳ ካገኛት በኋላ ነው። ስለዚህ በተነፃፅሮ ስትመለከተው የአክሱም መንግስት በጣም ዘመናዊና የራሱ የሆነ መገበያያ ሳንቲሞች አትሞ የሚሰራበትና የሚገበያይበት ዘመን ነበር። ወደኋላም ስንመለከት በላሊበላም፣ በጎንደርም ዘመነ መንግስት እና ሌሎችንም ስንመለከት ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ለመሥራት እያንዳንዱ ጥረት ያደረገበትና በቅብብሎሽ ያለፈ ነው።
ይህ ቅብብሎሽ ጥረት አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ አሁን የገዘፉና የፈጠጡ ችግሮች አሉ። ችግሮቹ ተደራርበዋል፤ የከረሙና የተሸጋገሩ ብሎም ከአንዱ ሥርዓት ወደ ሌላ ሥርዓት እየተንከባለሉ የመጡ ናቸው። ከዚያ አንፃር ሲታይ ምናልባት በእነዚህ ዘመናት ያለፍናቸው የማዘመን ሙከራዎች አጥጋቢ ላይመስሉ ይችሉ ይሆናል። ግን በዘመኑና በድባቡ ስንመለከት እነዚህ የማዘመን ሥራዎች ግዙፍ ነበሩ። እነዚህም ለኢትዮጵያ ጥንካሬ መሰረት ሆነዋል።
እነዚህ ሥርዓቶች ወደ ኋላ ስንመለከታቸው በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ችግር አልፈቱም የሚል ምስል ይሰጣል። ይህ ግን የኋላ ታሪክ አታያይ የመጣ ነው። አብዛኛው ችግር የነበረው በፖለቲካ ሥርዓት የዘመኑን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ሂደቶችን በጊዜው መሥራት አለመቻል ነው። ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የታሪክ ጉዞ ውስጥ ብዙ ችግሮች ተስተውለዋል። በአሁኑ ወቅት እጅግ ትልልቅ ችግሮች የፈጠሩብን አብዛኛዎቹ የመጡት በዚህ ዘመን ውስጥ ነው። ዛሬ ያለንበት የህልውና አደጋ በቀድሞ መንግስታት ውስጥ እንደዚህ ጎልቶ አልታየም። የታዩትም በተለያዩ ማህበራዊና ባህላዊ ችግር መፍቻ ዘዴዎች ሲፈቱ እናያለን። አሁን ያለው ችግር ውጤት በዘመኑ ያመጣው ችግር ውጤት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያን የመራው አካል ለአሁኑ ችግር መሠረት የሆነበት ምክንያት እንዴት ነው?
ዶክተር ዳግማዊ፡- ከውጤቱ ስንመለከት ዛሬ እጅግ አደገኛ የህልውና ችግር ላይ ነን። እነዚህ የህልውና ችግሮች መሠረታቸው ሲመዘዝ ከባለፈው ሥርዓት ጋር ሊያያዝ ይችላል። በእነዚህ ሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ የነበሩ መልካም አጋጣሚዎች አለመጠቀም፣ ችግሮችን አለማለፍ እና ሊሰሩ የሚገቡ ሥራዎችን አለማከናወን ነው። የዛሬ 30 ዓመት የተነሳው ለውጥ ኃይል ኢትዮጵያ ከነበረችበት ችግር ማውጣትና መለወጥን ትቶ በስብሶ እራሱ አሁን ለገባንበት የፖለቲካ ችግር ምክንያት ሆኗል። ይዞት የተነሳቸው የለውጥ ዕቅዶችን ትቶ አበስብሶና ማህበረሰባዊ ዕሴቶችን በማዳከም በታሪክ ጎልተው ያልወጡ ችግሮችን አፍጥጦ እንዲወጡ እና የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዲፈጥሩ አድርጓል።
ለምሣሌ በ1983 ዓ.ም ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል የእኩልነት ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ በ1960ዎቹ ተማሪዎች አንግበውት የተነሱት ጥያቄ ነበር። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ግጭትም የሚነሳው ጥያቄ የዕኩልነት ጥያቄ ነው። ጥያቄው ተሸጋጋሪ ነው፤ ግን ደግሞ አንድ ዓይነት ነው። ሊፈታ የተሞከረበት መንገድም የተለያየ ነው፤ ግን እስካሁን ዕልባት አላገኘም። በ1983 ዓ.ም የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ይዞ የተነሳው ኃይል እራሱ ፍትህና ዴሞክራሲና እኩልነት አፍኖ ይዟል። የነበረውን የመንግስት ሥርዓት ይዞ ቀጥሏል፤ ችግሮቹም ከሥርዓቱ ጋር የተያያዙ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያሉት ችግሮች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የሐሰት ትርክት፣ የታሪክ ጠባሳ ወይስ ሌላ?
ዶክተር ዳግማዊ፡- ጥያቄዎቹ በተወሰነ መልኩ ትክክል ናቸው። ለምሳሌ በ1960ዎቹ ኢብሳ ጉተማ ኢትዮጵያዊ ማነው የሚል ግጥም ፅፎ ነበር። ከብሄሮች ውስጥ ማነው ኢትዮጵያዊ የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር። ከ45 ዓመት በኋላ ማነው ኢትዮጵያዊ ብትል መልስ የሚሰጥ አታገኝም። ስለዚህ ችግሩ ምን ያህል ተሻጋሪ እንደሆነ ማወቅ እንችላለን። ይህን ጥያቄ በ1960ዎቹ ሲያቀነቅኑ የነበሩ ተማሪዎች ከ60 ዓመት በኋላ ይህንኑ ጥያቄ በራሱ ቅርጽና ይዘት አንስተውታል። አሁንም የሕልውና ዘመቻው ሊፈታው የሚፈልገው ነገር ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያዊነት ላይ የተጋረጡ
ችግሮችን ለመፍታት ነው። እነዚህ ችግሮች ዘመናትን የተሻገሩ ናቸው። ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን በደንብ አድርገን ስንመረምራቸው ውስጣዊና ውጫዊ ናቸው።
ሥርዓቱ ከመጀመሪያ እፈታቸዋለሁ ብሎ የተነሳቸው ፕሮግራሞች ነበሩ። እነዚያን ፕሮግራሞች አላሳካም። የተጠቀመባቸው አካሄዶች የተሰነካከሉ ነበሩ። እኩልነትን ለማምጣት የፈለገበት መንገድ ባርቆ ወደ ዓድሎዓዊነት መጣ። የእኩልነትን ጥያቄ ከብሄር አንጻር ተመለከተ። እኩልነትን ለማምጣት የተሄደበት መንገድ ብዙ አጥጋቢ አይደለም። ከ30 ዓመታት በኋላም ይህ ችግር አልተፈታም።
ሁለተኛው የህዝብ ንቃተ ህሊና በተወሰነ መንገድ አድጓል። በ30 ዓመታት ውስጥ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች መስተጋብሮችና ቴክኖሎጂ የተነሳ የህዝቡ ንቃተ ህሊና ተለውጧል። ስለዚህ ዘመናትን ሲሻገሩ የነበሩ ጥያቄዎችን በአዲስ አተያይ ይመለከታቸው ጀምሯል። ማህበረሰባችን ከ30 ዓመት በፊት የነበረ ማህበረሰብ አይደለም። ይህን ችግር እንፈታዋለን የሚሉት ደግሞ የዛሬ 30 ዓመት የነበሩ ሰዎች ናቸው። አስተሳሰባቸው፣ ስሜታቸው፣ እይታቸው ከ30 ዓመት በፊት የነበረ ነው። ስለዚህ ይህን ማስተናገድ አልቻሉም። ስለዚህ በትግሉ ላይ የሚያውቁትን አስተሳሰብ የሙጥኝ ብለው መቆየታቸውና የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባለማስገባታቸው የተነሳ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ምድር ለውጥ አምጥተናል ብለው ሲያወሩ የነበሩ ስብስቦች የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው እውነት ሀገራዊ ስሜት ካለው አካል ይጠበቃል?
ዶክተር ዳግማዊ፡- ይህ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። 1983 ዓ.ም ስልጣን ላይ የወጣው ኃይል በፖለቲካ ሚዛን አሰላለፍ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጤነኛ አመለካከት የለውም። ምክንያቱም ሰራዊቱን በጠቅላላ ፈርጆታል። የደርግ ሰራዊት የሚለውን አመለካከት ይዞ ይህን ሠራዊት በመልካም አይረዳውም ነበር። የራሱን ስርዓትና አመለካከት ብቻ የሚከተሉ ሰዎችን ለማሰባሰብ ሙከራ አድርጎ ነበር። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ የሚል ስሜትና አመለካከት ያላቸውን የወታደሩን አካላት የራሱ የሆነ ችግር ነበረው።
ሥርዓቱ የራሱን ጥቅም ለማስከበር እና ይዞት የተነሳውን ዓላማ ብቻ ለማሳካት ወይንም አጀንዳቸው ትግራይን ማስተዳደርና ነፃ ማውጣትና ኢትዮጵያን ማራቅ ነበር። እያደር ግን ኢትዮጵያን ነፃ ማውጣት ዘመቻ ገብተዋል። ስለዚህ ሰራዊቱ ተዋቅሮና ሥነ ልቦና የተከፋፈለ ነበር። ስለዚህ ከኢትዮጵያ ነገስታት የሰራዊት አወቃቀር በተለየ ሁኔታ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረተ አልነበረም። በ27 ዓመታት ውስጥ ሲቀነቀን የነበረው የብሄርተኝነት አመለካከት በሰራዊቱ የጋራ አመለካከት ለሀገር ያለውን ቀናዒነት በመሸርሸር ላይ የተመሰረተ ነበር።
ከ1983 የነበረው ለሰራዊቱ የነበረው ጥሬ ስሜት አልነበረም። የተሸናፊነትን መንፈስ የተጠመቀና ይህን ይዞ የተነሳ ነው። አንግበው የመጡት ዓላማም የተንሸዋረረ ነው። አሁን ያደረሱት ጥቃትም ያኔ ይዘው የመጡት የተንሸዋረረና የተቀባ አመለካከት ነው። ሌላው በሰራዊት ሥነ-ሥርዓትና ዓለም አቀፋዊ ኮድ አለማመን ነው። የእኩይ ድርጊቱ ፈፃሚዎቹ የወታደራዊ ብቃት ከፍታና ወታደራዊ ሞራል የዘቀጠ መሆኑ ማሳያ ነው። ሌላኛው ጉዳይ በኢትዮጵያዊነት አለማመናቸው ነው።
ከሀገር ይልቅ የራሳቸውን ፍላጎት የመጫን የሚፈልጉ ሰዎች የሠራዊቱን ክብር ለማሳነስ ያደረጉት ነገር ነው። ይህ እጅግ አሳፋሪና ዘግናኝ ድርጊት ነው። ድርጊቱ የኢትዮጵያን ህዝብ የከዱበትና ራሳቸውም የከሸፉበት አጋጣሚም ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም የዘቀጠ የወታደራዊ ሥነምግባር ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ያሳወቁበት ነው። ይህም ከመሠረታዊ ባህሪያቸው ተነጥሎ መታየት የለበትም። እነዚህ ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ በወታደራዊ ሥነ ምግባር የታነፁ አይደሉም። በታጋይነት፣ በብሄር ተዋፅዖ፣ በአገልግሎት እና በታማኝነት የመጡ ሰዎች እንጂ በሀገራዊ ፅንሠ ሃሳብ የተቀረፁ ሰዎች አይደሉም የሚለው ፅንሥ ሃሳብ ገዥ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪ ህወሓት በጦርነቱ ህፃናትና አዛውንቶችን ማሰለፍና መጨፍጨፍ፣ ንብረት ማውደምና የሀገር ሃብት መዝረፍ ላይ ተጠምዷል። ይህ በሌላ ጦርነት የተለመደ ነው?
ዶክተር ዳግማዊ፡- ይህን ቡድን ወደኋላ ስንመለከተው አሁን የምንሰማቸው ዜናዎች ዓረፍተ ነገሮቹ ይቀየራሉ እንጂ በደርግ ዘመን የምንሰማቸው ዜናዎች ናቸው። በትግል ውስጥም እያሉ የሚፈፅሟዋቸው ድርጊቶች በተለያዩ ዘመን ላይ የጊዜ ማሽን ተሻግረው መለወጥ አለመቻላቸውን ያሳያል። ጊዜና ዘመን ተሻግረው ያንኑ ድርጊት በተመሳሳይ ሁኔታ ሲፈፅሙ ይስተዋላል። ይህ ድርጊት ከእነርሱ መሰረታዊ ባህሪያቸው ጋር የተገናኘ ነው። ከማንነታቻውም ጋር የተገናኘ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ታሪካቸው በሙሉ በዚህ የጥፋት መንገድ የተቀረፀ ነው ማለት ነው?
ዶክተር ዳግማዊ፡- እንግዲህ ይህ አመለካከት በእርግጥ ይህን ለምን አደረጉት ብሎ ለመረዳት በእነርሱ ቦታ ገብቶ ማየት ያስፈልጋል። በእርግጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በክልላዊነት ወይንም በፖለቲካ ስልጣን ሽኩቻ እርስ በእርስ የተደረጉ ግጭቶች ነበሩ። ለምሳሌ እ.ኤ.አ 1769 እስከ 1855 ኢትዮጵያ በክልላዊ የጦር አበጋዞች ተከፋፍላ እርስ በእርስ የተደረገ ጦርነት ነበር። ነገር ግን ከዚህ ዘመን በኋላ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበሩ ጦርነቶች የፍተሻ ነበሩ። በዚህ ዘመን ብዙ ሃይማኖታዊ ተቋማት ወድመዋል፣ ህፃናትና አዛውንቶች ተጎድተዋል።
ነገር ግን ይህን ጦርነት ለየት የሚያደርገው ድርጊቱ የተፈፀመው ሀገሪቱን ለ30 ዓመታት ሲያስተዳድር የነበረ ኃይል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር ለ50 ዓመታት አልለቅም ብሎ የሙጥኝ ያለ ሥርዓት የፈፀመው መሆኑ ነው። የፖለቲካ ዕድል ተነፍጎም ሳይሆን ከእኔ በላይ ይህን የፖለቲካ ምህዳር የሚያውቀው የለም ብሎ የማውቀው እኔ ብቻ ነኝ የሚል አስተሳሰብ ያመጣው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ክስተቶችና ታሪካዊ ጠላቶች ነበሩ። በዚህ ጦርነት ውስጥ የውጭ ኃይሎች ሚና እስከ ምን ይደርሳል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ዳግማዊ፡- እነዚህ ሰዎች በ1983 ዓ.ም ወደ ስልጣን ሲመጡ ያደራደሯቸው የውጭ ኃይሎች ናቸው። ስልጣን ያረካከቧቸው፣ አይዞ ባይና ጋሻጃግሬዎች አላቸው። እነዚህን አካላት ተማምነው ያደረጓቸው ነገሮች አሉ። ቅድመ 1983 ዓ.ም ከምዕራባውያን ኃያላን ሀገራት ጋር የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል በተለያየ መድረክ ላይ ደንበኝነት ያፈሩ ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ በትግልም ላይ በነበሩበት ወቅት እና በቀዝቃዛው ጦርነት ዓለም በሁለት ጎራ ተከፍላ በነበረ ጊዜ እነዚህ ታጋዮች የቀዝቃዛውን ጦርነት የኃይል ሚዛን በመጠቀም ከምዕራባውያን ጋር በመወገን በሶሻሊስት ሥርዓት ሲመራ የነበረውን የደርግ ሥርዓት ለማጥቃት ያደረጉት ሁኔታ ከምዕራባውያን ጋር ለመደራደር ከፍተኛ ችሎታ፣ ደንበኝነትንና ታማኝነትን ያተረፉ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ ይህ አዲስ ነገር አይደለም። አሁንም ችግር በሚመጣበት ጊዜ የሚሄዱበት አካሄድ በፊት ከችግር የወጡበትን መንገድ መድገም ነው።
በመሆኑም መሠረታዊ ባህሪያቸው፣ እንቅስቃሴያቸውና ሁኔታቸው ይተነብያል። ስለዚህ ባይኖሩ እንኳን እነዚህ ይጋብዛሉ። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በሁለቱ የፖለቲካ ጎራዎች ከዚያም በጦርነት ወይንም በፖለቲካ በነበረው ሽኩቻ ውስጥ እያጫወቱ የመጡ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሸማቂ ሴራ የተቀረፁና የተፈለፈሉ ናቸው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን መጋበዛቸው አይቀሬ ነው። ምክንያቱም ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። እነርሱ የሥልጣን ማማ ላይ መቀመጥ እንጂ የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ ወይንም ከዚያ በኋላ የሚመጣው ጫና አያስጨንቃቸውም።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት በገሃድ ‹ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ› ብሎ ነው የተነሳው። በታሪክ እንዲህ ፅንፍ የወጣና ሀገር አፈርሳለሁ ብሎ የፎከረ አካል ያውቃሉ?
ዶክተር ዳግማዊ፡- በጣም በስልጣን የናወዙ ሰዎች ይኖራሉ። በነገራችን ላይ ታሪካቸውን ብንመለከትና አመጣጣቸውን ብናይ ለምሳሌ ፖለቲካቸውና የውስጥ አስተዳደራቸው እጅግ ደም አፋሳሽ ዘግናኝ ድርጊቶችን ያቀፈ ነው። በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ዕድገት ውስጥ የመጡ አይደሉም። ደም የጠማቸው፣ እርስ በእርስ ሲገዳደሉ ለፖለቲካ ወንበር ሲታገሉና ሲጨፋጨፉ የመጡ ናቸው። ይህ አመለካካት ወይንም የኋልዮሽ ታሪካቸው ከስልጣን በኋላም የሚያደርጉትን ያመላክታል።
በታሪክ ስንመለከት ምናልባት በኢትዮጵያ ታሪክ ለስልጣን፣ ለበላይነት ወይንም ለንጉሳዊነት ይታገሉ ይሆናል እንጂ ኢትዮጵያን የማፍረስ ነገር ተስተውሎ አያውቅም። ኢትዮጵያ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ የሚያስማማቸው ቃል ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደ ሃይማኖት ባህል አድርገው የያዙ እንጂ ለስልጣን ብሎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተደራደሩ ሠዎች ምናልባት በፋሽስት ዘመን ባንዳ የተባሉ ናቸው። ባንዳዎች በፋሺስት ዘመን የጣሊያንን ሥርዓት እያገለገሉ የነበሩ ሰዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪ ህወሓት የተለየ እኩይ ተግባር ነው እያሉኝ ነው?
ዶክተር ዳግማዊ፡- በትክክል! በነገራችን ላይ እነዚህ ሰዎች ከባንዳዎችም ጋር ይገናኛሉ፣ በባህሪያቸውና በሥሪታቸው። ከእነዚህ ሰዎች ውጭ ለስልጣን ብለው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጡ ሰዎች በታሪክ አልተመዘገቡም።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ፈተና በማለፍ የደማቅ ታሪክ ባለቤት ለመሆን እንደ ሀገር ምን መደረግ አለበት?
ዶክተር ዳግማዊ፡- ይህ ሁኔታ የራሱ የሆነ እንቅስቃሴ አለው፤ ኢትዮጵያዊነትን መታደግ። የኢትዮጵያ ህዝቦች መግባባት፣ አንድነት መፍጠር፣ የጋራ ጠላትን መለየትና በጋራ ጠላት ላይ እጃቸውን ማንሳትና መተባበር ጀምረዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች በጦርነት ብቻ ሳይሆን ታላቁን የህዳሴ ግድብ በጋራ ለመገንባት እጅ ለእጅ ተያይዘው ተነስተዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ በፅናት መታገል፣ ቁርጠኝነት፣ ለዓላማ መገዛትን ይጠይቃል። ይህ ፈተና ነው። በአንድ መልኩ አደገኛ የለውጥ ጊዜ ነው። ስንመለከተው የተያዘ ፅንስም አለ። ሊወለድ የፈለገ ፅንስና ቅርፁ ገና ያልታወቁ የሚመስሉ ነገሮች አሉ። ስለዚህ ይህ ለውጥ ወይንም ፅንስ እንዲወለድ ህዝቡ በፅናት፣ በቁርጠኝነትና በመሰጠት መታገል አለበት። የኢትዮጵያ መሪዎች ታሪክ እንደሚያሳያው ታሪካዊ ሂደቶችን መከተልና ህዝባቸውን መምራት የሚስፈልገውን ነገር ማድረግ አለባቸው።
ኢትዮጵያዊነትን ዓላማ አድርጎ እና የኢትዮጵያን ህዝብ አስቀድሞ ማስተባባር፣ ማግባባት፣ መምራት ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ በመተባባርና በመደጋገፍ የጋራ ታሪክ መሥራት ይገባል። የውስጥና የውጭ ጠላት ላይ በተባበረ ክንድ አቅምን ማሳየት ይገባል። የኢትዮጵያዊነትን አሻራ ለማሳረፍም ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍላችን ሥም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ዳግማዊ፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሃንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ.ም