አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ እያደረሰች ባለችው ተደጋጋሚ ጫና አንዳች ነገርን መቀልበስ እንደፈለገች ያሳብቅባታል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአደራዳሪነት ካባ ደርባ የልቧን ማድረስ ሳትችል ብትቀርም በተደጋጋሚ የተለያዩ ዛቻና ማስፈራሪያዎችን ስትሰነዝር መሰንበቷ ይታወቃል። በተለይም በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና መያዣ በማድረግ እጅ ጠምዛዥ የሆኑ በርካታ ጫናዎችን እያደረሰች ትገኛለች።
በአሜሪካ ፈርጣማ ክንድ የተማመነው አሸባሪው የትህነግ ቡድንም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ተቀን በሚወስደው እርምጃ በርካታ ንጹሐሃን እየተጨፈጨፉ፤ ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ ነው። ይህ መሬት ላይ ያለ እውነታ ለአሜሪካ ብዙም ስሜት የሚሰጣት አይደለም። ቡድኑ በአገሪቱ እያደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስም እሷን የሚያሳስባት አይሆንም። ከዚህ ይልቅ እሷን የሚያሳስባት የአሸባሪውን ሕወሓት አስትንፋት ማስቀጠል ነው። ለዚህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተጨማሪ ፈተና ለመሆን እየተዘጋጀች ነው።
ለሕዝባችን ፈተና እንዲሆን ከጥቂት ወራት አስቀድማ መያዣ ያደረገችው ደግሞ ‹‹አጎዋ›› ነው። ‹‹አጎዋ›› በምሥራቅ አፍሪካ ለሚገኙ አገራት ከቀረጥ ነጻ የገበያ ዕድል የሚሰጥ ሲሆን ይህን ዕድል ታሳቢ በማድረግ በርካታ የውጭ አገር ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በዕድሉ ተጠቃሚ በመሆን በርካታ የሥራ ዕድል በመፍጠር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
አሜሪካ ኢትዮጵያን ሊያፈራርስ ከተነሳው አሸባሪ የትህነግ ቡድን ጋር በማበር ቡድኑ ‹‹ሀ›› ብሎ የጥፋት በትሩን ኢትዮጵያ ላይ ካሳረፈበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ላይ ያልተገቡ ጫናዎችን በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ዓለም የሚውቀው ጉዳይ ነው። በአሸባሪው ሕወሓት የስልጣን ዘመን የነበራትን ተጠቃሚነት ለማስቀጠልም ያገኘችውን አጋጣሚ ሁሉ እንደመልካም እድል ለመጠቀም እየሞከረች ነው።
መንግሥት ከአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጋር እያደረገ ባለው የአገር ሕልውናን የማስቀጠል ዘመቻ የአሜሪካ ፍላጎትና ኢትዮጵያ ላይ ያላት አቋም ፍንትው ብሎ ታይቷል። አሸባሪ ናቸው የምትላቸውንና አይነ ውሃቸው ያላማራትን ግለሰቦችና ቡድኖች ዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር ሕግ አውጥታ ከምድረ ገጽ እንዳላጠፋች ሁሉ፤ ዛሬ ተሰምተውና ታይተው የማይታወቁ ግፎችን ከሚፈጽሙ ሽብርተኞች ጋር ጋብቻ ፈጽማ ኢትዮጵያን እናፈርሳለን ለሚሉ አካላት አቅም እየሆነች ነው። ከዚያም አልፋ ሁኔታውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የራሷን ፍላጎት ለማስጠበቅ ስትል ያልተገቡ ውንጀላዎችንና ማእቀቦችን ለማድረግ እየተዘጋጀች ነው።
የቡድኑን የሽብር ተግባራት በአደባባይ ለማውገዝ ፈቃደኝነት ከማጣት ጀምሮ፤ ቡድኑ ያጠቃ ሲመስላት ዝምታን የተጠቃ ሲመስላት ደግሞ በሕግ አምላክ አይነት ጨዋታና ማስፈራሪያ ዛቻዋን ጦርነቱ በወሰደው ጊዜ ሁሉ ስታሳየን ከርማለች።
ከጦርነቱ እኩል የአንድ ዓመት ጊዜን ያስቆጠረው የአሜሪካ ዛቻና ማስፈራሪያ ዛሬ በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ እየሆነ መጥቷል። በባለሥልጣናት ላይ የቪዛ እገዳ ከማድረግ ጀምሮ የጦር መሳሪያ ግዥ ማእቀብ እስከ ማድረግ ደርሳለች። ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ምርቶቿን ‹‹አጎዋ›› በሚባለው የገበያ ዕድል ተጠቅማ በግዛቴ ያለቀረጥ እንድትሸጥ የሰጠኋትን ፍቃድ ላነሳ ነው በማለት ውሳኔዋን አስተላልፋለች።
ውሳኔው ምንም እንኳን ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚፈጥርና ‹‹በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ቢሆንም፤ ማእቀቡ ከኢትዮጵያ ሕልውና ጋር ሊወዳደር የማይችል፤ ዋጋ እየከፈልን ካስጠበቅነው ነጻነታችን አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ ይታመናል። ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ አስበልጠው የሚደራደሩበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥቅም የላቸውም። ሊኖራቸውም አይችልም።
አሜሪካ ‹‹አጎዋ››ን ከኢትዮጵያ ለማቀብ ያሳየችው ፍላጎት በበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕልውና ላይ ያነጣጠረ ስለመሆኑ ምስክር የሚያሻው ጉዳይ አይደለም። ይሁንና አሜሪካ ኢትዮጵያ ተገዳ በገባችበት ጦርነት ተሸናፊ እንድትሆን አልያም አሸባሪው የትህነግ ቡድን ያሻውን እንዲያደርግ ካላት ፍላጎት በመነሳት እንዲህ ብታደርጉ እንዲህ እናደርግላችኋለን ፤ እንዲህ ባታደርጉ እንዲህ እንደርግባችኋለን እያለች ብትወተውትም፤ በኢኮኖሚ የፈረጠመ ክንዷ በመቶ ሺ በሚቆጠሩ ደሃ እንጀራ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ላይ ቢያነጣጥርም ኢትዮጵያዊ ኩሩ ነውና ተርቦ፣ ተጠምቶና ታርዞም ቢሆን ይህን ፈታኝ ጊዜ ተጣጥሮ ያልፈዋል እንጂ ለእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ እጁን አይሰጥም ።
እርግጥ ነው በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ውስጥ እንጀራ በልተው የሚያድሩ ከ200 ሺ የሚልቁ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች እንዲሁም በሥራቸው የሚተዳደረውን በርካታ ቁጥር ያለውን ቤተሰብ ጨምሮ ዛሬ በልቶ ማደር ጥያቄ ይሆን ይሆናል። ነገር ግን ‹‹ክፉ ጎረቤት ዕቃ ያስገዛል›› እንዲሉ ኢትዮጵያውያን ያልተጠቀምነውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና አቅም በሙሉ አሟጠን በመጠቀም ልንሠራ የግድ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
እኛ ኢትዮጵያውያን አገራችን አሁን የገጠማትን ፈተና ሁሉ እንደ ዕድል ተጠቅመን ጠንክረን ከሰራን የተጋረጡብን ጋሬጣዎች የችግሮቻችን ሁሉ መወጣጫ መሰላል ይሆኑናል። ካልሆነ ደግሞ ወደ አዘቅት ሊያንደረድሩን እንደሚችሉ ተረድተን እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።
‹‹የምወስዳቸው እርምጃዎች ሕዝብን የሚጎዱ አይሆኑም›› ያለችው አሜሪካ የአጎዋ ገበያን መንፈጓ በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት ላይ የሚያጠላውን ጥላ አልተረዳችው ይሆናል ብለን አንሞኝም። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ምን በልተው አደሩ የሚለውን ሳይቀር ልወቅ፣ ልመርምር፣ ልፈትፍት፣ የምትለው አሜሪካ ኢትዮጵያ ከአግዋ በምታገኘው ጥቅም ልክ ተጎጂ እንደምትሆንም ጠንቅቃ ታውቃለች።
ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የአግዋ ፎረምን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ በአግዋ በኩል ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የተለያዩ ምርቶችን በተለይም በስፋት ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ ለመቶ ሺዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ስታገኝ መቆየቷ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አሁንም አለ ከአግዋ አስቀድሞም ነበር። ኢትዮጵያ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊትም አሁንም ከደሃ አገራት ተርታ የምትገኝ አገር በመሆኗ የአግዋ ነገር ከአገር ሕልውና ቀድሞ የሚሰማ አይሆንም። የአገራችንን ሕልውና እያስጠበቅን የታጣው ዕድል የሚገኝበትን አማራጭ እንፈልጋለን። ካልሆነም የአገር ሕልውና ከተረጋጋጠ በኋላ የሚከተል ጉዳይ ነው።
ዕድሉን ታሳቢ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የውጭ ባለሃብቶችም ቢሆኑ ኢትዮጵያ ብዙ ተስፋ ያላትና ተፈጥሯዊ ሀብቷ ያልተነካች አገር ስለመሆኗ ጠንቅቀው በመረዳት አገር ሰላም ስትሆን የበዙ አማራጮች ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችል ሊያስተውሉ ይገባል። ‹‹ችግር ብልሃትን ይወልዳል›› እንዲሉ ችግሩን ለማለፍ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል።
እርግጥ ነው አሜሪካ ያሳለፈችው ውሳኔ የበርካታ ሴት እህቶቻችንን የሥራ ዕድል የሚዘጋ እንደመሆኑ እጅግ አሳዛኝ ነው። ግን ደግሞ ሀሞተ ኮስታራ በሆነው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ሐዘናችን የሐዘን ዳርቻ ያድረገው ብለን በሥራና በሥራ ብቻ ልናሸንፈው የምንችለው ድህነታችን ላይ በመዝመት ነው፤ ለዚህም ሁላችንም መታጠቅ አለብን።
አሁን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቅድሚያ አገርን ከጠላት ለማዳን እያደረገ ባለው ቁርጠኝነት ልክ የመሥራት ፍላጎትና ትጋትን ሊፈጥር ይገባል። አሸባሪው የትህነግ ቡድን ተወግዶ አገር ሰላም ውላ ሰላም ማደር ስትጀምር ያን ጊዜ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይሆናል። አፈርሳታለሁ ያለው ፈርሶ፤ አፍጣጭ ገልማጮቿ ጠፍተው ሁሉም ነገር መልኩን በያዘ ማግስት ለሥራ የደረሱ እጆች ሁሉ ሥራ ሳይፈቱ ሌት ተቀን ሠርተው የድህነት አቧራችን ይራገፋል። ያኔ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይሆናል። ‹‹አጎዋ››ም በዳግም ‹‹አድዋ›› ይዘከራል።
ፍሬህይወት አወቀ