ኢትዮጵያውን በየዘመኑ ስለአገር ከፍ ያለ ዋጋ በመክፈል የሚታወቁ፤ በዚህም የሚዘከሩ ሕዝቦች ናቸው። በተጋድሎ ታሪካቸውም ነጻነታቸውን፣ ብሎም ባህል እና ሃይማኖታቸውን ጠብቀው መኖር የቻሉ፤ በብዙ የግዞት ጨለማ ውስጥ ላሉ ሕዝቦችም ብርሃን ፈንጣቂ ፤ ፋና ወጊ በመሆን የሚጠሩና የሚከበሩ ሕዝቦች ናቸው።
ኢትዮጵያዊ ሁሌም ለአገሩ ለመሞቱ ቁርጠኛ የመሆኑ ሚስጥር ስለአገር ካለው ጥልቅ ትርጉም የሚመነጭ ነው፤ ከዚህ የተነሳም ለኢትዮጵያውያን ስለ አገር ለመስበክ መነሳት “ለቀባሪ አረዱት” እንደሚባለው ተረት ከመሆን ባለፈ ትርጉም የሚኖረው አይሆንም። ድንገትም እንደ ስድብ ሊታይ የሚችልበት አግባብ ሰፊ እንደሚሆን መገመት አዋቂነት ነው።
ለአገር መሞት ለኢትዮጵያዊያን የክብር አክሊል ነው። በችግር ወቅት ለአገር ቀድሞ መገኘት ዋጋው “ተወለደና ሞተ” ከሚለው የተለመደ ትርክት ከፍ ባለ የታሪክ መዝገብ ውስጥ ስፍራን የሚያስገኝ ትልቁ አገራዊ እሴት ነው። እሴቱ በዘመናት መካከል የተገነባና በተጨባጭ የመስዋእትነት ታሪክ እየታደሰ የመጣ ነው።
ዛሬም ቢሆን ይህ አገራዊ እሴታችን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ቢያልፍም አገር እንደ አገር ችግር ውስጥ ስትገባ የተጫነባትን ሸክም አራግፎ እና ህያው ሆኖ አደባባዮችን ሞልቶ እየታየ ነው። ስለ አገር መሞት ከሁሉም የላቀ የክብር አክሊል ስለመሆኑም በህይወት እየተዜመ ነው።
በዘመናት መካከል እንደሆነው ሁሉ፤ በየዘመኑ የነበረው ትውልድ ስለአገር መስዋዕት ለመሆን አደባባዮችን ሞልቶና ተርፎ እንደታየው፤ ዛሬም አገር የህልውና አደጋ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ትውልዱ የመስዋዕት ሰልፈኛ ሆኖ ለአገሩ ቆሟል። ለአገሩ ቀድሞ በመሞት በታሪክ ውስጥ ሕያው ለመሆን ጥድፊያም ውስጥ ገብቷል።
ይህ ትናንት በዓድዋ የታየው ስለ አገር የመሞት ክብር በዚህ ትውልድ ላይ ሕይወት ዘርቶና ጎምርቶ የመታየቱ እውነታ፤ አንድም ትውልዱ የአባቶቹ ልጅ መሆኑን፤ ከዚያም በላይ ያልተወላገደ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ የተዋቀረ ስለመሆኑ በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
የአሸባሪው ሕወሓት የባንዳነት ተልእኮ የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ በጨመረበት በዚህ ወቅት፣ መላው ሕዝባችን አደጋውን ለመቀልበስ ያሳየው ከፍ ያለ መነሳሳት ዛሬም ለኢትዮጵያውያን አገር በሕይወት የሚወራረዱበት ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ ስለመሆኑ ለዓለም ዳግም ማሳየት ያስቻለ ክስተት ሆኗል።
አሁናዊ እውነታው መላው ሕዝባችን ከአገር የሚያስቀድመው ጉዳይ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፤ ለአገር መሞት የቱን ያህል ክብር እንደሆነ፤ በተጨባጭ ለክብር ሞት ሰልፈኛ በመሆን፤ ለአገሩ በክብር ለመሞት ያለውን ዝግጁነት አደባባይ ወጥቶ እያረጋገጠ ይገኛል። ያለ አገር ህይወት በራሱ ሞት እንደሆነም ከፍ ባለቃል እያስተጋባ ነው።
ትውልዱ ከትናንት አባቶች የወረሰው ይህ ከፍ ያለ ስለ አገር የመሞት እሴት፣ አገርን ከአደጋ ከመታደግ ባለፈ ነገ ላይ ተስፋ አድርገን መንገድ ለጀመርንለት የብልጽግና ጉዞ ስኬት ዋነኛ መሠረት ነው። አዲሲቷን ኢትዮጵያ አስተማማኝ መሠረት ላይ ለመገንባትም የሚኖረውም ፋይዳ አልፋና ኦሜጋ ነው።
አሁን ላይ አገርን ከህልውና አደጋ ለመታደግ በየቦታው እየተፈጠረ ያለው ሕዝባዊ አቅምም በቀጣይ ልንገነባት ላለችው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያና አገራዊ አንድነት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን በጠንካራ መሠረት ላይ ከማዋቀር ባለፈ እንደሚያፋጥነውም ይታመናል።
ከነዚህ ተጨባጭ እውነታዎች በመነሳትም መላው ሕዝባችን አገሪቱ በአሸባሪው ሕወሓት ያጋጠማትን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ እያደረገ ያለው የሕይወት መስዋእትነት አገርን እንደ አገር ከማስቀጠል ያለፈ ትርጉምና ተልእኮ የተሸከመ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ.ም