እአአ በ2010 የዓለም መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ እንዲሁም የጋዜጦችና መጽሄቶች የፊት ገጽ አድማቂ የአንድ ስፖርታዊ ውድድር ዜና ነበር።ይህ ውድድር በቴኒስ ስፖርት ታላቅ በሆነው ዌምብልደን የታየ ሲሆን፤ ‹‹ማለቂያ አልባው ውድድር›› የሚለው የብዙዎች አርዕስትም ነበር።በዚህ ውድድር ምክንያትም መሰል ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ በሚል እሳቤ ስፖርቱ በደንቦቹ ላይ ለውጥ ለማድረግም ያስገደደው ሆኗል።
በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ብዙ የተባለለት ይህ ውድድር በሜዳ ቴኒስ ስፖርት እጅግ በርካታ ክብረወሰኖችን በመሰባበር እስካሁንም አቻ አልተገኘለትም።የክብረወሰኑ ባለቤቶች ደግሞ አሜሪካዊው ጆን ኢዝነር እና ፈረንሳዊው ኒኮላስ ማውት ናቸው።ይህንን ውድድር ልዩና አስደናቂ አያደርገውም እንደተለመዱት ስፖርታዊ ውድድሮች በተወሰነ ሰዓት ብቻ የተደረገ ሳይሆን ቀናትንም የወሰደ በመሆኑ ነው።
ጨዋታውን የእንግሊዙ ቢቢሲ እንዲሁም የአሜሪካው ኢኤስፒኤን የተባሉት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሁሉም ቻናሎቻቸው በቀጥታ ስርጭት ያስተላለፉት በመሆኑ በዌምብልደን ከታደሙት ባሻገር በመላው ዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ሊመለከተው ችሏል።ውድድሩ በመጀመሪያው ዕለት እንደተጠበቀው ባለመጠናቀቁ ለሚቀጥለው ቀን ቀጠሮ ሲሰጥ፤ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።ሆኖም በሁለተኛውም ቀን ባለመጠናቀቁ ምክንያት ለተጨማሪ ቀን ማሳደር አስፈላጊ ነበር፡፡
ሁኔታውም በጨዋታ ለመታደም የቻሉትን የስፖርቱ አፍቃሪዎች ብቻም ሳይሆኑ ተወዳዳሪዎቹንም ጭምር ከዚያ ቀደም ባልታየው ፉክክር ግርምት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸው ነበር።ፈረንሳዊው ተወዳዳሪ ማውት የሁለተኛው ቀን ጨዋታው ለሌላ ሶስተኛ ቀን መሸጋገሩን ከአወዳዳሪው አካል ሲረዳ ‹‹መጨረሻውን ማየት እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን ነገም መምጣት ይኖርብናል›› ሲል ነበር አስተያየቱን የሰጠው።
ለሶስት ቀናት ማለትም ለ11 ሰዓት ከ 05 ደቂቃ የቆየው ውድድር በመጨረሻም አሸናፊውን ሊያገኝ ቻለ።በወቅቱ ተመልካቹ በአስደናቂው ትዕይንት የተመሰጠ ቢሆንም ተጫዋቾቹ ግን እፎይታም ጭምር ያገኙበት መሆኑን ከሁኔታቸው ለመረዳት ይቻል ነበር።በቴኒስ ስፖርት
ታሪክ ረጅሙ ጨዋታ በሚል ከስፖርት ድርሳናት ሲሰፍርም፤ 70ለ68 በሆነ ውጤት በአሜሪካዊው ኢዝነር አሸናፊነት መጠናቀቁ ተመላክቷል።ውድድሩ በተካሄደበት የዌምብልደን ሜዳም ይህንን ውድድር የሚያስታውስ ታሪካዊ ማስታወሻ ተቀርጾላቸዋል።ሁለቱም ተጫዋቾች በጋራ ‹‹ምርጥ የክብረወሰን ሰባሪ ብቃት›› የሚል ክብርንም ተቀዳጅተዋል።ሁለቱ ተጫዋቾች ሽልማቱን ያገኙትም በሜዳ ቴኒስ ቀዳሚ ከሆኑት ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን ሮጀር ፌደረር እና በአጭር ርቀት ሩጫ አዲስ ክብረወሰኖችን የሰባበረውን ጃማይካዊ አትሌት ዩሴን ቦልትን በማሸነፍ ነው።
በስፖርቱ የሰው ልጅ ምን ያህል ሊጓዝ እንደሚችል የታየበት ውድድር ነበር፣ ውድድሩ የተጠናቀቀበት ውጤትም ቢሆን ተወዳዳሪዎቹ ምን ያህል በአካልና በአእምሮ ብቃታቸው ተመጣጣኝ እንደሆነ በግልጽ የሚያመላክት ነው።አንጋፋ የቴኒስ ተጫዋቾች እንዲሁም ሌሎች የስፖርቱ ባለሙያዎችም ታሪካዊና ከዚህም በኋላ ሊደገም የማይችል ውድድር ሲሉ ነበር የገለጹት።በዚህ ስፖርት ዝነኛ የሆነው ሮጀር ፌደረር ‹‹ይህንን ጨዋታ ማየት እጅግ አስደሳች ነው፤ ማልቀስ ወይም መሳቅ እንዳለብኝ አላወኩም ነበር።በጣም አስደናቂና ከየትኛውም በላይ የሆነ ጨዋታ ነው›› ሲልም የተሰማውን ስሜት አንጸባርቋል።
ሌላኛው ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪች ደግሞ ‹‹በዚህ ውድድር ማንም አሸነፈ ማን ሁለቱም አስደናቂ ተወዳዳሪዎች ነበሩ።ሁለቱም አሸንፈዋል›› ብሏል።የቀድሞ ቴኒስ ተጫዋች አሜሪካዊው ጆን ማክኢኖር ‹‹ይህ ስፖርቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያስተዋውቅ የሚችል ሲሆን፤ እኔም የዚህ አካል በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል።ከዚህ ቀደም በስፖርቱ የሚገባንን ያህል እውቅና አናገኝም ነበር፤ ይህ ግን ለስፖርቱ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያደርግ ነው›› በማለት ገልጾታል።
ሶስት ቀናትን ከዘለቀው ጨዋታ በኋላ ተጫዋቾቹ እጅግ ደክመው የነበረ ሲሆን፤ የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው ቢያንስ ለስድስት ወራት ያህል ማገገሚያ የሚያስፈልገው ጉዳት በአካላቸው ላይ መታየቱንም ነው የጠቆሙት።በቀጣዩ ዓመት ደግሞ በውድድሩ ተሸናፊ የነበረው ማውት ‹‹በህይወቴ ትልቁ ውድድር›› ሲል ከሌላ ጸሃፊ ጋር በመሆን ያሳተመውን መጽሃፍ ለአንባቢዎች አድርሷል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2014