የኢትዮጵያ ቱሪዝም የተስፋ ወጋገን እንደበራለት የሚያመላክቱ ተግባራትን እያስተዋልን ነው። መንግስት ለዘመናት ትኩረት ተነፍጎት የቆየውን ዘርፍ አሁን ካለበት ደረጃ በተሻለ መልኩ ለመምራት አዳዲስ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው። “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል” ይሉት አይነት አባባል ለቱሪዝሙ ከአሁን በኋላ የሚሰራ አይመስልም።
ይህ ውሳኔ መንግስትን ብቻ ሳይሆን በመስኩ የተሰማሩ አካላትን ጭምር ያነቃቃ ነው። በርካታ አካላትም ከወዲሁ በከፍተኛ መነሳሳትና አዲስ መንፈስ ስራቸውን ጀምረዋል። ይህን በማስመልከት የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው መሰናዷችን የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የአገር የጀርባ አጥንት ሆኖ ዜጎች ከዚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚተጉ የመስኩ ማህበራት መካከል አንዱ የሆነውን “የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር” ላይ ትኩረት በማድረግ አንዳንድ ቁምነገሮችን ለማንሳት ወድዷል። ለዚህም ከማህበሩ ፕሬዚዳንትና ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩምና ከዋና ስራ አስኪያጁ ጋዜጠኛ አስናቀ ብርሃኑ ጋር ቆይታ አድርገናል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ሄኖክ “በኢትዮጵያ ቱሪዝምና ባህል ላይ ትኩረታችንን አድርገን ከ15 ዓመታት በላይ ስንሰራ የቆየን በርካታ ጋዜጠኞች አለን” በማለት ዘርፉን ለማስተዋወቅና ለእድገቱ ሞጋች በመሆን መቆየታቸውን ይናገራል። አሁን ደግሞ በማህበር በመሰባሰብ የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የበለጠ እንዲነቃቃና የአገር ምሰሶ እንዲሆን ሙያዊ አበርክቶ ለማድረግ መነሳታቸውን ይናገራል። ከዚያ ባለፈ ጋዜጠኛው በዘርፉ ያለው እውቀት እንዲዳብር የሙያ ስልጠና በማሰናዳት፣ ከቀሪው ዓለም ጋር ግንኙነት እንዲፈጥር ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ያስገነዝባል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ቱሪዝምን በሚመለከት በየትኛውም አካባቢ ግንዛቤ የሚፈጠርበትና ዜጎች አገራቸው ያላትን እምቅ ሃብት ማወቅ የሚችሉበት አብዮት የመፍጠር ዓላማን ሰንቀናል” የሚለው የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ በተለያየ ቋንቋ ስለ አካባቢያቸው የቱሪዝም ሃብቶች የሚሰሩ ጋዜጠኞች ቢኖሩም በሁሉም ቋንቋ ስለ ኢትዮጵያ የመስህብ ሃብቶች እውቀት የሚያስጨብጡ ባለሙያዎችን መፍጠር ግን ዋነኛ ግባቸው መሆኑን ይናገራል። ለዚህም በሁሉም ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የዘርፉ ጋዜጠኞችን በበቂ ሁኔታ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ያነሳል።
የቅንጅት ስራ
የቱሪዝም ጋዜጠኝነት ከተለያዩ ያገባኛል ከሚሉ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራ ለፕሮሞሽንና ለገበያ ልማቱ ጉልህ ሚና የሚያበረክት ሙያ ነው። ከዚህ አንፃር ሁሉም አካላት በቀናነትና በትብብር ሊሰሩ ያስፈልጋል። ይህን በተመለከተ ጋዜጠኛና የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሄኖክ እንደሚለው፤ “ቀደም ባሉት ጊዜያት ዘርፉን ከሚመሩት አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት የሚያስችሉ ብዙ መልካም ነገሮች አልነበሩም” በማለት አሁን ላይ ግን የሙያ ማህበራትና መሰል ባለድርሻ አካላት ጠንካራ የእርስ በርስ ግንኙነት እየፈጠሩ ነው። ከዚህ አንፃር በቀላሉ ተግባብቶ ዘርፉ የሚጠይቀውን አቅም አውጥቶ ለመስራት ቱሪዝምና ባህላዊ ሃብቶቻችን ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጪ አገራት ዜጎች በበቂ ሁኔታ መሸጥ የሚቻልበት እድል እንደሚፈጠር ያስረዳል።
የጋዜጠኛው ሚና
የማህበሩ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህብና ሃብቶች ከማስተዋወቅ አንፃር በመገናኛ ብዙሃንና ሙያተኞች ረገድ በርካታ ነገሮች እንደሚቀሩ ይናገራል። ከውስንነቶቹ መካከል ጋዜጠኞች በራሳቸው አቅምና ጥንካሬ ላይ ብቻ ተመስርተው መስራታቸው መሆኑን በመግለፅ፤ በሙያቸው እንዲበቁ፣ በፋይናንስ አቅም እንዲጠነክሩና ዓለም አቀፍ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተደገፉ አልነበረም ይላል። ከዚህ በኋላ ግን ዘርፉ ለእድገቱና ለራሱ ጥቅም ሲል ከመገናኛ ብዙሃንና ከጋዜጠኞች ጋር ያለውን ግንኙነት አጠንክሮ መሄድ አለበት የሚል ምክረ ሃሳቡን ይሰጣል። አሁን ላይ ተወዳዳሪ የቱሪዝም ዘርፍ ለመገንባት በመንግስት በኩል የሚሰራው ስራም አበረታች መሆኑን ነው የሚረዳው። ጋዜጠኛው ሰፊውን የቱሪዝም ዘርፍ በጥልቀት በመረዳት በሙያው ብቁ “ሰብ ስፔሻላይዜሽን” በቅርስ፣ በተፈጥሮ፣ በባህልና መሰል የቱሪዝም ክፍሎች ላይ እውቀቱንና ትኩረቱን በማድረግ እንዲሰራ “የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር” በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ይናገራል።
“120 ሚሊዮንና እጅግ በርካታ የቱሪዝም ሃብት ላላት አገር 15 እና 20 የቱሪዝም ጋዜጠኛ በቂ አይደለም” የሚለው ጋዜጠኛ ሄኖክ በዚህ ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ ይህን ቁጥር ከፍ በማድረግ ቢያንስ እስከ 250 ድረስ ለማድረስ ማህበሩ በትጋት እንደሚሰራ ይናገራል። በዚህ ሂደት ውስጥም የኢትዮጵያን ዜጎችን ማገልገልና ዘርፉ ለአገር ያለው አበርክቶ ከፍተኛ እንደሆን መስራት ተቀዳሚ አጀንዳ እንደሆነ ይገልጻል። ይህን ማሳካት ከተቻለ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ ወፎች፣ ዱር እንስሳት፣ እፅዋትና መሰል ሃብቶች በልዩ ሁኔታ የሚያሳውቁና የሚዘግቡ ጠንካራ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃንን መፍጠር ይቻላል ይላል።
“ቱሪዝም ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ሃብታቸውን እንዲገነዘቡና እንዲረዱ ያደርጋል” የሚለው የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ አሁን ላይ የምናየው የሰላም እጦት ኢትዮጵያን በቅጡ ካለማወቅ መሆኑን ያነሳል። ይህን ችግር ለመፍታት በቱሪዝምና በባህል ዘርፉ ላይ ሃላፊነት ወስደው ኢትዮጵያዊነትን በተገቢው መንገድ የሚያስተዋውቁ ጋዜጠኞችን ማፍራት ግዜ ሊሰጠው የማይገባ መሆኑን ነው የሚያሳስበው።
ጋዜጠኛ አስናቀ ብርሃኑ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ነው። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ሆኖ ያገለግላል። “የኢትዮጵያ ቱሪዝም በተለይ ከመንግስት ጋር የሚሰራው የተግባቦትና ትኩረት ያለመስጠት ችግር አለበት ተብሎ ስለሚታሰብ በተደራጀ መልኩ ስራዎችን ለመስራት ተንቀሳቅሰናል” በማለት ባለፉት ስድስት እና ሰባት ዓመታት የሚዲያ ፎረም በማቋቋም በርካታ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር ይናገራል። ውስብስብ የአሰራር ሂደትን አልፎም አሁን ላይ የሙያ ማህበር ሆኖ መመስረት መቻሉንና በስሩ በርካታ ጋዜጠኞችን ማቀፉን ይናገራል።
“በዘርፉ ከሚሰሩ በርካታ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል” የሚለው የማህበሩ ስራ አስኪያጅ፤ ቱሪዝም አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ በቢሮ ተቀምጦ የሚሰራ አለመሆኑን አንስቶ በተለያዩ የመስህብ ቦታዎች ተገኝቶ ማየትና ከቦታው መዘገብ እንደሚያስፈልግ ይናገራል። ለዚህ የሚሆን እውቀትና ሪፖርት የማድረግ ክህሎት ደግሞ ጋዜጠኛው ሊኖረው ይገባል። ይህን ተከትሎ ማህበሩ ሃዋሳን ጨምሮ በተለያዩ ፓርኮችና የመስህብ ቦታዎች ላይ ለአባሎቹ የስልጠና መርሃ ግብር ማከናወኑን ይናገራል። በተጨማሪ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበርም አባላቶቹ የመረጃ እጥረት እንዳይኖርባቸው እገዛ የማድረግ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
ክፍተቶቹን ለመድፈን
ጋዜጠኛና የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አስናቀ በአገር ደረጃ የባህልና ቱሪዝም መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ጉልህ ድርሻን መረዳትና ጥቅም እንዳለው ማመን እንደሚያስፈልግ ይናገራል። ከዚህ አኳያ የአመለካከት ለውጥ መምጣት እንዳለበት ጠቅሷል። በአገር ደረጃ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ቀውሶች አገርን ካለማወቅና በጥበት አንድ ቦታ ላይ ከመኖር የሚመነጭ ነው በማለት፤ የጎበጠውን ለማቃናት ባህልና ቱሪዝም ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች በሚገባ መደገፍ እንደሚገባቸው ይናገራል።
“ጋዜጠኛው በራሱ በጎ ፍቃድ የባህል ቱሪዝም ነክ ዘገባዎችን ያቅርብ እንጂ ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ የአቅም ግንባታ አይደረግለትም” የሚለው ስራ አስኪያጁ፤ የተለያዩ ንኡስ የባህልና ቱሪዝም ክፍሎች ላይ በቂ እውቀት ኖሮት እንዲሰራ መታገዝ መቻል አለበት የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል። ከዚህ አንፃር ማህበሩ ለዚህ ተፈፃሚነት እንደሚሰራ ይገልፃል። ቱሪዝም ነፃነት እንደሚፈልግ፣ በመስህብና መዳረሻ ቦታዎች የሚታዩ እውነቶችን ኖሮ መልሶ ማድረስን ይሻል በማለት ከዚህ አንፃር በበቂ መልኩ ከቁሳቁስና ከሙያዊ ነፃነት አንፃር የዘርፉ ጋዜጠኞች ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ይላል።
የአገር ውስጥ ቱሪዝምና የማህበሩ ድርሻ
ኢትዮጵያውያን ባህላቸውን፣ ታሪካዊ ስፍራዎችን፣ ቅርሶችንና ተፈጥሯዊ የመዳረሻ ስፍራዎችን፣ የሃይማኖትና የተለያዩ ክብረ በዓላት ላይ ይገኛሉ። ይሄ ባህል ግን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ግንዛቤ ውስጥ ያልከተተና በመንግስት ስትራቴጂ ያልተደገፈ መሆኑን በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህን ሃሳብ ይጋራል የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ከመስራት ባሻገር “የአገርህን እወቅ ክበባት” በትምህርት ቤት ደረጃ ያሉትን ለመደገፍ እንደሚሰሩ ይናገራል። በፖሊሲና በተለያዩ ህጎች እንዲደገፍና ዜጎች አገራቸውን እንዲጎበኙ የሚበረታታበትን ሁኔታ እንዲፈጠር የበኩሉን ሙያዊ ድርሻ ለመወጣት እንደሚሰራም ይናገራል። የአገር ውስጥ ጎብኚ መጥፋት ሳይሆን በፕሮፌሽናል ደረጃ መለኪያ ተዘጋጅቶለት የመመራት ክፍተት መሆኑም ሊታወቅ ይገባል ይላል።
የአደረጃጀት ለውጥ
የማህበሩ ስራ አስኪያጅ መንግስት አሁን ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ተገቢና እንዲያውም የዘገየ ነው ብሎ ያምናል። ይህ እድል በኢትዮጵያ ቱሪዝም ላይ ትልቅ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣም ይናገራል። ከዚህ ባለፈ አዳዲስ ሊጎበኙ የሚችሉ መዳረሻዎች የሚፈጠሩበት ይህንን ተከትሎም ቀላል የማይባል የቱሪስት ፍሰት የሚታይበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ይናገራል። አዲስ አበባ ላይ በቅርቡ የተጠናቀቁ የመስህብ ስፍራዎች፣ እንደነ ወንጪ፣ ኮይሻ እና ጎርጎራ የመሳሰሉትን ብቻ መመልከት ከተቻለ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ስር ነቀል ለውጦች የሚታዩበት መሆኑንና ለወደፊት እድገቱም መሰረት መሆናቸውን ያስረዳል። እነዚህን መስህቦች ከማስተዋወቅ አንፃርም የቱሪዘም ጋዜጠኛው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ይናገራል።
“ለውጡ መልካም ቢሆንም ከዚያ ጋር ተያይዞ ግን መሰራት ያለባቸው በርካታ ጉዳዩች አሉ” የሚለው ጋዜጠኛ አስናቀ በመጀመሪያ ደረጃ “ቱሪስት (ጎብኚ) ፈረንጅ ብቻ ነው” የሚል አመለካከት መቀየር እንዳለበት ይገልፃል። ይህን የአመለካከት ችግር ለመቅረፍም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተረባርበው መስራትና ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንደሚኖርባቸው ይገልፃል። የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበርም ከዚህ አኳያ በርከት ያሉ ስራዎችን ለመስራት በእቅድ መያዙን ነግሮናል።
እንደ መውጫ
ጋዜጠኛና የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አስናቀ “ቱሪዝሙ አዲስ ተስፋን ሰንቋል” ይላል። ከዚህ በኋላ በተሻለ መንገድ መስራት ይኖርብናል በማለትም መልዕክቱን ያስተላልፋል። የኢትዮጵያ የመስህብ ሃብቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ነው። በዩኒስኮም የተመዘገቡትም ይሆን በሌሎች መስህቦች ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ነች። ስለዚህ ይህን እምቅ ሃብት በተገቢው ሁኔታ አስተዋውቆና ገበያ ላይ አውጥቶ የቱሪስት ፍሰቱን መጨመር ያስፈልጋል ይላል። ለፕሮሞሽን ስራው ደግሞ የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ድርሻ ጉልህ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፆልናል።
በመጨረሻም በቱሪዝም እና ባህል ዘርፉ ላይ የሚሰሩ ማናቸውም የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የጋዜጠኞች ማህበሩ የሚያከናውናቸውን ስራዎች እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል። በተለይ የዘርፉ ጋዜጠኞች በአባልነት እንዲቀላቀሉና በጋራ እንዲሰሩ መልዕክቱ ይድረሳችሁ ብሏል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2014